| ለአስራ አንድ ዓመታት በሣንቲም ሽያጭ |
|
|
| Wednesday, 26 March 2008 | |
|
ጠዋት በግምት ሦስት ሰዓት ገደማ ላይ ጋንዲ ሆስፒታል ፊት ለፊት ሰፋ ያለ ምንጣፋቸውን በመዘርጋት የተለያዩ አገራት ሳንቲሞችና ብሮችን፣ የጥንት ሜዳሊያዎችንና የልብስ ቁልፎችን እንዲሁም ሌሎች በርካታ ታሪካዊና ባህላዊ ቁሳቁሶችን ከወዲያ ወዲህ እያሉ በመልክ በመልኩ ሲደረድሩ ተመለከትናቸውና ጠጋ ብለን አነጋገርናቸው፡፡
አቶ ሐብታሙ ሹምበል የተለያዩ ታሪካዊና ባህላዊ ቁሳቁሶችን (ጌጣጌጦችን) ጨምሮ ማሰባሰብና መሸጥ ከጀመሩ ከአስራ አንድ ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ አሁን ይህን ሥራ በቋሚነት እየሰሩ ያሉት ጋንዲ ሆስፒታል አካባቢ ሲሆን ቀደም ሲል ደግሞ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ ተመሳሳይ እቃዎችን እያዞሩ ይሸጡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ታሪካዊና ባህላዊ እቃዎች ናቸው ያሏቸውን እቃዎች እየሰበሰቡ መሸጥ ከመጀመራቸው በፊት ከፍየል ቆዳ የሚሰሩና የተለያየ መጠን ያላቸውን ምንጣፎች ይሸጡ ነበር፡፡ አቶ ሀብታሙ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ አምስቱም ልጆቻቸው ገና ተማሪዎች ሲሆኑ የሚያስተምሯቸውም የግል ትምህርት ቤት እየከፈሉ እንደሆነ ገልፀውልናል፡፡ የተለያዩ ታሪካዊና ባህላዊ ቁሳቁሶችን ማሰባሰብና መሸጥ ለመጀመራቸውም ..ከበፊት ጀምሮ ታሪካዊ ቅርሶችን የሚያሰባስቡ ግለሰቦችን አደንቅ ነበር፡፡ እኔም እንደነሱ የማድረግ ፍላጎት አደረብኝ፡፡ ከዚያም በአንድ ወቅት ሥራ መቀየር ስፈልግ ለምን ይህን ሥራ አልሰራም? ብዬ አሰብኩ.. የሚለው ምክንያታቸው መሆኑን ገልፀውልናል፡፡ አቶ ሐብታሙ ከሚሸጧቸው የቁሳቁስ ስብስቦች መካከል በተለያየ ዘመን የነበሩ የተለያዩ አገራት ሳንቲሞችና ብሮች፣ ሜዳሊያዎች፣ የልብስ ቁልፎች፣ የእጅ አምባሮች፣ መቁጠሪያዎችና የነብር ጥርስ ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህን ቁሳቁሶች የሚያሰባስቡትም ከተለያዩ ሰዎች በመግዛት እንዲሁም እሳቸው ከሚሸጡበት ቦታ ድረስ በመሄድ ከሚሸጡላቸው ሰዎችም ጭምር መሆኑን ገልፀውልናል፡፡ እርሳቸውም መርካቶ ፣ቆሼ ተራ፣ በመሄድ እቃዎችን እንደሚሰበስቡ አልሸሸጉም፡፡ ከሚሸጧቸው ሳንቲሞች መካከል የኬንያ፣ የፈረንሳይ፣ የጣሊያንና የአሜሪካ ሳንቲሞች ተመልክተናል፡፡ ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ እስከ ደርግ ድረስ የነበሩ ሳንቲሞችና ብሮችን አንድ በአንድ አሳይተውናል፡፡ በአፄ ምኒልክ ጊዜ የነበሩ ሣንቲሞችና ብሮች ተፈላጊነት እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡ አቶ ሐብታሙ እንደገለጹልን ቁሳቁሶቹን ከክፍለ አገር የሚያመጡላቸው ሰዎች አሉ፡፡ እሳቸውም አንዳንድ ጊዜ ከተለያዩ ሱቆች የሚገዙበት አጋጣሚ አለ፡፡ አብዛኞቹ የልብስ ቁልፎች በተለያዩ መንግሥታት በተለያዩ የጦር ሠራዊት ክፍሎች ይለበሱ የነበሩ ቁልፎች ሲሆኑ ከሜዳሊያዎቹ መካከል ደግሞ የኦሊምፒክ፣ ከኮሪያ ዘማቾችና በአፄ ምኒልከ ዘመን የነበሩ ይገኙባቸዋል፡፡ ቁልፎቹን አብዛኛውን ጊዜ የሚገዟቸው ራስታዎች ናቸው፡፡ ወደ አስር ሺህ የሚሆኑ የተለያዩ ሳንቲሞች ያሏቸው ሲሆን ሳንቲሞቹ የምን አገርና የመቼ ዓ.ም እንደሆኑ በቀላሉ ይለዩዋቸዋል፡፡ ይህ ሥራው ላይ ረዥም ጊዜ በማሳለፋቸው ከልምድ የመጣ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የሚሸጧቸው ቁሳቁሶች የተለያዩ መሆናቸው የሚሸጡበትን ዋጋ በምን መልኩ እንደሚተምኑ ጠየቅናቸው፡፡ ..ለምሳሌ ቁልፎቹን አብዛኛውን ጊዜ የሚገዙኝ ራስታዎች ናቸው፡፡ አንድ ቁልፍ በአስር ብር እሸጥላቸዋለሁ፡፡ ይህ እቃ በብዛት ይሸጣል ብዩ መናገር አልችልም፡፡ ሳንቲሞቹን የውጭ ዜጎች ይገዙኛል፡፡ ሳንቲሞችንና ብሮችን የሚያሰባስቡ ግለሰቦችም በተደጋጋሚ እየመጡ ይገዙኛል፡፡ እዚህ ካሉኝ መካከል ከፍተኛ ዋጋ የምንሰጠው በተለያየ ዘመን ለነበሩ ብሮች ነው.. በማለት ክረምት ላይ ወደየአገራቸው የሚሄዱና የውጭ ዜጋ የሆኑ የሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት መምህራን ቋሚ ደንበኞቻቸው መሆናቸውንና በተለያየ ጊዜ ወደ አገር ቤት የሚመላለሱ ኢትዮጵያዊ ደንበኞችም እንዳሏቸው ገልፀውልናል፡፡ ዘወትር ከጠዋት እስከ ምሽት አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ እንደሚሰሩ የሚናገሩት አቶ ሐብታሙ እሑድን እንኳ ልረፍ ቢሉ የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸው ጫና ስለሚፈጥርባቸው ይህን ማደረግ እንደማይችሉ በተለያየ ጊዜ ሞክረው እንዳረጋገጡ አመልክተዋል፡፡ ..በቀን ይህን ያህል ገቢ አገኛለሁ ወይም ይህ ነገር በብዛት ይሸጣል ማለት ባልችልም የሰው እጅ አላይም፡፡ ሰርቼ ቤተሰቦቼን በማስተዳደር ላይ እገኛለሁ፡፡ አምስቱንም ልጆቼን እየከፈልኩ የግል ትምህርት ቤት ነው የማስተምራቸው፡፡ የተደላደለ ሕይወት ባንመራም፣ የሰው እጅ አንጠብቅም፣ ጾማችንን አናድርም.. ብለዋል፡፡ ለተለያዩ ሐይማኖታዊ በዓላት በርካታ የውጭ ዜጎች ወደ አገር ቤት በሚገቡባቸው ጊዜያት የተሻለ ገበያ ይኖራል፡፡ አንዳንዴ በከተማዋ ከፍተኛ ስብሰባዎች ሲኖሩ ለደህንነት ሲባል ከሚሸጡበት ጋንዲ አካባቢ በደንብ አስከባሪዎች እንዲነሱ እንደሚደረግ አልደበቁም፡፡ በዚህ ሥራ ላይ ይህ እቃ ይሸጥልኛል፣ ይህኛው አይሸጥልኝም የሚባል ነገር የለም፡፡ የገዥዎቹ ፍላጎት የተለያየ ከመሆኑና በእቃዎቹም ልዩነት ምክንያት ረዥም ጊዜ ሳይሸጡ የሚቆዩ እቃዎች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህም በዚህ ሥራ ላይ የተሰማራ ማንኛውም ሰው ትዕግስት ሊኖረው እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ የቆዩ ሳንቲሞች ከቅርብ ጊዜዎቹ የተሻለ ዋጋ ያወጣሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ ሰዎች የሚፈልጉትን እቃ እንዲያመጡላቸው ይጠይቋቸዋል፡፡ ከሚያሰባስቧቸው ታሪካዊና ባህላዊ ቁሳቁሶች መካከል እዚህ ቦታ ይገኛል ወይም በዚህ መንገድ ሊገኝ ይችላል ብለው እርግጠኛ የሚሆኑበት እቃ ባለመኖሩ ለእነዚህ ሰዎች ቃል አይገቡም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች አድራሻቸውን ሰጥተዋቸው ስለሚሄዱ የሚፈለገው እቃ በአጋጣሚ የሚገኝበት ሁኔታ ካለ ስልክ ይደውላሉ፡፡ በዚህ መልኩ ቋሚ ደንበኞቻቸው የሆኑ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ገልፀውልናል፡፡ ለማጓጓዝ ስለማይመች እንጂ ወደ አሥር ሺህ የሚሆኑ ሳንቲሞች፣ ሁለት ሺህ ቁልፎችና ሌሎችም ቁሳቁሶች እቤታቸው እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ሐብታሙ ይህን ሥራ በስፋትና በተደራጀ መልኩ ሱቅ ከፍተው ለመሥራ በሚኖሩበት ተክለሃይማኖት አካባቢ ለቀበሌ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ቀደም ሲል እሳቸው የሚሸጧቸውን ቁሳቁሶች የመግዛትም ሆነ የመሸጥ ሁኔታ ብዙም ትኩረት የሚሰጠው እንዳልነበር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኅብረተሰቡ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን ለማሰባሰብ ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡ በምሕረት አስቻለው |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |