Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
May 09th
Home arrow Sections arrow ዳንኤል በቀለና ነፃነት ደምሴ ይቅርታ ጠየቁ
ዳንኤል በቀለና ነፃነት ደምሴ ይቅርታ ጠየቁ Print E-mail
Wednesday, 26 March 2008
በዚህ ሳምንት ይፈታሉ ተብሎ ይጠበቃል

በታህሳስ ወር 2ዐዐዐ ዓ.ም. ሁለት ዓመት ተኩል እስር ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙትና የእስር ጊዜአቸውን ሊጨርሱ 33 ቀናቶች የቀራቸው አቶ ዳንኤል በቀለና አቶ ነፃነት ደምሴ ለመንግሥት ይፋ የይቅርታ ጥያቄ ማቅረባቸውን ምንጮች አረጋገጡ፡፡  በይቅርታ ጥያቄው መሠረት በያዝነው ሳምንት ውስጥ መንግሥት ይቅርታ ያደርግላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በእነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል የክስ መዝገብ ተከሰው ሁለት ዓመት ከስድስት ወር የተፈረደባቸው ዳንኤል በቀለና ነፃነት ደምሴ ከትላንትና በስቲያ መጋቢት 15 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የይቅርታ ደብዳቤ ፅፈዋል፡፡

ሁለቱ ተከሳሾች ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፃፉት የይቅርታ ደብዳቤ "እኛ ስማችን ከታች የተገለፀው ሰዎች ምርጫ 97ትን ተከትሎ በተፈጠረው ችግር በፈፀምነው ስህተት በከፍተኛው ፍርድ ቤት ተከሰን ጥፋተኛ ሆነን በመገኘታችን በእስራት ላይ እንገኛለን፡፡ በወቅቱ በፈፀምነው ሥህተት ከልብ መፀፀታችንና ለወደፊቱም በእንደዚህ ዓይነት ተግባር እንደማንሳተፍና ሕገ-መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ዜግነታዊ ግዴታችንን በአግባቡ እንደምንወጣ እያረጋገጥን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ይኸንኑ ተገንዝቦ ለፈፀምነው ስህተት ይቅርታ እንዲያደርጉልን በአክብሮት እንጠይቃለን" የሚል መሆኑን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

የይቅርታ ደብዳቤው የደረሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ደብዳቤውን ከተመለከቱ በኋላ ትናንትና መጋቢት 16 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም.፣ አቤቱታ አቅራቢዎቹ በይግባኝ ሂደት ላይ መሆናቸውንና፣ ይግባኙ ተነስቶ ለቦርዱ እንዲቀርብ ለይቅርታ ቦርድ ፅህፈት ቤት መላካቸውን ካገኘነው መረጃ ለማወቅ ችለናል፡፡

የይቅርታ ቦርዱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የደረሰውን የይቅርታ ደብዳቤ በነገው ዕለት መጋቢት 18 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ተሰብስቦ ከተነጋገረ በኋላ በቃለ ጉባኤው ላይ በመፈራረም ለኘሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ እንደሚያቀርብና፣ ይቅርታ አቅራቢዎቹም መጋቢት 19 ቀን 2ዐዐዐ ሊፈቱ ይችላሉ የሚል ግምት መኖሩን መረጃው ያመለክታል፡፡

አቶ ዳንኤል በቀለና አቶ ነፃነት ደምሴ ታህሳስ 16 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ያሳለፈባቸውን የቅጣት ውሳኔ በመቃወም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቀው፣ በትናንትና ዕለት መጋቢት 16 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ፍርድ ቤት ተገኝተው ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ (ጠቅላይ ፍርድ ቤት) አቤቱታውን ቀድሞ ያቀረበው የፌደራል አቃቤ ህግ በመሆኑና መጋቢት 16 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. መደመጥ ያለበት የክሱ ይግባኝ በመሆኑ የዳንኤልና ነፃነት ይግባኝ መታየት የሚችለው ከዐቃቤ ህግ ይግባኝ ከተሰማ በኋላ በመሆኑ፣ በቀጣይ ቀጠሮ መጋቢት 25 ቀን 2ዐዐዐ ሁለቱንም አጣምሮ እንደሚያቀርብ ተናግሮ ችሎቱ አብቅቷል፡፡

አቶ ዳንኤል በቀለ በተከሰሱበት የወንጀል ክስ የተያዙበት ጥቅምት 22 ቀን 1998 ዓ.ም. ሲሆን፣ የቅጣት ውሳኔያቸውን ከ33 ቀናት በኋላ ሚያዚያ 21 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ይጨርሳሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አቶ ነፃነት ደምሴም እጃቸው ከተያዘበት ጥቅምት 29 ቀን 1998 ዓ.ም. ጀምሮ የተወሰነባቸውን ሁለት ዓመት ከስድስት ወር የቅጣት ውሳኔ ሚያዚያ 28 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. እንደሚጨርሱ ለማወቅ ችለናል፡፡

በታምሩ ጽጌ
 
< Prev   Next >