Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
May 09th
Home arrow Sections arrow "ከምግብ ላይ ቫት እንዲነሳ ካለፉት...
"ከምግብ ላይ ቫት እንዲነሳ ካለፉት... Print E-mail
Sunday, 23 March 2008
Image"ከምግብ ላይ ቫት እንዲነሳ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ስንጠይቅ ነበር"
አቶ ጣሰው ኃይሌ

አቶ ጣሰው ኃይሌ የምስራቅ ዱቄትና ዳቦ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የኢትዮጵያ ዱቄት አምራቾች ማኀበር ሥራ አስፈፃሚ ፀሐፊ ናቸው፡፡ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በምግብ ቴክኖሎጂ ካጠናቀቁ በኋላ ላለፉት 2ዐ ዓመታት በተለያዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ፍሬው አበበ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት የአንድ ኩንታል ስንዴ ዱቄት አማካይ የገበያ ዋጋ ምን ያህል ነው? ባለፉት ሦስት ዓመታት የስንዴ ዱቄት ዋጋ በምን ያህል አድጓል?

አቶ ጣሰው፡-
በአሁኑ ሰዓት የስንዴ ዱቄት አማካይ የገበያ ዋጋ ከብር600 እስከ 680 አካባቢ ነው፡፡ ይሄ ቫትን ሳይጨምር ማለት ነው፡፡ የእኛ የመንግሥት የልማት ድርጅት ስለሆነ አንድ ኩንታል የምንሸጥበት ዋጋ ያለቫት ብር 588 ነው፡፡ ሌላው ባለፉት ሦስት ዓመታት የስንዴ ዱቄት ዋጋ ስንመለከት ከግብአቱ (ከስንዴ ዋጋ) ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የስንዴ ዋጋ መጨመር የዱቄት ዋጋ ከዓመት ዓመት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሦስት ዓመት አንድ ኩንታል ስንዴ ዱቄት ገበያ ላይ ከ3ዐዐ እስከ 35ዐ አካባቢ ይገኝ ነበር፡፡ የስንዴ ዋጋ ከ170 እስከ 180 ብር ይገኝ ነበር፡፡ በ1998 ዓ.ም. አካባቢ የስንዴ ዋጋ መጨመር የዱቄት ማምረቻ ዋጋ ላይ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በ1998 ዓ.ም. አንድ ኩንታል ዱቄት ከ350 እስከ 390 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ የስንዴ ዋጋ እየጨመረ መምጣት ጋር በተያያዘ በአሁኑ ሰዓት ገበያ ላይ ከ600 እስከ 680 አካባቢ እየተሸጠ ያለበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በዱቄት ላይ የታየው ጭማሪ ከሃምሳ በመቶ በላይ ነው፡፡ በቁጥር አስደግፌ ብነግርህ የዛሬ ሦስት ዓመት በ1997 ዓ.ም. በስንዴ በኩንታል እንገዛ የነበረው ከ180 እስከ 210 ብር ነበር፡፡ በቀጣዩ ዓመት ወደ 60 በመቶ ጨምሮ ከ280 እስከ 300 ብር ደርሷል፡፡ በተለይ የዘንድሮው ዓመት ካለፈው ዓመት ለውጡ ከፍተኛ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የስንዴ ዋጋ እየጨመረ መምጣት በተለይ በአምራቹ ላይ የፈጠረው ችግር በተጨባጭ ምንድነው?

አቶ ጣሰው፡-
ለዱቄት ምርት አስፈላጊ በሆነው ስንዴ ላይ በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የዋጋ ንረት አምራቹ ላይ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን ፈጥሯል፡፡ አንደኛ ለአምራቹ በቂ የሆነ የሥራ ማስኬጃ እጥረት ፈጥሯል፡፡ ለምን ቢባል ለግብአቶቹ መግዣ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በማስፈለጉ ነው፡፡ አምራቹ እንደቀድሞው በበቂ መጠን ገዝቶ ስቶክ መያዝ አይችልም፡፡ በዚህ ምክንያት የሥራ ማስኬጃ፣ የገንዘብ እጥረት እየፈጠረበት ይገኛል፡፡ ሌላው ዋጋው ውድ የሆነ ስንዴ አምራቹ ገዝቶ፣ አምርቶ ወደ ገበያ ሲያውል የመጨረሻ የምርት ዋጋ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል የህብረተሰቡ የመግዛት አቅም እየተዳከመ መምጣት የሽያጭ መጠኑ እንዲቀነስ ምክንያት ሆኗል፡፡ ሌላውና ሦስተኛው ምክንያት አምራቹ በውድ ዋጋ ስንዴ ገዝቶ፣ አምርቶ ገበያ ላይ ወስዶ ሲሸጥ ፍትሐዊ የገበያ ውድድር ያለመኖሩ ችግር ፈጥሮበት ቆይቷል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት አሁን ያነሳው ተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) እና ተርን ኦቨር ታክስ አምራቹ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል ትላላችሁ? ለህብረተሰቡስ በምታቀርቡት ዋጋ ላይ ለውጡ ምን ይሆናል?

አቶ ጣሰው፡
- መንግሥት በምግብ እህል ላይ ቫት እና ተርን ኦቨር ታክስ አንስቷል፡፡ ይኼ እርምጃ ጥሩ እና ለረጅም ጊዜ ስንጠብቀው የነበረ ነው፡፡ ይኼ ሁኔታ በአንድ በኩል አምራቹን፣ በሌላ በኩል ህብረተሰቡን የሚጠቅም ለውጥ ያመጣል፡፡ ለምን ቢባል ለአምራቹ የመሸጫ ዋጋውን ይቀንስለታል፡፡ ነገር ግን የመንግሥት፣ የግል፣ ከውጪ የሚያስመጡትን እኩል የመወዳደሪያ መድረክ ይፈጥራል፡፡ ከዚህ በኋላ እኛ አምራቾች የምንወዳደረው ቫትን በመክፈልና ባለመክፈል ሳይሆን በምናመርተው ምርት ጥራት ይሆናል፡ ይሄ ደግሞ ለዘርፉ ዕድገት፣ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው ትልቅ ጥቅም ይሰጣል፡፡ የቫት መነሳት ቀደም ሲል ለምሳሌ በኩንታል 575 ብር እንሸጥ የነበረውን ዱቄት በ500 ብር ማቅረብ ያስችላል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም በማህበራችሁ በኩል በተደጋጋሚ መንግሥት በዱቄት አምራቾች ላይ የጣለውን ቫት እንዲነሳ ስትጠይቁ ነበር፡፡ መነሻችሁ ምን ነበር?

አቶ ጣሰው፡-
ቀደም ሲል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የግል አምራቾች በማህበር ተደራጅተን አንደኛ ምግብ ላይ ቫት 15 በመቶ መሆኑ፣ ህብረተሰቡን በጊዜ ሂደት ሊጎዳው ይችላል፡፡ ይኼ ምግብ ነው፡፡ ዱቄት፣ ዳቦ፣ ብስኩት የሚገዛው ደግሞ አብዛኛው የከተማ ሕዝብ ነወ፡፡ የከተማ ሕዝብ ሠርቶ ደሞዝ ሲያገኝ ግብር ከፍሎ እንደገና የሚመገበው ላይ 15 በመቶ መክፈሉ ተገቢ አይደለም፣ ይጎዳዋል፡፡ ቫትን በሚመለከት ሌሎች አገሮች በተለያየ ደረጃ የሚያስከፈሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንዳንዶቹ እስከ 5 በመቶ የሚያስከፍሉ፣ ሌሎች ደግሞ ምግብ ላይ የሚደጉሙ አገሮች አለ፡፡ ይኼ ነገር መጀመሪያ አምራቹን፣ ቀጥሎ ሸማቹን፣ መንግሥትንም ሊጎዳ ይችላል በሚል ከሦስት ዓመት ያላነሰ ተከታታይ እንቅስቃሴዎችን በማህበራችን በኩል አድርገን ነበር፡፡ በአንድ ወቅትም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ስብሰባ ጠርተውን ይሄንኑ ሃሳባችንን ሰጥተን ነበር፡፡ በወቅቱ ቫት ከምግብ ላይ ቢቻል ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ፣ ካልተቻለ ክፍያው ከ5 በመቶ ባይበልጥ የሚል ሃሳብ አቅርበናል፡፡ በተጨማሪም ገበያውን ፍትሃዊ እንዲሆን ጠይቀናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ገበያው ፍትሀዊ እንደሚሆን፣ የታክሱም መነሳት ጉዳይ እንደሚጠና በገለፁልን ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ መነሳቱ ጥሩ ነው፡፡ አስፈፃሚ አካላትን ማለትም ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴርንም በተደጋጋሚ በጉዳዩ ላይ ስናነጋግር ቆይተናል፡፡ የአሁኑ ውጤት ህብረተሰቡን ጨምሮ የሁሉም ትግል ውጤት ነው፡፡ በውጤቱም የኢትዮጵያ ዱቄት አምራቾች ማህበር አባላትና ሠራተኞች ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል፡፡

ሪፖርተር፡- የቫት መነሳት ብቻውን በርግጥም በዋጋ ላይ ዘላቂ ለውጥ ያመጣል ብላችሁ ታስባላችሁ?

አቶ ጣሰው፡-
እንግዲህ ይሄ የሁላችንም ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ እንደ አንድ የመንግሥት ልማት ድርጅት አምራች የምንናገረው የዱቄት ምርት ከእኛ ለሚገዛ የቅናሹ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ዱቄት ቫትን ጨምረን 660 ብር በኩንታል የምንሸጠውን፣ ቫትን ቀንሰን 590  ብር ስንሸጥ ህብረተሰቡ 65 ብር ቅናሽ አገኝ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ሌሎች አምራቾች ጋር ይሄ ነገር በትክክል ይተገበራል ወይ የሚለው በሂደት የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ በተለይ በዚህ ላይ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ማለትም ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የመሳሰሉት እንዲሁም በየቀበሌው የሸማቾች የህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታ ከተፈጠረ ጥሩ ውጤት ማግኘት ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የዱቄት ዋጋን የስንዴ አቅርቦቱና ዋጋ አይወስነውም?

አቶ ጣሰው፡-
ትክክል ነው፡፡ ቫት እና ተርን ኦቨር ታክስ ማንሳቱ እንደ ሁለተኛ መፍትሄ የሚወሰድ ነው የሚመስለኝ፡፡ ዋናው ነገር የአቅርቦትና የፍላጎት ልዩነቱ ከፍተኛ ከሆነ እንደዘላቂ መፍትሄ ይሠራል ብሎ ለመገመት ያስቸግራል፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት አፈፃፀሙ ላይ ክትትል ካለ በጊዜያዊነት ችግሩን ሊቀርፍ ይችላል፡፡ ዋናው ግን የስንዴ አቅርቦት ወሳኝ ነወ፡፡ የስንዴ አቅርቦት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ገበያ ላይ የተፈጠረ ችግር አለ፡፡ የስንዴ ዋጋ ከነዳጁ ጋር ተያይዞ በዓለም ገበያ ላይ ጨምሯል፡፡ በሀገራችን በየዓመቱ የሚመረተው የስንዴ መጠን ከሕዝብ ፍላጎትና ዕድገት ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዱቄት አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ 19ዐ ደርሰዋል፡፡ የፋብሪካዎቹ የስንዴ ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡ እንደአምራች ስናስበው ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው የስንዴ አቅርቦት መጠን በሀገር ውስጥ ማሳደግና የአቅርቦት መጠኑንም ፍትሃዊ ማድረግ ሲቻል ይመስለናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ሰዓት በተጨባጭ በቂ የሚባል የስንዴ አቅርቦት በገበያ ላይ አለ?

አቶ ጣሰው፡-
በአሁኑ ሰዓት ባለን መረጃ መሠረት በገበያ ላይ በቂ አቅርቦት የለም፡፡ እጥረት አለ፡፡ የስንዴ ውጤት የሆነው ዱቄት ደግሞ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፡፡ የእነዚህ የሁለቱ ተጣጥሞ አለመሄድ፣ የፍላጎት መጨመር፣ የአቅርቦቱ ማነስ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ሌላው በአሁን ሰዓት አምራቹ ገበሬው ጋር፣ የኀብረት ሥራ ማኀበራት ጋር፣ የመንግሥት እርሻዎች ጋር ያለውን ምርት መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ ለፋብሪካዎች የሚያከፋፍልበት ሁኔታ ቢኖር ችግሩን ሊያቃልል ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- 190 ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው ቢያመርቱ የኢትዮጵያን የዱቄት ምርት ፍላጎት ሊያሟሉ ይችላሉ? በዚህ በኩል የተሠራ ጥናት ይኖር ይሆን?

አቶ ጣሰው፡-
በዚህ ላይ የተሠራ ጥናት የለም፡፡ ነገር ግን በዘርፉ ውስጥ ለረጅም ጊዜ እንደመኖራችን፣ በሥራውም ባህሪይ አንፃር መረጃዎችን ስለምንከታተል እነዚህ 190 ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ቢያመርቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዱቄት ፍላጎት ያሟላሉ የሚል ግምቱ አለን፡፡ ያሉትም የማምረት አቅማቸው ከ150 ኩንታል እስከ 1ዐዐዐ ኩንታል ነው፡፡ ምናልባት በቀን ወደ 8ዐዐ እና 1ዐዐዐ ኩንታል የሚያመርቱት ፋብሪካዎች ከ3ዐ አይበልጡም፡፡

ሪፖርተር፡- የተዘጉ የዱቄት ፋብሪካዎች አሉ?

አቶ ጣሰው፡-
አዎ" በዱቄት አምራቾች ማኀበር መረጃ መሠረት ከ60 በላይ ዱቄት አምራች ፋብሪካዎች ተዘግተዋል፡፡ የተዘጉት ትልቁ ምክንያት በስንዴ እጥረት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን መንግሥት በወሰደው እርምጃ ዱቄት አስመጪዎችም ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ይኸ መሆኑ የአገር ውስጥ አምራቹን ይጎዳ ይሆን?

አቶ ጣሰው፡-
አሁን ባለው ሁኔታ ዱቄት አስመጪዎችላይም ቫት መነሳቱ የአገር ውስጥ አምራቹን የሚጎዳበት ሁኔታ የለም፡፡ ፋብሪካዎቻችን ጥሬ እቃ አጥተው ማምረት እስካቆሙ ድረስ ከውጭ አስመጥተው ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ቢያቀርቡ ጥሩ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- የስንዴ ምርት ከውጪ ሀገር ለማስመጣት ለምን አልሞከራችሁም?

አቶ ጣሰው፡-
በአሁኑ ሰዓት ባለሀብቶች ተደራጅተን ስንዴ ከውጭ ሀገር እናስመጣ ብንል ጅቡቲ ወደብ እስኪደርስ በኩንታል ከ5ዐዐ እስከ 6ዐዐ ብርዋጋ ይፈጃል፡፡ ይኼ ስንዴ አዲስ አበባ ሲገባ 6ዐዐ ብር የሚደርስ ከሆነ፣ ይኼ ተመርቶ ገበያ ላይ ሲወጣ ዋጋው በጣም ከፍ ይላል፡፡ ስለዚህ ለጊዜው ስንዴ ማስመጣቱ አዋጪ መስሎ አልታየንም፡፡ ነገር ግን በዓለም ገበያ ላይ የስንዴ ዋጋ የሚቀንስ ከሆነ ወደፊት የሚታይ ሁኔታ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን የማያበረታታ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት እርሻዎች በቂ የስንዴ ምርት አላቸው?

አቶ ጣሰው፡-
በመንግሥት ከሚገኙ እርሻዎች መካከል ስንዴ የማያመርቱት አርሲ እና የባሌ እርሻ ልማት ድርጅቶች ናቸው፡፡ በዘንድሮ ዓመት ከሁለቱም የተገኘው 450 ሺህ ኩንታል ምርት መሆኑን በመገናኛ ብዙሃን ለመረዳት ችለናል፡፡ ይኼ ማለት ካሉት ዱቄትአምራች ፋብሪካዎች ማለትም በቀን ከ1ዐዐዐ እስከ 15ዐዐ ኩንታል ዱቄት ለሚፈጩት ለምሳሌ ለእኛ ፋብሪካ፣ ለቃሊቲ ምግብ ፋብሪካ እና ለድሬዳዋ ምግብ ኮምኘሌክስ ብቻ እንኳን ለዓመት ፍጆታ አይበቃም፡፡

ሪፖርተር፡- በሸማቹ ኀህረተሰብ ዘንድ ብዙውን ጊዜ የአገር ውስጥ ፍርኖ ዱቄት ጥራት ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፡፡ ማኀበሩ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለው?

አቶ ጣሰው፡-
የማኀበሩ አባላት 6ዐ አካባቢ ነን፡፡ ከነዚህ መካከል 9ዐ በመቶ ያህሉ የሚያመርቱት ዱቄት ሲሆን ቀሪዎቹ ዱቄትን እንደግብአት ተጠቅመው ብስኩት፣ ዳቦ፣ ፓስታ፣ መኮረኒ የማያመርቱ አሉ፡፡ ጥራትን በተመለከተ ሁሉም በእኩል ደረጃ ለህብረተሰቡ ያቀርባሉ ለማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም ጥራትን የሚወስኑ ነገሮች አንዱ ግብዓቱ ነው፡፡ የስንዴ ግብዓቱ አንድ ወጥ ከሆነ ከዚህ ግብዓት የሚሠሩት ፓስታ፣ መኮረኒ፣ ብስኩት፣ ዳቦ፣ ዱቄት ጥራት ይኖራቸዋል፡፡ ሌላው ደግሞ ጥራትን የሚወስነው የፋብሪካዎቹ የአመራረት ሂደትና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የባለሙያ ሁኔታ ነው፡፡ አንድ አምራች በቂ የሆነ ባለሙያ፣ ክትትል፣ መሳሪያ (ቴክኖሎጂ) ከሌለው ጥራት ያለው ምርት ሊያመርት አይችልም፡፡ ይሄን በሚመለከት የማኀበሩ አባላት በተገናኘን ቁጥር እንነጋገራለን፤ እንወያያለን፡፡ ሌላው ከዚህ ውጪ ጥራትን የሚወስነው የማምረቻ እና የመሸጫ ዋጋ ነው፡፡ የማምረቻ ዋጋ ከፍተኛ ከሆነ አምራቹ ጥራቱ ዝቅተኛ የሆነ ግብዓቶችን ሊጠቁም ይችላል፡፡ ለምሳሌ ዳቦን ለማምረት ዱቄት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ዱቄቱ የቱንም ያህል ጥራት ቢኖረው ከዱቄቱ ጋር የሚያስፈልገው እርሾ፣ የዳቦ ማሻሻያ፣ ጨውና ዘይት የመሳሰሉት በዋጋ ውድነት አምራቹ ዝቅተኛ የሆነውን ምርት የሚጠቀም ከሆነ ጥራት ላይ ተፅእኖ ያደርጋል፡፡ ይሄን በሚመለከት ከሚመለከታቸው አካላት ማለትም ጥራትና ደረጃዎች ባለሥልጣን፣ ከጤና ጥበቃ ጋር ማኀበሩ ተባብሮ የሚሠራበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ዳቦ ከጊዜ ወደ ጊዜ በግራም መጠኑ እያነሠ፣ ዋጋው እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እንደአንድ ዳቦ አምራች ድርጅት በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?

አቶ ጣሰው፡-
ካሉት የመንግሥት ፋብሪካዎች የእኛ ፋብሪካ ዳቦ በቀን እስከ 5ዐ ኩንታል ዳቦ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ለመንግሥታዊ ሆስፒታሎች፣ ለሌሎች የትምህርት ተቋሞች፣ ለኀብረተሰቡ ባሉን ዘጠኝ መሸጫ ሱቆች በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ዳቦ እንሸጣለን፡፡ ከስንዴ መወደድ ጋር በተያያዘ የማምረቻ ዋጋችን ስለጨመረ ከመክሰር፣ ከመዘጋት የዳቦ መሸጫ ዋጋችን ላይ ተመጣጣኝ ጭማሪ አድርገናል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ዋጋ ብቻ ሳይሆን ግራሙንም ከ5ዐ ግራም በታች የማውረድ እርምጃ ወስደዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ተጎጂው ኀብረተሰቡ ነው፡፡ ድሮ አንድ ሕፃንልጅ የ0.25 ዳቦ ቁርሱን በልቶ ይሄድ የነበረው በአሀኑ ሰዓት ያ ዳቦ በ0.50 ሳንቲም ገደማ ቢገኝ ነው፡፡ ላይገኝም ይችላል፡፡ይሄን በሚመለከት በሀገራችን ትንሹ ዳቦ መሸጥ ያለበት በሚል ጥራትና ደረጃዎች ባለሥልጣን ያስቀመጠው 50 ግራም ነው፡፡ እኛም የምናቀርበው ይሄንኑ ነወ፡፡ ችግሩ ግን የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት የሚሸጠው ትንሹ ዳቦ 5ዐ ግራም ነው ወይ ብለው አልተቆጣጠሩም፡፡ ከ5ዐ በታች የሚሸጡ አሉ፡፡ መጀመሪያ መንግሥት የግራም መጠኑን ማስከበር አለበት፡፡ ከዚያ በታች የሚሸጠው ላይ እርምጃ መውሰድ ነው፡፡ ወደ ዋጋው ስንሄድ 1ዐዐ ግራም ዳቦ ለማምረት ትንሽ የጎጆ ኢንዱስትሪ፣ መካከለኛ ማሽን ይዞ ከ1ዐ እስከ 15 ሠራተኛ ይዘው የሚጋግሩ፣ እንደ እኛ ደግሞ ከ100 እስከ 15ዐ ሠራተኞችን ይዞ የሚጋግረው ለአንድ ኪሎ ግራም በአሁኑ ሰዓት ስንዴ 42ዐ ብር በኩንታል ቢሆንና ዱቄት 58ዐ ብር ቢሆን ስንት ነው የማምረቻ ዋጋ ብሎ ማነፃፀሪያ ስታንዳርዶችን መሠራትና መታወቅ አለበት፡፡ ይኸ ከታወቀ እዚህ ላይ ስንት ጨምሮ አንደኛ ዳቦ አምራቾች በየመንደሩ ያሉት፣ ሁለተኛ ዳቦ አምራች እንደእኛ ዓይነት በስንት መሸጥ አለበት የሚለውን መቆጣጠር ይችላል፡፡ ይኼ ቴክኒካል የባለሙያዎች ሥራ ስለሆነ እንደ እኛ ዓይነት አምራቾች እና ማኀበር ጋር የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር ተቀራርበን ብንሠራ ጥሩ ውጤት ማግኘት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የምሥራቅ ዱቄትና ዳቦ ፋብሪካ መቼና እንዴት ተመሠረተ?

አቶ ጣሰው፡-
ምስራቅ የዱቄትና ዳቦ ፋብሪካ ከተመሠረተ 45 ዓመታት ሆኖታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ድርጅቱ 3ዐዐ ቋሚና 3ዐ ጊዜያዊና ኮንትራት ሠራተኞች አሉት፡፡ ከምርቶቹም 6ዐ በመቶ ያህል የሚይዘው የዳቦ ምርት ነወ፡፡ ምርቱንም ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ለሆስፒታሎችና ለኀብረተሰቡ በየዕለቱ ያቀርባል፡፡ ሌላው ብስኩት ነወ፡፡ ብስኩትንም እያመረተ ለመከላከያ፣ ለፌደራል ፖሊስ፣ ለወህኒ ቤቶች በትዕዛዝ ያቀርባል፡፡ ሌላው ዱቄት ለመንግሥታዊ ድርጅቶች፣ ለኀብረተሰቡ ደግሞ በ5 ኪሎ፣ በ1ዐ ኪሎ፣ በ15 ኪሎ እያደረግን በቀጥታ ሽያጭ እናቀርባለን፡፡ ለተለያዩ ዳቦ ቤቶችም እናቀርባለን፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ እያመረተ ነው?

አቶ ጣሰው፡-
ድርጅታችን በአሁኑ ሰዓት በሙሉ አቅሙ እያመረተ አይደለም፡፡ ከአቅሙ 5ዐ በመቶ ያህል አቅሙ ነው እየሠራ ያለው፡፡ ምክንያቱም የጥሬ እቃ (የስንዴ) እጥረት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
 
< Prev   Next >