| ተከታታይነት አለው |
|
|
| Sunday, 30 March 2008 | |
|
የአቶ ዳንኤል በቀለና ነፃነት ደምሴን የይቅርታ ጥያቄ በሚመለከት ረቡዕ እለት የተዘገበው ዜና ጥሩ ነው፡፡ ከቀድሞ ጀምሮ የታሠሩ የቅንጅት አመራሮችን የፍርድ ሂደት በሚመለከት ከተሠሩ ዜናዎች ጋር ግንኙነት ያለው በመሆኑ የዜናዎችን ተከታታይነት ያሳያል፡፡
በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ ዜናዎች መሠራት ለሕብረተሰቡ መረጃ በመስጠት በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ (ሳሌምታፈሰ፣ ከፈረንሳይ) ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ማበብ በወርሀ ሚያዚያ የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ውስጥ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ገዢውና የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ መገናኛዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በተከታታይ እትሞቹ በሪፖርተር ጋዜጣ እንደተረዳነው የምርጫ መንገዱ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች አልጋ በአልጋ አልሆነም፡፡ ብዙ ችግሮች በምርጫ ቦርዱም ሳይቀር እያጋጠማቸው መሆኑ ቢነገርም ቦርዱ ማስተባበያ እንደሰጠ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ በቀና ልቡና ቢመለከተው ለአገሪቱ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ማበብ ይረዳል፡፡ አሊያም ኘሮፌሰር ክላፋም እንዳሉት “ኢትዮጵያ ውስጥ በመርህ ደረጃ መድበለ ፓርቲ፣ በተጨባጭ ግን የአንድ ፓርቲ የበላይነት የነገሠባት አገር” ሆና እንዳትቀር ስጋት አለኝ፡፡ ለዴሞክራሲያዊው ምርጫ ገለልተኛ ተቋማት ብቻ ሳይሆን በመገናኛ ብዙኀን ፍትሐዊ ፉክክር እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ (ዮሐንስ ተክሉ፣ ከሳር ቤት) መሸፋፈን አያስፈልግም ባለፈው ረቡዕ በወጣው ጋዜጣ በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ አነጋጋሪ ሆኗል የሚለውን ዜና አንብቤዋለሁ፡፡ በየእለቱ በተለያየ ሰዓት መብራት መጥፋቱ የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡ በዜናው ላይ እንደተመለከተው የሚመለከታቸው ኃላፊ በአንድ በኩል የፈረቃ ኘሮግራም እንዳልተጀመረና የኃይል ችግር እንደሌለ በሌላ በኩል የኃይል መቋረጡ እስከ መጪው ክረምት መግቢያ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ መብራት በፈረቃ መጀመሩ ቢነገረን በኤሌክትሪክ በሚሠሩ እቃዎቻችን ላይ ጥንቃቄ እንድናደርግ ያስችለናል፡፡ ሆኖም ፈረቃ አልተጀመረም ብሎ መከራከር የሚታይ እውነትን መሸፋፈን ይሆናል፡፡ (ሩት፣ ከሳሪስ) ዘገባችሁ ተዘረፈ፣ ተጭበረበረ ብቻ ሆነ ብሔራዊ ባንክ የ156 ሚሊዮን ብር ወርቅ እንደተጭበረበረና የፌዴራሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዳረጋገጠ፤ በሕዝብ ግነኙነት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አሰፋ የተሰጠውን አስተያየት በሪፖርተር ጋዜጣ እሁድ መጋቢት 14 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ስመለከት እጅግ ገርሞኛል፡፡ ምክንያቱም የሰሞኑ ዜና ይህን ያህል ብር ተጭበረበረ ተዘረፈ ተረጋገጠ የሚል ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ፍርዱስ መቼ ይሆን? ጥፋተኞች እንደጥፋተኝነታቸው በሕጉ መሠረት ፍርዳቸውን እንደሚያገኙ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በየደረጃው መነገር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ አሁንም ግን ስለፍርዱ እየሰማን አይደለምና ተዘረፈ፣ ተጭበረበረ እንደሚለው ዘገባችሁ ስለፍርዱ ሂደት መዘግየትም ምክንያቱን በመከታተል አሳውቁን፡፡ (አበበ ላቀው፣ ባምቢስ) ጥቁር ገበያ አትበሉ ጀምስ ብራውን፣ "Say it loud, I am Black & I am Proud" ብሏል፡፡ ነጮች ከረዥም ጊዜ ጀምረው መጥፎን ነገር በጥቁር ነው የሚጭኑት፡፡ ሕገ ወጥ የሆነውን ንግድ (የገንዘብ ልውውጥ) ጥቁር ገበያ፣ በጥቁር ሄደ፣ በጥቁር ነው የሚሠራው፣ የሚለውንና ሌላም ማለት ይቻላል የእነሱ አቀራረብ ሆኖ ሳለ እናንተም በጥቁር ገበያ የሚለውን ስትጠቀሙ ሳይ እጅግ አዘንኩ፡፡ ሕገ ወጥ ገበያ፣ በሕግ ያልታወቀ ወዘተ እያላችሁ ብታቀርቡትስ? (በዛብህ ዘለቀ፣ ከሲያትል-አሜሪካ) የተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚና ምን ሊሆን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በሚያዚያ ወር በሚካሄደው ምርጫ የገዢው ፓርቲ በሰፋ ልዩነት እንደሚያሸንፍ ገልፀዋል፡፡ ለዚህም ገዢው ፓርቲ የቅድመ ምርጫ ሁኔታዎችን ለራሱ በሚመች መልኩ ማሰናዳቱን በመግለፅ ምርጫው ከወዲሁ ተጭበርብሯል ብለዋል፡፡ ተቃዋሚዎች ምርጫው የተጭበረበረ መሆኑን እያወቁ በምርጫወ መሳተፋቸው ጠቀሜታው ግልፅ አይደለም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ያለመሳተፍ መብታቸውን ተጠቅመው ከምርጫው እራሳቸውን ቢያገሉ የተሻለ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ምርጫ ሳይኖር ምርጫ ተካሄደ ከሚባል ገዢው ፓርቲ ብቻውን ተወዳድሮ አሸነፈ ቢባል ይሻላል፡፡ (አቡሽ ብርሃኔ፣ ከልደታ) በአግባቡ የሰራ ማርካቱ አይቀርም መጋቢት 17 በወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ ፖለቲካ አምድ ላይ አቶ ተስፋዬ መንገሻ ከምርጫ ቦርድ “የምርጫ ቦርድ ገለልተኛነት በፓርቲዎች እርካታ የሚለካ አይደለም” ብለውናል፡፡ ለምን? ተብለው ለተጠየቁትም የሚለካው ሥራን በአግባቡ በመወጣትና ባለመወጣት እንደሆነ ደስኩረውልናል፡፡ በአግባቡ ሥራውን የሰራ ደንበኞቹን ማርካት ተቀዳሚ ዓላማው መሆኑን ነበር የምናውቀው፡፡ በአቶ ተስፋዬ መርህ ግን አንድ ድርጅት ደንበኞቹ እየተከፉም በአግባቡ ሥራውን ይሰራል ልክ እንደ እሳቸው ምርጫ ቦርድ፡፡ (ሙከመር ሐሚድ፣ ከወሎ ሰፈር) የሕክምና አገልግሎቱ ይሻሻል በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አንድ የሞቱ ግለሰብ ለህክምና መጠራታቸውን የሚያትት ዜና በቅርብ በወጣ ጋዜጣችሁ ላይ አንብቤያለሁ፡፡ የህክምና አገልግሎቱ ጉዳይ እያደር አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ወረፋ በመጠበቅ ሳምንታትን አሳልፈን የሚረባ ህክምና ሳናገኝ ሌላ ቀጠሮ የሚሰጠን ታካሚዎች ቁጥራችን ቀላል አይደለም፡፡ ሃኪሙ አልገባም፣ ለሻይ ወጥቷል እየተባለ የሚመላለስ ታካሚ ቁጥር በዝቷል፡፡ አገልግሉቱ እንዲሻሻልና መዳን እየቻለ የሚቀጠፈው ህይወት እንዲድን የሚመለከተውን አሳስቡልን፡፡ (ጫላ በቀለ፣ ከተክለሃይማኖት) ማረሚያ “አይ ኤስ ኦ 9000 የጥራት ማረጋገጫ ወይስ የጥራት ጭምብል?” በሚል ርዕስ በእኔ የምለው ገጽ በወጣው ጽሑፍ የመጀመሪያው አንቀጽ፣ “ዓለም አቀፍ የደረጃዎች ድርጅት በምህፃረ ቃል አፃፃፍ አይሶ ማለት ሲገባው” አይ ኦ ኤስ በሚል ተስተካክሎ እንዲነበብ እንጠይቃለን፡፡ (ከዝግጅት ክፍሉ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |