| የሸማቾች ማኅበር ሲሮጡ የታጠቁት እንዳይሆን |
|
|
| Sunday, 23 March 2008 | |
|
የሸማቾች ማህበራት አስፈላጊነትን በተመለከተ መጋቢት 9 ቀን 2000 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርታቸው በሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ እርሳቸው ፓርላማ ቀርበው በዚህ ጉዳይ ከመናገራቸው ቀደም ብሎ በየቀበሌው የአመራር አባላት በኩል የሸማቾች ማህበር ለመመስረት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነበር፡፡
ይህ የሚያሳየው መንግሥት የሸማቾች ማህበር መመስረት አስፈላጊነት ላይ አምኖበታል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋው የኑሮ ውድነት ስር እየሰደደ በመምጣቱ ቢሳካም ባይሳካም ችግሩን ለማቃለል የተለያዩ አማራጮች እየተሞከሩ ነው፡፡ የሸማቾች ማህበር አስፈላጊነት ላይ የትኛውም ወገን ተቃውሞ ይኖረዋል አልልም፡፡ ነገር ግን እነዚህን ማህበራት ለማቋቋም ጥድፊያ የተጀመረው በዚህ ወቅት መሆኑ አንድ የሸማች ማህበር ሊተገብራቸው የሚችሉ ዋና ዋና ተግባራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ በለፀጉ በምንላቸው አገራት ያሉ የሸማቾች ማህበራት ሲቋቋሙ መነሻ የሚያደርጉት የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ብቻ ወይም በአገራቸው የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማስተንፈስ ብለው አይደለም፡፡ የኑሮ ውድነት ተከሰተም አልተከሰተም የሸማቾች ማህበር አስፈላጊ መሆኑን በማመናቸው ጭምር ነው፡፡ በአገራችን ግን በጥድፊያ ማህበራት እንዲመሠረቱ የተፈለገው ወቅታዊውን የኑሮ ውድነት ለማቃለልና መንግሥት ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ እየተወረወረበት ያለውን ቀስት ለመከላከል ይመስላል፡፡ መንግሥት በየአካባቢው የሸማቾች ማህበር እንዲመሠረት ፍላጐት ማሳየቱና ለዚህም ድጋፍ ለማድረግ መነሳሳቱ መልካም ነው፡፡ የአመሠራረቱ ሂደት ግን በዘመቻ መልክ እንዲሆን መደረጉና የማኅበሩ አስፈላጊነት ለጊዜያዊ ችግር ማቃለያ ተብሎ በቀረበ ንድፈ ሃሳብ መንደርደሩ ሩቅ አስቦ ቅርብ እንዳያድር እሰጋለሁ፡፡ በየቀበሌው ያሉ አመራሮች ወይም ሌላ አካላት የሸማቾች ማህበር ለማቋቋም ነዋሪውን የመመዝገቢያ፣ የአባልነት ወዘተ. እያሉ ክፍያ እየጠየቁ መሆናቸው መሰማቱ በራሱ ሌላ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ በማህበሩ አስፈላጊነት በመተማመንና የመንግሥት ፍላጐት በይፋ በተገለፀበት በዚህ ጉዳይ ላይ ህብረተሰቡ ስለሸማቾች ማህበር ያለው ግንዛቤ ገና መሆኑ እየታወቀ መሆኑ በምንገምትበት በዚህ የሸማቾች ማህበር ልናቋቁም ስለሆነ ገንዘብ አምጡ ማለት ተገቢ መስሎ አይታየኝም፡፡ ሥራውን ለመሥራት ገንዘብ አያስፈለግም ማለት ሳይሆን መቅደም ያለባቸው ስራዎች መሆራቸውን ግምት ውስጥ እንዲገባ ነው፡፡ የሸማቾች ማህበር ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገ እንዲያገለግል፤ የዛሬ ኑሮ ውድነትን ለማቃለል ብቻ ሳይሆን የአንድ ሸማች ማህበር ሙሉ ተግባራትን ለማስረፅ እንዲችል ከወዲሁ ታስቦበት ካልተሠራ የአንድ ሰሞን ግርግር ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ ስንዴና ዘይት ማደልን ዋንኛውን የሸማቾች ማህበር ተልዕኮ ትርጉም እንዳያዛባውም ልናስብበት ይገባል፡፡ እነዚህን ማህበራት ለማዋቀር የማስተባበር ሥራውን እየሠሩ ያሉት የቀበሌ ወይም እንደ እድር ያሉ የአመራር አባላት ብቻ ስራውን መተው ጠንካራ የሸማቾች ማህበር እንዲኖር አያስችልም፡፡ ማህበሩ ነፃ ሆኖ መመስረቱ ተገቢ ቢሆንም እነዚህ አካላት ስለሸማቾች ማህበር ያላቸው እውቀት ምን ያህል ነው? ብሎ ማሰብም ያስፈልጋል፡፡ ህብረተሰቡም የሸማቾች ማህበር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ በሆነ ቋንቋ ሊነገረውና አስፈላጊነቱን እንዲያምንበት የሚያስችል ሥራም መሠራት አለበት፡፡ ሕዝቡ በዚህ ዙሪያ ያለው ግንዛቤ እንዲሰፋ ካልተደረገና የሸማቾች ማህበር ተግባራት ሰፊ መሆኑን የሚያስረዱ ባለሙያዎች በዚህ ሥራ ውስጥ አንዲገቡ እና አቅጣጫ እንዲጠቁሙ ማድረግ እስካልተቻለ እንዲሁም እያንዳንዱ ማህበር የአጭርና የረዥም ጊዜ ግቡን የሚያሳይ መሪ እቅድ በግልፅ አስቀምጦ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ቅድሚያ እስካልተሰጠው ትክክለኛ የሸማቾች ማህበር ለመፍጠር ያስቸግራል፡፡ የሸማቾች ማህበር የሸማቹን መብት የሚያስጠብቅ እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ ምርቶችን ጥራት የመቆጣጠር ኃላፊነትን የሚሸከም ጭምር በመሆኑ አሁን ልንመሰርታቸው የምንፈልጋቸው የሸማቾች ማህበራት ራእይ ዘርፈ ብዙ እንዲሆንና ነገም የምንገለልበት እንዲሆን ለማስቻል በቂ ዝግጅት መደረግ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ዘርፍ እውቀት ያላቸው ወገኖችክፍያ ጠይቀው ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ ጥሩ የሚባል ማህበር እንዲቋቋም ማድረግም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ማህበራቱን ለጊዜያዊ ችግር ማቃለያ ሳይሆን ዘላቂ ሆነው ነገ ተነገ ወዲያ ሊከሰት የሚችለውን ችግር ለመቅረፍም የሚኖራቸው ሚና ትልቅ በመሆኑ ጉዳዩ ታስቦበት ቢሠራና አሁንም ማህበራት ለማዋቀር በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ አካላት ሙያዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ያስፈልጋል፡፡ በናታን ዳዊት |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |