| የትግልና የድል መንገድ ሕጋዊና... |
|
| Wednesday, 09 January 2008 | |
|
የትግልና የድል መንገድ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው ኢትዮጵያ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ እንደሚያስፈልጋት ደጋግመን ጮኸናል፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ስንል ትክክለኛ ፕሮግራም ያለውና ይህን ፕሮግራሙን እውን ለማድረግ የሚከተለው የትግል ስልት ትክክለኛ የሆነ ማለታችን ነው፡፡ አመቺ ማለትም አልጋ በአልጋ ማለት ነው ተብሎ ካልተተረጐመ በስተቀር፣ ከአሁኑ ተጨባጭ የአገራችን ሁኔታ አንፃር ሲታይ ትክክለኛው የትግል ስልትና የድል መንገድ ማለት ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ነው፡፡ በአገራችን በሰላማዊ መንገድ ታግሎ ዳር ለመድረስ አመቺ ሁኔታ አለ፡፡ ሕጋዊና ሰላማዊ የትግል ስልት የተቃውሞ፣ የትጥቅ፣ የማፈንዳት፣ የማቃጠል ስልት አድርጐ መውሰድ የተሳሳተ ነው፡፡ ሕጋዊ ሆኖ ሕዝብን በማስተማር አደራጅቶና ደጋፊ ፈጥሮ በድምፅ አሸንፎ ስልጣን መያዝ ነው፤ ጠንካራው የትግል ስልት፡፡ ሁለት ጐራዎችን እያነፃፀሩ ማየት በቂ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) የትጥቅ ትግል ከጀመረ ከአርባ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ የሚከተለው የትግል ስልት የትጥቅ ትግል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል አይቻልም፤ ብሎ ደምድሟል፡፡ ሰላማዊ የትግል መንገድ የተከተለው በሽግግሩ ወቅት ብቻ ነበር፡፡ አርባ ዓመት በሙሉ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር የነበረው መቀራረብና በአንድ ዓመት የሽግግር ወቅት የፈጠረው መቀራረብ ሲታይ በሽግግር ወቅት እጅግ የተሻለ ነበር፡፡ በተሻለ የመታወቅ፣ በተሻለ የማደራጀት፣ በተሻለ የመንቀሳቀስና የሕዝብን ድጋፍ የማግኘት ዕድል ተፈጥሮለት ነበር፡፡ ከሽግግሩ መንግሥት ለውጥ በኋላ ደግሞ ከሕዝብ እየራቀና እየወጣ መጣ፡፡ የትጥቅ ትግል አካሂዳለሁ የሚለው ኦነግና በስልጣን ላይ ያለው ኦሕዴድ አነፃፅረን የትኛው ድርጅት ለኦሮሞ ሕዝብ ጠቀሙ ብለን ስንጠይቅ፣ በማያጠራጥር ሁኔታ ኦሕዴድ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በታሪኩ አይቶት የማያውቀው ጤና ጣቢያ፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት፣ ኮሌጅ፣ መንገድ፣ የስልክ፣ የመብራት አልግሎትና ኢንቨስትመንት በከተማና በገጠር አይቷል፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ አዳማ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ሱሉልታና ቡራዩ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ሰበታ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ለገጣፎ ተንቀሳቅሶ ማየትና ማስተዋል ብቻ በቂ ነው፡፡ በሌላ በኩል ፓርላማ ገብተው በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እየታገሉ ያሉትና ከፓርላማ ውጭ ያሉት ተቃዋሚ ድርጅቶች ብናይም የተሻለ ተቀባይነት አግኝተው ማደራጀትና አባላትን የማበራከት ዕድል የሚያገኙት ፓርላማ ያሉት ናቸው፡፡ ከፓርላማ ውጭ ያለው ቅንጅትና ፓርላማ የገባው ቅንጅት ሲታይ የተሻለው ፓርላማ የገባው ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ፓርላማ መግባት ስህተት ነው፤ ይሉ የነበሩትም ተሳስተን ነበር፤ የሚል ቃል ከአፋቸው አልሰማንም እንጂ ፓርላማ ከገቡት ጋር ስምምነት ፈርመናል፤ ሲሉ ሰምተናል፡፡ ሕጋዊ መንገድን አለመከተል የሚያመጣው ችግር መገንዘባቸውም ያስመሰግናቸዋል፡፡ ትክክለኛው የትግል ስልት ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ነው ስንል፣ ይህ ስልት ችግር የለውም ማለታችን አይደለም፡፡ ችግር ቢኖረውም መፍትሔው ቃጠሎና ፍንዳታ ሳይሆን በሰላማዊ ትግል አባላትን አሰባስቦ በመንግሥት ላይ ጫና እያደረጉ መታገል ነው ማለታችን ነው፡፡ ኢሕአዴግ ራሱም ስልጣን ላይ የወጣው በትጥቅ ትግል ነው፡፡ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ አይደለም፡፡ ያ ወቅት መደራጀት፣ መቃወምና መወዳደር የተከለከለበት ወቅት ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ከነችግሩም ቢሆን ፓርቲ መፍጠር መቃወምና መወዳደር ይቻላል፡፡ የትጥቅ ትግል እያካሄድን ነን፤ ብለው ከሞቃዲሾም ይሁን ከአስመራ የሚያውጁት ሃይሎች፣ የትግል ስልታቸውን ቀይረው መሣሪያቸውን አስቀምጠው ወደ ሰላማዊና ሕጋዊ የትግል ስልት መግባት አለባቸው፡፡ በበርካታ የዓለም አካባቢዎች ሁኔታዎች እየተለወጡ ሲመጡ የትጥቅ ትግል እናካሂዳለን፤ የሚሉ ድርጅቶች መሣሪያቸውን አስቀምጠው ሰላማዊ የትግል ስልት እየተከተሉ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ትግል ይቁም አንልም፡፡ ይጠናከር ነው የምንለው፡፡ ተቃውሞ አይኑር አንልም፣ ይጠናከር ነው የምንለው፡፡ ተቃውሞው ጠንካራ ሊሆን የሚችለው ግን በሕጋዊና በሰላማዊ የትግል መንገድ ሲጓዝ ነው፡፡ ኦነግ፣ ኦብነግ ወዘተ. የትኛውም ድርጅት ሕይወት ሊያገኝ የሚችለው በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ነውና መሣሪያቸውን አስቀምጠው የትግል ስልታቸውን ሰላማዊና ሕጋዊ ያድርጉ እንላለን፡፡ አልፎ አልፎ በሚያገኙት የዜና ሽፋን ከመፅናናት ይልቅ ሕዝብን በማደራጀት የሚያገኙት ውጤት ላይ ሊያተኩሩ ይገባል፡፡ ..ቅንጅት.. በአሁኑ ጊዜ ሊማረው የሚገባው ትልቁ ነገር ፓርላማ አለመግባትና የከተማውን አስተዳደርን አለመረከብ ስህተት እንደነበረ ነው፡፡ ያለፈው አልፎ አሁን ትግሌን እቀጥላለሁ፤ የሚል የቅንጅት ሰው ከምን ጊዜም በላይ ለሰላማዊና ለሕጋዊ ትግል አፅንኦት መስጠት አለበት፡፡ ይህ በይፋ ሊነገርና ሊዘመርለት ይገባል፡፡ ያለፈውን ስህተት ማረም ብልጠት እንጂ ተሸናፊነት አይደለም፡፡ ብቸኛው መንገድ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ነውና፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |