| በዱቄትና በዱቄት ውጤቶች... |
|
|
| Sunday, 23 March 2008 | |
|
በዱቄትና በዱቄት ውጤቶች ዋጋ ላይ ለውጥ እየታየ ነው
በምግብ እህል ተጥሎ የነበረው የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስ መነሣቱ ዱቄትና የዱቄት ውጤቶች ላይ የዋጋ ለውጥ እየታየ ነው፡፡ የስንዴ አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል አምራቾች ለመንግሥት ላቀረቡት ጥያቄ መልስ እየተጠበቀ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ሚለርስ ኦሶሴሽን ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ 600 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል ዱቄት ወደ 510 ብር ሊወርድ መቻሉንና በተለይ ተጨማሪ እሴት ታክስ ይከፍሉ የነበሩ ማምረቻዎች ክፍያው ስለነተነሳላቸው ዋጋ እየቀነሰ ሲሆን አንዳንድ ዳቦ ቤቶችም እንደዳቦው መጠን የተወሰነ የዋጋ ለውጥ እያደረጉ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የስንዴ እጥረት በመኖሩ በዱቄትና በዱቄት አምራቾች ላይ ስጋት መፈጠሩን በመጠቆም ከሁለት ሳምንት በፊት ለመንግሥት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች አሶሴሽን መልስ እየጠበቀ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ይህንን እጥረት በማስመልከት የኢትዮጵያ ሚለርከ አሶሴሽን ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በፃፈው ደብዳቤ በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የስንዴ አቅርቦት ማነስና በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የስንዴ ዋጋ በዱቄት በፓስታ እና በመሣሰሉት አምራቾች ላይ ስጋ ት በመፍጠሩ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የሚጠይቅ ነው፡፡ የዱቄት፣ የፓስታ፣ የመኮሮኒ፣ የብስኩት፣ የህፃናት ምግቦችና የመሣሠሉትን ፋብሪካዎች በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ሚለርስ አሶሴሽን ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በፃፈው ደብዳቤ እንዳስታወቀው፣ አሁን በተደረሰበት የገበያ ሁኔታ ፋብሪካዎች በጥሬ እቃ እጥረት ምክንያት ተዘግተው ሠራተኞች የሚበተኑበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ስጋት እንዳደረበት ይፋ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ200 ያላነሱ ዱቄትና የዱቄት ውጤቶችን የማያመርቱ ፋብሪካዎች እንዳሉ የጠቀሰው የማህበሩ ደብዳቤ፣ የዘርፉ ዋና ጥሬ እቃ የሆነው ስንዴ በማነሱ ዋጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የዱቄት፣ የዳቦና ሌሎች ተዛማጅ ምርቶች የማምረቻ ዋጋም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱንም ይጠቅሳል፡፡ "ይህም ሆኖ ተፈላጊው ጥሬ ዕቃ በመጠን በአይነትና በጥራት በገበያ ላይ ባለመገኘቱ በቀጣይ ለማምረት የማይቻልበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ ነው" ያለው ይኸው ደብዳቤ፣ ይህ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ማህበሩ ባደረገው ጥናት አስቀድሞ የደረሰበት በመሆኑ ጉዳዩ መንግሥትና ህብረተሰቡ እንዲያውቁት እንዲደረግ አሳስቧል፡፡ አሁን ያለውን ችግር ለማቃለል ይረዳ ዘንድም ማህበሩ ጊዜያዊ መፍትሄ ብሎ ያመነባቸውን ነጥቦች ከደብዳቤው ጋር አያይዞ ለሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ልኳል፡፡ ጊዜያዊ መፍትሄ ያመጣሉ ብሎ ተፈፃሚ እንዲሆኑለት ያቀረባቸውም፡- መንግሥት በእጁ ካለው የመጠባበቂያ የስንዴ ክምችት፣ የመንግሥት እርሻዎች አምርተው በመጋዘናቸው ከሚገኘው በኅበረት ሥራ ዩኒዮኖች መጋዘን ከሚገኘው የስንዴ ክምችት አምራቹን በማይጎዳ መልኩ ለማኅበሩ አባላት እንዲሸጥ የሚሉ ናቸው፡፡ ከሚኒስትሩ አካባቢ ከተገኙ ምንጮች መረዳት እንደተቻለው፣ ማህበሩ ያቀረባቸውን እነዚህን ጥያቄዎች በአዎንታዊ መልክ ማስተናገዱ አስቸጋሪ እንደሚሆን በተለይ በዩኒዮኖችና በእርሻ ሰብል መጋዘኖች ያለው ስንዴ በጨረታ የሚሸጥ በመሆኑ ይህንን አሰራር ማስቀረት አይቻልም፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |