| የቻይና ኩባንያ 11 ኮንቴይነር እቃ... |
|
|
| Sunday, 30 March 2008 | |
|
የቻይና ኩባንያ 11 ኮንቴይነር እቃ በናዝሬት ጉምሩክ ተያዘ - የቻይና ኤምባሲ እቃው እንዲለቀቅ ጠይቋል ሲኖ ሀይድሮ የተባለ የቻይና የመንገድ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ ካስገባቸው አስራ ሁለት ኮንቴነሮች ውስጥ አስራ አንዱ በናዝሬት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ተያዙ፡፡ የፕሮጀክቱ ባለቤት ለፕሮጀክቱ ሥራ የሚውለው እቃ ብቻ እንዲለቀቅ ጠይቋል፡፡ ኩባንያው እቃውን ከማስገባቱ በፊት ለገቢዎች ሚኒስቴር የቀረጥ ነፃ ዲፓርትመንት አመልክቶ ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ ከተፈቀደለት መጠን በላይ ኮንቴነሮችን ሲያስገባ መያዙን የሪፖርተር የናዝሬት ምንጮች ገልፀዋል፡፡ እንደ ምንጮቹ ገለፃ “በህጋዊ እቃ ላይ ህጋዊ ያልሆኑ እቃዎችን አስገብቷል” በሚል የሲኖ ሀይድሮ ንብረቶች ሊያዙ ችለዋል፡፡ በኮንቴነር ታሽገው የተያዙትን እቃዎች በዝርዝር ያልገለፁት ምንጮች እንዳስታወቁት ኩባንያው እቃዎቹ ከተያዙ በኋላ ከቀረጥ ነፃ ፈቃድ ለማውጣት ጠይቋል፡፡ የናዝሬት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠይቆ የተጠቀሱት ኮንቴነሮች መያዛቸውን አረጋግጦ ዝርዝር መግለጫ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ገል..ል፡፡ በኮንቴነር የታሸጉት እቃዎች ሲኖ ሀይድሮ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለወሰደው አሶሳ ሸርቆሌ እስከ ብሉናይልና ቡሉናይል ጉባ ፕሮጀክት ሥራ ውስጥ ለብሉናይል ድልድይ ግንባታ በሚል ያስመጣቸው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኢንፎርሜሽንና የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ “ለብሉ ናይል ድልድይ ግንባታ የመጡት የስቲል ፎርም ወርክ ብረቶች ብቻ እንዲለቀቁ ጥያቄ ቀርቧል” ብለዋል፡፡ የመንገድ ሥራው እንዳይስተጓጐል ለሥራው ብቻ የመጡት ብረቶች እንዲለቀቁ የጠየቀው ባለስልጣኑ “ከጠየቀው ውጪ ያለው ጉዳይ በሚመለከተው አካል የሚታይ ነው” በማለት በህዝብ ግንኙነት በኩል ተናግሯል፡፡ የጉምሩክ ባለስልጣን የቀረበለትን ጥያቄ ስለመቀበሉ ተጠይቆ “የሕዝብ ግንኙነቱ የሉም” የሚል መልስ ሰጥቷል፡፡ ባለስልጣኑ መልስ ላለመስጠት ምክንያት ቢያቀርብም ታማኝ ምንጮች ፈቃድ ሳያገኙ በገቡት አስራ አንድ ኮንቴነሮች ጉዳይ በፍርድ ቤት ክስ እንደሚመሰረት አስታውቀዋል፡፡ በናዝሬት ጉምሩክ ቅርንጫፍ የተያዙትን ኮንቴነሮች አስመልክቶ እንዲለቀቁ ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ የሆነው የቻይና ኤምባሲ ለገቢዎች ሚኒስቴር በደብዳቤ ጥያቄ እንደቀረበና በጉዳዩ በተደጋጋሚ ውይይት እንደተደረገ የሪፖርተር ምንጮች ገልፀዋል፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |