| የስልከኞች መርሃ ግብር |
|
|
| Wednesday, 26 March 2008 | |
|
አብዛኛው መኳንንት ስልክ ሰይጣን ነው እያለ ባይነጋገርበትም በምኒልክና በጥቂት መኳንንቶቻቸው መሀል በስልክ መነጋገርና ጉዳይን መፈፀም እየተወደደ ሄደ፡፡ በስልክ መነጋገሩ እየተለመደ ቢሄድም ተነጋጋሪዎቹ የሚገናኙት በስልከኞች አማካይነት ስለነበረ ብዙውን ጊዜ ስልከኞች ከስልኩ ቤት እየጠፉ ችግር ፈጠሩ፡፡ በዚህ የተናደዱት ምኒልክም ለመጀመሪያ ጊዜ የመጀመሪያውን የስልከኞችን የተራና የሥራ ደንብ አወጡ፡፡ ደንቡም ቀጥሎ ያለው ነው፡፡
ለቴሌግራም ፀሐፊዎችና ለስልክ ቀጣዮች፣ ለባላገሮችና ለጭቃ ሹሞች፣ ለአበጋዞችም የተሰጠው ትእዛዝ ይህ ነው፡፡ መጀመሪያ ቴሌግራም ፀሐፊዎች ጧት በ12 ሰዓት ወደ ስልክ ቤት ገብተው እስከ 6 ሰዓት ይቀመጣሉ፡፡ ከ6 ሰዓት በኋላ ግን በተፈለጉ በ5 ደቂቃ እንዲገኙ ሆነው ተጠባባቂዎቻቸውን እየተው ይሄዳሉ፡፡ በተፈለጉ በ5 ደቂቃ ያልተገኙ እንደሆነ በወር ቀለባቸው ይቀጣሉ፡፡ 15 ደቂቃ የጠፋ እንደሆነ አንድ ወር ይታሠራሉ፡፡ 20 ደቂቃ የጠፉ እንደሆነ 4 ወር ይታሠራሉ፡፡ ሌሎችም የሚፈለጉበት ጉዳይ የተገኙ እንደሆነ ከስልክ ቤት አይለዩም በተራ ይጠባበቃሉ፡፡ የስልክ ሥራ ከሆነ ቴሌግራም ፀሐፊዎች የስልክ ቀጣዮችን ይዟቸዋል፡፡ ስልክ ቀጣዮችም ጧት በአንድ ሰዓት እስልክ ቤት ይገባሉ፡፡ ማታ በ2 ሰዓት ይወጣሉ፡፡ ሌሊትም በተራ ይጠብቃሉ፡፡ ተረኛውም ሌሊት ቢሆን ቀንም ቢሆን ከስልክ ቤት አይወጣም፡፡ ነገር ግን የሌሊትና የቀን ተረኛ ለብቻው ነው፡፡ ቀን የጠበቀው ሌሊት፣ ሌሊት የጠበቀው ቀን አይጠብቅም፡፡ ስልክ በተደወለ በ4 ደቂቃ ተረኛው ከዚያ መኖሩን ያላሳወቀ እንደሆነ በወር ቀለቡ ይቀጣል፡፡ 15 ደቂቃ የጠፋ እንደሆነ አንድ ወር ይታሠራል፡፡ ከዚያ ወዲያ ያለው ቅጣት ብርቱ ነው፡፡ (ጳውሎስ ኞኞ፣ አጤ ምኒልክ፣ 1984) የቀደምት ሮማውያን ዘመን አቆጣጠር በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (ከክርስቶስ ልደት በፊት) ሮማውያ 304 ቀናትን የያዘ ዓመትን ቀመሩ፡፡ ይህም ዓመት በውስጡ 10 ወራትን የነበሩት ሲሆን ከአሥሩ ወራት ስድስቱ ወራት ባለ ሠላሳ ቀናት እንዲሁም አራቱ ደግሞ ባለ 31 ቀናት ነበሩ፡፡ የዘመን መለወጫቸው ማርች ላይ ሲሆን ይህ ወር የግብርና ሥራዎች የሚጀመሩበት ነው፡፡ የዓመቱም የመጨረሻ ወር ዲሴምበር ነበር፡፡ ከዚህም በመቀጠል የኢትሩስካን ንጉሥ የነበረው ኑማፖምፒሊየስ አዲስ የጨረቃ አቆጣጠር ስልትን የተመረኮዘ የዘመን አቆጣጠር ሰራ፡፡ በፊት በነበሩት 10 ወራት ላይም 2 ወራትን በመጨመር 12 ወራት አደረጋቸው፡፡ አዲስ ያስገባቸውንም ሁለት ወራት ጃኑሪየስ ባላ 29 ቀን እና ፋብሪዩሪየስ ባለ 28 ቀን ብሎ ከዲሴምበር በኋላ አስገባቸው፡፡ በ153 ዓመተ ዓለም የኑማፖምፒሊየስ የዘመን አቆጣጠር ተሻሻለ፡፡ በዚህም መሰረት አዲስ በተመረጠው (በተሾመው) ዲፕሎማት ቀን የሮማውያን የዘመን መለወጫ ጃኑዋሪ እንዲሆን ተደረገ፡፡ (ማሕበረ ቅዱሳን፣ ዝክረ ዘመን፣ 2000) ትልቅ ወንዝ? ፖሌራ የተባለ ደራሲ እንደፃፈው የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ልክ እንደ አንድ ትልቅ ወንዝ ይቆጠራል፡፡ ይህም ወንዝ የሚፈልቀውና የሚመገበው በበርካታ ምንጮችና በሌሎች ትንንሽ ወንዞች እንዲሁም በጉዞው ጊዜ በየቦታ የሚያገኛቸውን ነገሮች አብሮ በማግበስበስ ድፍርስ ውሃ ሆኖ የሚጓዝ ነው፡፡ “በኢትዮጵያ በተናጠል ደረጃ አንድ ወታደር የለም፡፡ ባንፃሩ ግን በርካታ የበታች ሹማምንት እያንዳንዱ በዙሪያው አምስት፣ አሥር፣ አሥራ አምስት፣ ሃያ የሚሆኑ ሰዎች መሣሪያ የታጠቁ በየጊዜው የሚያጅቧቸው አሉ፡፡ ከፍተኛ ሹማምንትም እንደዚሁ በበኩላቸው በራሳቸው አስተዳደር ውስጥ የሚኖሩ መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ የአውራጃ አስተዳዳሪ ለእርሱ ታማኝ የሆኑ፣ የቅርብ ዝምድና ያላቸውን ሁሉ መሣሪያ እንዲታጠቁ ይፈቅዳል፡፡ ለዘመቻም ሆነ ለፀጥታ ጉዳይ አስተዳዳሪ የሚያሰባስበው በሥሩ የሚኖሩ የታጠቁ ሰዎችን ነው፡፡ “የታጠቁ ሰዎች ኃይል ወንዝ የሚወፍረው በታጣቂዎቹ ቡድን ብዛት ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ወጥ የሆነ ዝግጅት ሊኖረው አይችልም፣ ቡድኑ የተለያየ በመሆኑ አንድ ቡድን ለሌላው እንግዳ ነው፡፡ ሹማምንት ባላቸው የማዕረግ ደረጃ መሠረት የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሰዎችን በሥራቸው ሊያከማቹና ሲያስተዳድሩ መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን መሣሪያ የታጠቁት ሁሉ የመሣሪያውን አጠቃቀም ይወቁ እንጂ በሕብረት የውትድርናውን ተግባር ማከናወን ከቶውንም አያውቁም፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት በኮር በቅንጅትና በምርጥነት (እስፔሻይሊቲ) የተገነባ አይደለም፤ ነገር ግን የተገነባው የራስነት ማዕረግ ባላቸው ከፍተኛ ሹማምንት ወይም በሌሎች ሹማምንት የሚታዘዝ የበርካታ ወታደሮች ክምችት ነው፣ ይህም ክምችት እንደገና ሌሎች የተለያዩ ንዑሳን ክምችቶች አሉት ክምችቶች ተጠሪነታቸው ለቅርብ አለቆቻቸው ነው፡፡ የክምችቶቹ ኃይልና አመሰራረት የተለያየና ተቀያያሪ ነው፡፡ (ዘሪሁን ገብሬ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ናኦድ እስከ አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን (ትርጉም”፣ 1999) እውነት በሙዚቃ ጠቢብነቱ የሚታወቀው ቮልቴር ስለእውነት የተናገረው በተለያዩ ምሁራንና መፅሐፍ ሲጠቀስ ይስተዋላል፡፡ ቮልቴር እውነት መናገር ይገባል ይላል፡፡ ገና የወቅቱ እውነታዎች ግን ምስጥራዊነትን ይሻሉ ብሏል፡፡ ፓስካል የተባለ ጠቢብ በበኩሉ “እውነት ለሰሚዋ ጥቅም ለተናጋሪዎች ጥላቻን ታተርፋለች” በማለት እውነት የሚናገሩ በሸፍጠኞችና ውሸት ናፋቂዎች እንደሚጠሉ ያስረዳል፡፡ የሆኖ ሆኖ ሸፍጥና ውሸት በማንኛውም ጊዜ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ (ሕላዊ፣ 2000) ጥላዬ የቀደመው ቀረ ጀማሪው ፊተኛ ፊተኛው ከኋላ የኋላው አንደኛ፡፡ ያልዘቀጠው ወጣ የወጣው ዘቀጠ፡፡”. ፊት የወጣች ፀሐይ በ - ምዕራብ ሰማይ መጥለቂያው በር ላይ፡፡ አዲሷ ከምሥራቅ በንጋት አልፋ ላይ በማለዳ ርከን ላይ፡፡ እርከኑ እስቲሰበር በጭለማ በትር፡፡ የቀደመው ሲቀር፣ የወጣው ሲዘቅጥ፣ ምዕራብ ሲጠልቅበት፣ ጎኀ ሲቀድ ለምሥራቅ “. እነሱን ሲታዘብ”. በወጣ - ዘቀጠ ከገቡበት መቅረት ከወጡበት መግባት እንዴት ባመለጠ”? ጥላዬ፡፡ (ወንድዬ አሊ፣ ውበት እና ሕይወት፤ 1998) የሰውነትን መዋቅር መጠበቅ የሰውነታችን አፈጣጠሩ ለሰውነት የሚያስፈልጉ ኃይል ምንጮችን በረዥም ጊዜ ለማምረት ነው፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ የሰውነቱን መዋቅር በጠበቀ መልኩ በተመጣጠነ ምግብ፣ በእንቅስቃሴ፣ በእንቅልፍ፣ ከጉዳት በመከላከል ከጠበቀ የሰውነት ክፍል በሚያስደንቅ ሁኔታ ጤናማነቱ ተጠብቆ ለረዥም ጊዜ ያለ ህመም ይቆያል፡፡ ከዚህ በተመሣሣይም ስሜታዊነቱን በተመጣጠነ ሁኔታ ከተቆጣጠረ በሰውነት ውስጥ ያለ ኃይል (አቅም) ተጠብቆ ይቆያል፡፡ ሆኖም አንድ ሰው ስሜቱን መቆጣጠር ካልቻለ አብዛኛውን አቅሙን ያጣል፡፡ ሰውነት፣ አእምሮና መንፈስ ተረጋግተው የሚሰሩ ከሆነ ዘላቂነት ያለው የሃይል መተካካት ይኖራል፡፡ (ኖርማን ቪንሰንት፣ ዘ. ፓወር ኦፍ. ፖዘቲቭ ቲንኪንግ፣ 1990) ገራገር ቄሱ በየቀኑ ወሲብ እንዲደረግ መከሩ የፍሎሪዳ ቤተክርስቲያን መሪ በጋብቻ ውስጥ ያሉ የእምነት ተከታዮቻቸው በየቀኑ ለአንድ ወር የሚቆይ ወሲብ እንዲፈፅሙ መከሩ፡፡ በትዳር ውስጥ ለማይገኙ ተከታዮቻቸው ደግሞ እንደ ትልቅ ቅጣት የተቆጠረውን የ30 ቀናት ከወሲብ ታቀቡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ስካይ ኒውስ በኒውዮርክ የሚገኘው “ሬሊቫንት ቸርች” መሪ የሆኑትን ፖውል ዊርዝ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የቤተክርስቲያኒቷ መሪ ውሳኔውን ያስተላለፉት በከተማዋ እየተስፋፋ የሄደውን የፍቺ ቁጥር ለመቀነስ በማሰብ ነው፡፡ በአሜሪካ ያሉ ጥንዶችም ሆኑ ያላገቡት የእምነት መሪያቸውን ቃል ለመፈፀም እየጣሩ ነው፡፡ የቄሱ ትዕዛዝ ላገቡት ተከታዮቻቸው የየቀኑ የትግል አውድማ የሆነባቸው ሲሆን ላላገቡት ደግሞ “መቼ ወሲብ ፈፅሜ” በሚል እየተፈታተናቸው ነው፡፡ ማዶና መድረክ ላይ ልትሞት እንደምትችል ተነበየች ማዶና መድረክ ላይ ልትሞት እንደምትችል የተነበየችው መድረክ ላይ ስትወጣ በከባድ የፍርሃት ችግር ስለምትሰቃይ ነው፡፡ “በሚያስገርም ሁኔታ በመድረክ ላይ የተለየ የፍርሃት ስሜት እየወረረኝ መቸገር ከጀመርኩ ወራትን አስቆጥሬያለሁ፡፡ አድማጮቼ በእጄ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ሁሉ ነገርም በትክክል እየተከናወነ መሆኑ ይታወቀኛል፡፡ ከባድ የፍርሃት ችግር እንዳለብኝና ሁሉም ሰው የእኔን አየር እንደሚተነፍስም ይሰማኛል፡፡ ሆኖም የሁሉን ምኞት ማሳካት የምችል አይመስለኝም፡፡ መድረክ ላይ ልሞት እችላለሁ” ማለቷን የ50ኛ አመቷን ልታስቆጥር ጥቂት ወራት የቀራት ማዶናን ጠቅሶ ዴዝድ ኤንድ ኮንፊዩዝድ ሜጋዚን ገል”ል፡፡ መድረክ ላይ በብቃት መዝፈን እንዳላቃታት የምትናገረው ማዶና በመድረክ ላይ ስትሆን ከባድ በሆነ የፍርሃት ስሜት እንደምትሰቃይ አስታውቃለች፡፡ የከረመ ፍቅር የ101 እድሜ ያስቆጠሩት ጣሊያናዊ የ98 ዕድሜ ያላቸውን የሴት ጓደኛቸውን ሊያገቡ ነው፡፡ ጡረተኛው የማሕፀን ሐኪም ጁሴፒ ሪቡዲ የሚያገቧቸው የረዥም ጊዜ ፍቅረኛቸው የነበሩትንና በ1960 የተዋወቋቸውን ሲሊቪያ ቤጎንድን ነው፡፡ በትውልዳቸው ፈረንሳያዊት የሆኑት ሲልቪያ “እኔ የምፈልገው እስካሁን ያላገባሁ መሆኔን የፈረንሳይ ኤምባሲ ማረጋገጫ እንዲሰጠኝ ነው” ብለዋል፡፡ ሲልቪያ ከጓደኛቸው ጋር ለ50 ዓመታት ብቻ መኖራቸውን በቁጭት ነው የተናገሩት፡፡ ቦክስ ለጤንነት የ100 አመቷ የማንቸስተር አሮጊት ጤንነታቸውን የጠበቁት አዘውትረው በሚለማመዱት የቦክስ ስፖርት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዘ ሰን እንደዘገበው አሮጊቷ ሞሊ ሪቭስ የሰውነታቸውን ቅርፅ ለመጠበቅ በየሳምንቱ ጓንት በማጥለቅ የቦክስ ልምምድ ያደርጋሉ፡፡ “ልምምዴን ካደረግኩ በኋላ ትንሽ ህመም ይሰማኛል፡፡ ሆኖም የቦክስ እንቅስቃሴውን እወደዋለሁ” ብለዋል አሮጊቷ፡፡ ሞሊ በ100 ዓመት እድሜያቸውም ጠንካራ ናቸው፡፡ በሁሉም የአውሮፓ አገሮችም ይዘዋዋሉ፡፡ “ረዥም እድሜ የመኖር ምስጢሩም ደስተኛ መሆን ነው” በማለት መክረዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |