| ደብረብርሃን - ገበናዋን ሜዳ ላይ |
|
|
| Sunday, 23 March 2008 | |
![]() ነጋዴ ሀሚድ ማህሙድ ![]() ኤቫ ሆቴል ![]() አቶ ሥዩም ተፈራ "ተወልጄ ያደግኩት እዚች ቱቦ አጠገብ ነው" የሚለው የሱቅ ነጋዴ ሀሚድ ማህሙድ ነው፡፡ ተወልዶ ባደገበት ቤት መስኮቱን ከፍቶ ሥራ በመፍጠር ሆዱን ቢያሸንፍም "የሰገራ ሽታውን ግን ምን ላድርገው?" በማለት ይጠይቃል፡፡ ሌላው የዚያው ቀበሌ ነዋሪ ዮሴፍ ብሩክ የ1ዐኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ "ነፍስ ካወቅኩ ጊዜ ጀምሮ ቱቦውና አካባቢው ይገማል፡፡ እኔ እንኳን ሳውቀው 17 ዓመት ሆኖኛል፡፡ አስተዳዳሪዎች ይቀያየራሉ ቱቦው ከመግማት አካባቢያችንም የሰገራ መተላለፊያ ከመሆን ልናመልጥ አልቻልንም" በማለት አስተያየቱን ሰጥቶኛል፡፡ ቱቦውን ቀርቤ ስመለከተው ጠረኑ ክፉኛ ይገፋተራል፡፡ ከሙቀቱ ጋር በጣም የሚገማው ቱቦ በአካባቢው ነዋሪዎች ደጃፍ ጥግ ለጥግ ይወርዳል፡፡ ቀጭን ጥቁር ውሃ፣ ጥቁር ወፍራም ፍሳሽ በየዓይነቱ አለው፡፡ ቆሻሻና ኘላሰቲክም የቱቦው አካሎች ናቸው፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ኃ/ማሪያምም ደብረ ብርሃን ከንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግሯ ብትገላገልም በፍሳሽ ችግር ነዋሪዎቿ ለአስምና ለከአንገት በላይ በሽታ መዳረጋቸውን ያምናሉ፡፡ በከተማዋ ውስጥ የፍሳሽ ማስወገጃ በአግባቡ አልተዘረጋም፡፡ በየመንገዱ ዳርቻ ባሉት ዲቾች ላይ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሻቸውን የሚለቁ ሆቴሎች የሚቆጣቸው ያለ አይመስልም፡፡ አቶ ጌታባለው ሙሉጌታ ይባላሉ፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ ጤና ፅህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡ "ቅድሚያ የምንሰጠው ለህብረተሰቡ ጤንነት እንጂ ፍሳሻቸውን ወደ ውጪ ለሚለቁ ሆቴሎችና ድርጅቶች አይደለም" ይላለ፡፡ እሳቸውም ሆኑ የከተማዋ ጤና ኮሚቴ አባላት ፍሳሻቸውን ወደ ውጪ በሚለቁት ሆቴሎች ለመስተናገድ "ዲቹ"ን ዘለው አሊያም በሞተር ሳይክል ተሻግረው ሲገቡ በደብረ ብርሃን ቆይታዬ አስተውያለሁ፡፡ ደብረ ብርሃን ከተቆረቆረች ዓያሌ ዓመታትን ብታስቆጥርም የመሠረተ ልማቷና የከተማዋ እድገት አያስደስትም፡፡ አስተያየት የጠየቅኳቸው ነዋሪዎች ኢንቨስተሮች በአግባቡ ስለማይስተናገዱ ተመልሰው ይሄዳሉ፡፡ ጥያቄ ቢያቀርቡም አፋጣኝ ምላሽ አይሰጥም፡፡ በእድሜ የሚያንሷት ከተሞች እየበለጧት ብለውኛል፡፡ ከከተማዋ መግቢያ በስተቀኝ አፄ ያዕቆብ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ምንነቱ ጥቁር ውሃ ተኝቶ ይታያል፡፡ ከማረሚያ ቤቱ የሚወጣው የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ውስጥ ለውስጥ የሚሄድ ቢመስልም በቀበሌ 4 ማረሚያ ሰፈርና በቁጠባ ሰፈር መካከል ተጋግሮ ተኝቷል፡፡ ስፍራውን እየዞረ ያሳየኝ አስጐብኚዬ "ደብረ ብርሃን ያልሸተተችው የአየር ፀባይዋ ረድቷት እንጂ የሚያስብላት የማጣቷን ያህል ተፈጥሮም ቢጨክንባት ኖሮ ምን ትሆን ነበር?" በማለት አስተዳዳሪዎቹን እንድጠይቅለት አደራ ብሎኝ ነበር፡፡ ሼል አካባቢ 01 ቀበሌ ከተጉለት ቁርጥ ቤትና ጠጅ ቤት ወረድ ብሎ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሼል ነዳጅ ማደያ ወደ ላይ ለመስቀል መታሰቢያ ሆቴል ብሎም ጅቡቲ ሆቴል እስከ ኤቫ ሆቴል ድረስ በተመሳሳይ ከመፀዳጃ ቤት የሚወጣ ሽታ ያለው ፍሳሽ ማየት ለደብረ ብርሃን ነዋሪዎች የተለመደ ነው፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ አቶ ሥዩም ተፈራ የፍሳሽ አወጋገድ ችግር እንዳለ ያምናሉ፡፡ አስተዳደሩ አስጠንቶ በቅርቡ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን ለማሰራት ማቀዱን ይናገራሉ፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ መነጋገሪያ የሆነውና እኔም ርዕሰ ጉዳይ አድርጌ የሄድኩበትና ውስጥ በችግሩ የነበረበርኩበት ንብረትነቱ የጌጤ ዋሚ የሆነው ኤቫ ሆቴል መታሸጉን ተከትሎ ነው፡፡ ሆቴሉ የታሸገው በንፅህና ችግር ነው፡፡ "የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ትለቃላችሁ" በሚል፡፡ ሆቴሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ የደረስኩት ሐሙስ ጧዋት 4፡00 አካባቢ ሲሆን ግቢው ሙሉ በሙሉ ተቆፍሯል፡፡ በከተማው በተለያዩ ኃላፊነት ላይ ያሉ የጤና ኮሚቴ አባላት ተሰብስበዋል፡፡ "ፍሳሹ የሚወጣው በየት በኩል ነው?" በማለት ይነጋገራሉ፡፡ ይጠይቃሉ፡፡ በከተማዋ በንፅህናው የመጀመሪያ የሚባለው ኤቫ ሆቴል የከተማዋና የዞኑ ስብሰባዎች በዓሎችና የሽልማት ስነስርዓቶች የሚካሄዱበት ሲሆን ሆቴሉ ሊታሸግ የሳምንት እድሜ እስከቀረው ድረስ መንግሥታዊ ዝግጅቶችም ሲካሄዱበት ነበር፡፡ "ምን አዲስ ነገር ተገኘ?" የሚሉት የጌጤ ዋሚ ባለቤት አቶ ጌታነህ ተሰማ ናቸው፡፡ "ተለይቼ እኔ ለደብረብርሃን ችግር ፈጣሪ ከሆንኩ ኢንቨስትመንቱን ለቅቄ እወጣለሁ፡፡ ግን ችግሩ ይህ አይመስለኝም፡፡ የመንግሥት የበላይ አካላት ሊያዩትና ሊመረምሩት ይገባል" የሚሉት አቶ ጌታነህ፣ በሊዝ ተጨማሪ ቦታ ገዝተው በ5 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ባለአራት ፎቅ ሆቴል ለመስራት የግንባታ ፈቃድ ቢጠይቁም ሦስት ወር እንደሞላው፣ የዚህንም ምክንያት እንደማያውቁት ይገልፃሉ፡፡ "ወደፊትም ሌሎች ሆቴሎች ፅዳት ካጓደሉ ይታሸጋሉ፤ ይቀጣሉ" የሚሉት አቶ ጌታባለው ኤቫ ሆቴል ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው፣ በገንዘብ ቢቀጣም ሊያሻሽል እንዳልቻለና ባለቤቱ አቶ ጌታነህ ሲፈለጉ እንደማይገኙ ያስረዳሉ፡፡ እንደ እሳቸው እምነት ኤቫ ሆቴል ከተቆፈረ በኋላ የሚፈሰው ፍሳሽ ምንጩ ባይታወቅም የተወሰደው ርምጃ ትክክል ነው፡፡ የከተማዋ ነዋሪ አፍንጫ "ከጥቅም ውጪ" አድርጓል ስለተባለው አጠቃላይ ችግር ግን ያሉት ነገር የለም፡፡ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ስዩም ግን ለደብረ ብርሃን የሚያስፈልጋት መሰረታዊ ለውጥ እንደሆነ፣ ይህንንም በመረዳት መጥፎ ጠረን ያላቸውን ፍሳሾች ለማጠራቀም ማጠራቀሚያዎች የማሰራቱ ሥራ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች የሚሉት አንድ ጉዳይ ደብረ ብርሃን እውነተኛና የሚቆረቆርላት መሪ እንደሚያስፈልጋት ነው፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |