| "ወገኑን የሚረዳውን ዲያስፖራ... |
|
|
| Sunday, 23 March 2008 | |
"ወገኑን የሚረዳውን ዲያስፖራ መንከባከብና መርዳት ያስፈልጋል"ዶ/ር ሙሉጌታ በዛብህ የአርኤክስ አፍሪካ ኢትዮ አሜሪካ ፋርማሲቱካል ዋና ሥራ አስፈፃሚና የቦርድ አባል አርኤክስ አፍሪካ ኢትዮ-አሜሪካ ፋርማሲቱካል የተቋቋመው ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከቻይና መንግሥት ጋር ሽርክና ነበራቸው፡፡ አብረው ለመቀጠል ስላልቻሉ ከአሜሪካኖች ጋር በመሆን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከአሜሪካ ባለሃብቶች ጋር መስራት ብቻ ሳይሆን በእነሱ ጥረት በአሁኑ ጊዜ ዎል ስትሪት በሚባል ኒውዮርክ በሚገኘው የአለም የካፒታል ገበያ ውስጥ ገብተው አክሲዮኖቻቸውን በገበያው እየተሸጡ ይገኛሉ፡፡ በግሎባላይዜሽን የስራ ዘመን በዚህ የንግድ ማዕከል ገብቶ የመስራት እድል ያጋጠመው ድርጅት በአፍሪካ ውስጥ ይህ ብቻ ነው፡፡ ዶ/ር ሙሉጌታ በዛብህ ደግሞ የአርኤክስ አፍሪካ ኢትዮ-አሜሪካ ፋርማሲቱካል ዋና ሥራ አስፈፃሚና የቦርድ አባል ሲሆኑ ቆይታቸውን በአሜሪካ በማድረግ ለ25 አመታት ያህል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰርተዋል፡፡ ዶ/ር ሙሉጌታ እንደገለፁልን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩትን የመድሃኒት ማምረት ዘርፍ ወደ ሌሎች የአፍሪካና ለመድሃኒቶቻቸው ከፍተኛ ዋጋ ሊሰጡ ወደሚችሉ አገሮች የማስፋፋት አላማ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መንቀሳቀስ ከጀመሩ ሶስት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ሆኖም አንድን ድርጅት ድርጀት የሚያሰኘው መንቀሳቀሱ ብቻ አይደለም ይላሉ፡፡ ብዙ የፖሊሲ ችግሮች አጋጥሟቸዋል፡፡ በተለይ በኢንዱስትሪው ገና ግልፅ ያልሆነ ከአለማቀፍ የአሰራር ሥርዓት ጋር አብሮ የማይሄድ መሰናክሎች እንዳሉ ይገልፃሉ፡፡ እነዚህ መሰናክሎች ላይ መንግሥት የማሻሻያ ፕሮግራም ያወጣል የሚል እምነት በመያዝ በኢትዮጵያ እየሰሩም ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ መድሃኒቶቻቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ ከቻይናዎች ጋር የነበራቸው ግንኙነት ጥሩ ስላልነበረ በስድስት መድሃኒቶች ላይ ብቻ ነበር ምርታቸው ያተኩር የነበረው፡፡ ከአሜሪካኖቹ ጋር ከጀመሩ በኋላ ግን በአፍሪካ ከፍተኛ የሆነ የምርምር ማዕከል ለማቋቋምም ግንባታውን ጨርሰዋል፡፡ የተሟላ ቴክኖሎጂ ይዞ መድሃኒቶች ላይ ምርምር የሚካሄድበትም ይሆናል፡፡ በምርምር ማዕከሉ አማካይነት ብዙ መድሃኒቶች ይዘው ወደ ገበያ ለመቅረብም አላማ አላቸው፡፡ ዲያስፖራ ማነው ብሎ መጀመሪያ መጠየቅ ያስፈልጋል የሚሉት ዶ/ር ሙሉጌታ ሁሉም ዲያስፖራ አንድ አለመሆኑን ያብራራሉ፡፡ ለወገኑ የሚቆረቆር ዲያስፖራ አለ፡፡ ይህ ወገን አገሩን የሚወድ ነው፡፡ ተመልሶም በአገሩ መስራት የሚፈልግ ነው፡፡ ለተወለዱባት አገር ስሜት ያላቸው፣ ለደሃው ህዝብ የሚያስቡ፣ ግብር እየከፈሉ ላሳደጋቸው ሕዝብ ውለታ የሚከፍሉ አሉ፡፡ ይህ ወገን ወደ አገሩ ተመልሶ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነው፡፡ በሌላ በኩል ያለው ዲያስፖራ የእለት እንጀራ የሚፈልግ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከተሰማራበት ሥራ ውጪ ፖለቲካውን እያየ ብዙ ውዥንብር ውስጥ የገባም አለ፡፡ በፖለቲካ መስክ ዲያስፖራው አይሰማራ ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም ፖለቲካና ቢዝነስ አብሮ የማይሄዱበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ይሄኛው የዲያስፖራ ወገን የራሱ የሆነ የፖለቲካ አቋም ቢኖረውም ሃብት አለው፡፡ እነዚህን በማሳመን አገራቸው የሚመጡበትን መንገድ ማመቻቸት የመንግሥትና የዜጎች ግዴታ ነው፡፡ የትኛውም አገር የፖለቲካ አለመግባባት ሊኖር ይችላል፡፡ ሆኖም ለልማት ስራ መስራት በሕይወት ትልቁ አስተዋፅዖ ነው፡፡ ጊዜውን ተጠቅሞ በልማቱ የሚሰማራውንና ደሃ ወገኑን የሚረዳውን ዲያስፖራ መንከባከብና መርዳት ይገባል፡፡ ሌላኛው ዲያስፖራ ደግሞ ምንም ቢደረግለት አገሩን በመልካምና በጥሩ ዝና የማያነሳ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ባሉበት የራሳቸውን ኑሮ እየኖሩ ቢቀሩ ይሻላል፡፡ በልማቱ ረገድ መሻሻል ያለባቸው ፖሊሲዎች አሉ፡፡ መሰረታዊው ችግር ቀረብ ብሎ አለመነጋገር ነው፡፡ አሁን ያለው መንግሥትም ቢሆን የብዙ ጊዜ የልማት ልምድ ያለው መንግሥት አይደለም፡፡ ሆኖም የልማት ጅማሮ አለ፡፡ እስካሁን በአገራችን የነበረው ስልጣን በአንድ ቦታ ተከማችቶ ጥቂት ሰዎችን ብቻ የሚያሳትፍ ነበር፡፡ በአሁኑ የፌዴራል ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ሆኖም የፌዴራሊዝም ሥርዓት በራሱ የሚሻሻልበት ብዙ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ሥራውና አቅጣጫው ተጀምሯል፡፡ በአጭር ጊዜ የሚያልቅ ግን አይደለም፡፡ ለዜጎች መድረኩ እየሰፋ፣ የመወያየት መንፈሱ እየዳበረ ቢቀጥል ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳደግ ይቻላል፡፡ ዶ/ር ሙሉጌታ የቻይናን ዲያስፖራ እንደ ጥሩ ምሳሌ በማንሳት "የዛሬ ስምንት ዓመት አካባቢ 50ኛው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በአል ሲከበር ተጋባዠ በመሆን ቻይና ሄጄ ነበር፡፡ በወቅቱ አንድ መቶ ሺህ የሚደርሱ ዲያስፖራ ፀረ ኮሚኒስቶች ፖለቲካውን ሳይሆን አገራቸውን በማሰብ ተገኝተው ነበር፡፡ የፖለቲካ ልዩነታቸው አገራቸው ከመግባትና ከማልማት አላገዳቸውም፡፡ እኛ ይህንን መማር አለብን" ብለዋል፡፡ መድሃኒት ማምረትን በተመለከተ አገራችንን የሚጫወቱባት የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ናቸው፡፡ በአለም በአሁኑ ጊዜ የተበላሸ መድሃኒት በተለይ በአፍሪካ፣ በእሲያና በላቲን አሜሪካ ደሃ ሃገሮች ይሰራጫል፡፡ በዶላር ሲተመን 75 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ በአገራችንም የተበላሸ መድሃኒት ዝውውር በጣም ሰፊ ነው፡፡ መንግሥት አሁን ነቅቶ ከእነዚህ አገራት ለሚመጡ ጥራት ለሌላቸው መድሃኒቶች በሩን እየዘጋ ነው፡፡ ሆኖም የጠበቀ የቁጥጥር ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ እንደዚህ የተበላሸ መድሃኒት ይዘው የሚመጡ ባለሃብቶች ከአገራቸው ሲመጡ 60 በመቶ የሚሆን ከአገራቸው መንግሥት ድጎማ አላቸው፡፡ እዚህ ሲገቡ የሚቀረጡት 5 ከመቶ ነው፡፡ በአገር ውስጥ የምናመርተው በእያንዳንዱ ንጥረ ነገር መሸፈኛውን ጨምሮ እስከ 30 በመቶ እንቀረጣለን፡፡ ድጋፍ አናገኝም፡፡ ይህ መሻሻል ያለበት ነው፡፡ እንደ ናይጄሪያና ሱዳን የመሳሰሉ አገሮች ሁኔታውን ተረድተው በራቸውን ዘግተው የራሳቸውን ኢንዱስትሪ በማሳደግ ላይ ናቸው፡፡ በአገራችን ተጀምሮ ውሳኔ ያላገኘ ጥናት አለ፡፡ ጥናቱ መድሃኒት በማምረት ዘርፍ ብዙ የተማሩና በአሜሪካ መድሃኒት የማምረት እውቀት ያላቸውን ለማምጣት ነው፡፡ "የዲያስፖራን ጥያቄ ለመፍታት የዲያስፖራ አንድ ቢሮ ከፍቶ ቢሮ አለን ማለት ሳይሆን አንድ ዲያስፖራ በአገሩ ችግር ሲያጋጥመው ችግሩን በወቅቱ መፍታት ይገባል፡፡ የዲያስፖራው ቢሮ፣ ችግር ፈቺ መሆን አለበት" የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ በሌላ በኩል አብዛኛው ዲያስፖራ የተሠማራው በምርት ሳይሆን አገልግሎት በመስጠት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የካፒታል መጠኑ አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ ሆኖም አገልግሎት መስጫውን ከፍቶ እሱን እያሳደገ ወደ ምርት ሊሸጋገር በሚችልበት መንገድ ላይ ትምህርታዊ ገለፃ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ፖሊሲው ቢስተካከል፣ የታክስ አከፋፈሉ እየተሻሻለ ቢሄድ አብዛኛው ዲያስፖራ አገሩ ለመምጣት ፍላጎት ይኖረዋል፡፡ ዲያስፖራው በተለይ ለልማቱ ገንዘብ ያለው አገሩ ሲመጣ በሶስት ቀን ውስጥ ጉዳዩን ጨርሶ የሚሄድበት መንገድ መከፈት አለበት፡፡ እንጂ ከመስሪያ ቤት መስሪያ ቤት ሲዞር መዋል የለበትም፡፡ ይህ ሲኖርበት በቆየበት የውጭው አለም ያልለመደው አሰራር ስለሆነ እዚህ ያለው አሰራር ቶሎ ተስፋ እንዲቆረጥ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ባለሃብት ሲንጋፖር ሲሄድ በሶስት ቀን ውስጥ አስፈላጊውን መረጃን ትብብር አግኝቶ ይመለሳል፡፡ በአገራችን የጊዜ ጉዳይ የፖሊሲ ትኩረት የሚያስፈልገው ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያመጣው የዲያስፖራው ዘርፍ በመሆኑ ዲያስፖራውን በየዘርፉ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊው በብዛት በሚገኝባቸው የውጭው አለምም የዲያስፖራና የኢንቨስትመንት ቢሮ መክፈት ያስፈልጋል፡፡ ኒውዮርክ እንኳን ቢወሰድ ሽብርተኝነትን በመፍራት ገንዘባቸውን በሌላ አገር ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ብዙ ባለሀብቶች አሉ፡፡ እነዚህን ለማምጣት መስራት አለብን፡፡ ገንዘብ ለማምጣት ገንዘብ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ዲያስፖራው አገሩ ለልማት ሲመጣ ኢንቨስትመንት ቢሮ መሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ማቃለል የሚቻለው በያለበት ሄዶ መቀስቀስ ሲቻ ነው፡፡ ኤምባሲዎች ቢኖሩም ለዚህ ሥራ የተመቻቹ ባለመሆናቸው በአንድ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ጭምር ለምሳሌ በእንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ጣሊያንና ካናዳ የተለያዩ ቢሮዎች ማቋቋም ይጠቅማል፡፡ አሰራሩንም በአንድ ማዕከል ከማድረግ እስከተወሰነ ደረጃ ፕራይቬታይዝ ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ ይህ ስራዎችን ያቃልላል፣ ጊዜን ያሳጥራል፡፡ በጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |