| የመጠጥ ውሃ ሽፋን 80 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል |
|
|
| Sunday, 23 March 2008 | |
![]() አቶ አዱኛ ጀቤሳ "የመገናኛ ብዙሃን ሚና በውሃ ሀብትና በሳኒቴሺን ዘርፍ" በሚል ርዕስ መጋቢት 12 ቀን 2000 በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ አማካሪው "የሀገራችን የውሀ ሀብት አጠቃቀም ሽፋን እና ገጽታ" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንዳመለከቱት ይህንኑ ዕቅድ ለማሳካትም የተመቻቹ የሕግ መሠረቶች፣ ፖሊሲዎች የውሀ ሀብት አጠቃቀም ሕጎችና የልማት ስትራቴጂዎች ተነድፈዋል፡፡ ከዚህም ሌላ መንግሥት በዚሁ ሴክተር ከፍተኛ የልማት ሥራ ለማካሄድ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ አንዲሁም ለሴክተሩ በአሁኑ ጊዜ ከፌዴራል አስኮ ወረዳ ድረስ ከፍተኛ የሆነ የአገልግሎት የግንባታ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ ውሀ፣ ሳኒቴሺንና ሀይጂን ተነጣጥለው ሁሉም በየበኩሉ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ተወግዶ ሦስት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ማለትም የውሀ ሀብት፣ የጤና ጥበቃና የትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የውሀ ሰኒቴሺን ሀይጂን ፕሮግራም በሚል ተቀናጅተው አብረው የሚሰሩበት ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል፡ ከእነዚህ ሴክተር መሥሪያ ቤቶችም ውጭ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በባይላተራልስና መልቲላተራስ ዙሪያ አብረው ለመሥራት አንድ የጋራ መድረክ ፈጥረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በውሃና በሰኒቴሺን አካባቢ የሚካሄደው ልማት በአብዛኛው በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ነው፡፡ ሌላው አካል የሚያደርገው የሚስተካከልና ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ነው፡፡ የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑትን ሴቶች አቅም መገንባት እንደ አንድ አቅጣጫ ተወስዶ በፖሊሲና በሴክተሩ ባሉ ሕጎችም ተቀምጧል፡፡ ዶክተር ዓለማየሁ እንዳብራሩት ውሀ፣ ሳኒቴሺንና ሀይጂን በሕብረተሰቡ ጤንነት ላይ ለውጥ እንዲያመጡ ነው ልማት የሚሠራው፡፡ በሳኒቴሺን ላይ ብቻ ልማት ቢሠራ በማህበረሰቡ ላይ ምንም ዓይነት የጤና ውጤት አያስገኝም ወይም ደግሞ ከሰኒቴሺን ጋር የተያያዘ የተቅማጥ በሽታ በመቀነሰ በኩል ሰኒቴሺን ያለው አስተዋጽኦ 36 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ሀይጂን ደግሞ ከምግብ በፊትና ከመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም በኋላ እጅን በንጹህ ውሀና በሳሙና መታጠብ በተቅማጥ ላይ ያለው ውጤት 35 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ሰኒቴሺንና ሀይጂን ሳይካተቱ ንጹህ የመጠጥ ውሀ ብቻ ቢቀርብ ተቅማጥን በመቀነስ በኩል የሚገኘው ውጤት 15 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሦስቱን ማለትም ውሀ፣ ሳኒቴሺንና ሀይጂንን በማቀናጀት በአንድ ማህበረሰብ ላይ ቢሠራ የተቅማጥ በሽታን 65 በመቶ መቀነስ ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ውሀ፣ ሰኔቴሺንና ሀይጂንን በማቀናጀት ፕሮግራም ተቀርፆለት እንዲሠራ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፣ ይህ ዓይነቱም ፕሮግራም ለድህነት ቅነሳ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሲሆን ለሕዝብ ጤንነትና ለኢኮኖሚ እድገት መሠረት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ በዓመት ወደ 122 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የገጽ ምድር ውሀ እንዳለ ነው የሚታሰበው፡፡ ይህም ከዓለም ወደ አንድ በመቶ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ወደ ሦስት በመቶ የሚሆን ነው፡፡ ከዚህም ሌላ 12 የሚሆነ ከፍተኛ ተፋሰሶችና 15 ከፍተኛ ሀይቆች አሉ፡፡ እንዲሁም ወደ 120 ሺህ ሜትር ኪዩብ ስኬዌር ኪሎ ሜትር የሚሆነው መሬት በውሀ እንደተሸፈነ ይገመታል፡፡ ወደ 2.6 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚሆን የከርሰ ምድር ውሀ እንዳለም ይገመታል፡፡ በሀገሪቱ ያለው የዝናብ መጠንም ከ100 እስከ 2700 ሚሊ ሜትር ነው፡፡ በሀገሪቱ ወደ 3.7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ልማት እንደሚቻል፣ ከዚህ ውስጥ እስካሁን የለማው ከ200 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ እንደማይበልጥ፣ በሀይድሮ ፓወር አካባቢም ወደ 30 ሺህ ሜጋዋት የማምረት አቅም እንዳለ ዶክተር ዓለማየሁ አመልክተው በዚህም አፍሪካ ውስጥ ከኮንጎ ቀጥሎ ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ፣ አጠቃቀማችን ግን በጣም ደካማና እስካሁንም እየተጠቀምን ያለነው ወደ 3.5 በመቶ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በአሳ ምርትም በዓመት እስከ 50 ሺህ ቶን ማምረት ይቻላል፡፡ አሁን ግን እየተመረተ ያለው ከ30 እስከ 40 በመቶ በሚሆን ነው፡፡ በመጠጥ ውሀ አቅርቦት በኩል አሁን ያለው የሽፋን ሁኔታ ወደ 52 በመቶ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የገጠሩ ሕዝብ የሚያገኘው የመጠጥ ውሀ ሽፋን ወደ 46.4 በመቶ ብቻ ነው፡፡ 64 በመቶ የሚሆነው የገጠሩ ሕዝብ አሁንም የንጹህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ወደ 35 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሁኑ ጊዜ ወደ 1.1 ቢሊዮን የሚሆን ሕዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሀ እያገኘ አይደለም፡፡ ይህም ከዓለም አንድ ስድስተኛው ሕዝብ ማለት ነው፡፡ ከስድስት ሰዎች መካከል ቢያንስ አንድ ሰው የንጹህ ውሀ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ወደ 2.4 ቢሊዮን የሚሆነው ሕዝብም በቂ የሆነ የሰኒቴሺን አገልግሎት አያገኝምና ወደ 2.2 ቢሊየን የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ከውሀ ጋር በተያያዘ ችግር ሳቢያ ለበሽታ ይጋለጣል፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ ሕፃናት በንጹህ ውሀና በሳኒቴሺን እጦት በየቀኑ ለሞት ተጋልጠዋል፡፡ አቶ አዱኛ ጀቤሳ የውሀ ሀብት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር አውደ ጥናቱን ሲከፍቱ እንዳመለከቱት "የአነስተኛ መስኖ ልማት ከአስር ዓመታት በላይ በተለያዩ ክልሎች ሲካሄድ የቆየና አሁንም በመካሄድ ላይ ያለ ነው፡፡ በዚህ መልካም አጋጣሚ በርካታዎች ተጠቃሚ ሲሆኑ ሌሎችም እንደማሳያነት በማገልገላቸው ዛሬ የአቅም ውሱንነት ካልሆነ በስተቀር የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ለመሆን የማይፈልግ አርሶ አደር አለ ብሎ ለመገመት ያስቸግራል፡፡" ብለዋል፡፡ ተጠቃሚ እንድትሆን በሰፊው በመካሄድ ላይ ይገኛል ልማቶችም የሚካሄዱት በአብዛኛው በአገር አቀፍ በመሆኑ በጣም አበረታች ከመሆኑም በላይ በሚፈጠረውም አቅም ለወደፊቱ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ በስፋት ልማትና ለማካሄድ የሚያስችል መሠረት እየተጣለ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ የመጠጥ ውሀ ልማት በአብዛኛው ከተሞችን ግብ አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ገጠሩን ተጠቃሚ በማካተት እንቅስቃሴ የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ወቅት ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የንጹህ ውሀ ተጠቀሚ ለማድረግ አገር አቀፍ ፕሮግራም ተቀርፆ የትግበራው ጊዜ አንድ ሦስተኛው ያህሉ እየተገባደደ ይገኛል፡፡ በዕቅዱ መሠረት የምዕተ ዓመቱ ግቦች እ.ኤ.አ ከ2015 አስቀድሞ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ፕሮግራም ተጠናቅቆ መላው ሕብረተሰብ የንጹህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚ መሆን ሲችል አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ጤናማ ይሆናል፡፡ የማምረት አቅሙም ይጨምራል፡፡ የሀገሪቱ ዕድገትም በተጨባጭ እውን ሊሆን እንደሚችል ምክትል ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ በታደሰ ገብረማርያም |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |