Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 11th
Home arrow Sections arrow "ከእኛጋር ልዩነት ያላቸው ቡድኖች...
"ከእኛጋር ልዩነት ያላቸው ቡድኖች... Print E-mail
Sunday, 23 March 2008
Image"ከእኛጋር ልዩነት ያላቸው ቡድኖች ተመልሰው ፓርቲያችን ውስጥ እንዲታቀፉ በሩ ክፍት ነው፡፡ ሌላ አማራጭ ካላቸው ግን የሚያገባን ነገር የለም፡፡"
አቶ ክፍሌ ጥግነህ

አቶ ክፍሌ ጥግነህ የቀድሞው ቅንጅት አብዛኛው አባላትን ያቀፈውና በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በሚመራው በምስረታ ላይ ያለው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ አባል ናቸው፡፡ ሰለሞን ጐሹ በፓርቲው ምስረታና በአንዳንድ ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ያላችሁት ፓርቲ ምስረታ ሂደት ምን ላይ ነው ያለው?

አቶ ክፍሌ፡-
በቀድሞው ቅንጅት የነበረ ዓላማ፣ ራዕይ፣ እምነት የፖለቲካ ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብና ደጋፊዎቹ ለፓርቲው አስተዋጽኦ ለማድረግ ያላቸው ፍላጐትና ችሎታ አሁንም ባለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የሌለው ስሙና ምልክቱ ነው፡፡ የስምና የምልክትን ጉዳይ በፍርድ ቤትም ሆነ በምርጫ ቦርድ በኩል እናገኛለን የሚል እምነት የለንም፡፡ ስለዚህ እዚያ ላይ ጊዜ ከማጥፋት ሥራ መሥራት ስላለብን የስም ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተረድተናል፡፡ በዚህም መልኩ የስም ለውጥ አድርገን የቀድሞውን ቅንጅት በፕሮግራሙ፣ በእምነቱ በራዕዩ ተመስርቶ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ለመመስረት ነው የምንፈልገው፡፡ ለዚህም የምርጫ ቦርድ ለመመዝገብ የሚያስችሉ ፎርሞች አሉት፡፡ ፎርምና የድጋፍ ደብዳቤ እንዲሰጡን ጠይቀናል፡፡ የድጋፍ ደብዳቤው አባሎቻችን መሥራች አባላትን ለመመልመል በሚወጡበት ጊዜ በየደረሱበት ቦታ ችግር እንዳያጋጥማቸው ሰው እንዲተባበራቸው የሚጠይቅ ነው፡፡ ፎርሙን ተቀብለናል፡፡ የድጋፍ ደብዳቤውን በተመለከተ ከዚህ ቀደም የሚሰጥ የነበረ በመሆኑ የሚሰጠን ነው የሚመስለኝ፡፡ እሱን ስንጨርስ ፓርቲያችንን እናስመዘግባለን፡፡ በምርጫ ቦርድ የሚፈለጉ የተለያዩ መዛግብትና ሰነዶች አሉ፡፡ የመመስረቻ ጽሁፍ፣ የፖለቲካ ፕሮግራም፣ የፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብና ሌሎችም ሰነዶች ለምዝገባ አስፈላጊ ናቸው፡፡ እነሱ እየተዘጋጁ ነው፡፡ እነሱ እንደተጠናቀቁ ለመሥራች አባልነት የሚመዘገቡ ሰዎችን መመዝገብ እንጀምራለን፡፡ ስለዚህ የሂደቱ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ነው ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲሱ ፓርቲ ሊቀ መንበር ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል መሆናቸውንና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ ሀገር ውስጥ የሌሉ ግለሰቦችን የሥራ አስፈፃሚ አድርጋችሁ እንደምታስቡ ከተለያዩ ሚዲያዎች አይተናል፡፡ ይህ ምን ያህል ህጋዊ ነው?

አቶ ክፍሌ፡-
የህጋዊነት ጥያቄ ያስነሳል ብለን አናምንም፡፡ የሚኖርበትም ምክንያት አይታየንም፡፡ በተቻለ መጠን በአዲስ ስም በምንመዘገብበት ጊዜ በአብዛኛው ለፓርቲያችን በገንዘባቸው፣ በጊዜያቸው፣ በአቅማቸው ፅኑ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩና የፓርቲውን ጥንካሬና እዚህ መድረስ ሲደግፉ የነበሩ በተለይም መስራች አባላት የነበሩና ሌሎችም የፓርቲውን አላማና ፕሮግራም የሚከተሉ ኢትዮጵያዊያንን በሙሉ ልዩነት ሳናደርግ እንቀበላለን፡፡ እንመዘግባለን፡፡ አመራሩን በተመለከተ በህብረት አንድ ላይ ያለነው አንድነት ያለን አዲሱን ፓርቲ ለመመዝገብ እየሰራን ያለነው ብቻ ሳይሆን ኢንጂነር አዲሱና ሌሎች የቀድሞ የአመራር አባላት ለቅንጅት ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረጉ ናቸው፡፡ ይህን የምንክደውም አይደለም፡፡ መንገድም የለም፡፡ የምንፈለገውም አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ቦታቸው ተጠብቆ ያለው፡፡ እነሱም አንፈልግም የሚሉበት ሁኔታ ያለ አይመስለንም፡፡ ኢንጅነሩ አሁንም ሳይመለሱ የቆዩት ስለታመሙ ነው፡፡ ተሽሏቸው በሚመጡበት ጊዜ ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱ ነው የምንጠብቀው፡፡ ሌሎችም የሥራ አስፈፃሚውም ሆነ የላዕላይ ምክር ቤቱ አባላትም እንደዚሁ እንደሚያደርጉ እንጠብቃለን፡፡ ይህን ደግሞ ህጋዊነት የለውም ብሎ ጥያቄ ሊያስቀምጥ የሚችልበት እድል አለ ብለን አናምንም፡፡ ዞሮ ዞሮ አዲሱ ፓርቲ ከተመሠረተ በኋላ አዲስ አመራር ይመርጣል፡፡ ያኔ ሁላችንም ልንኖር ወይም ላንኖር እንችላለን፡፡ ከዚህ አንፃር በህጋዊነቱ ላይ ስጋት የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞውን ቅንጅት የፈጠሩት አራት ፓርቲዎች የራሳቸው አደረጃጀትና ንብረት ነበራቸው፡፡ ነገር ግን ከውህደቱ ሂደት በኋላ የጋራ ንብረት አፍርታችኋል፡፡ በአጠቃቀም ሪፖርቱ ዙሪያ ከተለያዩ ቡድኖች የተለያዩ ነገሮችን ነው እየሰማን ያለነው፡፡ እናንተ ስለ ሂሳብ ሪፖርቱ ምን የምትሉት ነገር አለ?

አቶ ክፍሌ፡-
ቅንጅት ከምርጫው በፊት የቆየው ለጥቂት ወራት ብቻ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ውስጥ እያንዳንዱ አባል ፓርቲ የራሱ አሰራር፣ ውህደት፣ ልምድ ነበረው፡፡ ለምርጫው ለምንዘጋጅበት ጊዜ ያሉንን ሀብቶች በሙሉ አብረን ስንጠቀም ነበር፡፡ ቅንጅት ከተባለ በኋላ ደግሞ እያንዳንዱ ፓርቲ የራሱን ህልውና እየተወ ስለነበር በእኛ አረዳድ የጋራ ንብረት ነበር፡፡ ሁሉም ደግሞ ለምርጫው ጉዳይ ውሏል፡፡ ከዚያ የተረፈ አለ የሚባል ንብረትም አልነበረም፡፡ የሂሳብ ሪፖርት ነበር ወይ? ለሚለው ጥያቄ እስከማስታውሰው በዚያ ጊዜ አልነበረንም፡፡ እንደተደረገም አላውቅም፡፡ በዚህ ጉዳይ ጥያቄ ያለው አካል ወደ ፓርቲው አመራር በመምጣት ጉዳዩን ግልፅ ማድረግ ይችላል፡፡ እንደግለሰብ እኔ በሒሳብ ጉዳይ ላይ የማልካፈል ነበርኩ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅድሚያ በመንግሥት የቀድሞው ቅንጅት አመራሮችን በማሰር የተወሰደው እርምጃ በኋላም ከእስር ከተፈቱ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጠረው አለመግባባት አባሎቻችሁ ተከፍተዋል፡፡ በአዲሱ ፓርቲ ምስረታ ሂደት ላይ የአባሎቻችሁ ስሜት ምን ይመስላል?

አቶ ክፍሌ፡-
አለመግባባቶች መፈጠራቸው የሚካድ አይደለም፡፡ ነገር ግን እነዚህ አለመግባባቶች የፓርቲውን መሠረታዊ የሆኑ የፖለቲካ እምነቶችና ፕሮግራም እንዲሁም መተዳደሪያ ደንብ በተለይም ስለኢትዮጵያ ያለው ራዕይ በተመለከተ የተነሱ አለመግባባቶች አልነበሩም፡፡ የተፈጠሩት ነገሮች ላለመግባባት በር መክፈት የነበረባቸው ጉዳዮች አልነበሩም፡፡ ለዚህ ኃላፊነቱ ማን ላይ ይወድቃል የሚለውን የኢትየጵያ ሕዝብ ላይ ነው የምንጥለው፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ በዚህ በጣም አዝኗል፡፡ ስላሳዘነውም እናዝናለን፡፡ ፓርቲው ትልቅ ተስፋ አሳድሮበት ነበር፡፡ መስዋዕትነትም ከፍሎለታል፡፡ ሕዝቡ ትንሽም ሆነ ትልቅ ልዩነትም ሆነ አለመግባባት በፓርቲው ውስጥ ስለመኖሩ መስማት አይፈልግም ነበር፡፡ የግለሰቦች አለመግባባት እንደነበር ለመግለፅ እድሉም አልነበረንም፡፡ በኋላ ግን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ለማስረዳት ተሞክሯል፡፡ ምን ያህል ውጤታማ ሆነናል? ወደ ፊት የምናየው ነው፡፡ በቅርቡ አሜሪካ በነበርኩበት ጊዜ ከአባሎቻችን ያየሁት ነገር ልዩነቱ የግለሰቦች እንጂ የፖለቲካ ፕሮግራምና ራዕይ እንዳልሆነ በደንብ ተረድተውታል፡፡ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ከእኛ ጋር አብሮ እየሰራ ነው፡፡ በሀገር ውስጥም ተመሳሳይ ምላሾች አሉ፡፡ አዲሱ ፓርቲ ከቀድሞው ቅንጅት የተሻለ ሁኔታ፣ ጥንካሬና ቦታ ይደርሳል የሚል እምነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞው ቅንጅት በዲያስፖው ተፅዕኖ ስር የዋለ ነበር ተብሎ ይተቻል፡፡ ስለዚህ የዲያስፖራው ለሁለት መከፈል ለቅንጅቱ መሰነጣጠቅ ምክንያት ይደረጋል፡፡ አንዳንዶች ግን የቅንጅቱ መሰነጣጠቅ ዲያስፖራውንም እንደሰነጠቀው ይገልፃሉ፡፡ የአሁኑ ፓርቲ በውጭ ካሉ ኢትዮጵያዊያን ጋር ያለው ግንኙነት ምን መልክ አለው?

አቶ ክፍሌ፡-
የዲያስፖራው ተፅዕኖ በሀገር ውስጥ በነበረው አመራር ላይ ከሚያስፈለገው መጠን በላይ ነበር የሚል እምነት እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ይሄ ነገር ሙሉ በሙሉ ትክክል ነበር ለማለት እቸገራለሁ፡፡ እርግጥ ዲያስፖራው ነፃ በሆነ ሚዲያ በጣም መጠቀም የሚችል ነው፡፡ የዲያስፖራው አስተዋፅኦ ሀገር ውስጥ ያለውን ፓርቲ በገንዘብ እና በዲፕሎማሲ (በያሉበት ሀገር ያሉትን የሕግ አውጭና አስፈፃሚ አካላት የፓርቲውንና የሀገራችንን ሁኔታዎች ግልፅ ለማድረግ) ጉዳዮች ሲረዱ ነበር፡፡ ከዚህ አልፎ ሀገር ውስጥ ያለውን የአመራርን አቅጣጫ የመወሰን ፍላጎትም እድሉም አልነበራቸውም፡፡ የቀድሞው ቅንጅት አመራርም ያን የሚፈቅድ አልነበረም፡፡ ውጭ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች ልዩነቱን ለማስፋት አስተዋፅኦ አላደረጉም ማለት ግን አይደለም፡፡ አሜሪካ ያሉ ድጋፍ ሰጭ ኮማቴዎች እንደገና በአዲስ መልክ ተደራጅተዋል፡፡ በየግዛቱ ያሉ ድጋፍ ሰጭዎች አሜሪካ አቀፍ አንድ ድጋፍ ሰጭ ኮሚቴ ሲመሰረቱ ነው እኔ እዚያ የተገኘሁት፡፡ ይህ ኮሚቴ ሀገር ውስጥ ካለው አመራር ጋር የሚኖረው ግንኙነት የገንዘብና የዲፕሎማሲ ድጋፍ እንደሆነም በአመራሩና በመተዳደሪያ ደንቡ በኩል አረጋግጦልናል፡፡ ልዩ ድጋፍ (expertise) ስንፈልግም እንጠይቃለን፡፡ ከዚህ የዘለለ ጣልቃ ገብነት የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞው ቅንጅት ከግለሰቦች ልዩነት በዘለለ የርዕዮተ ዓለም፣ የሁለት ትውልዶች እና የብሔርና የሃይማኖት ልዩነት ነበረው የሚሉ ግለሰቦች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ መጠኑ ይለያይ እንጂ መሰል ልዩነቶችን መጥፋት አይቻልም፡፡ በዚህ በኩል አዲሱ ፓርቲ ለእነዚህ ፈተናዎች ምን ያህል ዝግጁ ነው?

አቶ ክፍሌ፡-
ፓርቲውን በመሠረቱት አሁን ፓርቲዎች መካከል የርዕዮተ ዓለም ልዩነት አልነበረም፡፡ በዘር፣ በሀይማኖት፣ በቋንቋና በመሳሰሉት ልዩነቶች ላይ የተመሠረተ ልዩነት አልነበረም፡፡ እነዚህ ቢኖሩ ኖሮ ከመጀመሪያውም አንሰባሰብም ነበር፡፡ ይህን የሚሉ ሰዎች ወይ ተስስተዋል፡፡ አልያም የሌላ ነገር ፈጥረው የቅንጅትን አቋም ለማናጋትና አደጋ ላይ ለመጣል ይፈልጋሉ፡፡ የሁለት ትውልዶች ልዩነት ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ በዓለም ላይ ያለ ፓርቲ ሁሉ የሚያስተናግደው ነገር ነው፡፡ መኖርም አለበት፡፡ እንደ እኛ ያለው በእድሜ የገፋው ትውልድ ለአዲሱ ትውልድ ቦታ ማስረከብ አለበት፡፡ አረካከቡ ግን ለስላሳ መሆን አለበት፡፡ ይሄ ግን እንደልዩነት መታየት የለበትም፡፡ ልዩነቶች ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ሃሳብን ያለ ፍርሃት በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ልዩነትን መፈታት እንደሚቻል እናምናለን፡፡ ይሄ በሚሆንበት ጊዜ ለሽኩቻ፣ ለአሉባልታ፣ ላለመግባባት መንገዱ ይዘጋል፡፡ መተዳደሪያ ደንቡን ጥሶ ፓርቲውን አደጋ ላይ የሚጥል ግለሰብም ሆነ ቡድን ካለ በቅድሚያ መተዳደሪያ ደንቡ ባስቀመጠው የዲስፕሊን መመሪያ ይገኛሉ፡፡ ከዚያ ውጭ ውሳኔ ማሳለፍ ካለብንም እንደዚያው እናደርጋለን፡፡ በጊዜ ሂደት ግን ድርጅቱ ሲጠናከር የውስጥ አቋማችን መዋቅራችን መሠረት ሲይዝ የዴሞክራሲ አሰራሮች ራሳቸው የቅሬታዎች መፍትሔ ይሆናሉ፡፡ ለዚህም አሁን የፓርቲውን ተቋማዊ አሰራር ለማጐልበት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የቀድሞው ቅንጅት አመራሮች ከሰሜን አሜሪካና አውሮፓ ጉዞ መልስ የድርጅቱን ድክመቶች የሚዳስስና የለውጥ አቅጣጫ የያዘ ሰነድ (ብሉ ፕሪንት) አዘጋጅታችኋል፡፡ መሠረታዊ ነጥቡ ምንድን ነው?

አቶ ክፍሌ፡-
አንደኛው አብሮ የመሥራት ልምድ ነው፡፡ የቀድሞውን ቅንጅት የመሠረቱት አራት ፓርቲዎች እንኳን በአባላት ደረጃ በአመራር ደረጃም በደንብ አንተዋወቅም ነበር፡፡ አሁን የአለመተዋወቅ ችግር ይወገዳል፡፡ ሌላው በምርጫውና ከምርጫው በኋላ ከተፈጠሩት ችግሮች ብዙ የተማርናቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ የሕዝብን ሀሳብ በመቀበል በኩል የነበረው ነገር ዋነኛው ነው፡፡ የአመራር ጉድለቶች እንደነበሩ እናምናለን፡፡ ከዚህ ልምድ ወስደናል፡፡ ለመማር የእኛ ዝግጁነትና ፍላጎት ወሳኝ ነው፡፡ የአዲሱ ፓርቲ አመራርም በዚህ በኩል ቁርጠኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በድህረ ምርጫ 97 ቅንጅትን ሕዝብ መራው እንጅ ቅንጅት ሕዝቡን አልመራም ተብሎ ይተቻል፡፡ አሁንስ ለሕዝብ አስተያዬትና ስሜት የምትሰጡት ቦታ ምንድን ነው?

አቶ ክፍሌ፡-
የሕዝብን አስተሳሰብና ፍላጎት እንዲሁም ድምፅ መስማት የዴሞክራሲ ዋነኛው ሃሳብ ነው፡፡ ሕዝብ ነው የሚመራው፡፡ የሕዝብ ፍላጎት ነው መሟላት ያለበት፡፡ ይህ የቅንጅት ትልቅ እምነት ነው፡፡ አሁንም አዲሱ ፓርቲ ከዚያ እምነት ወደ ኋላ ይላል ብዬ አልገምትም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሕዝቡ የሚመርጣቸው ፍላጐቴን አስፈፅሞልኝ ብሎ ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝቡን ስሜት በመቀበላችን ተሳስተናል ብለን አናስብም፡፡ ነገር ግን የሕዝብን ስሜት የምንሰማው ሰላማዊነትን በጠበቀ መልኩ፣ የፓርቲውን አቋም በማይጎዳ መልኩና ለዘለቄታዊ ጥቅም ሲባል ነው፡፡ ቅንጅትን ሕዝብ ነው የመራው ለሚሉት አዎ ልክ ነው፡፡ ፓርቲው ግን አደጋ ላይ የወደቀው የሕዝብን ስሜት ስለሰማ ሳይሆን መንግሥት የሕዝብን ስሜት አልሰማም በማለቱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕዝባችን እኮ አንድ የሚያደርገው ነገር እንዳለ ሁሉ የሚለያይባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ የተለያዬ ዓይነት የሕዝብ ድምፅ እንዳይመጣ ለማድረግና ሀገራዊ አጀንዳዎችና መስማማቶች እንዲፈጠሩ ለማድረግ ከእናንተ ወደ ሕዝቡ የሚወርደው የተሻለ ተፈፃሚነት አይኖረውም? የሕዝብ መድረክ ከመፍጠርስ ጋር ምን የተሰራ አዲስ ነገር አለ?

አቶ ክፍሌ፡-
የቀድሞው ቅንጅት በፊትም በአዲስ አበባና በየክፍለ ሃገሩ በመዘዋወር ብዙ የሕዝብ መድረኮችን በመፍጠር ውይይት አድርጓል፡፡ ወደፊት ይህንን ለማድረግ ዝግጅቶች አሉን፡፡ መተዳደሪያ ደንባችን ይሄን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ የስራ ክፍፍል አለን፡፡ ከሕዝብ ጋር የሚደረገው የውይይት መድረክ በቋሚነት የሚደረግ ነው፡፡ በቅርቡ በየክፍለ ሀገሩ ተዘግተው የነበሩ ቢሮዎቻችንን በመክፈት አባሎቻችንንም እንደገና ስለምናሰባስብ ከሕዝቡ የሚመጣውን ምክርና እንቀበላለን፡፡ የእኛንም ሀሳቦች ወደ ሕዝቡ እናፈሳለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከምርጫ 97 በኋላ የፓርቲዎች አቋም ተዳክሟል፡፡ አሁን ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ በፓርቲዎች የገንዘብ ምንጭ ላይ ጠበቅ ያለ አንቀጾች ይዟል፡፡ ከገንዘብ አቅም አኳያ ምን ደረጃ ላይ ናችሁ?

አቶ ክፍሌ፡-
የፓርቲዎችን የገንዘብ አቋም በተመለከተ ህጉ ጠንከር ብሎ የድጋፍ ሰጭዎች ዝርዝር በስማቸው እንዲታወቅ ያዛል፡፡ ይሄ በራሱ ጉዳት አለው ብለን አናምንም፡፡ ዋናው አፈፃፀሙ ላይ ነው፡፡ ህጎቹ በትክክል ለሁሉም በአንድ ዓይነት መልኩ አይፈፀሙም፡፡ የሚፈፀሙት ተቃዋሚዎችን ለማዳከም እና አቅም ለመቀነስ ሲባል ብቻ ነው፡፡ ወደፊት እናየዋለን፡፡ የእኛ አቅም እየጎለበተ የሚሄድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከቀድሞው ቅንጅት የሚመዘዙ አካሎች አሉ፡፡ ከእነሱ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን መልክ አለው?

አቶ ክፍሌ፡-
የእነዚህ ቡድኖች መኖር እኛን የሚያሳስብ አይደለም፡፡ በእኛ እምነት የቅንጅት ቅጣት የነበሩ ሁሉ የቅንጅትን አላማ የፖለቲካ ፕሮግራም ለማስፈፀም ዝግጁ የሆኑ ሁሉ ተመልሰው ፓርቲያችን ውስጥ እንዲታቀፉ በሩ ክፍት ነው፡፡ ሌላ አማራጭ ካላቸው ግን ስለእሱ የሚያገባን ነገር የለም፡፡ ሙሉ መብታቸው ነው፡፡
 
< Prev   Next >