Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow 265 ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሊያገኙ ነው
265 ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሊያገኙ ነው Print E-mail
Wednesday, 26 March 2008
Image
አቶ ቡልቻ ደመቅሳ
ኦፌዴን ድልድሉ ፍትሀዊ አይደለም ይላል


በሶስት ክልሎች የሚገኙ 265 የሚጠጉ የገጠር ከተሞችና መንደሮች በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ጊዜ ውስጥ የኤሌክትሪክ ሀይል ያገኛሉ፡፡ በአገልግሎቱ አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ አንድ ሺ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
 
የተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ መንግሥትና በአለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል የተደረገው የ115 ሚሊዮን 370  ሺህ ዶላር የብድር ስምምነት በጸደቀበት ወቅት እንደተገለጸው በብድር በሚወሰደው ገንዘብ በሚካሄደው ፕሮጀክት ሶስት ክልሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በአማራ ክልል 131 የወረዳ ቀበሌዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ለ77 የወረዳ ቀበሌዎች፣ በደቡብ ክልል ለ57 የወረዳ ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር በብድር የተገኘው ገንዘብ ከወለድ ነፃ ነው፡፡ የ10 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ ያልቃል፡፡

የብድር ስምምነቱ በክልላዊ መንግሥታት ፍትሀዊ የሆነ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ድልድል እንዲኖርና የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ሽፋንም ከ15 ከመቶ ወደ 50 ከመቶ ለማሳደግ መንግሥት ለአምስት አመት ከያዘው የስትራቴጂክ እቅድ አንዱ አካል መሆኑ ተገል"ል፡፡

በቀረበው አጀንዳ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የምክር ቤት አባል የቀረበው የብድር ስምምነት አገሪቱ ላለመችው የልማት አቅጣጫ ጠቃሚ መሆኑን ቢገልጹም ባለፈው ዓመት ከተደረገው የብድር ስምምነት ጋር በተመሳሰለ መልኩ ሶስት ክልሎች ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ ድልድሉ ፍትሃዊነት እንደጎደለው የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለኤሌክትሪክ አገልግሎት ማስፋፊያ አገሪቱ 43 ቢሊዮን ዶላር መበደሯን የገለፁት አቶ ወርጮፋ የብድር ከፋዮች የወደፊቱ ትውልድ ሆኖ አያለ ሶስቱ ክልሎች ብቻ (ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ) ተጠቃሚ መሆናቸው ተገቢ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡

የምክር ቤት አባሉ እንዳሉት ባለፈው ዓመት በተደረገው የብድር ስምምነት 375 ከተሞችንና የገጠር መንደሮችን የሚያካትት ፕሮጀክት ሲነደፍ ተጠቃሚ የሆኑት የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ናቸው፡፡

"ረበብድር ስምምነቱሪ ፍትሀዊ ስርጭትና የአቅርቦት ድልድል የተካተተ አይመስለኝም" ካሉ በኋላ ሌሎች ክልሎች የሚጠቀሙበትና የአቅርቦት ተቋዳሽ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡

የኦፌዴኑ ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በበኩላቸው የአገር ውስጥ እዳውን የማያውቅ የኢትዮጵያ ፓርላማ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ እስከ አሁን ድረስ ያለባት እዳ ካልተገለጸ በቀር የብድር ስምምነቱን እንደማይቀበሉት ተናግረዋል፡፡
 
በደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኙት ከተሞች በድምር ከአማራ ክልል ከተሞች እንደሚያንስ የጠቆሙት አቶ ቡልቻ የተገኘውን ብድር የሚከፍሉት ሁለቱ ክልሎች (ኦሮሚያና ደቡብ) ሆነው እያለ የአማራ ክልል በብድሩ ተጠቃሚ መሆኑ ተገቢ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ በብድር አከፋፈል እንደሚታየው ሁሉ በጥቅም ስርጭቱም ላይ ተመሳሳይ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

አቶ ተመስገን ዘውዴ በበኩላቸው በተገኘው የብድር ስምምነት የኤሌክትሪክ ሀይል መስመር መዘርጋቱ ትልቅ አስተዋፅኦ ቢኖረውም ጥያቄው መመንጨት ያለበት ከክልሎች መሆን እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ ለክልል መንግሥታት እኔ አውቅላችኋለሁ የሚል አካሄድ ፌዴራል መንግሥት የሚከተል ከሆነ ስህተት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተመስገን የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኙ የገጠር ከተሞችና መንደሮች በምን መመዘኛ እንደተቀመጡ ሊቀመጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የተገኘውም ብድር በምን መልኩ እንደሚከፈል መገለጽ እንዳለበት አክለው ገልፀዋል፡፡

የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስምምነቱን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት የኤሌክትሪክ ሀይል ስርጭቱ አደላደል ፍትሀዊ መሆኑን እንደሚጠራጠር ተናግረዋል፡፡

በየክልሎቹ ስንት ከተሞች እንዳሉ እንደማያውቁ የገለፁት ዶ/ር ነጋሶ በሰነዱ ላይ ክልላዊ መንግሥት ፍትሀዊ የኤሌክትሪክ እንደሚያካሂድ ቢገለጽም በአማራ ክልል መብራት የሚያገኙት ከተሞች ከደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች በቁጥር መብለጣቸው በድልድሉ ላይ ጥርጣሬ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡

ከተቃዋሚዎች ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የኢህአዴጉ ተወካይ አቶ ወንድሙ ለገጠር ከተሞቹ የሚደረገው የኤሌክትሪክ ስርጭት ከክልል የሚመጡ ጥያቄዎች መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመው ድልድሉ ፍትሀዊ መሆኑን ለመረዳትም ከዚህ ቀደም የተደረጉ ስምምነቶችን ወደኋላ ተመልሶ መመልከት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

አገሪቱ ያለባትን እዳ በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄም ጉዳዩ በሚስጥር የሚያዝ ባለመሆኑ የሚፈለገውን መረጃ ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል አያይዘውም "የተበደርነው ለጦር መሣሪያ ግዥ አይደለም ለልማት ነው" በማለት የብድር ስምምነቱ መጽደቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ሌላው የኢሕአዴግ ተወካይ አቶ መለስ በበኩላቸው አንድ የብድር ስምምነት የሚካሄደው በዘፈቀደ ሳይሆን በአለም ባንክ አሰራር መሰረት መሆኑን ጠቁመው ብድሩ የሚከፈለውም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን ወደፊት ከሚያገኘው ገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኃይሌ ሙሉ
 
< Prev   Next >