Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 11th
Home arrow Sections arrow የውርስ እንጀራ
የውርስ እንጀራ Print E-mail
Sunday, 23 March 2008
Image
ወ/ሮ መንበረ በድሩ
Image
ቅርጫትና እንስራ በጀርባቸው ያዘሉ፣ በትከሻቸው ቅል የተሸከሙ በራቁት ገላቸው ላይ ቀጥ ያለ ጡታቸው ጎልቶ የሚታይና ከወገባቸው በታች ሦስት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ቆዳ ያገለደሙ፣ በተለያየ የሹራብ አሰራርና በአለባበሳቸው የተለያዩ የኢትዮጵያን ሴቶችና ወንዶች የሚወክሉ የሰው ምስሎች በእንጨት ተቀርፀው ተደርድረዋል፡፡

 

ባፈለው ሳምንት ..ከታላላቅ ሥራዎች ጀርባ ታላላቅ ሴቶች አሉ.. በሚል ርዕስ ሳክርድ ኢንተርናሽናል ባዘጋጀው የሴቶች ፌስቲቫል ላይ ከቀረቡ ሥራዎች መካከል አይናችንን የሳበው ከላይ የተጠቀሰው የቅርጻ ቅርጽ ሥራ ነበር፡፡ ቅርፃ ቅርጾቹ ግማሾቹ ሽሮ መልክ ቀለም ያላቸው ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ የሰዎቹ የፊት ገጽታ ብቻ ጥቁር ሌላው ሽሮ መልክ ነው፡፡ ጥቁር ቀለም ግን አልተቀቡም፡፡ የተሰሩበት እንጨት ውስጡ ጥቁር ስለሆነ የተፈጠረ ነገር መሆኑን ቅርፃ ቅርፆቹን  ሰርተው ለእይታና ለሽያጭ ያቀረቡት ወ/ሮ መንበረ በድሩ ይገልፃሉ፡፡

ወይዘሮ መንበረ እንደገለፁት የቅርፃ ቅርጽ ሥራውን የጀመሩት ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ ሙያውን የወረሱት ከእናታቸው እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ እናታቸው በቀንድ ውጤቶች ማንኪያ፣ ጭልፋና የተለያዩ ጌጣጌጦችን እየሰሩ ያስተዳድሯቸው ነበር፡፡ የመጀመሪያ ልጅ የነበሩት ወ/ሮ መንበረም ሙያውን ከእናታቸው የተረከቡ ብቸኛ ልጅ ሆነዋል፡፡ ..ቀንዱን ከቄራ እንረከብና ባህላዊ የሆኑ ዕቃዎችንና ጌጣጌጦችን ቅርጽ እያወጣች እናቴ ትሰራለች፡፡ እኔ መደምደሚያውን እሰራ ነበር፡፡ እሷ ቅርጽ እያወጣች ስትሰጠኝ መፋቅ፣ ማለስለስ፣ መሞረድ አይነት ሥራዎችን ከእናቴ ጎን እሰራ ነበር..

ከእናታቸው በቀንድ ቅርጽ አውጥቶ መስራት የሥራ ልምዱን የወሰዱት እኚህ ወይዘሮ እሳቸውም ትዳር ይዘው የራሳቸውን ቤት ከመሰረቱ በኋላ ሙሉ በሙሉ የቀንድ ውጤቶችን መስራት ጀምረው ነበር፡፡ የቅርፃ ቅርጽ ሥራው ገበያው ውስጥ ተፈላጊነት ያለው ቢሆንም ሥራውን ለማቆም ተገደዋል፡፡ ምክንያቱም ከቄራ የሚያወጡት ቀንድ ለውጭ ገበያ እንዲውል ታስቦ ከተከለከለ በኋላ ወደ እንጨት ሥራው እንደገቡ ይናገራሉ፡፡

..በአጋጣሚ ባለቤቴም ተቀጥሮ የሚሰራው የቅርጻ ቅርጽ ሥራ ነበር፡፡ ስለዚህ እንጨቱን እንገዛና እቤት ውስጥ እየቀረጽኩ መስራት ጀመርኩ፡፡.. በእንጨት የተለያ ቅርፃ ቅርጽን ማለትም፣ የእንስሳት፣ የሰው የተለያዩ ታሪካዊ ምስሎች (ምኒልክን በፈረስ ላይ ሆኖ..ን ጨምሮ በትዕዛዝና በራሷ ፍቃድ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራች ለገበያ ማቅረብ ከጀመረች ስድስት ዓመታትን አሳልፋለች፡፡

ለቅርፃ ቅርጽ ሥራዎቿ የምትጠቀምባቸው ኢቦኒና ወይራ የተባሉ እንጨቶችን ነው፡፡ ነጋዴዎች እንጨቶችን የሚያመጧቸው ለማገዶ ሲሆን ቅርፃ ቅርጽ ለማውጣት የሚጠቀሟቸውን እንጨቶች መርጠው በኪሎ ይገዛሉ፡፡ ቅርፃ ቅርፆቹን ለመስራት የመጀመሪያ ሥራቸው እንጨቶቹን በመጥረቢያ መፍለጥ ይሆናል፡፡ ሁለቱም የእንጨት አይነቶች ለመፍለጥ አስቸጋሪ ቢሆኑም በተለይ ኢቦኒ ግን ..ብረት.. ነው ይላሉ ምን ያህል ጉልበት እንደሚያስፈልገው ሲገልጹ፡፡

ወይዘሮ መንበረ እንደሚሉት እንጨቶቹን ለቅርፃ ቅርጽ ሥራቸው በሚመች መልኩ ከተፈለጠና ካጠረ በኋላ ቅርፃቸውን በማየት ምን ሊሰራበት እንደሚችል አስበው ይወስናሉ፡፡ ምንም የስዕል ችሎታ እንደሌላቸው የሚናገሩት ወ/ሮ መንበረ አጠገባቸው ያለው እንጨት ምን አይነት ቅርጽ ሊሰሩበት እንደሚችሉ የሚወሰንላቸው ራሱ እንጨቱ የያዘው ቅርጽ ነው፡፡ ..አጠገቤ እያየሁ የምሰራው ሌላ ቅርጽ ወይም ስዕል አላስቀምጥም፡፡ የእንጨቱን ቅርጽ በማየት ሁለት ባላ ካለውና ባላው አንደኛው ወደ ታች ዝቅ ያለ ከሆነ ቅርጫት የያዘች የገጠር ሴት አደርጋታለሁ፡፡ ባላው ወደ ላይ ወጣ ያለና አንደኛው ወደታች ጎንበስ ያለ ከሆነ ዝቅ ብላ እንስራ የያዘች ሴት አደርጋታለሁ፡፡ ከጎን ጉጥ ያለውን ደግሞ ቅል የያዘች ሴት ላደርገው እችላለሁ ቀጥ ያለውን ቀጥ ብሎ የቆመ ወንድ ወይም ሴት መሥራት እችላለሁ፡፡..

ክርክሮቹን የሚያወጡበት ዘመናዊ ማሽን የላቸውም፡፡ የምስሎቹን አይን፣ አፍንጫ፣ ፀጉርና ቁመና ለመቅረጽ እንደ መሰርሰሪያ የሚጠቀሙት የተለያየ መጠን ያላቸውን መጥረቢያዎችና ፑንታ በተባለ መሳሪያ መሆኑ ይናገራሉ፡፡ አባጣ ጎርባጣውን ፍቀው ካስተካከሉ በኋላ በብርጭቆ ወረቀት ይለስልሳል፡፡ ተቦርሾና ተጠራርጎ በደንብ መለስለሱ እያንዳንዱ የምስሉ አካል ቁልጭ ብሎ እንደሚታይ ካረጋገጡ በኋላ ሰም ቀብተው ያለሰልሱታል፡፡ ሌላ ቀለምና ኬሚካል አይነካውም፡፡ በዚህ መልኩ ቀኑን ሙሉ ቀጭ ብለው መሥራት የሚችሉት ሁለት ቅርፆችን ብቻ ነው፡፡

እንደ መስሪያ ቦታ የሚጠቀሙት በመኖሪያ ቤታቸው የልጆች መኝታ ቤት ውስጥ ነው፡፡ የራሳቸው የሆነ የመሸጫ ቦታም የላቸውም፡፡ የራሳቸው የሆነ የመሸጫ ቦታ አለመኖሩም ለገበያ የሚያቀርቡትን ቅርፃ ቅርጽ መጠን ውስን እንዲሆንና በሥራቸውም ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ጫና መፍጠሩን ይናገራሉ፡፡ ..የሥራ ግላጎቱ እያለኝ የመሥሪያ ቦታ ስለሌለኝና ሥራዎቼን ለገበያ ለማቅረብ ስል የሰው ፊት ሲገርፈኝ በጣም ይሰማኛል፡፡ እያንዳንዱን ሥራ ለመጨረስ የሚወጣ ጉልበት፣ የማንጠፈጥፈው ላብ በገንዘብ አይተመንም፡፡ እንጨቱ ክብደት አለው፡፡ ጥንካሬው ለመፍለጥም ሆነ ለመሸከም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በጭንቅላቴም በወገቤም ተሸክሜ ሥራዎቼ ይሸጡልኛል ወዳልኳቸው ቦታዎች ይዤ እሄዳለሁ፡፡ ብሩን የሚሰጡኝ ሸጠው ከጨረሱ በኋላ ነው፡፡ የማስረክባቸው በዱቤ ነው፡፡ በጥሬው አይከፍሉኝም፡፡ ስለዚህ የላቤን ዋጋ ለማግኘት ለረጅም ጊዜ መመላለስ ይጠበቅብኛል፡፡ መሸጫ ቦታ ያላቸው ግን ከእኔ ተረክበው ከእኔ የተሻለ ገንዘብ ያተርፋሉ..

ገንዘቡን በቶሎ አለማግኘታቸው ደግሞ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት የሚፈጅባቸውን ጊዜ ያራዝመዋል፡፡ ብር ከሌላቸው ሌላ እንጨት መግዛትና ማምረት እንዳይችሉ ያግዳቸዋል፡፡ የመስሪያና መሸጫ ቦታ ከሌላቸው የላባቸውን ውጤት በአጥጋቢ መልኩ እንዳላገኙ ቢሰማቸውም ሥራውን ግን ማቆም አይፈልጉም፡፡ ለመኖር፣ ራስን ለመለወጥና ህይወትን ለማሸነፍ ጉልበት እስኪደክም ድረስ መስራት የግድ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

ወ/ሮ መንበረ ከገዥዎቻቸው ጋር ፊት ለፊት የሚገናኙት ባዛሮች ላይ ከተካፈሉ ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም በአንዳንድ ባዛሮች ላይ ሥራዎቻቸውን የጎበኙ ድርጅቶች ሌላ ጊዜ ባዛር ሲያዘጋጁ እንዲካፈሉ ይጋብዟቸዋል፡፡ ገዥዎችም በትዕዛዘ እንዲሰራላቸው ይጠይቋቸዋል፡፡ ከክፍለ ከተማና ቀበሌም በባዕልና ቀናት ስፖንሰር አድርገው የሴቶችን ሥራ ለማሳየት ኤግዚቢሽን ወይም ባዛር ሲያዘጋጁ ይጋብዟቸዋል፡፡ ..እነዚህ አጋጣሚዎች የሥራዬን ትክክለኛ ውጤት የሚገኝባቸው ናቸው.. ይላሉ፡፡

ባዛር ላይ ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ሲጋበዙና ትዕዛዝ ሲመጣላቸው ባለቤታቸው እገዛ ያደርጉላቸዋል፡፡ በተጨማሪም በቋሚነት ከቀጠሯችው ሦስት ሠራተኞች በተጨማሪ በአጣዳፊ የሥራ ወቅት ተጨማሪ አራት ያህል ጊዜያዊ ሠራተኞችን ቀጥረው እንደሚያሰሩ ወይዘሮዋ ይናገራሉ፡፡ በትዕዛዝ ቅርፃ ቅርጽ የሚሰሩ ሲሆን አንድ ሜትር ተኩል ርዝመት ያለው የሰው ምስል ቀርፀው አስረክበው ያውቃሉ፡፡

ክልል ሄደው የመስሪያ የመሸጫ ቦታ እንዲሰጣቸው ማመልከታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ መንበረ ቦታ ሲኖር በአንደኛ ደረጃ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተነግሯቸው በተስፋ እየጠበቁ ነው፡፡ መሥሪያ ቦታ ካገኙ ደግሞ ባለቤታቸውም ተቀጥሮ ከመስራት ወጥቶ በጋራ መሥራት እንደሚጀምሩ ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶችም የሥራ እድል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ ..በተለይ ሥራ አጥተው ቤታቸው ውስጥ ቁጭ ያሉ ሴቶችን አሰልጥኜም መቅጠር እፈልጋለሁ፡፡ ሴቶች የተለያዩ ሙያዎችን አውቀው በራሳቸው መሥራት ቢችሉ ጥገኛ መሆናቸው ይቀንሳል.. የሚል አመለካከት አላቸው፡፡   
በትዕግስት ዘሪሁን

 
< Prev   Next >