Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 11th
Home arrow Sections arrow ክቡር ሚኒስትር
ክቡር ሚኒስትር Print E-mail
Wednesday, 26 March 2008
(ባንኩ የመኖሪያ ቤት በሐራጅ ሸጠ፡፡ በገዢው ቤት የቀለጠ ግብዣ ተዘጋጅቷል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩም በግብዣው ላይ ተገኝተዋል)

- ክቡር ሚኒስትር እንዴት እንደማመሰግንዎት አላውቅም፡፡ በደስታዬም በሐዘኔም ሁሌም ከጎኔ ነዎት፡፡ እርስዎ ባይኖሩ ኖሮ ይህን ቤት እገዛው ነበር?
- አንተ ሁሉም ወዳጅህ ነው፡፡
- ፈጣሪ ይመስገን ቁልቢ እሄዳለሁ፤ ግሸን ማርያም ቀርቼ አላውቅም፤ ደብረ ሊባኖስ ከመስሪያ ቤቴ የበለጠ የምመላለስበት ነው፡፡ የእኔ አምላክ ይሰማኛል፡፡ የሰው ፍቅር ሰጥቶኛል፡፡ የባንኩ ቦርድ፣ የባንኩ ማኔጅመንት፣ የባንኩ ሠራተኛ ሁሉ መጥቷል፡፡
- የባንኩ ሰው ሁሉ ይወድሃል ማለት ነው፡፡
- ማቴዎስ ወደ ተሰሎንቄ ሲጽፍ ..ፍቅርህን ለእግዚአብሄር አሳይ፣ ሰው ሁሉ ፍቅር እንዲያሳይህ ይረዳሃልና.. ብሏል፡፡ ክቡር ሚኒስትር አንዲት ሉዊ ካርቶዛ እሺ ይበሉኝ፡፡
- እሱ እጅግ በጣም ውድ መጠጥ ነው ይባላል፤
- እዚያ ያሉት የቦርድ አባላትኮ ሲቀልዱብኝ ነበር፡፡ ይህ መጠጥ የአንድ ዓመት ወለድ ይሸፍንልህ ነበር እያሉ፡፡ ክቡር ሚኒስትር እሽ ይበሉኝ ልዩ መጠጥ ነው፡፡
- እሺ፡፡ ድግስ አይደለም እንዴ?
(ሰውየው መጠጡን ሊያመጣ ሄደ፡፡ አንድ የባንኩ የማኔጅመንት አባል ወደ ክቡር ሚኒስትሩ መጣ)
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጤና ይስጥልኝ፡፡ አንተ አለህ እንዴ?
- አለሁ፡፡ በእርስዎ ድጋፍ አለሁ፡፡ እንደ ምቀኛ ብዛት ቢሆን ኖሮ ይሄኔ ጠፍቼ ነበር፡፡
- አንተ ምን ምቀኛ አለህ? ተበዳሪው ሁሉ ይወድሃል፡፡
- ተመስገን ነው የሚባለው፡፡ ተበዳሪው እውነትም ይወደኛል፡፡ መስራቾቹ ግን ችግር አለባቸው፡፡
- አይወዱህም?
- የሚወዱኝ አሉ፡፡ የማይወዱኝ አሉ፡፡ እርስ በራሳቸው የማይዋደዱ ስለሆኑ እነሱ በተናከሱ ቁጥር ጣጣው እኛ ላይ ነው፡፡
- ሰምቼ ነበር፡፡ አሁን ታርቀዋል መሰለኝ፡፡
- ውሸት ነው፣ ክቡር ሚኒስትር ማስመሰል ነው፡፡ ዛሬ ይታረቃሉ ነገ ይጣላሉ፡፡
- ምንድነው የሚያጣላቸው? አስታርቄያቸው ተሳስመው ነበር የተለያዩት፡፡
- ከባንኩ የወጡ ሰዎች አሉ አይደል፡፡
- ወጣን ይላሉ ግን አልወጡም፣ አለን ይላሉ ግን የሉም፡፡ ወጥተው ሌላ ባንክ አቋቁመው እየታመሰ ነው፡፡
- እናንተ ገንዘብ ላይ ተጠንቀቁ እንጂ ምንም ቢባሉ ምን አገባችሁ፡፡
- ገንዘብ የት አለና ክቡር ሚኒስትር፡፡ እርስዎ የማያውቁት ነገር አለ እንዴ?
- ብዙ ንብረት እየሸጣችሁ አይደለም እንዴ?
- የውሸት አሻሻጥ ነውኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት የውሸት?
- ለምሳሌ በዚህ ቤት የተወሰደው ብድር 28 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ አሁን በአራት ሚሊዮን ብር ነው የሸጥንለት፡፡
- ለምን?
- ሰውየውኮ መላው ባንክ በቁጥጥሩ ሥር ነው፡፡ ቦርዱ፣ ማኔጅመንቱ፣ ሠራተኛው በቁጥጥሩ ሥር ነው፡፡ ይኸው ይዩት ክቡር ሚኒስትር፡፡ ይህ ተጋባዥ ሁሉ የባንኩ ሠራተኛ ነው፡፡ የባንክ ሠራተኛ ማኅበር ክበብ አይመስልም? በሠራተኛው ክበብ እንኳ ይህን ያህል ሠራተኛ ተገኝቶ አያውቅም፡፡
- ሰውየው መስራች አይደለም እንዴ?
- ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ አራት ሚሊዮን ብር ይሸጥ ብሎ አስወስኖ ነው ራሱ፡፡
- ሰውየው ከማይወዱህ መስራቾች አንዱ ነው ማለት ነው?
- እንዴት ከማይወዱህ?
- የእሱ ጠላቶች አንተን የሚወዱ ይመስላሉ፡፡
- ይሆናል፡፡ የእርስዎ ነገር ግን ይገርመኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምንድነው የሚገርምህ?
- መስራቾቹ ቢጣሉም ሁሉም የእርስዎ ወዳጆች ናቸው፡፡
- ስለምቆጣቸውና ስለምመክራቸው ይሆናል፡፡
- ለምን ይህን ጋባዥ አይመክሩትም ታዲያ?
- ምን አጠፋ?
- ሌላ ባንክ ሌላው ንብረቱን በሐራጅ እየሸጠው ነው፡፡ እሱ ደግሞ ሌላ ንብረት ከእኛ ባንክ እየገዛ ነው፡፡

(ሰውየው መጠጡን ይዞ መጣ፡፡ የማኔጅመንቱ ሰውዬ ሄደ፡፡ ጋባዡ ከሚኒስትሩ ጋር ያወራል)

- ቺርስ..
- ቺርስ..
- የትኛው ንብረትህን ነው ባንክ ሐራጅ ያወጣበት?
- አምስቱን ድርጅቶች ሊሸጣቸው ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እነዚያን ግን አይነካቸውም አይደል?
- ዕድሜ ለእርስዎ ክቡር ሚኒስትር ሁሉም ባንተ ስም አታድርገው ብለው በመከሩኝ መሠረት ሌሎቹ ስድስት ድርጅቶች በዘመዶቼ እንጂ በራሴ ስም አላደረግኳቸውም፡፡
- የድሮ መኖሪያ ቤትህንም ሸጠው እንዴ?
- ዕድሜ ለወዳጆቼ መልሰው ገዝተው ሰጡኝ፡፡ ከቤትህማ አትወጣም ብለው ገዝተው ሰጡኝ፡፡
- እድለኛ ነህ፡፡ የሰው ፍቅር አለህ፡፡
- ብቻዬን አልበላም፡፡
- አምስቱም ተሸጡ አሉ፡፡
- ሁለቱ ገና ናቸው፡፡ እኔ ራሴም እነሱን ለመግዛት እጫረታለሁ፡፡
- በራስህ ስም፡፡
- እሱን አልወሰንኩም፡፡
- መግዛት የምትችል ከሆነ ለምን ብድሩን አልከፈልክም ስለምትባል ተጠንቀቅ፡፡
- ብድሩ ሁለት መቶ ሚሊዮን ነው፡፡ በሐራጅ የምገዛው በአምስት ሚሊዮን ነው፡፡
- ሃምሳ ሚሊዮን ነው የተገመተው፡፡
- ምን የተገመተው፡፡ እኛ አስገመትነው እንጂ፡፡ ክቡር ሚኒስትር እዚያ ዳር ቆመው የሚጠጡትን ያዩዋቸዋል?
- አዎን፡፡
- ገማቾቹ እነሱ ናቸው፡፡
- ያቺ ልጅ የታለች?
- የትኛዋ ክቡር ሚኒስትር?
- ቅጠራት ትረዳሃለች ብዬ የላኳት፡፡
- ያቺ ባለጌ አንድ ድርጅት አቋቄሜ ልበደር ስጠይቅ ድርጅቱ በሌላ ስም ስለሆነ ማጭበርበር ነው ብላ ተቃወመችኝ፡፡ በአክስቶቹ ልጆች ስም ያቋቋምከው ድርጅት ስለሆነ አጋልጥሃለሁ አለችኝ፡፡
- እናስ?
- ወዲያው እንዲያባርሯት አደረግኳ
- አሁን የታለች?
- እዚህ መስራች ነኝ የሚለው ሰውዬ ባንኩን ሊጠቀልለው እየተንቀሳቀሰ ነው፤
- ጠርጥሬያለሁ፡፡
- እሱ ቀጠራት፡፡
- ለምን?
- አንድ ቀን ምስጢር ታወጣለች ብሎ እኔን ለማስፈራራት እንደ ተቀበረ ፈንጂ ሊጠቀምባት ፈልጎ ነዋ፡፡
- እና እየተጠነቀቅክ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር የእናንተን ያህል ፊደል ላልቆጥር እችላለሁ፡፡ በእውቀት እኩል ባልሆንም በክፋት ግን የማንስ አይመስለኝም፡፡ ቀድሜ የማጠቃ እንጂ የምጠቃ አይደለሁም፡፡
- እንዴት ልታጠቃው ትችላለህ?
- ከሌላው ቡድን ጋር ሲጣላ የእኔን ድጋፍ ፈልጎ የነገረኝ ብዙ ምስጢር አለ፡፡  ብዙ ዶክሜንቶችን ሰጥቶኛል፡፡ በዚያ ላስጠይቀው እችላለሁ፡፡
- የሚያስጠይቀው ቢሆን ኖሮ ዶክሜንቱን አይሰጥህም፡፡
- ተሰጥቶኝማ በእጄ ገብቷል፡፡
- ጠበቅ አድርገህ ያዝ፡፡

(ሌሎች እንግዶች ሲገቡ ጋባዡ ሊቀበላቸው ሄደ፡፡ ሌላ ሰው ወደ ክቡር ሚኒስትሩ መጣ)

- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጤና ይስጥልኝ ረሳሁህ ልበል?
- ዮሐንስ ነኝ የአስቴር ልጅ፡፡ እርስዎ ነበሩ እዚህ ያስቀጠሩኝ፡፡
- ውይ ውይ አንተ ነህ እንዴ፡፡ እናትህ ደግሞ ምነው ጠፋች?
- አለች ሚኒስትር ጋር መደወል ፈርታ ይሆናል፡፡
- ቀልደኛ ነህ ልበል፡፡ ሥራ እንዴት ነው?
- ምን ሥራ አለና ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የባንኩ ሥራ ነዋ
- ምን ባንክ አለ ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት ምን ባንክ አለ፡፡ የለም እንዴ?
- የለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምትሰራበትን ባንክ የለም ትለኛለህ፡፡
- መቼ ሰራሁና፡፡
- አትሰራም?
- ምን ሥራ አለና ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አልገባኝም፡፡ ዮሐንስ ነው ያልከኝ አልገባኝም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይህ ባንክ የውሸት ባንክ ነው፡፡ ገንዘብ የለው፣ ቦርድ የለው፣ ማኔጅመንት የለው፣ መስራቹ አይታወቅ፣ አስቀማጩ አይታወቅ፣ ተበዳሪው አይታወቅ፡፡
- እና ሥራ ልትለቅ ነው?
- እኔ ከመልቀቄ በፊት ባንኩ ይወድቃል፡፡
- እንዲህ ቢሆን ኖሮማ ብሄራዊ ባንክም ዝም ብሎ አያየውም ነበር፡፡
- ብሄራዊ ባንክ ራሱ እየወደቀም ዝም ብሎ የሚያይ ነው፡፡
- እንደ ዘመድ ልምከርህ?
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሌላ ጣጣ ውስጥ አትግባ፡፡ ዝም ብለህ ሥራ፡፡ እኔ የቅርንጫፍ ማናጀር እንዲያደርጉህ እነግርልሃለሁ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እንኳን ቅርንጫፍ ባንኩም የለም አይኖርም ነውኮ የምልዎት፡፡
- ወደዚህ ግብዣ የመጣኸው ለምንድነው ለመታዘብ?
- ለመታዘብ አይደለም፡፡ ለሌላ ምክንያት ነው የመጣሁት፡፡
- ምን ምክንያት?
- አስቴር ልካኝ ነው የመጣሁት፡፡
- እናትህ?
- አዎን፡፡
- ምን ላከችህ?
- እርስዎን እንዳገኝ ነው፡፡
- እንደምመጣ እንዴት አወቀች?
- ክቡር ሚኒስትር ዋናው ምክንያት ይኸው ነው፡፡ እርስዎ አይታወቅብኝ ይላሉ፡፡ ሰው ሁሉ ግን ያወራል፣ ይነጋገርበታል፣ ይስቅብዎታል፡፡
- ምን ብሎ ነው የሚያወራው? ምን ብሎ ነው የሚስቀው?
- ክቡር ሚኒስትር እኔም የማወቀው ሰውም የሚያወራው በብሄራዊ ባንክ እርምጃ እንዳይወሰድ የተደረገው በእርስዎ አማላጅነት ነው፡፡
- እኔ እንደዚህ ዓይነት ተግባር ላይ የለሁበትም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በዚህ ባንክ በኩል የሚላክ የውጭ ምንዛሬ እዚያው ውጭ እንደሚቀር ያውቃሉ፡፡
- ኧረ እንደዚህ ዓይነት ሥራ ውስጥ የለሁበትም፡፡
- ኤል.ሲ የሚከፈትለት ነጋዴ በእርስዎ አማላጅነት እየተመረጠ ነው፡፡
- ኧረ እኔ የለሁበትም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይህ ጋባዡ ሰውዬ ይህን ቤት በርካሽ የገዛው  በእርስዎ ድጋፍ ነው፡፡
- ኧረ እኔ የለሁበትም፡፡ ባንክ ውስጥም እኮ መደበኛ ሥራ የለኝም፡፡ የልማት ደጋፊ ስለሆንኩ ነው ባንኮችን አይዟችሁ የምላቸው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎ እኮ በተዘዋዋሪ አክስዮን ተገዝቶ ተሰጠቶዎታል፣ ባለአክስዮን ነዎትኮ፡፡
- ኧረ እኔ በእንደዚህ ዓይነት ሥራ ውስጥ አልገባም፡፡
- እናቴ ለአጎትህ ሂድና ንገራቸው ብላኝ ነው የመጣሁት፡፡ እሷ ሁሉንም ነገር ታውቃለች፡፡ ቨርጂንያ ቤት እንደገዙም አክስቷ ነግራታለች፡፡ ባለፈው ለዕረፍት ሄዳም ቤቱን አይታዋለች፡፡ እዚያም አድራለች፡፡ ይህን ሁሉ ታውቃለች፡፡
-  እኔ የለሁበትም፡፡
- ከባንክ ዶላር እየወጣ በጥቁር ገበያ እንዲመነዘር ያደርጋሉ፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት እኩይ ተግባርም እርስዎ ሽፋን ይሰጣሉ፡፡
- ኧረ እኔ የለሁበትም፡፡
- ለአጎትህ ንገራቸው ብላ ነው አስቴር የላከችኝ፡፡
- እኔ ንፁህ ነኝ፡፡ ብከሰስ ወይም ብታሰር እንኳ አንተና እናትህ ናችሁ ንፁህ መሆኔን መመስከር የምትችሉት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኛ የለንበትም፡፡
 
< Prev   Next >