| "ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አልሆነም" |
|
|
| Sunday, 23 March 2008 | |
![]() አቶ ተስፋየ መንገሻ "ገለልተኛነቱ በፓርቲዎች እርካታ የሚለካ አይደለም" ምርጫ ቦርድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ሂደት ምርጫ ቦርድ ገለልተኛነቱን አላረጋገጠም በማለት የወቀሱ ሲሆን ቦርዱ በበኩሉ ገለልተኛነቱ በፓርቲዎች እርካታ የሚለካ አለመሆኑን ይገልፃል፡፡ የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መስፍን ሽፈራው ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ በአዲስ አበባ ምክር ቤት የሚወዳደሩ የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች ቅፅ ሆን ተብሎ በአግባቡ እንዳይለጠፍ ተደርጓል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የኢህአዴግን ጨምሮ የሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲ ዕጩዎች ዝርዝር መግለጫ ቅጽ "በአንድ ጊዜና በተመሳሳይ ቦታ መለጠፍ እያለበት ሆን ተብሎ በቅድሚያ የገዢው ፓርቲ ተወዳዳሪ ዕጩዎች ብቻ" መለጠፉንና፣ የተቃዋሚ ዕጩዎች ግን ዘግይቶና በተለየ ቦታ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ እንደውም በአንዳንድ ቦታዎች "በፍፁም እንዳልተለጠፈ" ገልፀዋል፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋየ መንገሻ በበኩላቸው፣ ምርጫ ቦርድ ተወዳዳሪ ዕጩዎች ያስተዋወቀው በአንድ ቀን እንደሆነ ገልፀው፣ ራሳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባሉበት መለጠፉን ማረጋገጣቸውን አስገንዝበዋል፡፡ አልተለጠፈልንም የሚሉት ተቃዋሚዎች ያልተወዳደሩባቸው ጣቢያዎች አይተው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እንደ አቶ መስፍን አባባል ከሆነ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጩዎች ዝርዝር ቅፅ ተለይቶና ዘግይቶ በመለጠፉ ለብቻው እንዲላጥና እንዲቀደድ ተደርጓል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩዎች አንድ ላይና በተመሳሳይ ጊዜ በመለጠፉ እንዲህ ዓይነት ችግር ሳያጋጥመው፣ እስከ አሁን ድረስ በየትኛውም ስፍራ ሳይቀደድ ተለጥፎ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ አቶ ተስፋየ ይህንን አስመለክተው በሰጡት አስተያየት፣ የኢህአዴግና የተቃዋሚዎች የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዕጩዎች የተለጠፈው ለየብቻ ሳይሆን ጎን ለጎን መደረጉን ገልፀው፣ ይህም የሆነበት ምክንያት እያንዳንዱ ፓርቲ 14 ዕጩዎች ማቅረብ ስላለበት ለሕዝቡ እንዳያምታታ በማሰብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በፓርላማ ምክር ቤት የሚቀርቡት ዕጩዎች ግን ከእያንዳንዱ ፓርቲ አንድ ሰው በመሆኑ የሚያምታታ አይደለም፡፡ በመሆኑም አንድ ላይ እንዲለጠፍ መደረጉን ገልፀዋል፡፡ "".ተቀደዱ የተባሉበት አካባቢም ከፍተኛ ክትትል በማድረግ አስቸኳይ ሪፖርት ቀርቦልን እንዲተካ አድርገናል፡፡ ጉዳዩንም ለአዲስ አበባ ፖሊስ ሪፖርት አድርገናል"". ይላሉ አቶ ተስፋየ፡፡ አቶ መስፍን፣ የተወካዮች ምክር ቤትና የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ተለያይቶ እንዲለጠፍ የተደረገበት ምክንያት፣ ተወዳደሪዎቹን "ሕዝቡ ለይቶ እንዲያውቃቸው" የሚለው የምርጫ ቦርድ ምላሽ ተችተውታል፡፡ "ሕዝቡ ይህንን መረዳት ያቅተዋል የሚል አመለካከት ትልቅ ስህተትና ንቀት ነው" በተጨማሪም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጩዎች ፖስተር ሲቀደድ በፖሊስ ተገቢ ክትትል አለመደረጉና ምርጫ ቦርድም የተቀደደውን የዕጩዎች ዝርዝር ቅፅ ተከታትሎ እንዲለጠፍ ለማድግ ባለመቻሉ ነቅፈዋል፡፡ አቶ መስፍን፣ ነፃ የአየር ጊዜ ድልድሉን አስመልክተው የኢህአዴግና የእሳቸው ፓርቲ ሲነፃፀር 57 ለ1 መሆኑን ገልፀው፣ ችግሩ የመጣው በመጀመሪያ መስፈርት አወጣጥ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደእሳቸው አገላለፅ 60 በመቶው የአየር ሰዓቱ ለፓርላማ መቀመጫ መመደቡ አዳዲስ ፓርቲዎችን የሚጎዳና፣ ኢህአዴግን ብቻ እንዲጠቅም ሆን ትብሎ የተደረገ ስሌት እንደሆነ ነው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት አብዛኛው የሰዓት ድልድሉ መስፈርት ለዕጩዎች ብዛት ትኩረት የሰጠ መሆን ነበረበት፡፡ አብዛኛው የፓርላማ ወንበር በኢህአዴግ እጅ በመሆኑ "ምርጫ ቦርድ ገዢውን ፓርቲ ሆን ብሎ ለመጥቀም ያደረገው ስሌት ነው"". እንደ አቶ መስፍን እምነት፡፡ አቶ መስፍን ይህ ዓይነት የአየር ሰዓት ስሌት "ተራና ማንም ሊቀበለው የማይችል ኋላ ቀር ነው" ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይ ህብረትና ኦፌዴን በመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ቅሬታ በማቅረብ ለገዢው ፓርቲ በሚጠቅም መልኩ መደረጉን በመግለፅ ተቃውሞውታል፡፡ የአየር ሰዓቱ ድልድል በተመለከተ አቶ ተስፋየ በቀጥታ እንደማይመለከታቸው በመግለፅ ሆኖም ግን ድልድሉ በተካሄደበት ወቅት ራሳቸው ተገኝተው እንደተከታተሉትና ፓርቲዎቹ በደስታ እንደተቀበሉት አስታውሰዋል፡፡ በመጀመሪያ የቀረበው ረቂቅ ላይ ለዕጩዎች ቁጥር የተሰጠው ዋጋ ከፍተኛ እንደነበርና በዚሁ መስፈርት ተቃዋሚዎች ሊያገኙት የሚችሉት የአየር ሰዓት በጣም አነስተኛ ሊሆን እንደነበር ገልፀው፣ ነገር ግን ከዚህ ላይ ተከፋፍሎ 30 በመቶ የሚሆነው የአየር ሰዓት እኩል እንዲከፋፈሉ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በፓርላማ መቀመጫም ሆነ በዕጩ ተወዳደሪዎች አብላጫ ቁጥር ያለው ኢህአዴግ ስለሆነ በየትኛውም መስፈርት ቢሰላ፣ የኢህአዴግን ያህል ሰዓት ሊያገኝ የሚችል ፓርቲ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ በእኩል የሚከፋፈሉት ሰዓት ከፍ እንዲል የተደረገበት ምክንያትም ይሄው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አዳዲስ ፓርቲዎችን አስመልክተው በፓርላማ ከፍተኛ ቁጥር ያለውና በርካታ ዕጩዎችን ያቀረቡ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ስለሚወክል ከዚህ ውጭ ለመሥራት እንደሚያስቸግር ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች ያልተጠቀሙበት የአየር ሰዓት ክፍለ ጊዜ ዝም ብሎ እንዲባክን መደረጉ ፍትሃዊ አለመሆኑን ተቃውመዋል፡፡ አሁንም ቢሆን የሚመለከተው አካል ጉዳይ አይቶ ሌሎች ሊጠቀሙበት ያልቻሉ የአየር ሰዓቶች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ጊዜው ሳይረፍድ እንዲጠቀሙበት ቢደረግ አግባብ እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ተስፋየ ይህንን ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመገናኛ ብዙሃን አካላት በመሆኑ አስተያየት መስጠት አልቻሉም፡፡ በአጠቃላይ ምርጫ ቦርድ የምርጫው ሂደት በጥሩ ሁኔታ የጀመረው ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ገለልተኝነቱ አጠራጣሪ እየሆነ መምጣቱን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ "ሁሉም ነገር ገዢው ፓርቲ በሚጠቅም መልኩ ማድረጉ የምርጫው ጨዋታ ኢህአዴግ ብቻ እንዲቆጣጠረው መንገድ ከፍቶለታል" አቶ ተስፋየ በበኩላቸው የምርጫ ቦርድን ገለልተኛነት አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ "የቦርዱ ገለልተኛነት በፓርቲዎች እርካታ የሚለካ" አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የቦርዱ ገለልተኛነት የሚለካው ኃላፊነቱ እየተወጣ እንደሆነ በማየት ብቻ ነው፡፡ ቦርዱ ህጋዊ ኃላፊነቱ ሲወጣ ሁሉም ፓርቲዎች ላይጠቀሙና ላይረኩ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ በቅርቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአየር ሰዓት ድልድሉን አስመልክቶ ላሰሙት ቅሬታ የብሮድካስት ባለስልጣን ጠይቀን የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀምን አስመልክቶ ለተደረገው ድልድል የተወሰዱ ዋና ዋና መስፈርቶችን ማብራራቱና የቀረበው ቅሬታ ማስተባበሉን ይታወሳል፡፡ በየማነ ናግሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |