| እ...ን...ዴ... ተጠያቂነት ይኑር እንጂ! |
|
|
| Wednesday, 26 March 2008 | |
ተጠያቂነት ማለት ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር አንድ መሥሪያ ቤት አንድ ሥራ እንዲያከናውን ኃላፊነት ተሰጥቶት ሥራውን ካልሰራ ለድክመቱ ወይም ለውድቀቱ ተጠያቂ ይሆናል ማለት ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱ ለጥፋቱና ለውድቀቱ ተጠያቂ ይሆናል ማለት ደግሞ የመሥሪያ ቤቱ ሕንፃ፣ ጠረጴዛና ወንበር፣ ዛፍና አበባው ሳይሆን መሥሪያ ቤቱን በኃላፊነት የሚመሩቱ ሰዎች ተጠያቂ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱ ቀላል ጉንፋንና ቀላል እንቅፋት በያዘውና በመታው ቁጥር ኃላፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ አስፈላጊ የማይሆንበት አጋጣሚ ሊከሰት ይችል ይሆናል፡፡ መሥሪያ ቤቱ ካንሰርና ሌላ "አይምሬ" በሽታ እንዲይዘው ያደረጉ ኃላፊዎች ግን ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ምን ዓይነት ባንክ እንደሆነ ገሃድ ወጥቷል፡፡ በወርቅ ጨዋታ አንድ መቶ አምሳ ስምንት ሚሊዮን ብር እንደተጭበረበረ ይፋ ሆኗል፡፡ በልማት ባንክና በሌሎች መንግሥታዊ ባንኮች ያለው ጉዳት በወቅቱ ማየትና ማስተካከል የማይችል ባንክ እንደሆነ ግልፅ ሆኗል፡፡ ያሳተመው ብር የማይሰራም፣ የሚሰራ ብር ደግሞ የሚያቃጥል ባንክ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ባንኩ ማዕከላዊ ባንክ ሆኖ ለመስራት አቅሙ የተሰለበ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ታዲያ ምን እየተጠበቀ ነው? የታየው ድክመት አነስተኛ ነው? አይደለም፡፡ ገንዘባዊ ትርጉሙም ከፍተኛ ነው፡፡ ተቋማዊ ትርጉሙም ከፍተኛ ነው፡፡ አገርን መሳቂያ ያደረገም ነው፡፡ ከፍተኛ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው፡፡ መንግሥት የሾመውን ሰው መንግሥት ከኃላፊነት ማንሳትና ተጠያቂ ማድረግ መንግሥትን ለአደጋ ያጋልጣል? በጭራሽ፡፡ እንዲያውም መንግሥት የሾመውን ሰው መንግሥት ሲያነሳ የመንግሥትን የኃላፊነት ስሜት የሚያሳይና መንግሥትን ደግ አደረገ የሚያሰኝ እንጂ የሚያጋልጥ አይደለም፡፡ የሚያጋልጠውና አደጋ የሚያስከትለው ከነ በሽታው ይዘው ሲጓዙ ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱ ሲደክም ኃላፊው ችግሩን አያውቁም ነበር፤ እጃቸውም የለበትም ያሰኛልን? ኃላፊው ያስጠይቃቸዋል፡፡ ችግሩን ካላወቁት ይህን ችግር የማያውቁ ኃላፊ እዚያ ሊቀመጡም አይገባም ነበር፡፡ ቢያውቁም ባያውቁም ያስጠይቃቸዋል፡፡ የፓርቲ ፖለቲከኛን መንካትና ማንሳት የፓርቲ ፖለቲካን ያዳክማል? በመጀመሪያ ደረጃ ለፓርቲ ፖለቲካ ተብሎ አገር አይጎዳም፡፡ ደካማ የፓርቲ ሹመኛ ማንሳት ፓርቲውን ያጠናክረዋል ድጋፍንም ያስገኝለታል እንጂ አይጎዳውም፡፡ ፓርቲው የሚዳከመው ኃላፊውን ካላነሳ ነው፡፡ ተተኪ እስኪገኝ ድረስ ይቆይ ተብሎ ነው? ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ተጨማሪ ጥፋት እንዳያይደርስ ጊዜያዊ ተወካይ ተወክሎ ይሰራል እንጂ ከነድክመትህ ቆይ አይባልም፡፡ መንግሥትም ይሁን ገዢው ፓርቲ የብሔራዊ ባንክን ችግር መረጃ ስለሌለው ወይም ድምዳሜ ላይ ስላልደረሰ ነው? የመረጃ መብዛት እንጂ የማነስ ችግር የለም፡፡ መንግሥት ለእርምጃ የሚያበቃው በቂ ማስረጃ አለው፡፡ "እርምጃ ለመውሰድ የሚያበቃኝ በቂ መረጃ የለኝም" ካለ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ነው የምንለው፡፡ መንግሥት በባንኩ ዙሪያ ለተፈጠረው ችግር ኃላፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ አለበት፡፡ አቶ እንትና የዋና ክፍል ኃላፊ፣ አቶ እከሌ የትሬዠር ኃላፊ እያለ ታች ታቹን ብቻ ማየቱ ይበቃው፡፡ ከታች እስከ ላይ ድረስ ያሉት ኃላፊዎች ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ በአስቸኳይ ተጠያቂ ይሁኑ፡፡ ተጠያቂ ይሁኑ ማለት ይታሰሩ ይሰቀሉ ማለት አይደለም፡፡ መጀመሪያ ከኃላፊነታቸው ይነሱ፡፡ ከዚያ በኋላ በሕግ የሚጠየቁ ካሉ ተለይተው ይጠየቃሉ፡፡ የማይጠየቁ ካሉ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ሊሰሩ በሚችሉበት መደብ ይመደባሉ፡፡ ግለሰቦች ቅር እንዳይላቸው ተብሎ ግን አገር ለአደጋ አይዳረግም፡፡ መንግሥት የባንኩ ኃላፊዎችን ተጠያቂ ካላደረገስ? መልሱ ቀላል ነው፡፡ መንግሥት ራሱ እንደመንግሥት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ መንግሥት የራሱ ሹመኞች ቢያጠፉ ተጠያቂ ማድረጉ ለአገር በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ ገዢ ፓርቲውና መንግሥት ተጠያቂነትን ያከብራሉ ተብለው ከሕዝብ ከበሬታ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቅርንጫፍ ሲታመም እርምጃ ካልተወሰደ ቀስ በቀስ አደጋው በግንዱ ላይ ይመጣል፡፡ የተጠያቂነቱ እርምጃ ዘግይቷል፡፡ ከዚህ በላይ መዘግየት ግን የለበትም፡፡ ኃላፊዎች ተጠያቂ ይሁኑ፡፡ ተጠያቂ ለማድረግ ፈቃደኛነት ከሌለ በሌላ ጥፋት ሌላውን ተጠያቂ ለማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |