| የኢትዮጵያ መድን ድርጅት |
|
|
| Wednesday, 26 March 2008 | |
|
- የገበያ ድርሻውን ወደ 43 በመቶ አሳደገ
- ለሠራተኞቹ 35 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ አደረገ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኝ የኢንሹራንስ ኩባንያ ነው፡፡ ከተቋቋመ ከ34 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ከደርግ ውድቀት በኋላ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ገበያው ገብተው እንዲሰሩ ከተፈቀደ ወዲህ በብቸኝነት ይዞት የነበረውን ሥራ ከሌሎች የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር ተወዳድሮ መስራት ግድ ሆኖበታል፡፡ የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ገበያ ከመግባታቸው በፊት የአገሪቱን የኢንሹራንስ ሥራ 100 በመቶ ይዞ የቆየ ቢሆንም ይህን ድርሻውን በአሁኑ ጊዜ ዘጠኝ የሚደርሱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተጋርተውታል፡፡ ይህ የገበያ ድርሻው እስካለፈው የበጀት ዓመት መጠናቀቂያ ድረስ ወደ 39 በመቶ ድረስ በመውረዱ የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የገበያ ድርሻ 59 በመቶ መድረስ ችሏል፡፡ ኩባንያው ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ በውስጡ ብዙ ችግሮች እንደነበሩትና በተለይ የሠራተኛውና የማኔጅመንቱ ግንኙነት ጥሩ ባለመሆኑ መሥራት ያለበትን ያህል እንዳልተሰራ ያነጋገርናቸው ሠራተኞችና የድርጅቱ የሠራተኞች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ኃይሌ ኪሮስ ይገልፃሉ፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ያለው ችግር በመባባሱ ምክንያት በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ሁለት ማኔጅንግ ዳይሬክተሮች ተቀያይረዋል፡፡ እንደ ሠራተኞችና እንደ ሠራተኞቹ ማኅበር አመራሮች ከሆነ ደግሞ በ2000 የበጀት ዓመት በድርጅቱ ውስጥ ይታይ የነበረው ችግር እየተቀየረ በመምጣቱ ድርጅቱም የአትራፊነት እድገት አሳይቷል፡፡ አዲሱ ማኔጅመንት ሥራ ከጀመረ 6 ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ በአጭር ጊዜ ለውጥ መታየት ጀምሯል፡፡ ቀድሞ የነበሩ ችግሮች ተቃለዋል፡፡ ሠራተኛውና ማኔጅመንቱ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መልኩ መግባባት ችለዋል፡፡ በተለይ የደመወዝ ጭማሪን በተመለከተ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች በአዲሱ ማኔጅመንት ተፈትቷል የሚሉት ሠራተኞች "ለአመታት ዛሬ ነገ ሲባል የነበረው የደመወዝ ጭማሪ አሁን መልስ አግኝቷል" ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ተ/ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ አለምሰገድ አብርሃም በበኩላቸው በኩባንያው ውስጥ ለውጥ እየመጣና በተለይ የደመወዝ ጭማሪውን በተመለከተ ከማኔጅመንቱ በበለጠ መመስገን ያለበት መንግሥት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የደሞዝ ጭማሪውን በተመለከተ የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅት ኤጀንሲ የካቲት 28 ቀን 2000 ዓ.ም አዲስ የደመወዝ ስኬል ስለመፈቀድ በሚል ርዕስ በፃፈው ደብዳቤ በቀረበው ጥያቄ መሠረት አዲሱ የድርጅታችሁ የደመወዝ ስኬል በሥራ ላይ እንዲውል መፈቀዱንና አዲሱ ስኬል ከኅዳር 1 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልፆ ሁሉም ሠራተኛ በአዲሱ የደሞዝ ስኬል መሠረት ተጠቃሚ እንደሚሆን ያመለክታል፡፡ በዚሁ ደብዳቤ ላይ ወደፊት የሚደረጉ የሠራተኞች ደመወዝና የቦነስ ጥያቄ በተሻለ መንገድ መልስ ለመስጠት አዲስ መመሪያ ኤጀንሲው እንደሚያወጣ ጠቅሷል፡፡ ይህ የደመወዝ ስኬል ባለፉት ሁለት ሣምንታት ለሁሉም የድርጅቱ ሠራተኞች ደርሶ በጭማሪው መደሰታቸውን የገለፀው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሠራተኞች ማኅበር ባለፈው ሣምንት በፃፈው ደብዳቤም "ድርጅቱ በገበያው ውስጥ ያለውን የመሪነት ሚና ከአሁኑ በተሻለ ሁኔታ ውጤታማነቱን ካረጋገጠ ለሠራተኛው በየወቅቱ የደመወዝ ጭማሪና የማበረታቻ ጉርሻ (ቦነስ) እንደሚደረግ ኤጀንሲው የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እምነታችን ነው" ብሎ በደመወዝ ጭማሪው ምስጋና አቅርቧል፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት በተደረገው የድርጅቱን የ6 ወራት የሥራ እንቅስቃሴ በሚያመለክተው ሪፖርት ላይ እንደተጠቆመውም ድርጅቱ ለሠራተኞች የተደረገው ጭማሪና ተግባብቶ ለመስራት የተደረገው እንቅስቃሴ ውጤት ማስመዝገቡን ያስረዳል፡፡ ለሠራተኞች የተጨመረውም የደመወዝ ጭማሪ በአማካይ 35 በመቶ መሆኑን ያስረዳል፡፡ የድርጅቱ የገበያ ድርሻን በተመለከተም ባለፈው ዓመት 39 በመቶ የነበረ ሲሆን በስድስት ወሩ የሥራ ክንውን ግን የገበያ ድርሻውን ወደ 43.2 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ማኔጅንግ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ ማኔጅመንቱ በሽግግር ላይ ነው፡፡ ቦርዱም አዲስ ነው፡፡ ቀደም ብሎ የሠራተኛው እንቅስቃሴ ከማኔጅመንቱ ጋር ችግር ስለነበረበት ያንን ማረጋጋት ይጠበቅብን ነበር ያሉት አቶ አለምሰገድ አሁን ሁሉም ነገር እየስተካከለ ለመሆኑ እምነት አላቸው፡፡ ቀደም ብሎ በነበረ አሰራር ሠራተኛውን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ያልነበረ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አለምሰገድ "ድርጅቱ አትራፊ ነው ግን በማኔጅመንትና በድርጅቱ ሠራተኛ ማኅበር መካከል የነበረው ግጭት ተጨማምሮ የሠራተኞች ጥያቄ ምላሽ ሳያገኙ" መቅረታቸውን ተናግረዋል፡፡ አዲሱ ማኔጅመንት ግን ይህንን ለመቅረፍ ጥረት ማድረጉን በዚህ ምክንያት የሠራተኛን ፍልሰት በመቀነስ ሠራተኛው ከቀድሞ በበለጠ እንዲሰራ በማድረግና ተቀራቦ ለመስራት የሚያስችል አሰራር በመዘርጋቱ ሠራተኛውና ማኔጅመንቱ በጋራ በመስራታቸው ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ በ2000 በግማሽ የበጀት ዓመት የድርጅቱ በጠቅላላ ገቢ 72.9 ሚሊዮን ብር ለማግኘት የቻሉና 37.2 ሚሊዮን ብር ትርፍ ከታክስ በፊት ማግኘቱም የአዲሱ አሰራር ውጤት ነው፡፡ ይህ የተገኘው ትርፍ ከእቅዱ 7.2 ሚሊዮን ብር ወይም በ24.1 በመቶ ከፍ ያለ ነው፡፡ ካለፈው የበጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋርም 13.1 ሚሊዮን ብር ወይም 54.3 በመቶ ከፍ ያለ መሆኑንም አቶ አለምሰገድ ጠቁመዋል፡፡ ኩባንያው ቀደም ብሎ በነበረው አሰራር ችግር የገበያ ድርሻውን አሳልፎ እየሰጠ እንደነበር የሚገልጹት ሠራተኞች አሁን ትልቁ ሥራችን ያለንን የገበያ ድርሻ ማሳደግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "በስድስት ወሩ ሥራችንም ይህንን ድርሻ ከፍ አድርገናል. . ". ይላሉ አቶ አለምሰገድ፡፡ "ገበያው ጤናማ ነው ብለን ባናስብም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ነው፡፡ ባለፈው አመት የገበያ ድርሻችን 39 በመቶ አካባቢ ነበር፡፡ አሁን 43.1 አካባቢ ደርሰናል"፡፡ በዚሁ የስድስት ወራት የሥራ ክንውኑ ድርጅቱ እስከ የካቲት 30 ቀን 2000 ዓ.ም ድረስ የብር 157.8 ሚሊዮን የጉዳት ካሳ ለደንበኞቹ የፈፀመ ሲሆን ይህም በዕቅድ ከተያዘው በብር 32.2 ሚሊዮን ወይም በ25.8 በመቶ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅትም በብር 62.2 ሚሊዮን ወይም 65.1 በመቶ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከተከፈለው የጉዳት ካሣ ውስጥ ብር 69.6 ሚሊዮን ወይም 44.1 በመቶ የሚሆነው ለተሽከርካሪ ዋስትና የተከፈለ ሲሆን ይህም ከዕቅዱ በብር 8 ሚሊዮንና ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በብር 18.5 ሚሊዮን ብልጫ አሳይቷል፡፡ በ2000 የመጀመሪያው ግማሽ በጀት ዓመት በጠቅላላው 26"252 ውሎች የተስተናገዱ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 10"529 ውሎች የተሸጡ እና 15"722 ውሎች የታደሱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የገበያ ድርሻውን ለማስፋትና ያለውን ከፍተኛ የገበያ ውድድር በአሸናፊነት ለመወጣትና በገበያው ይበልጥ ዘልቆ ለመግባት የሚያስችለውን ስልት አጠናክሮ በመቀጠል ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት ድርጅቱ ተቃዋሚ ለውጥ ለማስገኘት የአሰራር ሥርዓት ማሻሻያ ጥናቶችን (BPR) እያካሄደ ነው፡፡ የድርጅቱን አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ደንበኛ ተኮር ለማድረግ በተደረገው የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያ ጥናት በተሽከርካሪ ዋስትና ሙሉ በሙሉ፣ በመርከብ ጭነት እና በእሳትና ተዛማጅ አደጋዎች ዋስትና ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በአበባ ኢንሹራንስ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት የአበባ ኢንሹራንስ አዲስ ሥራ ሆኖ ሳይሆን ትክክለኛ የኢንሹራንስ ሽፋን አለመግዛት እንዳለ እራሱን የቻለ የሆርቲቻልቸር ፖሊሲ ቢኖርም ብዙዎቹ የአበባ አምራቾች የገቡት ለእሳት አደጋ ዋስትና መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ "ይህንንም የሚያደርጉት አረቦን ይጨመርብናል ከሚል ስጋት ነው፡፡ አሁን ይህንን ስጋት ለማስቀረትና ትክክለኛውን ኢንሹራንስ እንዲገዙ የራሳችንን ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ከማኅበሩም ጋር እየተነጋገርን ነው" ያሉት አቶ አለምሰገድ እስካሁን ለአበባ እርሻዎቻቸው ዋስትና የገቡ ስድስት ኩባንያዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የመድን ድርጅት የአየር ንብረት ኢንሹራንስ አገልግሎት ለመስጠት ጥናት እየተደረገበት መሆኑም ይታወቃል፡፡ "የአየር ንብረት ኢንሹራንስ ለመስጠት ሜትሮሎጂ ራሱ መጠናከር አለበት፡፡ አደጋ ሲደርስ ትክክለኛ የሆነ ማስረጃ የሚሰጠን አካል መኖር አለበት፡፡ ውሉ አለም አቀፍ ስለሆነ በትክክል ሞያዊ መረጃ ማግኘት ይኖርብናል" ሲሉ ጉዳዩ ከድርጅቱ አልፎ የሌሎች ድርጅቶችን መጠናከር የሚጠይቅ መሆኑን ማኔጀራል ዳይሬክተሩ ይገልፃሉ፡፡ በመድን ድርጅትም ሆነ በሌሎች ኩባንያዎች የሞተር ኢንሹራንስ አክሳሪ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በድርጅቱ የስድስት ወራት ሪፖርትም ይህንኑ ያሳያል፡፡ አቶ አለምሰገድ የድርጅቱን ስም በበጎም ሆነ በመጥፎ ሊያስነሳ የሚችለው የሞተር ኢንሹራንስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ የሞተር ኢንሹራንስ አስቸጋሪ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ዘርፉ ብዙ ወጪ ይጠይቃል፡፡ የጋራዥ ወጪ አለው፡፡ የመለዋወጫ ዕቃ አለ. . . .ይህንን ወጪ የሚሸፍን ተመጣጣኝ የሆነ ውድድር ባለመኖሩ ችግሩን እንዳባባሰውና ተመጣጣኝ ዋጋ አስከፍሎ ችግሩን ለማቃለል አለመቻሉን የሚጠቅሱት አቶ አለምሰገድ "ስለዚህ ይህንን ችግር ለማቃለል አሰራራችንን በመፈተሽ ላይ ነን፡፡" በኢንቨስትመንት ደረጃ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ካላቸው ገንዘብ 65 በመቶ የሚሆነውን ባንክ እንዲያስቀምጡ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ስለሚያዝ በብዙ ኢንቨስትመንቶች ላይ ለማዋል አለመቻሉንና የበለጠ ኢንቨስትመንት ውስጥ ለመግባት ገንዘቡን አዋጭ በሆኑ አንቨስትመንቶች ላይ ለመዋል እንድንችል የሚያደርግ ጥናት ለብሔራዊ ባንክ አቅርበናል በማለት አቶ አለምሰገድ ገልፀዋል፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |