| “ዩኒቨርሲቲው ጥራት ከሌለው ጥራት... |
|
|
| Wednesday, 26 March 2008 | |
“ዩኒቨርሲቲው ጥራት ከሌለው ጥራት ያላቸው ዜጎችን ማፍራት አይቻልም”አባ ፀጋዬ ቀነኒ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዩኒቨርሲቲ ኘሮጀክት ዳይሬክተር አባ ፀጋዬ ቀነኒ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ የቤተክርስቲያኒቷ ዩኒቨርሲቲ ኘሮጀክት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን ጊንጪ አካባቢ በሚገኘውና ልዩ ስሙ ሜጫ በርዶ በተባለው የገጠር ቀበሌ ተወለዱ፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደብረዘይት፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዘርአ ክህነት ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል፡፡ በጣሊያን ሮም አርካኖ ኮሌጅ ውስጥ በፊሎዞፊና በቲዎሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ በላትራን ዩኒቨርስቲ በቲዎሎጂ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ ቺካጎ ሎዩላ ኢየሱሳውያን ዩኒቨርሲቲ በፓስተራልና በሜሬጅ ካውንስሊንግ በእያንዳንዳቸው የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዩኒቨርሲቲ መቋቋምን አስመልክቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዩኒቨርሲቲን ለማቋቋም የታሰበው መቼ ነበር? የማቋቋሙ መንስኤስ ምንድነው? አባ ፀጋዬ፡- የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዩኒቨርሲቲ እንዲቋቋም ፍላጎቱ የተነሳው ቆየት ባሉት ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ ተጠናክሮ የመጣውና የመጀመሪያ ጥናት የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1997 ነው፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል በቆየው በዚህ ጥናት ሞዴል የሆነ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋም ለገሪቱ ጠቀሜታ እንዳለው ታምኖበታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ገለልተኛ የሆነና በመንግሥት በኩል ቀጥተኛ ቁጥጥር የሌለበት መሆን እንደሚኖርበት ነው፡፡ ጥናቱም የተከናወነው በውጭ አገር ባለሙያዎች አማካይነት ሲሆን የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው ዩኒቨርሲቲውን ለማቋቋም ቅድመ ዝግጅቶች እንደሚያስፈልጉት ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በሕዝብ ዘንድ ያለው ዕይታና አስፈላጊነቱ እንዲሁም የሚያዋጣ መሆን አለመሆኑ በዚህ የመጀመሪያ ጥናት ላይ ተዳስሷል፡፡ ይህም እንዳበቃ ሌላ አዲስ ጥናት ተጀመረ፡፡ በሁለተኛው ዙር የተካሄደው ይኸው አዲስ ጥናት ዝርዝር ውስጥ የገባ ነበር፡፡ በጥናቱ ላይ ትኩረት ከተደረገባቸው በርካታ ነጥቦች መካከል ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ምን ዓይነት ትምህርት መቅደም አለበት? ለምን? የቤተክርስቲያኒቷ የገቢ ምንጭ ምን ሊሆን ይችላል? አገልግሎት መስጠት የምትችለውስ በምን ደረጃ ነው? የሚሉና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲው ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ምን ዓይነት እርምጃ ይወሰዳል? አባ ፀጋዬ፡- ዩኒቨርሲቲው ደረጃውን ጠብቆ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችለው ዓለም አቀፍ ግንኙነትን ይጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፋዊ ባህሪ ያላት ስለሆነች ከዓለም አቀፋዊ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ግንኙነቷን ማጠናከር አለባት፡፡ ይህ ዓይነቱ ግንኙነት ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ባህሪ የሚኖረው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ድጋፍ ያስገኛል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የባለቤትነት መብት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሲሆን ዓለም አቀፋዊ አብያተ ክርስቲያናት ግን ድጋፍ ሰጪ ይሆናል፡፡ ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲውን በማቋቋም ረገድ ከዓለም አቀፍ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የተደረገ ስምምነት አለ? አባ ፀጋዬ፡- በዩኒቨርሳል ደረጃ ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዶሜኒካን ማህበር (ገዳማውያን) ጋር ውል አድርገናል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሙሉ በሙሉ ኃላፊነት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሆኖ ማኀበሩ ማዕከላዊውን የአስተዳደር ኃላፊነት ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህም ማለት የዲሞኒካያን ማኀበር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሰው ኃይል በቅጥርም ሆነ በጎ ፈቃደኞችን በማፈላለግ ያሰባስባል፡፡ የዩኒቨርሲቲውን ሕንፃ የማስገንባት፣ ለግንባታው ማስፈፀሚያ የሚውል ገንዘብ የማሰባሰብና የአመራሩን ኃላፊነት የመቀበል ጉዳይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ገንዘብ በማፈላለጉ ረገድ ትኩረት የምናደርገው ከዓለም አቀፍ ካቶሊክ ማኀበረሰብ ነው፡፡ በጎ ሃሳብ ያላቸውን ሌሎች ድርጅቶችንም ሁሉ ድጋፍ መጠየቅ እንችላለን፡፡ ግዴታም ነው፡፡ የምንጠይቀው የምንተማመንበትን ድርጅት ብቻ ነው እንጂ ሁሉንም አይደለም፡፡ ምክንያቱም የራሳችን የአሠራር ፍልስፍና ወይም ስልቶች ስላሉን ነው፡፡ የምንጠይቀውም ዕርዳታ በዚህ ፍልስፍና መሠረት መከናወን አለበት፡፡ ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲውን መቋቋም አስመልክቶ ከመንግሥት ጋር ስምምነት መፈራረማችሁ ይታወሳል፡፡ ስምምነቱ ያካተታቸው ነጥቦች ምንድናቸው? አባ ፀጋዬ፡- መንግሥት ለዩኒቨርሲቲው ማቋቋማያ የሚውል ቦታ በነፃ እንዲሰጠን፣ ለመማር ማስተማሩ ሥራ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ዓይነት ዕቃዎችን ከውጭ አገር ስናስገባ ከማንኛውም ቀረጥ ነፃ የሚሆኑበትን መንገድ፣ እንዲሁም ከውጭ አገር ምሁራንን በድጋፍ ሰጪነት ለማስገባት በምናደርገው ሕጋዊ እንቅስቃሴ ላይ አስፈላጊውን እገዛና ትብብር እንዲያደርግልን ወዘተ የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህኑ ጉዳዮችን ለማስፈፀም መንግሥት ተስማምቶ በፊርማ አፅድቆልናል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ትምህርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡ በምስክርነት ደግሞ በኢትዮጵያ የቫቲካን አምባሳደር፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሥዩም መስፍን ፈርመዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዲፈርሙ ያስፈለገበት ምክንያት ዩኒቨርሲቲው ዓለም አቀፍ ባህሪ ስላለው ነው፡፡ ለዩኒቨርሲቲው መቋቋም አስፈላጊነት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቫቲካንን በጎበኙበት ጊዜ ፓፓውንና የቫቲካን ሴክረተሪ ኦፍ ስቴትን ሲያነጋግሩ የዩኒቨርሲቲውን መቋቋም እንደሚደግፉ ገልፀው ነበር፡፡ ይህም ድጋፍ የዩኒቨርሲቲውን መቋቋም አስፈላጊነት እንደገና እንደ አዲስ እንዲነሳሳ አድርጎታል፡፡ ከመንግሥት ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 6ዐ ሄክታር መሬት አግኝተናል፡፡ ቦታውንም የዩኒቨርሲቲው ደረጃ በሚፈቅደው መሠረት በግንብ እያጠርነው ነው፡፡ በየጊዜውም እየተከታተልን እያየነው ነው፡፡ ቦታው በአራቱም ማዕዘን የአስፋልት መንገዶች ያልፉበታል፡፡ ከዚህም ሌላ ከቀለበትና ወደ ክልሎች ከሚወስዱት መንገዶች ጋር ይገናኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ክብሩንና ደረጃውን ጠብቆ በሚታነጽበት ጊዜ ግሩም አካባቢ ሊፈጠር ይችላል፡፡ የቦታ ካርታም ተሰጥቶናል፡፡ ሪፖርተር፡- አጥሩ ስለታጠረ ብቻ ነገሮች አለቁ ማለት ይችላል? አባ ፀጋዬ፡- የዩኒቨርሲቲው ግንባታ እስከሚከናወን ድረስ የትምህርት እንቅስቃሴው መቆየት የለበትም፡፡ ስለሆነም በተወሰኑ ፋካልቲ ላይ በጊዜያዊ ቦታዎች ትምህርቱ እንዲጀመር የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ ወስኗል፡፡ ጊዜያዊ ቦታዎቹ ቤተክርስቲያኒቷ የምታስተዳድራቸው ሕንፃዎች ወይም ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ ባለፈው ጥር ወር ትምህርት እንዲጀመር ተወስኖ ነበር፡፡ በውሳኔውም መሠረት ትምህርቱን ለመጀመር ቅድመ እውቅና ማግኘት ግድ ይላል፡፡ ቅድመ እውቅናው ደግሞ በትምህርት ኒስቴር በኩል የሚያስፈልጉ መመዘኛዎች አሉት፡፡ ከመመዘኛዎቹም መካከል በሰነድና በማቴሪያል እንዲሁም በቤተ መጻሕፍት፣ በላቦራቶሪ፣ በመማሪያ ክፍልና በበጀት ወዘተ. ሙለ መሆንን ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ዝርዝሮች በሙሉ ተሟልተውና ተጠናቅቀው የቅድመ እውቅና ጥያቄ ለትምህርት ሚኒስቴር ቀርቧል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ቅድመ እውቅና ከመስጠቱ በፊት ትምህርቱ በጊዜያዊነት የሚሰጥባቸውን ቦታዎች ሄዶ ያያል፡፡ ትምህርቱ በጊዜያዊነት እንዲሰጥባቸው ከተመረጡ ቦታዎች አንደኛው ጉለሌ አስኮ አካባቢ የሚገኘው የቅዱስ ፍራንቺስክ ገዳም ውስጥ ያለው የቴዎሎጂ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በአገልግሎት ላይ ያልዋሉ ክፍሎችን እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ቴዎሎጂና ፍልስፍና ትምህርት የሚሰጥባቸውንም ክፍሎች ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው ትምህርት ቤቱ የሚጠቀምባቸው እኛ ደግሞ በቀረው ጊዜ አገልግሎት ለመስጠት መጀመር አለብን፡፡ እነሱ ትምህርታቸውን የሚማሩት እስከ እኩለ ቀን ነው፡፡ ከእኩለ ቀን በኋላ ደግሞ ዩኒቨርሲቲው ሊገለገልበት ይችላል፡፡ ይህ እየተካሄደ በአዲሱ ቦታ ላይ የሕንፃ ግንባታ መጀመር አለበት፡፡ ለዚህም እየተዘጋጀን ነው፡፡ የሕንፃው ግንባታ የሚካሄደው በምዕራፍ ነው፡፡ የመጀመሪያ ሕንፃ ምን መሆን አለበት? ሁለተኛውስ ሕንፃ? የሚለውን ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ጋር እየተመካከርን የሕንፃው ግንባታ ይቀጥላል፡፡ ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲው በስንት ዓይነት የትምህርት ዘርፎች ነው የማስተማሩን ሥራ ለመጀመር የታሰበው? አባ ፀጋዬ፡- በአምስት የትምህርት ዘርፎች ነው፡፡ አንደኛው የትምህርት ዘርፍ ኤጂዩኬሽን ነው፡፡ በኤጁዩኬሽን ዲፓርትመንት ወይም ፋክልቲ የከፍተኛ ትምህርት መምህራንን (ከሁለተኛ ደረጃ በላይ የሚያስተምሩ) ማፍራት ነው፡፡ ሌላው የመረጃ ቴክኖሎጂ (አይ.ቲ) ነው፡፡ ይህም ባለሙያዎችን ማፍራት ነው፡፡ መሠረተ ሃሳቡም የኢንፎርሜሽን ጥቅሙን ለማዳበር ነው፡፡ ጥቅሙንና አገልግሎቱን በትክክል በተግባር ላይ ካዋልነው ጥቅሙ ያመዝናል የሚለውን ፍልስፍና ይዞ መጓዝም ጭምር አለበት፡፡ ሦስተኛው ኢንተርኘሪነርሽኘ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወጣቱ ትውልድ የሚያጋጥመው የሥራ አጥነት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በአንዱስትሪ ተቀጥሮ መሥራት ወይም ደግሞ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ እየተቀጠሩ መሥራት ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም ፈጠራ በማሳደግ በራሳቸው አነሳሽነት የገቢ ምንጮቻቸውን በማሳደግ በፈጠራ ችሎታቸው ውጤታማ ማድረግ ነው፡፡ አራተኛው ሜዲካል ቴክኖሎጂ ሴክሽን ይኖረናል፡፡ ሜዲካል ቴክኖሎጂ ላቦራቶሪ ነው የሚሆነው፡፡ አስኮ ላይ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ማዕከል አለን፡፡ በአንድ በኩል የሴቶች ማገገሚያ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሕፃናት ማሳደጊያ ቦታ ነው፡፡ የሕፃናቱም ቁጥር እስከ 4ዐዐ ይደርሳል፡፡ በዚሁ ማዕከል ውስጥ ትምህርት ቤቱ አለ፡፡ ሌላም ምርምር ለማካሄድ እንዲያስችለው ላቦራቶሪ አለው፡፡ ይህንን ማዕከል ጠንከር ያለ የላቦራቶሪ ምርምር ማካሄጃና የማድረግ ፍላጎት አለን፡፡ ስለሆነም ዩኒቨርሲቲው ይህንን ሜዲካል ቴክኖሎጂ በዚህ ማዕከል ውስጥ የማቋቋም ሀሳብ አለው፡፡ አምስተኛው የትምህርት ዘርፍ ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ማኀበራዊ ሠራተኛን ማፍራት ነወ፡፡ ይህም የሲስዮሎጂ አካል ነው፡፡ ነገር ግን ተልዕኮው ወጣቶች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው ከአስተዳደግና ከአመራር አኳያ፡፡ የአመራር ሰጪነትንም የሚያስተምር ዘርፍ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የተጠቀሱትን የትምህርት ዓይነቶች መቼ ነው ለማስተማር የታቀደው? አባ ፀጋዬ፡- ቅድመ ዕውቅናው እንደተሰጠን ሥራውን መጀመር እንችላለን፡፡ መቼ ይጀመራል ለተባለው እርግጠኛ ቀኑን ለመናገር ያስቸግራል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ላይ ሊጀመር ይችል ይሆናል፡፡ ሪፖርተር፡- ቤተክርስቲያኒቱ ከምትከተለው ፍልስፍና አኳያ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራን በምን ምልኩ ነው መቅጠር የሚቻለው? አባ ፀጋዬ፡- በዓለም አቀፋዊነት መልካም ፈቃጀኞችን በጊዜያዊነት እናፈላልጋለን፡፡ በሀገሪቷ ያሉትንም ምሁራን በተቻለ መጠን ልንጠቀምባቸው አስበናል፡፡ ለምርጫም የቅጥር ሕግ አለን፡፡ ይህንን ያዘጋጀው ዩኒቨርሲቲው ነው፡፡ በዚህ መሠረት የቅጥር ኮሚቴ ይኖራል፡፡ ኮሚቴው ያሉትን ክፍት ቦታዎች ያስታውቃል፡፡ ለዚህም መስፈርት ተዘጋጅቷል፡፡ አመልካቾች ሲመጡ የፅሁፍ ፈተናና ኢንተርቪው ይኖራል፡፡ በዚህ መልኩ ተጣርቶ ያለፉትንና በቅደም ተከተል ባገኙት ውጤት በጊዜያዊነት ይቀጠራሉ፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሃሳብ ለሁለት ወር በጊዜያዊነት ቅጥር ፈቃደኛ ሆነው መሥራት አለባቸው የሚል ነው፡፡ ቋሚ ቅጥር ከመካሄዱ በፊት የሚታዩበት ጊዜ ነው፡፡ ከሠራተኛ ሕግ አንፃር ደግሞ አንድ ሰው 45 ቀን ከቆየ ቋሚ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይህም የዩኒቨርሲቲው ሃሳብ ከሕጉ ጋር ያስኬዳል ወይስ አያስኬድም የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡ በተለይ በአሁኑ በመነሻ ላይ አዲስ የማስተማር ባህልን ለማዳበር የውጭ አገር ልምዶችን ማግኘት የግድ ይላል፡፡ የውጭ አገር መምህራንን መቅጠር ያስፈልጋል፡፡ በአገር ውስጥ እንደነዚህ ዓይነት መምህራን አይገኙም ከተባለ ነው እንጂ ዝም ብለን የውጭ አገር መምህራንን አንቀጥርም፡፡ አንዳንድ አገሮች መምህራንን በነፃ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ በነፃ ስለተሰጠን ብቻ የማይሆነንን የውጭ መምህር አንቀበልም ወይም አናስመጣም፡፡ ሪፖርተር፡- አሁንም ሆነ ወደፊት የምትቀበሏቸው ተማሪዎች ከፍለው ነው የሚማሩት? አባ ፀጋዬ፡- ክፍያ ይኖራል፡፡ነፃ መሆን ግዴታ የሚሆንበትን ቦታ በመነሻ ላይ በቀጥታ ማግኘት ባይቻልም የስኮላርሺኘና የስፖንሰር ሺኘ ሲስተሞች ሁሉ እየተጠኑ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለእንቅስቃሴው በጀት ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ በበጀት ውስጥ ስኮላርሺኘ መኖር አለበት፡፡ አለበለዚያ መክፈል የሚችሉትን ብቻ ከተወሰደ አገልግሎቱ የተወሰነ ይሆናል፡፡ ማወቅ ያለባቸው ገንዘብ ያላቸው ብቻ መሆን አለባቸው የሚል ሕግ የለም፡፡ በእጦት ምክንያት ያላቸውን እንዳያፈሩበት በመደረጉ ተጠያቂዎች ነን ባይ ነኝ፡፡ እውቀትና ተሰጥኦ አላቸው፡፡ ይህንን እውቀታቸውንና ተሰጦአቸውን ለማሳደግ ግን ዕድሉ የላቸውም፡፡ ሪፖርተር፡- የሚቋቋመው ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ጥራት ላይ የሚኖረው ትኩረት ምን ያህል ነው? አባ ፀጋዬ፡- ዩኒቨርሲቲው የዓላማውን መነሻ ያደረገው በጥራት ላይ ነው፡፡ ይህንንም ከራሳችን ትምህርት ቤት ነው የበለጠውን ልምድ ያገኘነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለተሳካልን ብቻ ይህ በቂ ነው በሚል መንፈስ አይደለም፡፡ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች አገልግሎታቸው ሲታይ ጥሩ ውጤት እንዳላቸው ነው የሚጠቀሰው፡፡ ይህም መንፈስ አዲስ በሚቋቋመው ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ደረጃ በቀዳሚነት ትኩረት ተሰጥቶት ነው የሚታየው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ጥራት ከሌለው ጥራት ያላቸው ዜጎችን ማፍራት አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ በምኞት ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በጥረት ነው፡፡ ለዚህም ትብብር ያስፈልጋል፡፡ መልካም አስተሳሰብና ትኩረት መስጠት ከሚፈልጉ ዜጎች ጋር በመመካከር ብዙ ነገሮችን ማምጣት ይቻላል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |