| መንግሥት ዘመናዊ የጭነት መኪና... |
|
| Wednesday, 09 January 2008 | |
|
መንግሥት ዘመናዊ የጭነት መኪና መግዛቱን የግል ባለንብረቶች ተቃወሙ በደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ሥራ የተሰማሩ ባለንብረቶች ..መኪናዎቻችን ሥራ አጥተው በቆሙበት ወቅት መንግስት አዳዲስ መኪናዎች መግዛቱ አግባብ አይደለም.. አሉ፡፡ ..መኪናዎቻቸው የቆሙት ሥራ አጥተው ሳይሆን ዘመናዊ የትራንስፖርት ማኔጅመንት ስለሌላቸውና ሥራም ስሩ ሲባሉ አንሰራም በማለታቸው ነው.. በማለት የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ምላሽ ሰጥቷል፡፡ መንግስት እየገነባቸው ላለው የቤቶች ልማትና የግንባታ ፕሮጀክቶች ሲሚንቶና ሌሎች የግንባታ ዕቃዎችን ከወደብ በፍጥነት ለማጓጓዝ ስለሚቻልበት ሁኔታ ታህሳስ 25 ቀን 2000 ዓ.ም በመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን አዳራሽ ባደረጉት የጋራ ውይይት ባለሃብቶቹ እንደገለፁት፣ ..አገራችንን ያጨናነቀው የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ነው፡፡ ዘመናዊ መኪናዎች ሥራ አጥተው ቆመዋል.. በማለት የአሰራር ችግር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ጅቡቲ ላይ ከአንድ ሺ በላይ የጭነት መኪናዎች ሥራ በማጣት ቆመው ሲውሉ መንግስት ኃላፊነት ወስዶ በአግባቡ ስለማያሰራን ለደላላ፣ ለትራንዚተር ጉቦ እየከፈሉ ጭነት ሲያፈላልጉ እንደሚውሉ የተናገሩት ባለንብረቶቹ የአንድ ወገንን ስሜት በመጠበቅ የሚሰራው አሰራር ለከተማ ልማት ገንቢ ሊሆን ቢችልም የትራንስፖርት ባለንብረቶች ግን ያጠፏቸዋል ብለዋል፡፡ በደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ሥራ ዘርፍ የተሰማራው የሚበላው በማጣቱ መኪናዎቹን ለመሸጥ ጨረታ እንዳወጣ፣ ነገር ግን መንግስት ከ2000 የማያንሱ ገልባጭ መኪናዎችን ገዝቻለሁና ..ግዙኝ.. ማለቱ አግባብ አለመሆኑን ባለሃብቶቹ ተናግረዋል፡፡ ..በአሁኑ ወቅት በደረቅ ትራንስፖርት ሥራ ለተሰማራን ባለንብረቶች በመንግስት በኩል ቀና አስተሳሰብ የለም፡፡ በመሆኑም ሁሉም ባለንብረት እየተማረረ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም ውድቀት ነው፡፡ ባንክ ለትራንስፖርት ባለንብረቶች አያበድርም፤ ምክንያቱም ውጤታማ እንደማንሆን ያውቃል፡፡ መንግስት ይህንን ሁሉ አስተካክሎልን ቢሆን እኛም አድገን አገርም ያድግ ነበር፡፡ አሁን ግን መንግስት የሚሰራው ሥራ እኛንም ያላማከረበትና ጥናትም ያላደረገበት በመሆኑ አሰራሩ አግባብ አይደለም.. በማለት ያለባቸውን ችግር በውይይቱ ወቅት በስፋት አስረድተዋል፡፡ ባለንብረቶቹ አሉብን ባሉት ችግሮች ላይ የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርት መገናኛ ሚኒስቴርና የትራንስፖርት ባለስልጣን በጋራ በሰጡት ምላሽ፤ መኪናዎቻቸው የቆሙት ሥራ ጠፍቶ ሳይሆን በዘመናዊ ትራንስፖርት ማኔጅመንት ስለማይሰሩና ስራም ሲኖር አንሰራም በማለታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ..የደረቅና ፍሳሽ ትራንስፖርት ድርጅት የተደራጁ አለመሆናቸውን፣ የሰለጠነ ማኔጅመንት አለመኖርና ያልተስተካከለ ኦፕሬሽን ብቃት መኖር፣ እየታየባቸው መሆኑን በአገራችን ከ14ሺ የማይበልጡ የደረቅ ጭነት መኪናዎች ቢኖሩም 50 ከመቶ የሚሆኑት ከ20 ዓመት በላይ ያገለገሉ መሆናቸው፣ ባላቸው ኋላ ቀር የማኔጅመንት አሰራር የተነሳ ሁሉም ተነስተው ጂቡቲ ለመግባት በሚያደርጉት ግብግብ ችግር እንደሚፈጥርና በመኪናዎች እጥረት በመኖሩ መንግስት መኪናዎችን ለማስመጣት ከውሳኔ ላይ መድረሱን የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ጁነዲን ሳዶ ገልፀዋል፡፡ ..የደረቅ ጭነት መኪና እጥረት የለም የሚለውን ለማመን እቸገራለሁ፡፡ ምክንያቱም በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች በደረሰ የምግብ እጥረት ሲከሰት ወደብ ላይ እርዳታ ሲመጣ የምናጓጉዝበት ትራንስፖርት ችግር ገጥሞን እንደነበር ሁላችንም እናውቃለን፡፡ አሉን የምትሏቸው መኪናዎች ጥራት፣ ቅልጥፍናና በሚፈለጉበት ደረጃ ላይ አይደሉም.. በማለት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ አቶ ጁነዲን አክለው እንደተናገሩት፣ የመጋዘንን ችግር ለማቃለል፣ በሰመራና ሞጆ ላይ የደረቅ ወደብ አገልግሎት ለመስጠት ቦታና ካርታ መረከባቸውን በቅርቡ ግንበታ እንደሚጀምሩ፣ በተለይ በሞጆ በሚቀጥለው ሳምንት ግንባታ እንደሚጀመር አብራርተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ ያለውን የመንገድ ችግር መመልከታቸውንና ለማሻሻል ጥናት እያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ ባለንብረቶቹ አሰራራቸውን ዘመናዊ በማድረግ አዲስ ያስመጧቸውን የደረቅ ጭነት መኪናዎች እንዲገዙ፣ ዋጋቸው በጣም ዝቅተኛ የሆነ ዋጋ መሆኑን፣ ነገር ግን ከዓለም የትራንስፖርት ዋጋ ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዋጋ ውድ መሆኑን ገልጿል፡፡ መንግስት በዋናነት መኪናዎቹን ሊያስገባ የወሰነበትን ምክንያት በአገር አቀፍ የተቀናጀ የቤቶች ልማት በዓመት 150ሺ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስፈልገውን ከፍተኛ የኮንስትራክሽን እቃዎች ማጓጓዢያ አቅም ለመፍጠር መሆኑን አቶ ጁነዲን ተናግረዋል፡፡ ..የትራንስፖርት ሥራ የራሱ የሆነ እቅድ ይፈልጋል፡፡ ብዙዎቹ የጭነት ባለንብረቶች በዘመናዊ የትራንስፖርት ማኔጅመንት የሚሰሩ አይደለም፡፡ ዕቅድ እንኳ የላቸውም፡፡ ባለፈው ዓመት የተለያየ የኮንስትራክሽን እቃ አስመጥተን፣ ጫኑልን ብለን ስንጠይቅ ሌላ ስራ ስላለን አንጭንም፣ ነው ያላችሁን፡፡ (በተለይ የተባበሩት ተራንስፖርተርስ) የመከላከያ ትራንስፖርትን በመጠየቅ ከሦስት ወር በላይ ጊዜ ፈጅቶ ነው ያስመጣነው፡፡ አሁን በጣም ከፍተኛ ቶን እያስመጣን ነው፡፡ ታዲያ ይህ መንግስትን ሊያስወቅስ፣ ሥራ የለም ሊያስብል ይችላል?.. በማለት የጠየቁት የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አርከበ ዕቁባይ ናቸው፡፡ መንግሥት 40ቶን የሚጭኑ 2000ሺህ ገልባጭ የደረቅ ጭነት መኪናዎች ከ850ሺ እስከ 875ሺ በሆነ ዋጋ ከቻይና ኩባንያ ለመግዛት ስምምነት ላይ መደረሱን፣ አገር ውስጥ ያሉትን ሾፌሮች የሚያሰለጥኑ 20 መካኒካል ኢንጂነሮች እንደሚመጡና ለ2000 ሾፌሮች ስልጠና የሚሰጡ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡ ..ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ብዙ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ወደ ጅቡቲ ሾፌሮቻቸውን መኪና አስይዘው በመላክ ችግር አለብን የሚሉትን አንቀበልም፡፡ ምክንያቱም ለደላላና ለትራንዚስተር ጉቦና ሌላ ሌላ ነገር ከመስጠትና ጭነት ከመፈለግ፣ በእቅድና ከእኛ ጋር ተባብረው ቢሰሩ ይህ ችግር አይደርስባቸውም፡፡ ይህንን በተያያዘ መድረክ ተገናኝተን ተነጋግረናል፡፡ እናንተም አትክዱም.. ሲሉ የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ኃይለማርያም አብራርተዋል፡፡ ማንም ተበዳሪ ከየትኛውም ባንክ የተበደረውና ያልከፈለው ዕዳ ካለበት መበደር እንደማይችል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለትራንስፖርት ባለንብረቶች አላበድርም አለማለቱን መንግስት ለሚያስገባቸው አዳዲስ መኪናዎች ገዢዎች 30 በመቶውን አስይዘው 70 በመቶውን ባንክ ሊያበድራቸው እንደሚችልና፣ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ስምምነት ላይ ስለተደረሰ መበደር እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተወካይ ተናግረዋል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |