Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 11th
Home arrow Sections arrow የገበያ ውድድር በመፍጠር ገበያውን...
የገበያ ውድድር በመፍጠር ገበያውን... Print E-mail
Wednesday, 26 March 2008
የገበያ ውድድር በመፍጠር ገበያውን ማረጋጋት እንደሚቻል ተጠቆመ

የምርት ገበያ አገልግሎት፣ ሻጭና ገዢ የሚዋዋሉበትን ዋጋ በግልፅ በማስቀመጥ የገበያ ውድድርን በመፍጠር ገበያውን ሊያረጋጋ እንደሚችል ተጠቆመ፡፡

የኢትዮጵያ ስትራቴጂ ድጋፍ ፕሮግራም ኃላፊ ዶክተር እሌኒ ዘውዴ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ የዋጋ ንረቱ የመጣው ትክክለኛ ፍላጐትና አቅርቦት ባለመገናኘቱ ከሆነ ገበያው ሁለቱንም አካላት በማገናኘት ትክክለኛ ዋጋ የመወሰን አቅም ይኖረዋል፡፡ አገልግሎቱ ሚያዚያ ውስጥ እንደሚጀምርም ተናግረዋል፡፡

አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ ገዥና ሻጭ ሲዋዋሉ የሚገበያዩበት ዋጋ እንደማይታወቅ ዶ/ር እሌኒ ጠቁመው በዚህ ሂደት አምራችና ገዢ የሚዋዋሉበትን ዋጋ በ2ዐ የአገሪቱ ትልልቅ ከተሞች በተገጠሙ ስክሪኖች በየቀኑ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በነፃ የስልክ ጥሪ የሚያገኙበት ሂደት በማመቻቸት የገበያ ውድድርን የመፍጠር አቅም ይኖረዋል፡፡

በምርት ገበያ አገልግሎት ተሳታፊ እንዲሆኑ በመጀመሪያ ዙር 1ዐዐ አባላትን ለመመዝገብ አቅደው 136 ማመልከታቸውን ሆኖም መስፈርቱን እስከ አሁን አሟልተው የመጡት 6ዐ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ሻጭና ገዢ ለመሆን አባል ከሆኑት ውጪ የአባል ደንበኛ በመሆን አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚቻልና አቅራቢዎቹ አምራቾች፣ ነጋዴዎችና ፋብሪካዎች ሊሆኑ እንደሚችሉም ዶ/ር እሌኒ ተናግረዋል፡፡

ገበያውን ለመጀመር የተመለመሉትን አባላት በሲስተሙ ለማለማመድ ገንዘብና እህል ሳይኖር ገበያ የሚመስል ሁኔታን በመፍጠር ከሚቀጥለው ረቡዕ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ ስለ ገበያ ግንዛቤ እንዲኖረውና የአባላቱ ደንበኛ እንዲሆኑ ለማድረግ ማስታወቂያና የምርት ገበያ አገር አቀፍ ውይይት ከመጋቢት 26 እስከ 27 የሚመለከታቸው አምራቾች፣ ሸማቾች፣ ባለስልጣኖች፣ አምባሳደሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡

አገልግሎቱ በተዘጋጁት 6 መጋዘኖች በአዲስ አበባ፣ በናዝሬት፣ በሻሸመኔ፣ በሁመራ፣ በቡሬና በነቀምት እህል በመረከብ የምርቱን ደረጃ በማውጣት ማስቀመጥ እንደሚቻል በሁሉም ቦታ ወይም በተመረጡ ቦታዎች ይጀመር በሚለው ሂደት ላይ እየተወያዩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

አባላት በሲስተሙ ውስጥ ለመግባትና ለመገበያየት በተመረጡ ባንኮች የሂሳብ ደብተር መክፈት አለባቸው፡፡ የባንክ ሲስተሙ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ከምርት ገበያ ጋር ግንኙነት ያለው ሲሆን ግዢው ሲፈፀም ወደ ምርት ገበያ አካውንት በቀጥታ በማስተላለፍ በዚያው ባንክ ውስጥ ባለው የሻጭ አካውንት እንደሚዛወርም ገልፀዋል፡፡

በሀገር ደረጃ የርክክብ አፈፃፀም ባለመኖሩ ከአንድ አካል ተረክቦ ወደ ሌላ ለማስተላለፍ የራሳቸው ባንክ ስለሌላቸው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከዳሽን ባንክ ጋር የትብብር ስምምነት መፈራረማቸውንም አመልክተዋል፡፡

ገንዘብ እንዲዘዋወር ሲፃፍላቸው ወዲያውኑ የገንዘብ ዝውውር የርክክብና የክፍያ አፈፃፀም፣ የሽያጭና የግዢ ልውውጥ በባንኮቹ ሂደት ያልፋል፡፡

አገልግሎቱን እንዲሰጡ ሁሉም ባንኮች እንዲዋዋሉ ጥያቄ እንዳቀረቡ ዶ/ር እሌኒ ጠቁመው፣ አገልግሎቱ አዲስ በመሆኑ በሁሉም ባንክ አገልግሎቱን መጀመር የሁሉንም አቅም ለመደገፍ የሚገናኙበትን ፕሮቶኮል ለማስተካከል የሚያስፈለጉ ስልጠናዎችን ለመስጠት ካላቸው አቅም አንፃር ቁጥሩን ውሱን ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

ባንኮች መጋዘን በሚገኝባቸው አካባቢዎች መገኘታቸውና በኔትወርክ ሲስተም ከአንዱ አካል ተረክበው ወደሌላኛው ለማስረከብ የሁለቱንም ወገኖች አደጋ ስላለ ከባንኮቹ ጋር በቅርበት እየሠሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

የመጋዘኖቹን ቁጥር መጨመር የሚሰጠውን አገልግሎት፣ ምርትን የማግኘት አቅማቸው እንደሚዳብር ለዚህም አሁን ባሉት መጋዘኖች አቅማቸውን በማሳደግ በቀጣይ ተጨማሪ መጋዘኖችን ለመክፈት እንዳሰቡም ተናግረዋል፡፡

ምርቱን ለመጋዘን ለማቅረብ የአባል ደንበኛ መሆን በቂ ቢሆንም ወደ ልውውጥ መድረኩ ለመግባት የመጋዘን ደረሰኝ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ ከሻጮች የእህሉን ናሙና በመውሰድ ያለውን ደረጃ መጠን በመግለፅ በተሰጣቸው ደረሰኝ የዋጋ ድርድር እንደሚካሄድም ገልፀዋል፡፡  

ደረሰኙ የመሰረቅና በፎርጅድ የመሠራት አደጋ ስላለው፣ ይህን ለመከላከል ለሻጭ የሚሰጠው ደረሰኝ በኤሌክትሮኒክስ ሲስተም እንደሚመዘገብ አስረድተዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክ መጋዘን ሲስተም አንድ ሻጭ ነጋዴም ሆነ አምራች ንብረቱን ሲያስረክብ በሚሰጠው መረጃ የደረሰኝ ቁጥር መጠንና ዓይነቱ እንደሚመዘገብ ለመሸጥ ሲፈልግ አባል ከሆነ በራሱ አለበለዚያ የአባልነት ወረቀት ባላቸው ሻጮች እንደሚከናውን ጠቁመዋል፡፡

የእለቱ ገበያ ዋጋ የተለያዩ ገዥና ሻጭ ለየብቻቸው እንደሚዋዋሉ በጨረታው ሰዓት በየደቂቃው የሚቀያየረውን ዋጋ በወቅቱ በሚካሄድበት ጊዜ በድረ ገፅ  እንደሚገልፁ ጠቁመዋል፡፡ ዋጋው እንደየ ሰው ብዛትና እንደ ውሉ መጠን እንደሚቀያየርና ለእያንዳንዱ ምርት የ15 ደቂቃ የጨረታ ሰዓት እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡

የመክፈቻ፣ የመዝጊያ፣ ከፍተኛ፣ ዝቅተኛ ዋጋና ለውጥ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ በየቀኑ መሠራጨቱን የጨረታ ድርድር በሚካሄድበት ሰዓት ግን ዋጋውን በየደቂቃው በአገሪቷ 2ዐ ዋና ከተሞች ላይ በተተከሉ ስክሪኖች እንደሚገለፅ ጠቁመዋል፡፡

በጨረታ የሚወሰነው በተለያየ ጊዜ ገዥና ሻጭ የደረሱበት የስምምነት ዋጋ በእለቱ የገበያ ዋጋ እንደሆነና ተደራዳሪዎች በጣም ብዙ ፍላጐት ካለ ዋጋን የሚጨምሩበት፣ ብዙ አቅርቦት ካለ በየደቂቃው ዋጋ የሚቀንስበት ሂደት ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል በነጋዴዎች መካከል ዋጋን በስምምነት የሚወስኑበት ሂደት አንዳለና ይህ እንዳይፈጠር የምታደርጉት ጥንቃቄ ካለ ብለን ለጠየቅናቸው ሲመልሱ መድረኩ ትክክለኛውን አቅርቦትና ፍላጐት ማገናኘት ሲሆን የሁለቱ ጥምረት የሚፈጥረው የተስተካከለ ዋጋ እንደሚሆንና በአገሪቷ በሲሰተሙ ተሳታፊ የሚሆኑት አባላት ቁጥር ሲጨምር ትክክለኛ ዋጋ የማምጣት አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ትክክለኛ ዋጋን ለመወሰን በየትኛውም ገበያ ላይ አቅርቦትና ፍላጐትን በመቀያየር የሚፈጠር ችግር እንዳለ ጠቁመው አንድ ሰው ገበያ ላይ የቀረበውን በሙሉ በመግዛት ዋጋን የሚሰቅልበት ሂደት ሲኖር ከመደበኛ የአቅርቦትና የፍላጐት መገናኘት ውጪ የተለየ ሥራ እንዳይሠራ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በሲስተሙ በገበያ ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ለማስተካከል በአንድ ጨረታ ላይ ከተወሰነ መጠን በላይ እንዳይገዛ፣ ዋጋውን በመስቀል የውሸት ዋጋ መናገርና እንዲታይ ተደርጓል፡፡ በስምምነት ዋጋ የሚሰቅሉበትን የሚያወርዱበት ሂደት የነፃ ገበያ አሠራር እንደሚያሰናክል የገበያ ክትትል ቡድን እንዳለና የገበያውን ሂደት እንደሚከታተሉ ተናግረዋል፡፡

የገበያ ቁጥር ከተለመደው ሂደት ውጪ ሲፈጠር እንዴት ተከሰተ፣ ችግሩ የት ነው የሚለውንም ማጥናት የገበያው ሥራ መሆኑን በደንቡ መሠረት የገበያ ሥራ አስፈፃሚ ለተወሰነ ሰዓት ገበያው የሚቆምበትና ለማረምና ለማብረድ የሚያስችል የተለያዩ ሂደቶችን እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል፡፡

በቤዛዊት ሥዩም
 
< Prev   Next >