| “ከ76ሺ በላይ ኢትዮጵያዊያን... |
|
|
| Sunday, 30 March 2008 | |
|
“ከ76ሺ በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ አረብ አገሮች ሄደዋል”
ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ የዓረብ አገሮች በመንግሥትና በኤጀንሲዎች አማካኝነት ሥራ ፍለጋ የሄዱ ሴቶች ቁጥር 76ሺ 60 መድረሱን የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሶሪያ፣ ሊባኖስ፣ ኩዌት፣ ኳታርና ሣዑዲ ዓረቢያ የሄዱት፣ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፈቃድ አግኝተው በውጭ አገር ሰራተኛንና አሠሪን በሚያገናኙ 80 ኤጀንሲዎችና በመንግሥት በኩል በሚፈፀም የሥራ ግንኙነት ውል አማካኝነት መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታዋ ይኸንን የተናገሩት መጋቢት 17 ቀን 2000 ዓ.ም በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሆን፣ ከ1993 እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ 97ሺ 315 ዜጎች በኤጀንሲዎች አማካኝነት እንዲሁም ከ1995 እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ በመንግሥት በኩል 18ሺ 745 ዜጎች ወደ አረብ አገራት ለሥራ መሄዳቸውን ገልፀዋል፡፡ ለሰራተኛና አሠሪ አዋጅ 377/96 ተደርሶ በቅርቡ የሚፀድቀውና በሰራተኛና አሠሪ መካከል ያለውን ግንኙነት አጠቃላይ ሁኔታ የሚያይና የዜጎችን መብትና ደህንነትን ለማስጠበቅ፣ ማንም ሰው ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ሕገ መንግሥታዊ መብቱን በሚያስከብርበት አዋጅ ቁጥር 104/90 አማካኝነት በሁለት መንገድ ብቻ (በመንግሥትና ኤጀንሲዎች) ዜጎች ያለምንም ስጋት ወጥተው መስራት የሚችሉ መሆኑን ወ/ሮ ዘነቡ አብራርተዋል፡፡ “ሕብረተሰቡ ከህገወጥ ደላሎችና ወደ ውጭ ሀገር እንልካለን በሚል ግለሰቦች አጭበርባሪዎች መጠንቀቅ አለበት” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ አሠሪው የኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ሚሺን አባል ከሆነ ወይም መንግሥት የሁለትዮሽ ስምምነት ካላደረገ ወይም በአገር ውስጥ ያለ አሰሪ፣ በውጭ ላለው ቅርንጫፍ ሰራተኛ የሚያስፈልገው ከሆነ ወይም ሰራተኛው በራሱ እድል የሚያገኝ ከሆነ፣ የውጭ አሠሪ ከኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጋር ተነጋግሮ ሠራተኛውን ለመቅጠር ሲፈልግ፣ የመንግሥታዊ የውጭ ሥራ ሥምሪት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በሕገወጥ ዝውውር እድሜያቸው ከ15 የማይበልጡ ህጻናት በቀበሌ፣ በቤተክርስቲያንና በአንዳንድ ማዘጋጃ ቤቶች አማካኝነት በሚሰጣቸው የሰነድ ማስረጃ አማካኝነት ሕጋዊ ፓስፖርት ይዘው ስለሚመጡ ሚ/ር መስሪያ ቤቱ ምንም ሊቆጣጠርበት የሚችልበት መንገድ ባለመኖሩ፣ ከቤተሰብና ከአገራቸው ወጥተው ለወሲብ ጥቃትና ለጉልበት ብዝበዛ እንደሚጋለጡ ወ/ሮ ዘነቡ ተናግረዋል፡፡ ወደ ውጪ አገሮች የመውጫ መንገዶች የቱሪስት ቪዛ፣ ነፃ ቪዛ፣ የንግድ ቪዛ፣ ነፃ የመግቢያ ፈቃድ፣ ከአሚሮችና ከሺኮች ጋር በጉዞ ወኪሎች አማካኝነት የሚወጡ፣ ከኡምራና ሐጂ ጋር በተያያዘ የሚወጡ በሙሉ በህገወጥ ሁኔታ ስለሆነ የሚደርስባቸውም አደጋና ስቃይ ከፍተኛ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ህገወጥ ነጋዴዎች በሚያደርጉት የሚዲያ ላይ ጥሪ የሚጠቅሱት የክፍያ ገንዘብ እያማለላቸው ለከፍተኛ ጉዳት የተዳረጉትንና ህይወታቸው ያለፈውን ቤት ይቁጠረው ያሉት ወ/ሮ ዘነቡ፣ ወደ ውጪ ከሚሄዱት (ዐረብ አገር) ውስጥ ኢንጂነሮች፣ የህክምና ዶክተሮችም እንደሚገኙበት ገልፀዋል፡፡ ወደ አረብ አገሮች ከተጓዙት ኢትዮጵያውያን መካከል በርካታዎቹ መሞታቸውና አስከሬናቸው መመለሱ ይታወቃል፡፡ ቁጥራቸው ምን ያህል ይሆናል ተብለው ለተጠየቁት፣ “ወደ አረብ አገሮች መላክ የተጀመረው ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ “መረጃውን አሰባስበን ስላልጨረስን ይኸን ያህል ነው ብሎ ለመናገር ያዳግተኛል” በማለት ምላሽ መስጠት አለመፈለጋቸውን ወ/ሮ ዘነቡ ተናግረዋል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |