|
Sunday, 23 March 2008 |
 ዲያቆን ዮሐንስ መኮንን "እኛ አካባቢያችንን እናበጀዋለን፡፡ አካባቢያችን እኛን ያበጀናል" ሩዝቬልት ይህን ያለው በተበላሸ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የሚኖራቸው ሰብዕና ወይም ማህበራዊ መስተጋብራቸው እንደሚኖሩበት አካባቢ መለያየቱንና እነሱ አካባቢያቸውን እንደሚያበጁት አካባቢያቸው ለእነሱ ምቹ ወይም አስቸጋሪ መሆኑን ለመግለፅ ነበር፡፡
ኪነ ሕንፃ ወይም የሕንፃ ጥበብ የተጀመረው የሰው ልጅ የሚኖርበትን አካባቢ ሲመሰርት ነው፡፡ የሰው ልጆች በዋሻ ውስጥ ለመኖር ሁኔታዎችን ሲያበጁ፣ አካባቢያቸውን ማሳመር፣ ማሰናዳትና ማፀዳዳት ሲጀምሩ ነው፡፡
እያንዳንዱ ማህበረሰብ ኪነ ሕንፃን በተመለከተ የራሱ የሆነ ጥበቡን የጀመረበት የራሱ መንገድ አለው፡፡ ይህም በየአካባቢው ካለ ቁሳቁስ፣ ባህል፣ ስነቃልና የአኗኗር እንድምታ ጋር ተያይዞ ያደገ ነው፡፡
ኢትዮጵያም የራሷ የሆነ ጅማሮ ነበራት፡፡ የማሳደግና የመንከባከብ ጉዳይ ግን አልተሰራበትም ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንድ አገሮች ላይ ደግሞ የነበራቸው የኪነ ጥበብ ጅማሮ ደብዝዟል ወይም ጠፍቷል፡፡ ከግሎባላይዜሽን ጋር ተያይዞ በብዙዎቹ አገሮች የራሳቸው ሳይሆን የውጭው ተፅዕኖ ጎልቶባቸው እናያለን፡፡ በአገራችንም ተፅዕኖው ይታያል፡፡
ዲያቆን ዮሐንስ መኮንን የጊፍት ሪል እስቴት ዲዛይን ቢሮ ሃላፊ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከመንግሥት ጋር በነበራት ቀረቤታ የነበረው የኪነ ሕንፃ ጥበብ በተሻለ መልኩ ወደ ቤተክርስቲያን ገብቶ ስለነበረ የጅማሮው አሻራ እስካሁን ቆይቷል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃ አለ ወይ? የሚለው እስካሁን አወዛጋቢ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደቡብ ካምፓስ ኢትዮጵያን አርክቴክቸር (የኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃ) የሚባል ኮርስ አለ፡፡ ይህ ሲባል ስለተበታተነ ሁሉን ጎልቶ የሚያስማማ አንድ የኪነ ሕንፃ ጥበብ ላይኖር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ጅምሩ ተሰባስቦና አድጎ በብሄራዊ ደረጃ የምናየው የኪነ ጥበብ መስመር ጎልቶ ስላልታየ ነው፡፡ በትምህርቱ ላይ የጉራጌ የወላይታ፣ የኮንሶ የትግራይ፣ የኦሮሞ እንዲሁም የሌሎቹ ኪነ ሕንፃ አለ፡፡ ሆኖም የወላይታን ወይም የጉራጌን ወይም የሌሎቹን አሳድገን አንታይም፡፡ ጠብቀንም አላቆየናቸውም፡፡ መጠበቅ ስንል አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት እንደነበረ አድርጎ ማቆየት ማለት ሳይሆን ቀድሞ የነበረውን ኪነ ሕንፃ እያሻሻሉ መሠረታዊ ትርጉሙን ይዞ ማሳደግ ነው፡፡ በሌሎች አለማትም የሚሰራበት እንዲሁ ነው፡፡ ሆኖም በአገራችን የነበረንን ኪነ ሕንፃ አድጎና ተጠናክሮ አይታይም፡፡
የኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃ ጥበብ ቢኖረንም ጎልቶ የማይታይበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ለምሳሌ ሮማወያን ሲሚንቶን መጀመሪያ እንዳገኙ ከግብፅ እና ከግሪክ የወሰዱትን ስልጣኔ ከእነሱ ሲሚንቶ ጋር በማዳበል እያሳደጉት መጡ፡፡ በሲሚንቶዋቸው ጥበብን አሳደጉ፡፡ በአገራችን የሚታየው ግን ከሮማውያን ሲሚንቶን ስንወስድ የኪነ ሕንፃ ጥበብንም ነው አብረን ያመጣነው፡፡ ቁሳቁሱን ብቻ ወስደን የራሳችንን ለማሳደግ አልተጠቀምንበትም፡፡ ጎልቶ የሚታየውም የኪነ ሕንፃ ጥበብን ማምጣታችን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃ ጥበብ ያደገው በቤተክርስቲያን አካባቢ በመሆኑ እስካሁንም አጥረው ቆይቷል፡፡ ቀድሞ በነበረው የኪነ ሕንፃ ጥበብ ላይ ጎልቶ የሚታይ የራሱ የሆነ ወጥነት አለው፡፡ የላሊበላ ኪነ ሕንፃ ቢታይ ብዙ ሰው የሚያውቀው ከአንድ ወጥ አለት መሰራቱን ነው፡፡ በሳይንሱ ሲታይ ግን የተለያዩ ጥበቦችን ማየት ይቻላል፡፡ ንብርብር፣ ለሕንፃውና ለሰው ተጠቃሚዎች አስፈላጊ የሆኑ የውስጥ አሰራሮች (detail) ይታያል፡፡ በአሁኑ አሰራር ያሉ ሕንፃዎች ላይ እነዚህ (details) አይታዩም፡፡
አክሱም የሳባ ቤተ መንግሥት በመባል በሚታወቀው ፍርስራሽ ቦታ ላይ ሳይቀር ግቢው ውስጥ የሚፈሰው ውሃ እንዴት እንደሚወጣ በወቅቱ የነበሩ ባለሙያዎች አስበው የድንጋይ ማፍሰሻ ሰርተውለት ነበር፡፡ በሕንፃ ስራዎቻችን ላይ ጥቃቅን ሊመስል የሚችል ነገር እንኳን አይረሱም፡፡ እያንዳንዷን ነገር ውስጥ ለውስጥ ይሰሩ ነበር፡፡ በአሁኑ በሰለጠነው ዘመን በኮምፒውተር እየተሰራ የፍሳሽ ማስወገጃ ግድግዳ ላይ ተለጥፎ ይተያል፡፡
በቀድሞው ዘመን ለእያንዳንዷ ነገር ትኩረት ሰጥተው ይሰሩ ነበር፡፡ ኪነ ሕንፃ ላይ ለውበት ያለ አመለካከት፣ ቀለሙ፣ የህንፃው መጠን፣ አቀማመጥ". ታስቦላቸው በዘመኑ ያሉት በጥሩ መልኩ ተሰርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃ ይገለፅባቸዋል ከሚባሉት አብያተ ክርስቲያናት ቤተ ጊዮርጊስ ሲታይም እያንዳንዱ የህንፃው ክፍል የተሰራበት ጥበብና ጥልቅ ሃሳብ የህንፃውን ጥበብ አስደናቂ የሚያደርገው ነው፡፡ ውሃ ወደ ውጭ እንዲንጠባጠብና ጣራውን ለመሸፈን የተጠቀሙበት ጥበብ፣ ግድግዳውን ቀጥ ለማድረግ የፈለፈሉበት ዘዴ አስደናቂ ነው፡፡ ይህ በሳይንሱ ሲታይ በዛ ዘመን የነበረውን የኢትዮጵያን ኪነ ሕንፃ፣ የነበረውን ጥበብና ጥሩ ስሜት ተሰርቶበትና አድጎ ቢሆን የተለየና የጎላ ለአለም የምናበረክተው የኪነ ጥበብ ድርሻ ይኖረን ነበር፡፡
በቀድሞው አሰራር ህንፃው ከመጀመሩ በፊት እያንዳንዷ ነገር ቀድማ ታስባ ነበር የምትሰራው፡፡ ከአሁኑ ጋር ሲነፃፀር መጀመሪያ የታሰበው ነገርና የሚያልቅበት ሁኔታ የተለያየ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በቀድሞው አሰራር ከላይ ምን ጀምረው ታች እንዴት መጨረስ እንዳለባቸው ቀድመው ያውቁ ነበር፡፡
የፋሲል ግንብ ላይ የምናየው የኪነ ሕንፃው ጥበብ የራሱ የሆነ መለያ አለው፡፡ ጎልቶ እንዲታይም አድርጎታል፡፡ ሃረር የሚገኘው የጀጎል መግቢያም እንዲሁ፡፡ አካባቢያቸውን የሚያንፀባርቁ የኪነ ሕንፃ ጥበብ ይታይባቸዋል፡፡ የቅዱስ ላሊበላን ለየት የሚያደርገው ብዙ ባህሪ ቢኖርም ጎልቶ የሚታየው እያንዳንዷ የሕንፃው ክፍል ጥልቅ በሆነ ጥበብ የተሠራች መሆኗ ነው፡፡
አንድን ዘመን ሌላ ዘመን ላይ ሆኖ መፈረጅ ባይቻልም ስልጣኔው ለምን ቀጣይነት አልነበረውም ለሚለው፡፡ የየዘመኑ የአኗኗር ሁናቴ መቀያየር፣ ቀድሞ መጠቀም ይቻል የነበሩ ቁሳቁሶችን አሁን አለመጠቀም እንደ ምክንያት ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም የቀድሞውንም ሆነ የአሁኑን ዘመን መሠረታዊ አድርጎ የሚያገናኛቸው ኪነ ሕንፃ ለሰው ልጆች እና ለአካባቢ አመቺ የሆነ መኖሪያ የሚፈጠርበት በመሆኑ ነው፡፡ በሁለቱም ዘመን ሰውን የሚያበጅ አካባቢ ነው ሲሰራ የቆየው፡፡ ሆኖም በአሰራር ሂደት የቀድሞዎቹ ያሰቡበት መንገድና የአሁኑ ልዩነት መጀመሪያ የሚነሳው የህንፃው ዝርዝር ጉዳይ ማለትም በውስጡ የሚያካትታቸው እያንዳንዷ ነገር ላይ ነው፡፡ የቀድሞዎቹ ያሰቡበትና የሰሩበት ጥልቅ ጥበብ ዛሬ አይታሰብም፡፡ በአሁኑ ውሃ በየት መፍሰስ እንዳለበት እንኳን አስቦ የማይሰራ አርክቴክት አለ፡፡
እንደባለሙያ በከተማው የሚታየው የኪነ ሕንፃ ጥበብ ያበሳጫል፡፡ ይህ ክፍተት የተፈጠረው ደግሞ ባለሙያዎች እያንዳንዷን ዝርዝር የኪነ ሕንፃ ጥበብ ስለሚረሱ ነው፡፡ አለማችን የደረሰበት ኪነ ህንፃ ደግሞ እያንዳንዷን አስፈላጊ ነገር አስቦ የመስራት ጥበብ ላይ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ስራ በቂ መረጃ አላቸው፡፡
አንድ አካባቢ ህንፃ መስራት ሲታሰብ በአካባቢው የሚበሩ ወፎች ምን አይነት እንደሆኑ፣ የአፈሩ አይነት፣ የውሃ መስመር በአካባቢው ማለፍ አለማለፉ፣ የስልክ፣ የመብራትና የመሣሰሉት እንዲሁም ከ10 ዓመት በኋላም ሊሆን ይችላል መንገዱ ይሰፋል አይሰፋም እንዲሁም ህንፃው ችግር የሚያስከትለበትን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አላቸው፡፡
በኢትዮጵያ ሕንፃ ሲሰራ የምንነሳበት ጥልቅን ዝርዝር መነሻዎች የሉም፡፡ በሌላ በኩል ባለሙያዎች በት/ቤት ተምረው የወጡትና ያነበቡዋቸው የኪነ ሕንፃ ሳይንሶች በተግባር ላይ ሲወሉ ክፍተት አለ፡፡ ትምህርቱን ተግባር ላይ መዋሉ ልዩነት አለው፡፡
ከተማችን ውስጥ የኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃ አለ አይባልም፡፡ የኢትዮጵያን ኪነ ሕንፃ ለማየት ቤተ ክርስቲያን ወይም ባህላዊ ሆቴሎችና የቱሪስት መስህብ ያለበት አካባቢ መሄድ ያስፈልጋል፤ ወይም ጥንታዊ የሆኑ መኖሪያዎችን መፈለግ አለብን፡፡
ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሳው አንድ ንድፍ ተሰርቶ ወደ ማስፈፀም ሲመጣ "የኔ ቤት ነው ምን አገባችሁ?" ማለት አይቻልም፡፡ ጎረቤትን፣ በአካባቢው የሚያልፈውንና አካባቢው ላይ ያለው ተፅዕኖ መታየት አለበት፡፡ ሕንፃ የባለቤቱን ፍላጎት ብቻ ጠብቆ የሚሰራ ሳይሆን በአካባቢው ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ መታየት አለበት፡፡ የህንፃ ንድፉም ልቅ መሆን የለበትም፡፡
የውጭው ልምድ ሲታይ አንድ ህንፃ ሲሰራ የቤቱ ከለር ምን መሆን እንዳለበት፣ የህንፃው አይነት፣ የእንጨት ከለር፣ "" እንደየአካባቢው ሁኔታ እንዲሰራ መረጃ ይሰጣል፡፡ የሚታሰበው ህንፃው ለአካባቢው የሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ነው፡፡ ማህበረሰቡን፣ ት/ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን ሁሉ በማይጎዳ መልኩ እንዲሰራ ነው የሚደረገው፡፡ በአገራችን የዚህ አይነት የንድፍ የአሰራር መመሪያ የለም፡፡
"አንድ አርክቴክት ንድፍ እንዲሰራ ይጠየቃል፡፡ ሰርቶ ይሰጣል፡፡ ባለሃብቱ ወስዶ ያቆመዋል፡፡ መዘጋጃ ለግንባታ ፈቃድ ሲጠየቅ የሚቀርበው ጥያቄ ከድንበር ምን ያህል ርቋል የሚለው አይነት መሠረታዊ ጥያቄ ብቻ ነው፡፡ ዝርዝር ጉዳይ አይጠይቅም፡፡ መገለጫችንን የጠበቀ መስፈርት የለም፡፡"
የስነ ሕንፃ ባለሙያዎች ቢበረታቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሕንፃና ሰፈር እንዲኖረን ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ከሌሎች የምንዋሰው የለም ማለት አይደለም፡፡ ስንዋስ ግን ለአገራችን በሚስማማ መልኩ መሆን አለበት፡፡
ለምሳሌ በአውሮፓና በሜዴትራኒያን በመስታወት የሚሰራ ሕንፃ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የአየር ፀባዩ ጥሩ ነው፣ ጫካ አላቸው፡፡ ከሙቀቱ አንፃር ይህንን አምጥቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ልጠቀም ማለት ከባድ ነው፡፡ ቦሌ፣ መገናኛ አካባቢ ያሉ ህንፃዎችን ብናይ የሙቀቱ ሁኔታ ችግር ፈጥሯል፡፡ ይህ የሆነው ህንጻው ሲሰራ ንድፍን የሚፈቅዱና በንድፈ መሰረት መሰራቱን የሚከታተለው አካል ቁጥጥሩን የሚያካሂድባቸው መስፈርቶች በጣም ልል ናቸው፡፡ በመሆኑም በኪነ ሕንፃዎቻችን ላይ ችግር እየታየ ነው፡፡ ለመስተዋት አጠቃቀምና በምን አቅጣጫ መሆን እንዳለበት መስፈርት ቢቀመጥ ጥሩ ነበር፡፡
ንድፍ የሚሰራበት ዘዴም ችግር አለው፡፡ የአካባቢውንና የሰውን አኗኗር ችላ በማለት በግዴለሽነት የሚሰሩ ስራዎች አሉ፡፡ ከመሰረቱ ሊስተካከል የሚገባውን ችግር ችላ በማለት ምክንያት በህንፃ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች እድሜልካቸውን ሲቸገሩ የሚኖሩበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህ የሆነው በአገራችን የንድፍ ስራ እንደ ንግድ በድርድር ስለሚሰራ ነው፡፡ ቋሚ የሆነ ጥሩ ክፍያ ቢኖር ጠንካራ የንድፍ ስቱዲዮ ይኖራል፡፡ አሁን ያሉት ስቱዲዮዎች ሲታዩ በሚያሳዝን ሁኔታ ነው ያሉት፡፡
በደረጃ አንድ የኪነ ሕንፃ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ብዙ ማሟላት ያለባቸው ነገር ቢኖርም ቢሮ ሲኬድ አንድ ባለሙያ እንኳን አይገኝም፡፡ ቢሮ ውስጥ አንድ ሥራ አስኪያጅ ከሁለት ቀያሾች ጋር ብቻ ተቀምጦ ነው የሚገኘው፡፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ጥሩ ደረጃ ያለው ሕንፃ ይሰራል ማለት ከባድ ነው፡፡
ንድፍ የሚሰሩ ቢሮዎች ላይ ፍቃድ የሰጠው አካል ቁጥጥር ማድረግ አለበት፡፡ የንድፍ ቢሮዎች የመረጃ ማግኛና ጥናት ማድረጊያ ጭምር መሆን አለባቸው፡፡
ስራ ለመስራት ድንጋይ ከግሪክ የሚመጣበት ጊዜ አለ፡፡ ይህ የሚያሳየው በአገሪቱ ሃብት ምን ያህል እንዳልተጠቀምንበት ነው፡፡ የንድፍ ቢሮዎችም ወደዚህ ደረጃ አላደጉም፡፡ የኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነው ያላደገው፡፡ ንድፍ ሰራተኞች በአገር ውስጥ የሚገኙ የግንባታ ቁሳቁሶችን በማጎልበት ደረጃ ብዙዎቹ አስተዋፅኦ የላቸውም፡፡ በመሆኑም የንግድ ንድፍ እየጎላ መጣና የኢትዮጵያው ኪነ ሕንፃ እየደበዛ ሄደ፡፡
ቢሮዎች ንድፎቻቸውን የሚያወጡበት የጥራት ደረጃ በጣም የተቻኮለና በመጀመሪያ ደረጃ ያሉ መሆናቸው የኢትዮጵያን የኪነ ሕንፃ ጥበብ እንዳናሳድግ ተፅዕኖ አድርጓል፡፡ በት/ቤት ደረጃም መነሳት ያለበት የኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃ ኮርስ አምስተኛ ዓመት ላይ በስነ ሕንፃ ሳይንስ ውስጥ እንደ አንድ ክፍል ሆኖ ነው የሚሰጠው፡፡ ተማሪው ራሱን ችሎ ጎላ ባለ መልኩ የሚያጠናበት እድል የለውም፡፡
አንጋፍ በሚባለው የኪነ ሕንፃ ማሰልጠኛ ህንፃ ኮሌጅ ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ደቡብ ካምፓስ በቀድሞ ጊዜ የነበሩ የኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃ ሞዴል ህንፃዎች ዛሬ አብዛኞቹ የሉም፡፡ የቀረው አንድ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ተማሪው ምን አይቶ ሊሰራ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
የትምህርቱ ይዘት መሆን ያለበት የኢትዮጵያን ኪነ ሕንፃ ማሳደግ በሚቻልበት መልኩ ነበር፡፡ ኪነ ሕንፃ የማህበረሰብ መለያ በመሆኑ ከውስጥ ስሜትን በሚፈጥር መልኩ የኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃዎች መታየትና መቅረብ ነበረባቸው፡፡
ኪነ ሕንፃ ቅንጦት ማለት አይደለም፡፡ የሕዝቦች መለያና ነፀብራቅ ነው፡፡ ይህ እንዲያድግ የት/ቤቶቻችን ካሪኩለም የውጭውን ማጥናት እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃ የተቃኘ መሆን አለበት፡፡ ከተማዋን እያሳመረምንም እያጠፋም ያለው የተማረው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃ አድጎ ያላየነው ተማሪው የአገሩን ኪነ ሕንፃ በአግባቡ እድሉን አግኝቶ አይቶ ስላልተማረው ነው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ያላት ማደግ የሚችል የኪነ ሕንፃ ጥበብ ነው፡፡ በምሕረት ሞገስ |