| ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ገለልተኛ... |
|
|
| Wednesday, 26 March 2008 | |
|
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ገለልተኛ ተቋማትና ፍትሃዊ ፉክክር ይፈልጋል
ኢህአዴግ ደርግን ጥሎ ሥልጣን ሲይዝ የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓትንና ነፃ ገበያን መሠረት ያደረገ ኢኮኖሚን ለመመስረት ቃል ገብቶ ለዚሁ ተግበራዊነት እንደሚንቀሳቀስ አስታውቆ ነው የሥልጣን ጉዞውን የጀመረው፡፡ እነኚህን ነገሮች ለማሳካትም ኢህአዴግ በርከት ያሉ ርምጃዎችን እንደወሰደ "Politics and Elections in Ethiopia 1991-2005" በተሰኘ ፅሁፋቸው ላይ ዶ/ር መረራ ጉዲና አስፍረዋል፡፡ ከእርምጃዎቹ መካከል ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የተካሄዱ የአካባቢና የሀገር አቀፍ ምርጫዎች ዋንኛ ተጠቃሽ ናቸው እንደ ዶክተሩ፡፡ በነዚህ ምርጫዎች ብዙ ኢትዮጵያዊያን ተወካዮቻቸውን ለመምረጥ ወደ የምርጫ ጣቢያዎች መለስ ቀለስ ብለው ከተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች መሀል ይበጀናል ያሉትን ሲመርጡ ተስተውሏል፡፡ በዚህም ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ለማስፈን ህዝቡ የበኩሉን ጥረት እንዳደረገ የሚነግሩን ደግሞ አቶ ታፈሰ አሊቃና አቶ አክሊሉ አብረሃም ናቸው፡፡ እነኚህ ምሁራን "Legislation, Institutions and the Post-1991 Elections in Ethiopia" በተሠኘ ፅሁፋቸው እንደሚነግሩን የፓርላማ ምርጫ በአፄ ኃይለ ስላሴ ጊዜ ተጀምሮ በደርግም የተሞከረ ቢሆንም በሁለቱም ሥርዓቶች የነበሩት ምርጫዎች ሀቀኛ የህዝብ ውክልናን ለህዝቡ ያስገኙ አይደሉም፡፡ በአንፃሩ እነኚህ ምርጫዎች ለህዝቡ ትተውለት ያለፉት ነገር በምርጫ መንግሥትን መምረጥ እና መለወጥ እንደማይቻል እና ምርጫ ለዴሞክራሲ ግንባታ የሚኖረውን ፋይዳ በማኩሰስ የምርጫን ዋጋ ማሳነስን ብቻ ነው በማለት ያስረዳሉ ምሁራኑ፡፡ ከ1983 በኋላ የተካሄዱት ምርጫዎችም ቢሆኑ በዚህ ዓይነት እሳቤ ውስጥ ነበር፡፡ ስለዚህ የህዝብ ተሳትፎ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ምርጫዎች ያን ያህል አልነበረም፡፡ በዚህ ላይ የ1997ቱን ምርጫ ሳይጨምር ሌሎቹ የተካሄዱት በማይመጣጠኑ ፓርቲዎች መሀል እና በቂ የሆነ ፉክክር ያልታየባቸው፣ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎችም "በምርጫ እንዳንሳተፍ ተከልክለናል" በማለት የተለያዩ አቤቱታዎችን በገዢው ፓርቲና በመንግሥት ላይ ሲያቀርቡ የነበረበት፣ በምርጫ አስፈፃሚ ተቋማት ገለልተኝነት ላይ ጥርጣሬ የነበረበት ወዘተ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ እንደነበር እነ አቶ ታፈሰ ፅፈዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ ደግሞ አንዳንዶቹ ራሳቸውን ከምርጫ ያገለሉ እና ተሳትፎ ያልነበራቸው ፓርቲዎችም ነበሩ፡፡ እነኚህ ችግሮች አንድ ላይ ተደማምረው ፓርቲዎች ትርጉም የሚሰጥ ፉክክር አልታየም ነው የሚሉን፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የፃፉ ምሁራን፡፡ ነገር ግን እንደ ምሁራኑ ትንተና ለነኚህ ሁሉ ችግሮች መፈጠር ገዢውን ፓርቲና መንግሥትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አግባብ ካለመሆኑም ባሻገር የፖለቲካ ፓርቲዎችን ባህሪ በትክክል የሚያሳይ አይሆንም፡፡ ለምን ቢባል የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሊወቀሱባቸውና ሊያስተካክሏቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በምሳሌ ሲያስረዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውስጣቸው የሚፈጠሩ የሃሳብ እና የአመለካከት ልዩነቶችን ዴሞክራሰያዊ በሆነ መንገድ ማስወገድ ወይም ተቻችለው በሚግባቡባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መስራት ሲገባቸው በመካሰስ እና በመጠላላት የመከፋፈል መንገድን የሚመርጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህን በማድረግ የራሳቸውን ድርጅታዊ እና ፖለቲካዊ ጥንካሬ በማጐልበት ከገዢው ፓርቲ ጋር የመነጋገር እና የመደራደር አቅማቸውን ማፈርጠም ሲችሉ የራሳቸውን ችግር ወደ ውጭ አካላት በማላከክ መንግሥት (ገዢው ፓርቲ) አላሰራን አለ፣ ነገሮችን አላመቻች አለን ብሎ ወቀሳ ማቅረቡ ሁልጊዜ ሮሮ አሰሚ እንጂ የህዝቡን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የመፍታት አቅም እንዳይኖራቸው አድርጓል ነው የሚሉት፡፡ ከዚህ አንፃር ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያደርጉት የሚገባ ነገር እንደ ጅምር ዴሞክራሲ ትንሹን የዴሞክራሲ ምርጫ መስፈርት ማሟላት ነው፡፡ ይህም የህገ መንግሥቱንና የምርጫ ህጉን ህግጋት በማክበር በመቻቻል ፖለቲካ እና በድርድር የህዝቡን ስሜት በማድመጥና በማክበር ድጋፍን ማግኘት እንደሆነ እነ አቶ ታፈሰ በፅሁፋቸው አስቀምጠዋል፡፡ ይህን ለማሳካት ደግሞ በመንግሥት (በገዢው ፓርቲ) በኩል ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች አሉ፡፡ አቶ ደረሰ ጌታቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሽዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው አባባል የዴሞክራሲ ግንባታ በአጠቃላይ የምርጫ ፖለቲካ ደግሞ በተለይ ነፃ፣ ገለልተኛና ጠንካራ የፖለቲካ ተቋማትን ይፈልጋል፡፡ እንደ የምርጫ ቦርድ ዓይነት የፖለቲካ ተቋማት ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ለማስፈፀም ሁሉም ፓርቲዎች የሚስማሙበት አደረጃጀትና አባላት ሊኖሩት ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተቋም የህዝብን እና የፖለቲካ ኃይሎችን አመኔታ በማግኘት ሰፊ ተሳትፎን ያስገኛል፡፡ ይህ ደግሞ የህዝብ ውክልናን ያረጋግጣል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ባህላችን ራሱ ምርጫዎቻችን ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳለው ኘ/ር ዶናልድ ሌቪን ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል እንደ እርሳቸው አባባል "የወንድነት ባህሪ ያጠቃዋል፡፡ በእርሳቸው አገላለጽ "ወንድነት" ማለት አልሸነፍም፣ የእኔ ሀሳብ ትክክል ነው፣ ፍላጐቴ መሟላት አለበት ማለት እና መወያየት እና መደራደርን እንደ ሽንፈት የሚያይ ባህሪ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዴሞክራሲ ባህሪያት ጋር አይጣጣምም፡፡ ለዚህ አባባላቸው የ1997ቱ ሀገራዊ ምርጫ ዓይነተኛ አስረጂ ነው፡፡ ውጤቱም ምን እንደሆነ ያየነው ነው፡፡ ስለዚህ "ወንድነትን" በሠለጠነ መንገድ እንቀይረው ነው የሚሉት ኘሮፌሰሩ፡፡ በነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ መጪውን የሚያዚያ ምርጫ ብዙ ፓርቲዎች ተስፋ የቆረጡበት ከዕጩዎች ብዛት አነፃፃርም ገዢው ፓርቲ ፍፁም የበላይነትን በያዘበት ሁኔታ ውስጥ ሊካሄድ እንሆ የአንድ ወር ዕድሜ ቀርቶታል ነው የሚሉን የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር መረራ ጉዲና፡፡ ይህ ደግሞ የአልሸነፍም ባይነትና የሌሎችን ሀሳብ ያለመቀበል ባህል ውጤት ነው እንደ እርሳቸው ገለፃ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ "በኢትዮጵያ ውስጥ በመርህ ደረጃ መድበለ ፓርቲ በተጨባጭ ግን የአንድ ፓርቲ የበላይነት ነው ያለው" የሚሉት ኘ/ር ክላፋም ሲሆኑ ሌሎች ፓርቲዎች ከሰው የሚታዩበት ሁኔታ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ምርጫዎች ሁሉ አሸናፊው ቀድሞ የሚታወቅባቸው ናቸው፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ እንደእነ አክሊሉ ፅሁፍ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሄርን መሠረት ያደረገ አደረጃጀት መከተላቸውና ሀገር አቀፋዊ የሆነ አደረጃጀት ለመፍጠር ያላቸው ተነሳሽነት በጣም ውስን መሆኑ፤ ሀገር ዓቀፋዊ ፓርቲ መስርተው የሚንቀሳቀሱትም ቢሆኑ እርስ በርሳቸወ እየተከፋፈሉ የፈረሱ እና ገሚሶቹም ከሀገር ወስጥ ፖለቲካ ርቀው በውጭ ሀገር የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው እና ገዢው ፓርቲ መንግሥትን እንደ መምራቱ የመንግሥትን ሀብት መጠቀም መቻሉ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ተፎካካሪነት ስለማይኖር የትንንሽ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ጥምረት የሚያበረታታ ህግና የህዝብን ውክልና የሚጨምር የምርጫ ሥርዓት መመስረት ለመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እና በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላለች የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ሀገር እጅጉን አስፈላጊ ነው በማለት ምሁራኑ ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ እና ሀቀኛ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ከሚያደርጉ ተቋማት መካከል ደግሞ መገናኛ ብዙሃን አንዱ ሲሆን ለምርጫ ፖለቲካ ወሳኝ የሆነውን የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ከማካሄድ አንፃር ላቅ ያለ ማና መጫወት ይገባዋል ይላሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኑ፡፡ በምርጫ ቅስቀሳ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪ እጩዎች የፖለቲካ ኘሮግራሞቻቸውን የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ለህዝብ የሚያደርሱበት እንዲሁም መራጩ ህዝብ ከተወዳዳሪ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የሚፈልጉት ዓይነት የፖለቲካ ኘሮግራምና ፖሊሲ አማርጠው እንዲለዩ እና በምርጫ ቀን የሚመርጡበትን ሁኔታ በማመቻቸት ረገድ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ስላለው በቅንነትና በህጋዊነት መከናወን አለበት፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በፍትሃዊነት እና በነፃነት ለተወዳዳሪዎች አገልግሎት መስጠት አለባቸው፡፡ በዚህ ላይ ለሚያዚያው ምርጫ የሚወዳደሩ አንዳንድ ፓርቲዎች በአየር ሰዓት ድልደላ ላይ ቅሬታ ሲያሰሙ ተደምጧል፡፡ ጥያቄው ተገቢ ነው አይደለም የሚለውን ትተን ሚዲያው ለዲሞክራሲ ግንባታ ተገቢውን አስተዋፅኦ ማበርከት በሚችልበት መንገድ መሥራት እንዳለበት ግን መታወቅ አለበት፡፡ በመጪው ሚያዚያ በሚደረገው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ቅሬታቸው በአየር ሠዓት ድልድሉ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የህብረት ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ለቀበሌ፣ ለወረዳ እና ለከተማ ምክር ቤቶች አባላት ቁጥር ከገዢው ፓርቲ ውጪ ያሉ ፓርቲዎች ሊያሟሉ ስለማይችሉ ፍትሃዊ ፉክክር ሊኖር አይችልም ሲሉ፤ በተመሳሳይ አቶ ልደቱ አያሌው የአዴአፓ መድህን ሊቀመንበር ደግሞ በበኩላቸው ምርጫውን የሚሳተፉት ለተሳትፎ እና የዴሞክራሲን መርህ ለማስከበር ብቻ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የመጪው ምርጫ ውጤት ቀድሞ የታወቀ እንዲመስል ሆኗል፡፡ በስተመጨረሻም ለዴሞክራሲ ግንባታ የተቋማት መጠናከርና ገለልተኛ መሆን እንዲሁም ውይይትና ድርድር መኖር ፍትሃዊ ፉክክርን በመፍጠር ትክክለኛ የህዝብ ተወካዮችን ያስገኛል፡፡ ጥቅሙም ለሁሉም ነው በማለት ምክራቸውን በሚለግሱን ምሀሯን ምክር እንቋጭ፡፡ በሄኖክ ሥዩም |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |