Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 11th
Home arrow Sections arrow የፓርቲዎቹ ክርክር ባለመግባባት ሳይካሄድ ቀረ
የፓርቲዎቹ ክርክር ባለመግባባት ሳይካሄድ ቀረ Print E-mail
Wednesday, 26 March 2008
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር በአምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ባለፈው እሁድ እለት በስብሰባ ማዕከል ሊያካሂድ አቅዶት የነበረው ክርክር በፓርቲዎቹ በሰዓት ክፍፍል በተፈጠረ አለመግባባት ሳይካሄድ ቀረ፡፡

በክርክሩ ላይ እንዲገኙ ተጋብዘው ፈቃደኝነታቸውን ለማኅበሩ ከገለፁት ፓርቲዎች መካከል ኢህአዴግ፣ ኢዴአፓ-መድኅን፣ መኢብን፣ ኦፌዴን፣ ቅንጅት እንደነበሩ ሆኖም ፓርቲዎቹ አቋማቸውን የሚገልፁበት፣ ከተሳታፊዎቹ የሚነሱ ጥያቄዎችን የሚመልሱበት ሰዓት ክፍፍልን በሚመለከት መግባባት ላይ ሊደርሱ ባለመቻላቸው ስብሰባው በተያዘለት ዕለት ሊከናወን እንዳልቻለ ታውቋል፡፡

አቶ ልደቱ አያሌው የኢዴአፓ መድኅን ሊቀመንበር ስለጉዳዩ ከሪፖርተር ጋዜጣ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በውይይቱ ላይ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በውይይቱ ርዕሰ ጉዳዮች፣ በአቀራረቡ፣ በቅደም ተከተሉ፣ በሰዓት አጠቃቀሙ ላይ ተገናኝተው መወያየታቸውን አስታውሰው ሆኖም ኢሕአዴግ ከሌሎች በተሻለ የሰዓት ተጠቃሚ መሆን ያለብኝ እኔ ነኝ በማለቱ ስምምነት ሊገኝ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

"ሁኔታውን ለማስታረቅ በፓርቲያችን በኩል በአጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ለሚሰጥ ገለፃ እኛ 15 ደቂቃ ስንጠቀም ኢሕአዴግ 20 ደቂቃ ይጠቀም የሚል ሀሳብ አቅርበናል፡፡ ከውይይት ለሚነሱ ጥያቄዎች ለሚሰጥ ምላሽ ግን አወያዩ እንደ ጥያቄዎቹ ብዛት አይቶ ከ1-3 ደቂቃ ብቻ የመጨመር ኃላፊነት እንዲኖረው፣ ከዚህ ውጪ አስቀድሞ ለኢሕአዴግ ሰፊ ሰዓት ይሰጥ ማለት እንደማይቻል ኃሳብ አቅርበናል፡፡ ኢሕአዴግ ግን ሊቀበለው አልቻለም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ መስፍን ሽፈራው የመላው ኢትዮጵያ ብሄራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ሊቀመንበር በበኩላቸው ምን ዓይነት ጥያቄ ለማን ፓርቲ እንደሚቀርብ ሳይታወቅ አስቀድሞ ለኢሕአዴግ ተጨማሪ ሰዓት ሊሰጥ የሚችልበት አሳማኝ ምክንያት የለም በማለት በፅሁፍ ባቀረቡት ምላሽ ገልፀዋል፡፡

ወጣት ታጠቅ ካሣ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት ፓርቲዎቹ በወጣቶች ጉዳይ የያዟቸውን አቋሞች ይፋ እንዲያደርጉ፣ ወጣቶችም በጭፍን ከመደገፍና በጭፍን ከመቃወም ይልቅ የሚበጃቸውን አውቀው እንዲመርጡ በማሰብ መድረኮቹ መዘጋጀታቸው አስታውቀዋል፡፡

መጋቢት 14 ቀን 2000 ዓ.ም ተይዞ የነበረው ፕሮግራምም የተቋረጠው ፓርቲዎቹ በሰዓት አጠቃቀም ጉዳይ ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ወጣት ታጠቅ አያይዘውም የማኅበሩ ዓላማ መወያያ መድረኮቹን መፍጠር መሆኑን በማስታወስ ፓርቲዎቹ አለመግባባትን አስወግደው በቅርቡ ቀጣይ ውይይት እንደሚያካሂዱ እምነታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ አንድ፣ በክፍለ ከተሞች ደረጃ 10 ያህል የፓርቲዎች የክርክር መድረኮችን ለማዘጋጀት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ወጣት ታጠቅ አስታውሰዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ኢሕአዴግ አስተያየት እንዲሰጥበት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡   

በጋዜጣው ሪፖርተር
 
< Prev   Next >