| ኢሕአዴግ ውስጡን ይፈትሽ! |
|
|
| Sunday, 30 March 2008 | |
|
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለፈው ሳምንት ለፓርላማ ያቀረቡት ሪፖርት ሁለት አበይት ይዘቶች ነበሩት፡፡ አንዱና ግልፁ የኢኮኖሚክ ሪፖርት ይዘት የነበረው ውይይት ነው፡፡ ሌላኛው ከይዘቱ ባሻገር በፓርላማው የነበረው የክርክር መንፈስና የፈለገው የሃሳብ ግጭትና የመረረ ተቃውሞ ቢመጣም ለምን እንዲህ ትናገራለህ? የሚል የፀብም ሆነ የፀረ ዴሞክራሲ እንቅስቃሴ መንፈስ አለመታየቱ ነው፡፡
አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተናጋሪዎች አልቻላችሁምና ስልጣን አጋሩን ብለዋል፡፡ አንዳንዶቹ ኢኮኖሚ አደገ የሚትሉት ውሸታሞች ናችሁ ብለዋል፡፡ አንዳንዱ ትወድቃላችሁ ብሏል፡፡ ይህ ሁሉ ሲባል ግን ለጥያቄው መልስ ከመስጠት አልፎና ተርፎ ከመሳቅ በስተቀር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁጣም ሆነ ዘለፋ ወይም የተናገሩትን የመዝለፍና የማስጨነቅ ሁኔታ አልታየም፡፡ ብዙ ቢቀረውም የዴሞክራቲክ መድረክ የፓርላማ ወግና መንፈስ ታይቶበታል፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ተቃዋሚዎች ሃሳባቸውን የመግለፅ መብት አላቸው የሚለውን ጉልህ መንገድ ያሳየ ነውና፡፡ ፓርላማውም ፓርላማ መስሎ ውሏል፡፡ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ነው በሁሉም ዕለታዊ የመንግሥትና የፓርቲዎች እንቅስቃሴ መታየት ያለበት፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን ሃሳብን የመግለፁና የመቃወም መብት መከበር በተግባር በየትም ቦታ መቸም ቀን ሊታይና ሊረጋገጥ ይገባዋል፡፡ ችግሩ ግን በሁሉም ቦታ አይደለም፡፡ ሁለት አይነት ኢሕአዴግ፣ ሁለት አይነት መንግሥት ነው ወይ ያለውም ያሰኛል፡፡ በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች የበላይ ኃላፊን ተቃውማችኋል፤ በሚልና በቢፒአር (BPR) ፕሮግራም ሽፋን ለረጅም ዓመት ያገለገሉና ልምድና ዕውቀት ያካበቱ ሰዎች ሲባረሩና ሲንገላቱ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት መውደቅና ስልጣኑን ማጋራት አለበት፤ ሲባል የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ይፈቅድለታል መብቱ ነው ይባላል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብት የትም ለሁሉም መሆኑ ተግባር ላይ ይዋል ስንልም ይህን ማለታችን ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ በቢሮክራሲው ከፍተኛ አደጋ እየተንፀባረቀ ነው፡፡ ቢሮክራሲው መንግሥትና ሕዝቡን የሚያገናኝና መንግሥትን ወክሎ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ሳይሆን ሆን ብሎ መንግሥትንና ሕዝብን እያጋጨና እያጣላ የሚውል ቢሮክራሲ ሆኗል፡፡ የመንግሥት ዋና ጠላት የመንግሥት ቢሮክራሲ ሆኗል፤ ቢባልም ምንም ማጋነን የለበትም፡፡ በቢሮክራሲው አስተሳሰብ ሕዝብን መብቱ ነው የሚል የለም፡፡ በሕዝብ ግብርና ገንዘብ ነው ደሞዝ የሚከፈለኝ የሚል ቢሮክራሲ ጠፍቷል፡፡ የድሮ ቢሮክራሲ መንግሥት ለዘለዓለም ይኑር፤ የሚል ነበር፡፡ የዘንድሮ ቢሮክራሲ ይህን መንግሥት ካልጣልኩ ሞቼ እገኛለሁ የሚል ሆኗል፡፡ ኢሕአዴግ አምኖ የሾማቸው ሰዎችም በሶስት ተፈርጀው ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ሕዝብን ከልብ ለማገልገል ቀንና ሌሊት የሚጥሩና የሚሰሩ የሕዝብ አገልጋዮች አሉ፡፡ በሌላው ጫፍ ደግሞ ኢሕአዴግ የሰጣቸውን ሹመት ለግል ንብረትና ገንዘብ መዝረፊያና ማካበቻ አድርገው የሚጠቀሙ የነቀዙና የዘቀጡ አሉ፡፡ “ስግብግብ” የምንለው ነጋዴው ብቻ ሆኖ እንጅ “ስግብግብ ባለሥልጣን የማንልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሶስተኛው ፈርጅ ደግሞ ሕዝቡንም አያገለግልም፣ አይሰርቅምም አይዘርፍምም ለሕዝቡና ለመንግሥትም የማይሆን ወንበር ብቻ እያሞቀ የሚውል ባለሥልጣን አለ፡፡ እዚህ ግባ የማይባል ወኔም እልህም ሕዝባዊ ፍቅርም የሌለው ነው፡፡ ሕዝቡን ከልብ ለማገልገል የሚፈልጉ አንድ እጅ ሆነው ስግብግብና ግድየለሽ ባለሥልጣናት ሁለት ሶስተኛው እጅ መያዛቸው እጅግ አሳሳቢ ነውና መንግሥት ቢሮክራሲውን በሚገባ ሊፈትሽና ሊያስተካክል ይገባዋል፡፡ ግንባር ቀደም የተሰለፈው ጠላት ይህ ቢሮክራሲ ሆኗልና፡፡ ኢሕአዴግ ውስጡን ይፈትሽ፣ ኢሕአዴግ ቢሮክራሲውን ይፈትሽ፤ ስንል በቅንነት አንፃር ብቻ አይደለም፡፡ በአቅም አንፃር ቢሆንም ኢሕአዴግ ራሱን ሊፈትሽ ይገባል፡፡ አቅም ስንል ምን ማለታችን ነው? የእውቀት አቅም፣ የልምድ አቅም፣ ነገሮችንና ችግሮችን የመረዳት አቅም፣ የተሰጠው ኃላፊነት በእውቀት በተደገፈ አቅም መምራትም፣ የሚነሱ ጥያቄዎች በአጥጋቢ ሁኔታ የመመለስ አቅም ማለታችን ነው፡፡ ያለውን የኑሮ ውድነት ስንቱ ባለሥልጣን ነው በትክክል የሚገነዘበው? ስንቱ ባለሥልጣን ነው ተቃዋሚዎች ላነሱት ሃሳብ አጥጋቢ መልስ መስጠት የሚችለው? ምን ያህሉ ነው የወርቅ ማጭበርበር ችግር ጉዳቱን በትክክል መገንዘብ የሚችለው? ትህትና የሌላችሁ ናችሁ ካልተባልን የሚከተለውን ጥያቄ እንድናቀርብ ይፈቀድልን፡፡ ስንቱ ሚኒስትር ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሉት የሚገባው? በጠቅላይ ሚኒስትሩና በሚኒስትሮች መካከል ስንት ፌርማታ አለ? በነገራችን ላይ ይህ ጥያቄ የዚህ ፅሁፍ ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉም እያነሳው ያለ ጥያቄ እንጂ፡፡ ስለ ቅንነትም፣ ስለአቅምም እያነሳን ያለነው ለመገንባት እያሰብን ካለነው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ ስርዓትና ልናስመዘግበው ከምንፈልገውና የሚሊንየም ራዕያችን ብለን ካስቀመጥነው አንፃር በቂ ቅንነትና አቅም ሳንይዝ እንዴት እውን ይሆናል የሚል ተጨባጭ ስጋት ስላለን ነው፡፡ መንግሥት በአጠቃላይ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ወጥነት ይዞ የማይንቀሳቀስ ከሆነ ወጥነት ያለው ሥርዓት ለመገንባት ያስቸግራል፡፡ መንግሥት እየሰራው ያለው ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴም በተፈለገው ፍጥነት ሄዶ የተፈለገው ስኬት ለማስመዝገብ ችግር ያጋጥመናል፡፡ ስለዚህ በጥረትና በአቅም አንፃር መንግሥት ቢሮክራሲውን ይፈትሽ ኢህአዴግ ውስጡን ይፈትሽ፤ ያጥራ፡፡ ይህ ለፓርቲው ጥራትና ጥንካሬ ብለን የምንሰጠው ሃሳብ አይደለም፡፡ ስለፓርቲው ጥንካሬ ራሱ ፓርቲው ያስብበት፡፡ ነገር ግን መንግሥታዊ ስልጣን የያዘ ፓርቲ ስለሆነና ቢሮክራሲው ተመልሶ የመንግሥት ጠላትና እንቅፋት እየሆነ ስለሄደና ሕዝብን እየጎዳ ስለሆነ ብርታትና ጥንካሬው ለአገርና ለሕዝብ እድገት ሲባል ይፈለጋል፡፡ ጠንካራና ብቁ የሆኑት ባለሥልጣናት ይበልጥ ተጨምረው ይቀጥሉ፡፡ ብልጣ ብልጥ ስግብግብ ዳተኛና ግድየለሽ የሆኑት ባለሥልጣናት ደግሞ እንዳይቀጥሉ ይደረግ፡፡ ለዚህ ሁሉ የጥበብ መጀመሪያ ውስጥን መፈተሽ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |