|
Sunday, 30 March 2008 |
|
የዝምባቡዌ ኘሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ውጤት ቢሸነፉ የአመፅ እንቅስቃሴ እንዳያካሂዱ ማስጠንቀቃቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ኘሬዚደንት ሙጋቤ ተቃዋሚዎች የምርጫ ውጤቱን ተከትሎ ህገወጥ እንቅስቃሴ እንዳያካሂዱ አስጠንቅቀዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዋርጋን ዲያንግሪያ "ሙጋቤ ምርጫውን የማጭበርበር እንቅስቃሴ ጀምረዋል" በማለት ወንጅለዋል፡፡ ዳያንግሪያ "ምርጫውን ማሸነፍ በሀገሪቱ ተቀባይነት ማግኘት ማለት አይደለም" ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የኘሬዚደንቱ ተቃዋሚ የሆኑት የቀድሞው የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ሲንባ ማኮኒ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመገንባት ከአሥር ዓመት በላይ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው "የሙጋቤ መንግሥት ሀገሪቱን ለመምራት ብቁ አይደለም" ብለዋል፡፡ ሲንባ የሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት አንድ መቶ ሺ በመቶ በላይ መድረሱን ገልፀዋል፡፡
ኘሬዚደንት መጋቤ በበኩላቸው የምርጫው ውጤት ሲገለፅ ተቃዋሚዎች በኬንያ የተካሄደው ዓይነት የተቃውሞ አመፅ የሚያስነሱ ከሆነ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስ አስጠንቅቀዋል፡፡ በዚህም "ተቃዋሚዎች አመፅ የሚያስነሱ ከሆነ አንታገሳቸውም" ብለዋል፡፡
* * *
ሰሜን ኮርያ የሚሳኤል ሙከራ አደረገች
ሰሜን ኮርያ ያለፈው ሀመስ የአጭር ርቀት ሚሳኤል ሙከራ ማድረጓን የደቡብ ኮሪያ የዜና አገልግሎትን በመጥቀስ አሶስየትድ ኘሬስ ዘገበ፡፡
በዘገባው መሠረት በሀገሪቱ ምዕራባዊ የባህር ዳርቻ የሚሳኤል ሙከራ ተካሂዷል፡፡ የደቡብ ኮርያ ኘሬዚደንት ቃል አቀባይ ቼንግ ዋዴ የሰሜን ኮርያ የጦር መሳሪያ ሙከራ ሰላማዊ ወታደራዊ ልምምድ ይመስላል" በማለት ገልፀዋል፡፡
ዘገባው ሰሜን ኮሪያ በርካታ የሚሳኤል ተኩስ ማድረጓን አመልክቷል፡፡ ቼንግ ዋዴ ደቡብ ኮሪያ በሚሳኤል ሙከራው ተቃውሞ እንደሌላት ገልፀዋል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች የሰሜን ኮርያ የሚሳኤል ሙከራ በኮርያ ባህረ ሰላጤ ያለውን የጦር መሳሪያ እሽቅድድም ያባብሰዋል ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሰሜን ኮርያ የኒውክሊየር መሳሪያዎችን ለማምከን በጀመረችው እንቅቃሴ ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥር ተሰግቷል፡፡
* * * የባግዳድ የሰዓት እላፊ አዋጅ ዛሬ ይጠናቀቃል
በባግዳድ በሺአ ሚሊሻዎችና በኢራቅ የደህንነት ኃይሎች መካከል ሰሞኑን የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማብረድ በከተማዋ የታወጀው የሰዓት እላፊ አዋጅ ዛሬ የሚጠናቀቅ መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡
በዘገባው መሠረት ካለፈው ሀሙስ ጀምሮ የታወጀው የሰዓት እላፊ አዋጅ ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡ አዋጁ ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ለመጠበቅ ሲባል በሀገሪቱ መንግሥት ታውጇል፡፡ በሺአ ሚሊሻዎችና በኢራቅ የደህንነት ኃይሎች መካከል በባዝራ ከተማ ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ ሲሆን ከአንድ መቶ ሰላሳ በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፡፡
* * * በቲቤት የመነኩሴዎች አመፅ ቀጥሏል
በቲቤት የሚገኙ መነኩሴዎች የቻይናን አገዛዝ በመቃወም የሚያካሂዱት ተቃውሞ አለመርገቡን የአሶሲየትድ ኘሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡
በቲቤት የሚገኙ መነኮሳት የቻይናን አገዛዝ በመቃወም እንዲሁም የዳይላ ላማን መሪነት በመደገፍ ተቃውሞ ሰልፍ እያካሄዱ ነው፡፡ በአመፁ አሥራ ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል፡፡ የአሜሪካ ኘሬዚደንት ጆርጅ ቡሽ ቻይና ከቲቤት መንፈሳዊ መሪ ዳይላ ላማ ጋር ውይይት እንድታካሂድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ |