| በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሕይወት... |
|
|
| Wednesday, 26 March 2008 | |
|
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሕይወት የሌሉ ግለሰብ ለሕክምና ተጠርተዋል
ማደንዘዣ ተወግተው ሳይታከሙ የሚመለሱ አሉ አንድ የታመሙ አባት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተሉ ይቆዩና የቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው ተነግሯቸው ረዥም ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ በጥቅምት ወር 2000 ዓ.ም መዝገብ ሲገለበጥ የእኚህ ህመምተኛ የጊዜ ቀጠሮ ይታያል፡፡ ከሆስፒታል ወደ ህመምተኛው መኖሪያ ቤት ስልክ ይደወልና "ቦታ ስላለ በሽተኛው ይምጡና ይታከሙ" የሚል መልዕክት ይተላለፋል፡፡ አስቸኳይ የቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ታማሚ በሆስፒታሉ ረዥም ቀጠሮ ምክንያት አስቀድሞ ህይወታቸው አልፎ ኖሯልና ቤተሰብ ልዩ ሀዘን ይሰማዋል፡፡ የሟች ወገን በሁኔታው በመበሳጨት ሆስፒታሉ ድረስ በመሄድ በሐኪሞቹ ላይ የነፍስ ግድያ ሙከራ እስከ ማድረግ መድረሳቸው የሚሸሸግ ጉዳይ አልሆነም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ሌሎችም አስገራሚ የተባሉ አጋጣሚዎች የሆስፒታሉ ህክምና የሚከታተሉ በሽተኞች ላይ ይደርሳል፡፡ የቀዶ ህክምና እንዲደረግላቸው የረዥም ጊዜ ቀጠሮ የተሰጣቸው እድል ቀንቷቸው ተራ ያገኛሉ፡፡ የቀዶ ህክምና ለማካሄድ የማደንዘዣ መርፌ (አንስቴዥያ) ይወጋሉ፡፡ ኦፕራሲዮን ለመደረግ ሰውነታቸው ከደነዘዘ በኋላ "ሐኪሙ የሉም፣ አልመጡም" ተብለው እስከ ሦስት ቀናት ሆስፒታል ቆይተው ወደ ቤታቸው የተመለሱም አሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ፣ በቅዱስ ጳውሎስና በየካቲት 12 ሆስፒታሎች የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጥናት ያካሄደው የፌደራል የስነምግባርና የፀረሙስና ኮሚሽን ለሆስፒታሎቹ የላከው የጥናት ውጤት በርካታ ጉዳዮችን አካቷል፡፡ ጥናቱ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር እንዳለ ይፋ አድርጓል፡፡ ከጥቅምት 2000 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደውና የየሆስፒታሉ ኃላፊዎች በየደረጃው መልስ እንዲሰጡ በተደረገበት ጥናት ላይ ሐኪሞች ሰዓት አያከብሩም፣ ሲያጠፉ በአግባቡ አይቀጡም፡፡ ህክምና በአግባቡ አይሰጡም፡፡ ሐኪም ከሆኑ ህግና ደንብ የሚዳኛቸው የማይመስላቸውም አንዳሉ ተመልክቷል፡፡ ሆስፒታሎች የባለሙያ ችግር እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡ የኮሚሽኑ ጥናት ግን በተለይ ጥቁር አንበሳ ለስፔሻላይዜሽን የሚገቡ ሐኪሞች በብዛት ስላሉት ያለውን የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀም የሚችልበት ሁኔታ ያለመኖሩ ችግሩን እንዳጎላው ያመለክታል፡፡ የአንዳንድ የግል ክሊኒኮችና ሆስፒታል ባለአክስዮን ወይም ባለቤት የሆኑ ወይም ቅጥር የሆኑ ባለሙያዎች ሕሙማን ከመርዳትና የሙያ ግዴታቸውን ከመወጣት ይልቅ የግል ጥቅም ለማጋበስ የተለያዩ ሳንካዎችን በመፍጠር ኅብረተሰቡ ተገቢና ተመጣጣኝ ሕክምና እንዳያገኙ እንቅፋት መሆናቸው በየጊዜው የመገናኛ ብዙሃን ርዕሰ ጉዳይ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |