| ምክንያቱን እንጂ መፍትሔውን አልነገሩንም |
|
|
| Wednesday, 26 March 2008 | |
|
የኑሮ ውድነት የሃገር ምድሩ መነጋገሪያ ከሆነ ሰነበተ፡፡ ሁሉም መነጋገሪያ ብቻ ሳይሆን የፀሎቱ መጀመሪያ ያደረገው እስኪመስል ድረሰ የኑሮ ውድነትን በስጋት ስሜት ያነበንባል፡፡ በቤተክርስቲያናትና በመስጊድ፣ በታክሲና በአውቶብስ፣ በዕድርና በስብሰባ፣ በቡና ቤትና በጠጅ ቤት፣ በከተማና በገጠር አጀንዳው የኑሮ ውድነት ሆኗል፡፡
ተፈጥሮና መሪዎቻችን እንደሚሉንም የዓለም ገበያ ዋጋ መቃወስ፣ የኑሮ ውድነትን ከፍ ስላደረገው ስጋቱ ነፍስና ሥጋችንን አንጠልጥሎታል፡፡ የሕይወት ጉዳይ፣ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ፣ የመብላትና የመራብ ጉዳይ የሆነው የኑሮ ውድነት አሁን አሁን ከፊታችን የደቀነው ቀውስ፣ ከምንጊዜውም በላይ በአስፈሪ መልኩ ተጋርጧል፡፡ የኑሮ ውድነት በገጠርና በከተማ ያሳደረውን የመኖርና ያለመኖር ጭንቅና ጥብ በቅጡ ለመረዳት የችግሩ የቀጥታ ተጎጂ የሆኑትን በአካል ተገኝቶ ማየት ጥሩ መረጃ ይሆናል፡፡ በገጠር የትኛው ነው የተቸገረው? የትኛው ከተሜ ነው የችግሩ ሰለባ የሆነው የሚለውን ለክቶና መዝኖ ለማወቅ የመጀመሪያ እጅ መረጃ ማግኘት እውነቱን ለማግኘት ይረዳል፡፡ በቅድሚያ በአሁኑ ጊዜ የኑሮ ውድነት የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ እየሆነ መምጣቱን መስማማት አለብን፡፡ አንዳንድ ጊዜ በመንግሥት ባለስልጣኖችና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር የሚነገረው፣ የገጠሩ ሕዝብ የኑሮ ውድነቱ ተጠቃሚ እንደሆነ ነው፡፡ በኑሮ ውድነቱ ተጠቃሚ የሆነው ገበሬ በሃገሪቱ ክፍል በሙሉ የሚኖረው መሆኑንም በመቶኛ ጭምር እያሰሉ ይነግሩናል፡፡ እውነቱን ለማወቅ ወደ አካባቢው መጠጋት ይጠይቃል፤ የምለውም ለዚህ ነው፡፡ ስሌቱ በወረቀት ላይ የታሰበ ሂሳብ ይመስላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እውነታና የወረቀት ስሌት ክፉኛ የሚላተሙበት ጊዜ አለ፡፡ በርበሬ ስለተወደደ ተጠቃሚ የሚሆነው በርበሬ አምራች ገበሬው መሆኑ ባይካድም ነገር ግን በሃገሪቱ በስንቱ ክፍል በርበሬ እንደሚመረትና ተጠቃሚው ገበሬው ምን ያህሉ እንደሆነ በመቶኛ ቢተመን የተሻለ ሥዕል ያሳያል፡፡ እህል ተወደደ ሲባል መጀመሪያውኑ ከራሱ ተርፎ ወደ ገበያ የሚያወጣው ምን ያህሉ ገበሬ ነው፤ ብሎ ማጠያየቅና የታመነ መረጃ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ እኔ በማውቃቸው አካባቢዎች አብዛኛዎቹ ማለት ባልችልም ግን ትንሽ በማይባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ገበሬዎች እህል ለመሸጥ የሚችሉ አይደሉም፡፡ በሰሜን በሃገሪቱ ክፍል በተለይ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜንና በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ የመኸር ምርት የሚጠበቀውን ያህል ሳያገኙ እየቀሩ የክረምት ወራት በረሃብ እየተሸነቆጡ እንደሚከርሙ የሲ.ኤን.ኤን ጋዜጠኛ ባቀረበው ፕሮግራም ወይም በአካባቢው ካድሬዎች ሪፖርት ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን መጠየቅ ነው፡፡ በዚያም ላይ የሰብል ምርት በማዳበሪያ አጠቃቀም አድጓል፤ ቢባልም የማዳበሪያ ዋጋው ቀላል ስላልሆነ ለክፍያ የሚያወጣው ገንዘብ ለችግር እንደዳረገው በተደጋጋሚ ሲገለፅ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ከላይ በገለፅሁዋቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች፣ በተለይ የበልግ አብቃይ የሆኑት አካባቢዎች ከአምስትና ስድስት ዓመታት በላይ የበልግ ምርት አግኝተው አያውቁም፡፡ እንኳን በቂ የበልግ ምርት ማግኘት ይቅርና፣ ተስፋ ሳይቆርጡ በመዝራታቸው የተረፋቸው የዘር መዋጮ ብቻ ነው፡፡ ዘራቸውን እንኳ ሳይመልሱ አጨብጭበው ሲቀሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የበልግ መሬት ውሃማ ስለሚሆን ለመኸር ምርት ሊዘራበት ስለማይችል ቢዘራም ፍሬያማ ሊሆን ስለማይችል ለወደፊቱም በተስፋ ከመቀጠል የዘለለ ሌላ ጥቅም ሊያገኙ አይችሉም፡፡ እነዚህ ገበሬዎች በመቶኛ ሲሰሉ ስንት እንደሆኑ ለማወቅና ለተከታታይ ዓመታት በምርት እጦት ምክንያት መቸገራቸውን ለማየት ከሪፖርት ስሌት ይልቅ ወደነሱ ተጠግቶ ማነጋገርና ማየት እውነቱን ያመለክታል፡፡ እስከ ዛሬም በተደጋጋሚ አዝመራ አለማገኘታቸው መደበቁ ከሀገሪቱ ገበሬዎች መቶኛ ስሌት አልተካተቱ ይሆን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በአማራው ክልል በምግብ ሰብል ራሳቸውን ያልቻሉ አካባቢዎች በመንግሥት እገዛ ሥር ወድቀው ሳለ፣ እነሱም ደልቷቸውና የኑሮ ውድነቱ የጠቀማቸው መሆኑን ከመንግሥት ኃላፊዎች ሲነገር መስማት የሚያደናግረውን ያህል ለመቀበልም እጅግ ያስቸግራል፡፡ የእነዚህ ዓይነት በምግብ ሰብል ራሳቸውን ያልቻሉ ወረዳዎች ምናልባት በትግራይና አነስተኛም ቢሆን በኦሮምያ ክልሎች አይጠፉም፡፡ ባለፉት ዓመታት ለድርቅ የሚያጋልጥ አየር ፀባይ በተለያዩ ክልሎች ታይቷል፡፡ የሶማሊያና የአፋር ክልሎች በዚህ ተርታ ይጠቀሳሉ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ገበሬዎች ቁጥራቸው በኑሮ ውድነቱ ተጠቃሚ ናቸው ከሚባሉት ከሆነ እንዴት ሊተመን ይችላል? ገበሬው በኑሮ ውድነቱ የተጠቀመው አብዛኛው ነው፤ የሚባል ከሆነም አነስተኛውም ቢሆን፣ በረሃብና በእርዛት ጉዳይ፣ በመቶኛ የበዛው ተመችቶታል ተብሎ አነስተኛው ሊረሳ አይገባውም፡፡ ወይም 90 በመቶ እየተባሉ በስሙ መግለጫ ሊወጣበት አይገባም፡፡ ቡናን የመሳሰሉ የገበያ ምርት አምራቾች፣ ለአጠቃላይ የሃገሪቱ የገጠር ነዋሪዎች እድገት መለኪያ ሊሆኑ እንደማይችሉ የሚያከራክረን አይመስለኝም፡፡ በአንዳንድ የሃገሪቱ ክፍል ገበሬው ስንዴና ገብስ ሸማች መሆኑ አሁን አሁን እየበዛ መምጣቱን እያየን በውድነቱ ተጠቃሚ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዥነት የሚታየው፣ በተለይም በልግ አብቃይ ለሆነው የበግ አርቢ ገበሬ፣ በበልግ ዝናብ እጥረት ምክንያት በጎቹ ስለሚያልቁበት ችግሩን አባብሶበታል፡፡ ከየካቲት ጀምሮ በፀሐዩ ብርታት ምክንያት የሚበሉት ማጣታቸው ሳያንስ፣ የበልጉ እህል መክኖ ሊቀር በክረምትም ያለመብል የሚያገልግላቸው ቃርሚያ ስለሚያጡ ያልቃሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት በዚህ ሁኔታ በርካታው የበልግ አብቃይ ገበሬ ዋነኛ የገንዘቡ ምንጭ የሆኑትን በጎቹን አጥቷል፤ በድህነቱ ላይ ድህነት ተጭኖታል፡፡ እነዚህ ገበሬዎች በምንም ስሌት የኑሮ ውድነት ተጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በዚህ ዓመት በድርቅ አደጋ ይከተላል፤ ተብሎ ከፍተኛ ሥጋት በገበሬው ዘንድ ተፈጠሩዋል፡፡ በእህል ብቻ ሳይሆን በመኸሩ እጥረት በተፈጠረው የምርት እጥረት የከብት መኖ እጥረት በመፍራት ከአሁኑ ዋጋው እየሻቀበ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከላይ በገለፅሁዋቸው አካባቢዎች ከብቶች ወደገበያ ለግዥ ማውጣት ጀምረዋል፡፡ ግን ገዥው እጁ አጥሩዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ ባለፈው ሳምንት የፓርላማ ንግግራቸው የከብት ዋጋ አለመቀነሱን ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው በገለፁዋቸው 90 በመቶ የገበሬ አባላት ውስጥ አይካተቱም፤ ካልተባለ በስተቀር፣ በዋድላ ደላንታ፣ በተንታ፣ በመቅደላ (በደቡብ ወሎ..ና በሰሜን ሸዋ፣ ከአሁኑ የከብት ዋጋ መቀነስ ጀምሯል፡፡ በቅርቡ በገበያ ላይ ተዘዋውሬ እንዳየሁትና ተወላጆቹ እንደነገሩኝ፣ ነጋዴው ካልሆነ በስተቀር ገበሬ ለእርሻ በሬ ከመግዛት ተቆጥቧል፡፡ ከእነዚያ ቀበሌዎች የሚገዛው ነጋዴ መጠነኛ እንደመሆኑ በርካታ የቀንድ ከብቶች ሲቀርቡ ዋጋው ይረክሳል፡፡ ከአሁኑ የከብት ዋጋ መቀዝቀዝ መንስኤው የበልግ ዝናብ መቅረትና ከሱም ጋር ተከትሎ የሚመጣው የከብት መኖ ችግር ስላሰጋው ነው፡፡ የአሁኑ ዋጋ መቀነስ ለወትሮው የቀንድ ከብት ውድ በሚሆንባቸው በየካቲትና በመጋቢት ላይ መሆኑ በቀጣዮቹ ወራት በተለይ የክረምት ወቅት ሲገባ የከፋ እንደሚሆን ገበሬዎቹ ከልምዳቸው በመነሳት ሰግተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ በኑሮ ውድነት ሁሉም ገበሬ እንዴት ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል? እውነቱ እንደዚህ ነው፡፡ አቶ መለስ የዝናቡ እጥረት የሚፈጥረውን ቀውስ ለመቋቋም መንግሥት እያሰበበት መሆኑ የተናገሩት እውነትና ውጤታማ እንዲሆን እንመኛለን፡፡ ነገር ግን አደጋው በአንድ ቀን ዜናና የፓርላማ ንግግር የማድረግን ያህል የቀለለ አለመሆኑን የዜግነት አስተያየቴን መስጠት እፈለጋለሁ፡፡ አደጋው በቅድሚያ በከብት ተከትሎም በሰው ሕይወት ላይ ያነጣጠረ እንደሚሆን ወደ አካባቢው ዘልቆ በማየት መገንዘብና ማመን ይቻላል፡፡ ከከተማው ነዋሪም ችግሩ በአብዛኛው የሚጎዳው ዝቅተኛውን ክፍል ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በእርግጥ የችግሩ ጉዳት መጠኑ ይለያይ እንጂ የሕይወቱን አቅጣጫ ከመመራት አኳያ ካየነው የብዙዎች ችግር እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሰራተኛው ደመወዙ በከፍተኛ ሁኔታ የተጨመረለት መሆኑን ጠቅሰው ጥሩ ኑሮ እንደሚኖር ጠቅሰዋል፡፡ ግን የተጨመረው ከወጪው ጋር ሲተያይ ርቀቱ የሰማይና የምድር ያህል በመሆኑ ከችግሩ የተላቀቀ አለመሆኑን ባለጉዳዩን ቢያነጋግሩት ልብ በሚሰብር ቋንቋ ሊነግራቸው በቻለ ነበር፡፡ ሠራተኛው የተጨመረለት ገንዘብ የአሁኑን የዋጋ ጭማሬ ተጭኖበት ይቅርና ቀድሞውንም ቢሆን እንደማረጋጊያ እንጂ ኑሮውን ያገናዘበ ነው ተብሎ አይገመትም፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሠራተኛ ራሱን ሸክፎ፣ ፍላጎቱን ገትቶ ለትንፋሹ መዋያ ማደሪያ ብቻ ያህል እንደሚኖር ለማወቅ የወር ደመወዝ ተከፋይ ከሆኑት ሠራተኞች ቤት ገብቶ ጓዳቸው ቢታይ የበለጠ እውነቱን ያሳያል፡፡ የወር ተከፋይ ሠራተኞች (ከሁለት ሺህ እስከ አራት ሺህ) ብር ድረስ የሚከፈላቸው እንኳ ቢሆኑ፣ ቤት ለመሥራት ይቅርና በየጊዜው እየተፈነጠረ የሚወረወረውን የኑሮ ውድነት ተቋቁመው የመኖር ዋስትናቸውን ሊያረጋግጡ አልቻሉም፡፡ በደረጃና በመቶኛ ከተመዘኑ በልቶ ጠግቦ ከሚያድረው የተሻሉ መስለው ቢታዩም፣ ውድነቱ በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ ድምራቸው ከዚያ በታች ተከፋይ በሆኑና በረሃብ አርጩሜ እየተሸነቆጡ፣ መስለው ለማደር ደረቅ ፈገግታቸውን ከሚያሳዩት፣ ልጆቻቸውን በቅጡ ለማሳደግ ቸግሯቸው ለብቻቸው ማውራት ከጀመሩት፣ ራሳቸውን እንደሠራተኛ ሊያስደስቱ ካልቻሉት ጋር መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ለአፍ የሚሞቅ የብር ቁጥር እየቆጠሩ ግን ቤት ለመገንባት አቅቷቸው ቦታ ወስደው የጀመሩትን ግንባታ አቋርጠዋል፡፡ ልጆቻቸውን ካስገቡባቸው የተሻሉ ትምህርት ቤቶች ማስወጣት ጀምረዋል፡፡ የመኪና ባለቤትነት ነገር ማሰባቸውን አቁመዋል፡፡ ተከራይተው መኖር አዳግቷቸዋል፡፡ ይክን ሁሉ የምናገረው በሺዎች የሚከፈሉትን በተመለከተ ነው፡፡ ከዚያ በታች የሚከፈለውማ ቆሞ ከሄደ ..ተመስገን.. ብሎ የሚያድር አይደለምን? በየዕለቱ ኑሮ እያደቀቀው የሄደው እየበዛ ..አብዛኛው የተሻለ ይኖራል.. ሲባል አድማጭ አለ ወይ? ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የኑሮ ውድነቱን ምክንያቶች ነግረውናል፡፡ የስንዴና የነዳጅ መወደድ ምክንያቱን ነግረውናል፡፡ ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ጥያቄው የእኛ መንግሥት አሁን አደረኩት ከሚለው በላይ ማድረግ አይችልም ነበር ወይ? ኧረ መፍትሔውስ ምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ ምክንያቶቹ ገብተውናል፡፡ ኢኮኖሚያችን ዕድገት ማሳየቱንም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጭምር መመስከሩን ሰምተናል፡፡ ነገር ግን ለመስማማት የሚያዳግተን ኢኮኖሚያችን ለማደጉ 90 በመቶ የሚሆነው የገጠር ገበሬ ተጠቃሚ ነው በሚለው አሳሳች መግለጫ ነው፡፡ ሠራተኛው ደመወዙ አድጓልና የኑሮ ውድነቱ ተጠቃሚ ነው ሲባል ነው፡፡ ይኸ እውነቱን አያሳይም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ባለፈው ሳምንት በተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ባለገንዘቡ የወለድ ምጣኔ ከዜሮ በሆነበት ሁኔታ በባንክ ማስቀመጡ ያልገመቱት መሆኑንና ይኸም እንዳስገረማቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ መለስ ሻዕቢያ እንደሚወረን እየተነገራቸው ሊወረን ይችላል፤ ብዬ በሕልሜም በውኔም አልገመትሁም ነበር፤ ማለታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ አንዳንድ ጉዳዮች ባልተጠበቀ ሁኔታ ሲሄዱ መንግሥት ምን ማድረግ አለብኝ ብሎ ማሰብና መገመት የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ አለበለዚያ ስህተት በተፈጠረ ጊዜ ሁሉ ያልገመትነው ነገር ነበር፤ ብሎ ማለፉ ስሜት አይሰጥም፡፡ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ጠቅላይ ሚኒስትራችን የኑሮ ውድነቱን፣ የጉስቁልናችንን፣ የአበሳችንን ምክንያት ገልፀው መፍትሔ ያሉትንም ጠቁመውልናል፡፡ በምግብ እህሎች ላይ የቫትና የሱር ታክስ መቀነሱ ተነግሮናል፡፡ ግን እውነት መፍትሔው መፍትሔ ነወይ? በየቦታው ገብተን ዘይትና የቅባት ምግቦች ስንጠይቅ ቫት አልተነሳላቸውም፤ ተብለናል፡፡ የታሸጉ ምግቦች ቫት አልተነሳላቸውም ተብለናል፡፡ ታዲያ ለጤፍና ለበቆሎ ልውውጣችንማ ወትሮስ ከየገበያውና ከየወፍጮ ቤቱ ስንገበያይ አልነበረምን? እስከ ዛሬ ለጤፍና ለጥራጥሬ እህሎች ደረሰኝ ተቆርጦ ገዛሁ የሚል ሰምቼ አላውቅም፡፡ ስለዚህ አሁንም መፍትሔውን አግኝተውለታል ለማለት አይቻልም፡፡ ተስፋ ሊኖረን ይችላል፡፡ አሁን ግን ችግር ላይ ነን፡፡ የረሃብ አደጋ የመኖርና አለመኖር አስደንጋጭ ጥያቄ ከፊታችን ተደቅኗል፡፡ የክስተቶችን ምክንያት መናገር ጥሩ ቢሆንም ዋናው ግን መፍትሔውን መፈለግና ማሳወቅ ነው፡፡ ምክንያቱን መደርደር እስኪሰለቸን እየነገሩን መፍትሔውን ካላስረዱን ምን ይረባናል? ምክንያት ረሃብ ለጎነጠው ሆድ ማስታገሻ አይሆንም፡፡ ምክንያት መተንተን ብቻውን እንደቋጥኝ እየከበደ የሄደውን ኑሮ አያቃልልም፡፡ ከሃብታሙ በቀለ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |