Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
May 09th
Home arrow Sections arrow ሒስና ሐያሲ አለን?
ሒስና ሐያሲ አለን? Print E-mail
Wednesday, 26 March 2008
የስነ ፅሑፍ ውጤቶች በአገራችን አድገዋል የሚያስፈነድቅ ደረጃ ደርሰዋል ባንልም ተስፋ ያለው አካሄድ ግን አለው፡፡ የስነፅሁፍ እድሜ የመርዘሙን ያህል ከቀጨጨበትና ድንክ ከሆነበት ምክንያት የበቁ ሐያሲያንና የበቃ ሒስ አለመኖር በዋነኝነት ደረጃ ይመደባል፡፡ በመሆኑም የስነ ፅሁፍ አዝመራ በዋግና በአረማሞ እንዲመታ ግድ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር "ሒስና ሐያሲ" በሚል አጀንዳ ዙሪያ መጋቢት 15 ቀን 2000 ዓ.ም ባካሄደው ውይይት አቶ ጌታቸው በለጠ የማህበሩ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ሥነ ፅሁፍ የተጓዘበትን ጐዳና በወፍ በረር ቅኝት ከ1933 ጀምሮ ያለውን አቅርበው ነበር፡፡

ከ1933 እስከ 1953 ባሉት ዓመታት የተፃፉት መፃህፍት በዋነኛነት ያተኮሩት የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ያፈራረሳትን ኢትዮጵያ እንዴት መልሰን እንገንባ በሚል መሪ ጭብጥ ዙሪያ ነበር፡፡ በግጥሞችም ሆነ በልብ ወለድ በዘመኑ ደራሲዎቹ ያስተላለፉዋቸው መልዕክቶች በዋነኛነት ከወራሪው ፋሽስት ጣሊያን ጋር ተያያዥነት የነበራቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ጭብጦቹም የሕዝቡን ጀግንነት ተራኪዎች፣ የደከሙት ማህበራዊና መንፈሳዊ እሴቶች እንዲያንሰራሱ የሚያመላክቱ የግብረገብ ዓይነት አስተማሪነት ያላቸው ነበሩ፡፡ ውጭ ተምረው የሚመጡ ምሁራን ለአገራቸው ቁም ነገር ይስሩ አገርም ትበልፅግ የሚሉ ሰባኪ ፅሁፎች ነበሩ፡፡

አብዛኞቹ የዘመኑ ፀሃፍት የጦርነት ገፈት የቀመሱ ወይም የአይን ምስክር የነበሩ፤ በድሉ ማግስትም በውጭ ተምረው የተመለሱ ወይም ለመጐብኘት እድሉ የገጠማቸው ምሁራን ነበሩ፡፡ ዘመኑ የስነ ፅሁፉ ስራዎች ላይ የሚሔስበት ሳይሆን ስነፅሁፎች ራሳቸው ዘመኑንና ትውልዱን የሔሱበት ነበር፡፡

1953 እስከ 1966 ባሉት ዓመታት የነበሩ ፅሁፎች ይዘት ደግሞ በባህሪያቸው የተለዩ ነበሩ፡፡ በጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ የተመራው መፈንቅለ መንግሥት መክሸፍ በዋነኛነት መነሻ ሆኖ የፀሃፍት ብዕር በሙሉ የተቆጣበት፣ የዘመኑ ምሁራን የንጉሱን ዘውድ የሚሸረሽሩና የቁጣ ውርጅብኝ የሚያወርዱበት፣ የጦፉ ንዴቶች እንደወጨፎ የተወረወሩበት ዘመን ነበረ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበልባል ብዕሮች የተንቦገቦጉበት የፊውዳሉ ዘውዳዊ ስርዓትና ከዘውዱ ስር በቅለው የነበሩ ባህል፣ ወጐችና ትውፊቶች የተኮነኑበት፣ የተበሻቀጡበትና የተጋለጡበት ጭብጦች ነበሩት፡፡ ዘመኑ ሲፈተሽ ብዕር ሆ" ብሎ በስርዓቱ ላይ የዘመተበት ወቅት እንጂ ፋታ ተገኝቶ የወቅቱ ስነፅሁፍ ቅርፅና ይዘት በሒስ የተመረመረበት ዘመን ነበር ለማለት ያስቸግራል፡፡ ሊሞከር የሚችልበት ሁኔታም ነበር ብሎ ለመደምደምም ይከብዳል፡፡ አልፎ አልፎ ብልጭ ያሉ ሒሳዊ ጋዜጣዎች አልነበሩም ማለት ግን አይቻልም፡፡ በየከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በተለይ በወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር እና በቀድሞው ቤተ መዛግብት (ወመዘክር) አዳራሾች ውስጥ ስነፅሁፍ ነክ ውይይቶች በዘርፉ ባለሙያዎች ብልጭ ብለው ነበር፡፡

ከ1967 እስከ 1983 ያለው ስነፅሁፍ ዘመን በበረከተ መርገምነቱ በስነፅሁፍ ሥራዎች ላይ ተጭኖ የነበረው የሶሻሊዝም ርዕዮተ አለም ለስነፅሁፍ ጉዞአችን አንድና ወጥ የጭብጥ መስመር ማስመሩ ነበር፡፡ ብዕሮች ሁሉ በቀይ ኮሚንስታዊ ቀለም ብቻ እንዲፃፉ፣ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ የርዕዮተ አለም ጫና በቢሮክራሲውና በመንግሥት በኩል መደረጉ፤ የርዕዮተ አለሙ ጡንቻ ባብዛኛው ይገለፅ የነበረው በሳንሱር ተቋም አማካይነት መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ይህ መሰሉ ጥቁር ደመና በስነፅሁፍ ላይ ያንዣበበ ቢሆንም ደፋር ደራሲዎች የበቀሉበት፣ የተዋጣላቸው ሥራዎች የተጀመሩበት፣ የሳንሱሩን ግድብ ጥሰው የወጡና እስከዛሬ ተጠቃሽ የሆኑ ሥራዎች የተጀመሩበት ዘመን ነበር፡፡ በዘመኑ የመጨረሻ ዓመታት ግድም አብቦ የነበረው የሐያሲያን የሰላ ጥበብ ፍልሚያ ለዘመኑ ፈርጥ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከደራሲያን ቁጥር ባልተናነሰ መልኩ የብዕር ስሞች የገነኑበት፣ ጋዜጦችና የሬዲዮ ሞገደች በፀሃፊያን የብዕር ፍልሚያ በመድረክነት ያገለገሉበት የመጨረሻ ዓመታት ነበሩ፡፡ ተፋላሚዎቹ ሐያሲያንና የብዕር ጐምቱዎች አሁንም የሚመሰገኑ ናቸው፡፡

ከ1983 እስከ 2000 ዓ.ም ያሉት 17 ዓመታት ከፊሉ የዝምታ፣ ከፊሉ የትርጉም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሀገሪኛ ጉዳዮች እና በራስ ህይወት ዙሪያ እኔነትን ማዕከል አድርገው የተሰሩ ሥራዎች እየታተሙ ይገኛሉ፡፡ የዚህ ዘመን ደራሲዎች በ1 ሺህና 2 ሺህ የህትመት ጣሪያ የፈነደቁባቸው ዓመታት ናቸው፡፡ መፅሃፌን መርቁልኝ የሰርክ ቋንቋ ሆኗል፡፡ ሆኖም ሐያሲያንና ሒስ በአደባባይ የተኳረፉ ይመስላል፡፡ ተፅፏል፡፡ እንጂ ፅሁፍ ሲፈተሸ እጅግም አይታይም፡፡ የመገናኛ ብዙሃንና የሚዩዚክ ሜይዴይ ጥረት ባይዘነጋም፡፡ ዘመኑ የአለማቀፉ የስፖርት ጡንቻ በንባብ ላይ ሰልጥኖ አብዛኛው ወጣት ለአውሮፓ ክለቦች በፍቅር ያበደበት ንባብ አዲዮስ የተባለበት ዘመን ይመስላል፡፡

አቶ ጌታቸው ከ1933 ጀምሮ ያለውን በአራት ከፋፍለው በወፍ በረር ካስቃኙት ለመረዳት እንደሚቻለው ከዘመኑ ርዝመት አንፃር በቂ አይባሉም እንጂ ጥቂት ሐያሲዎችና የሒስ ጅማሮ መኖሩን ነው፡፡

ደራሲና ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም በበኩሉ የመጀመሪያው አንባቢና ሐያሲ ራሱ ደራሲው ነው ብሏል፡፡ "ደራሲው ስራዬ ውብ ነው ብሎ ራሱን ማድነቅ ይኖርበታል" የሚል አመለካከት አለው፡፡ የድርሰት አላማ ራስን ማወቅ ነው፡፡ ማህበረሰቡም ራሱን ሊያውቅበት ይችላል፡፡ ደራሲው ድርሰቱን እንደጨረሰ የራሱን የፈጠራ ዋጋ እንደሚያውቅ ሁሉ አንባቢውም የደራሲውን ሥራ አንብቦ የራሱን ማንነት ሊያውቅ ይችላል" የሚለው በዕውቀቱ አያይዞም ሐያሲ ከራሱ ሃሳብ ፀድቶ ፅሁፎችን ሊያሔስ እንደሚገባ ገል"ል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች ከነበሩት ፀሃፍት ደራሲያን፣ ገጣሚያንና ምሁሮች "ሒስና ሐያሲ" አለን ወይስ የለንም በሚለው ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገው ነበር፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች የመጀመሪያውን አስተያየት የሰጠው ገዛኸኘ እንዳለው ሐያሲ ጥሩ አንባቢ ነው፡፡ ሐያሲ እንደ ደራሲው የሃሳብ ልግስና ሊኖረው ይገባል፡፡ የሃሳብ ልግስና የሌለው ሐያሲ ቀማሪ ማለት ነው፡፡ ሐያሲ ሃሳብ ካልለገሰ እንደማያፈራ ተክል ነው፡፡ የሃሳብ ልገሳ የሚገኘው ደግሞ ከቅንነትና ከየዋህነት ከሚያነብ ነው፡፡ ድርሰት መጣልኝ ብሎ የሚያነብ ሐያሲ ሲኖር ብቻ ነው ሐያሲ የሚኖረን፡፡ ድርሰቱን እንደማንኛውም አንባቢ ለራሱ የሚያደርግ እንጂ ድርሰቱን ልገምግመው ብሎ የሚነሳና መፅሃፍ የሚገዛ ሐያሲ የደረቀ ዛፍ ዓይነት ማለት ነው፡፡

"ብቁ ደራሲ ከብቁ ንባብ ጋር ብቁ ሐያሲ ይወጣዋል፡፡ ብቁ ደራሲ በጥሩ ሁኔታ አንብቦ ከደራሲነት ራሱን ከፍ ካደረገ ጥሩ ሐያሲ ይወጣዋል፡፡ የሃሳብ ልገሳው ከደራሲነቱ ይመነጫል፣ በአንባቢና በሥራው መካከል ድልድይም ይሆናል" ሲል ተናግሯል፡፡

ሒስ አንድ የንባብ ስልት እንደመሆኑ ሐያሲ ድርሰቱን ከሚገመግምበት ይልቅ አንባቢውንና ደራሲውን የሚያገናኝባቸው መንገዶች ይበዛሉ፡፡ ድርሰትን መገምገም አንዷ ንቁጥ ሥራ ናት፡፡ ዋናው ሥራው ድርሰቱ ምን እንደሚመስል ውስጡን ማሳየት፣ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮችን በማብራራት ለድርሰቱ ህይወት መስጠት ነው፡፡ በድርሰቱ ያሉ ሃሳቦች፣ ሃይለቃሎች፣ የሚያስደንቁትን ነገሮች ብቻ ሳይሆን ድርሰቱ ውስጥ ራሱን የቀሰቀሱትን ነገሮች ማብራራትና ማስረዳት ነው፡፡ መተንተንም ሌላው ክፍል ነው፡፡ መገምገም ትርፍ ነገር ሲሆን፡፡ የሚገመገምና የማይገመገም ሥራም አለ፡፡ ገምጋሚ ሐያሲ አይደለም፡፡ የሐያሲ ትልቁ ሥራ ሐያሲው አንብቦ አንባቢን ማፍራት ነው፡፡

ለአብነት ደበበ ሰይፉንና ዮሐንስ አድማሱን በመጥቀስ አገራችን ውስጥ ጥሩ ሐያሲያን ነበሩ ብሎ ያስባል፡፡

በድሉ የተባለ አስተያየት ሰጪ በበኩሉ ሒስ  አንድ ሥራ ከወጣ በኋላ አንባቢው ስነፅሁፍን የመረዳት ችሎታው እንዲጨምርና ራሱ አንባቢው ሐያሲ እንዲሆን ደራሲው ደግሞ መጥፎ ጐኑንና ጥሩውን ተከትሎ ራሱን እንዲያዳብር፤ በዚህም የአንድ አገር የስነፅሁፍ ሥራ እንዲያድግ የሚያደርግ ነው ብሏል፡፡ ከዚህ አንፃር "አሁን ያሉን ሐያሲያን ፅሁፉን ሔሰው ሕብረተሰቡ ፅሁፉን የማጣጣም ልምድ እንዲኖረው የሚያስችሉ ሒሶች ይሰጣሉ ወይ? ለሚለው የለም በሚለው እስማማለሁ" ብሏል፡፡ አሁን ያሉት ሐያሲያን በበድሉ አመለካከት በፀሐፊዎች የሚቀኑ ወይም አድር ባዮች ናቸው፡፡ ቡድን ለይተው፣ መደብ ሰርተው የሚሞጋገሱበት ዓይነት አካሄድ አላቸው፡፡ አንድ ሥራ ሲወጣ በስነፅሁፍ ላይ ሰልጥነው እንዲታዩ እንጂ የሠራውን ትርጉም ከፍ ለማድረግ፣ እንከን ለመልቀም የሚሰሩ አይመስልም፡፡ ደራሲውን ብጥቅጥቅ አድርገው በደራሲው ላይ መሰልጠን የሚፈለጉ ናቸው፡፡

ሐያሲ ትሁት መሆን አለበት፡፡ ሥራውም ማስተማር ነው፡፡ "በእኛ ሐያሲያን ላይ ይህንን አላይም" ብሏል፡፡ የተወሰኑት ደግሞ የሚረባውንም የማይረባውንም ሥራ በእነሱ አይን ብቻ በተለያየ ቡድናዊ ስሜት የሚያሔሱ ናቸው፡፡ ሚዲያዎች የሚያወድሱት እና የሚነቅፉት ዝርዝር ያላቸው እስኪመስል የተወሰኑ ሥራዎችንና ደራሲዎችን ነው በተደጋጋሚ የሚያነሱት፡፡ አሁን ያለው የሒስ አካሄድ ጥሩ ባለመሆኑም የወረዱ ሥራዎ"ች ለንባብ እየበቁ ይገኛሉ፡፡  

እንድሪያስ ተረፈ "ሂስ የሚባለው ነገር ጠፍቷል ቢባልም የመጀመሪያም በነበረው የሒስ አካሄድ አንድ መፅሃፍ በገፀ ባህሪው፣ በቋንቋው፣ በመቼት ወይም በመደምደሚያው ላይ የተለያዩ ነገሮች ለየብቻ እየተነሱ ሒስ የሚሰራበት አግባብ አልነበረም፡፡ የነበረው አሰራር አንድን መፅሃፍ ደብዘዝ ባለ አካሄድና በነበረው መረዳት ይሰራ እንደነበር ነው፡፡ አሁን ደግሞ በዚያም ደረጃ የነበረው ነገር ጠፍቷል" ብሏል፡፡

ሒስ በተወሰነ መልኩም ተፃፈ በሚባልበት በ1980"ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ያሉ ሐያሲያን ዛሬም አሉ፡፡ ሆኖም ሒስ ሲሰጡም ሆነ ሲፅፉ አይታዩም፡፡ በአሁኑ ዘመን እያሉ እንዳይፅፉ ያደረጋቸው ምንድን ነው? የሚለው መጠናት አለበትም ብሏል፡፡

"አሁን አልፎ አልፎ የምናያቸው ሥራ"ዎች እንደ ሒስ ሳይሆን ቢስ (ይደገም) እንደማለት ነው፡፡ አንድ አምስት ግሩፕ ያለው ሰው ከፃፈ ጓደኛው ደግሞ ሒስ ይሰራል፡፡ በመጨረሻም ስራው ከአቅሙና ከሚገባው በላይ ተጋንኖ መፅሃፉ ባልደረሰበት ቦታ ፅሁፎች ተፅፈው እናያለን"፡፡

ደራሲው ሥራውን ለማህበረሰቡ ካስረከበው በኋላ ቅርስ ነው፡፡ ይህንን ስነፅሁፍ ነው አይደለም፣ አላባዊያኑን አሟልቷል አላሟላም በሚል ጤናማ ሒስ መስጠት ለሃገር ቅርስ ማስቀመጥ ነው፡፡   

የፕሮግራሙ ተሳታፊ ኤፍሬም ስዩም እንዳለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ስነፅሁፍ ዘርፍ ማሰልጠን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ተማሪዎችን ያስመረቀ ቢሆንም በጣት የሚቆጠሩ ብቁ ሐያሲያንና ፀሃፍትን አውጥቷል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡

ሒስ የደራሲን ስራ መንቀፍ ብቻ አይደለም፡፡ ስለፅሁፍ አስተያየት መስጠት ነው፡፡ በፅሁፉ የተደበቀውን ሚስጥር ማሳየትና ማመላከት ነው፡፡ በአገራችን "50 ጨ ተጠቅሟል/ተጠቅማለች የሚሉ፣ ስርዓተ ነጥቦችን እንደ ትልቅ መስፈርት የሚያነሱ ሐያሲያን ነው ያሉን፡፡ ይሄ የኤዲተሮች ሥራ ነው፡፡ ሐያሲው መሔስ ያለበት ይዘቱን ነው" ብሏል፡፡

"መፅሃፍ የሚፃፈው በተወሰኑ ከዩኒቨርሲቲ በወጡ ብቻ አይደለም፡፡ የሚያነበውም ማንኛውም ማንበብና መፃፍ የሚችል ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የሚጠቀመውም የራሱን አእምሮና ችሎታ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ያሉ ሰዎች ሒስ ማድረግ አይችሉም፤ አይገባቸውም ማለት አይቻልም፡፡ በራሱ አእምሮና የአመለካከት መጠን ሊተቸው ይገባል፡፡ ለራሱ የሰጠውን ስሜት መናገር ይችላል፡፡ ሒስ ለተወሰኑ ለተማሩ ሰዎች የተሰጠ ብቻ አይደለም" የሚል አስተያየት የሰነዘሩት አቶ ልዑልሰገድ ደራራ ናቸው፡፡

ዘሪሁን ብርሃኑ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ የሒስ ሥራ የስነፅሁፍ ሥራን መገምገምና ማሔስ ብቻ ሳይሆን መንገድ ማሳየትም ነው ብሏል፡፡ "አንድ ሥራ ሲሔስ ጥሩ ሥራ አይደለም ከተባለ ጥሩ የሚሆንበት መንገዱን ማሳየትም የሐያሲው ሥራ ነው መፍትሄ የማይሰጥ ሒስ ሒስ አይደለም"፡፡

ሒስ አዲስ አስተሳሰብና መንገድ የሚያሳይ መሆን አለበት፡፡ ስነፅሁፍ በየዘመኑ ባለው ትውልድ የአስተሳሰብ ልክ ይለያያል፡፡ ከአስርት ዓመታት በፊት በወጣ ሕግ የዘመኑን ሥራ ማሔስ ተገቢ አይደለም የሚል አመለካከት አለው፡፡ አሁን ካለው የትውልድ የአስተሳሰብ ምጥቀት ጋር በተመጣጠነ ፅሑፍ አንዲወጣ ማሳየት የሐያሲው ሥራ ነው፡፡ "አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ የአፃፃፍ ስልትና ዘይቤ ያስፈልገናል"፡፡ ሲል ገል"ል፡፡

ጋዜጠኛው እንደሚለው በአሁኑ ሰዓት ሐያሲ የለም፡፡ በሙያዊ አካሄድ የበሰለ ሒስ ሲፃፍ አይታይም፡፡ አሁን የሚወጡ ሒሶች ሥራን ለማሻሻጥ የሚሰሩ ናቸው፡፡

አቶ አፈወርቅ በቀለ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል "በሒስና በአስተያየት መካከል ያለውን ልዩነት የተረዳነው አይመስለኝም፡፡ አስተያየት አሉታዊም አዎንታዊም ሊሆን ይችላል፡፡ ሒስ ግን በራሱ ድርሰት ነው፡፡ በአገራችን ሒስ አለ ወይ? ለሚለው እድሜዬ ከ60 ዘሏል፤ በዚህ ጊዜዬ ውስጥ አንድም በመፅሃፍ መልክ ታትሞ የወጣ ሒስ አይቼም አጋጥሞኝም አያውቅም፡፡ በውጭ አገር የተሠሩ ሥራዎችን ብንመለከት እንደ አንድ መፅሃፍ በተለያዩ ሥራዎች ላይ የቀረቡ ሒሶች ታትመው ገበያ ላይ ውለው ይታያሉ፡፡ በአገራችን ይህ ዓይነቱ የለም፡፡ ስለሆነም በአገራችን ሒስም ሐያሲም የለም፡፡ ያለው የአስተያየት ሥራ ነው" ብለዋል፡፡

ውይይቱ በአገራችን ሒስም ሐያሲም የለም የሚሉ የመድረክ ተሳታፊዎች የበዙበት የነበረ ቢሆንም ጥቂቶች ደግሞ ሒስና ሐያሲ የለም ብለን መደምደም የለብንም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በምሕረት ሞገስ
 
< Prev   Next >