Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow “ተፈትኖ እየወደቀ ያለው ሰላማዊ...
“ተፈትኖ እየወደቀ ያለው ሰላማዊ... Print E-mail
Sunday, 30 March 2008
Image“ተፈትኖ እየወደቀ ያለው ሰላማዊ ትግሉ ሳይሆን ትግሉ ውስጥ ያለን ሰዎች ነን”
አቶ ልደቱ አያሌው

አቶ ልደቱ አያሌው የኢዴአፓ-መድህን ፓርቲ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በመጪው ሚያዚያ በሚካሄደው የማሟያና የአካባቢ ምርጫ፣ በኑሮ ውድነት እንዲሁም ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ የማነ ናግሽ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዓመት የሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ሆኖም በተለይ ኢዴፓ መድህን ቀዝቀዝ ብሏል፡፡ ፓርቲው የሚወዳደረውም ለተሳትፎ ብቻ ነው?

አቶ ልደቱ፡- እኛ አይደለንም የቀዘቀዝነው ፣ የቀዘቀዘው ሂደቱ ነው፡፡ በእኛ በኩል ከሌሎች የቅንጅት አባል ድርጅቶች ጋር ልዩነት ሲፈጠር ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ስሜትና ሁኔታ እንዳይፈጠር ነበር ስጋታችን፡፡ ሆኖም ተፈጥረዋል፡፡ ዛሬ ከሶስት ዓመት በፊት የነበረው ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ የማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡  በአብዛኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ላይ ከፍተኛ የሆነ የመዳከም ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ በእርግጥ ሂደቱ ውስጥ ያለን የፖለቲካ ኃይሎችም የፈጠርነው ስህተትና ችግር አለ፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ በቂ የሆነ ተወዳዳሪና የውድድር ስሜት ሳይኖረን አጋንነን ብናቀርበው ጥቅም አይኖረውም፡፡ ያቀረብናቸው ዕጩዎች ለተሳትፎ በሚመጥን ቁጥር ነው፡፡ በዚህ ምርጫ 99.9 በመቶ ኢህአዴግ እንደሚያሸንፍ አስቀድሞ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ሆነን ጠንካራ ፉክክር ውስጥ እንዳለን አድርገን መናገሩ ትክክል አይሆንም፡፡

በትክክል አሁን ያለንበት ሁኔታ በቂ ውድድር ለማድረግ ያላስቻለን ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የተዳከምን እንደሆነ ከዚህ ወጥተን ወደ ተሻለ አቅጣጫ ለመሄድ በግልፅነት እውነቱን መናገር አለብን፡፡ የተዳከምን መሆኑንና ትግሉ የተጎዳ መሆኑን ሕዝቡ ማወቅ አለበት፡፡ ይህንን አውቆ ነው ሕዝቡ በቁጭት ተነሳስቶ ትግሉን ሊያጠናክረው የሚችለው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምርጫ 97  ቅንጅት ከሕዝቡ ላገኘው ድጋፍ የእርስዎ አስተዋጸኦ ከፍተኛ እንደነበር ሲነገር ነበር፡፡ (ከቀድሞ) ከቅንጅት ከወጡ በኋላ ግን ሕዝቡ እንደከሀዲ ያይዎታል፡፡ ይሄ የሚያሳየው ሕዝቡ ለእርስዎ የነበረው ድጋፍ የቅንጅት አመራር በመሆንዎ ነው ወይስ ለእርስዎ ግለሰባዊ የፖለቲካ ብቃት?

አቶ ልደቱ፡- በእርግጥ ከቅንጅት ግለሰብ ሊወጣም ሊገባም አይችልም፡፡ የቅንጅት አባላት ድርጅቶች ናቸው፡፡ ኢደአፓ መድህን ነው በወቅቱ ከቅንጅት የተለየው፡፡ ልደቱ እንደወጣ ተደርጎ የሚወራው ነገር ስህተት ነው፡፡ ሁልጊዜ በተቃዋሚ ዙሪያ ድጋፍ የሚሰጥ ህብረተሰብ ምን ዓይነት አስተሳሰብ፣ መርህና ራእይ እንዳለን ሳያውቅ ኢህአዴግን በመቃወማችን ብቻ የሚደግፈን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የህብረተሰብ ክፍል በእኛና በኢህአዴግ መካከል ስለአለው አንድነትና ልዩነት ጠንቅቆ አያውቅም፡፡ በተቃዋሚዎች መካከል ልዩነት ተፈጠረ ተብሎ ሲሰማ ከፍተኛ የሆነው መደናገጥና ውዥምብር ውስጥም ገብቷል፡፡ ሁለተኛው፣ በተቃዋሚ ጎራ ውስጥ ያለው ሰው ሁሉ እንደ ሃቀኛ፣ ትክክለኛና እንደ አገር ወዳድ ሰው የመቁጠር ስሜትና ባህሪ በከፍተኛ ደረጃ አለ፡፡ በተለይ ደግሞ በተቃዋሚዎች ጎራ በኃላፊነት ያሉት ሰዎች ትንሽ የተማሩ የሚመስሉ ከሆነ እነሱን ከማድነቅም አልፎ የማምለክም ባህል አለ፡፡ ከእኛ አቋም በተፃራሪ ያለውን አቋም ያራመዱ ሰዎች በዕድሜያቸውና በትምህርታቸው የገፉ ስለነበሩ ከእኛ ይልቅ እነሱ ትክክል ናቸው ብሎ የማመን ባህሪ ነበር፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ ተሳስተዋል፡፡ መሳሳቱ ደግሞ ከምንናገረው በላይ ሂደቱና የሰዎቹ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ያሳየው ይመስለናል፡፡ በእኛና በእነሱ መካከል በነበረን የሃሳብ ልዩነት፣ የማን አቅጣጫና ሃሳብ ትክክል እንደነበር፣ የተቃዋሚዎች ጎራ ወደዚህ ዓይነቱ የዘቀጠ ደረጃ የወረደ በማን ጥፋት እንደሆነ ሕዝቡ አሁን ጠንቅቆ የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ የእኔ የመወደድና የመጠላት ጉዳይም በዛ ውዥምብር ውስጥ የመጣ ነው፡፡ ዓላማየንና አቋሜን በአግባቡ ሳይረዱ የተቃዋሚ መሪ በመሆኔ ብቻ ይደግፉኝ የነበሩ ሰዎች በውል አያውቁኝም ነበርና ጠልተውኛል፡፡ በአግባቡ ደግሞ የተረዱኝ ሰዎች የድሮ ፍቅራቸው አሁንም እንዳለ እምነቴ ነው፡፡ ጠልተውኝ የነበሩ ሰዎች ደግሞ በትክክል ማንነቴን እየተረዱ ሲመጡ ወደ መውደድ ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በተፈጠረው ቀውስ አንድ አዲስ ባህል የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚደግፈውን ሰው የሚመዝንበት መስፈርት የተለየ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በሀብት፣ በዕድሜ፣ በትምህርት ሰርትፍኬት ሳይሆን በትክክል ለአገሪቱ ያለው ራእይና አመለካከት ይደገፋል ወይም ይነቀፋል ብዬ አምናለሆ፡፡ እንዲህ ዓይነት ባህል ለመፍጠር ያሳለፍነው ሂደት ትልቁ ተሞክሮ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ትግሉ አብቅቶለታል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ በነፍጥ እንጂ በምርጫ ስልጣን አይለቅም ይላሉ፡፡ የእርስዎ እምነት ምንድን ነው?

አቶ ልደቱ፡- የሰላማዊ ትግል ምንነት ካለማወቅ የመነጨ ይመስለኛል፡፡ ምን ያህል መስዋዕትነት ይጠይቃል፣ ምን ያህል እልህ አስጨራሽ ትግል እንደሆነ ሳይገነዘቡ አንድ መሰናክል ሲገጥማቸው ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ስለዚህ በሰላማዊ ትግሉ ሂደት እነሱ እራሳቸው ውድቀት ይደርስባቸውና በሰላማዊ ትግሉ የደረሰ ውድቀት አድርገው የቆጥሩታል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈትኖ እየወደቀ ያለው ሰላማዊ ትግል አይደለም፡፡ ትግሉ ውስጥ የተቀላቀልን ሰዎች ነን፡፡ አንዳንድ ሰዎች ውጭ አገር ሆነው ሰላማዊ ትግሉ አልሰራም ይላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሽሽት መንገድ ነው፡፡

ካለው አጠቃላይ ሁኔታ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው በሰላማዊ ትግል ብቻ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ የትጥቅ ትግል የተዘጋ አማራጭ ነው ብለን እናምናለን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢህአዴግ ስልጣን ይለቃል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ግን እንዲዘጋጅ ማድረግ እንችላለን፡፡ ኢህአዴግን ስልጣን ስንይዝ እናሳይሀለን፣ እንበቀልሀለን እያልን በዚያ መጠን ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲያደርግ መጠየቅ እርስ በርሱ የሚጣረስ ነው፡፡ ስለዚህ ከበቀል የፀዳ የፖለቲካ ባህል ካሳየነው ለዘለዓለም ስልጣን ይዤ እቆያለሁ ብሎ የሚታገል አይመስለኝም፡፡ ፅንፈኛ የሆነ የፖለቲካ አቅጣጫ ይዘን አንዳችን ሌላችንን ጠላት አድርገን ፖለቲካ እንሰራለን በምንልበት ሁኔታ ግን ኢህአዴግ ስልጣን እንዲለቅልን መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተቃዋሚ የመፈረካከስ አደጋ ሲገጥመው አንዱ ቡድን በሌላው ላይ በወያኔነትና በከሃዲነት የመፈረጅ አዝማሚያ ይታያል፡፡

አቶ ልደቱ፡- የተቃዋሚዎች ትልቁ ጠላት አሉባልታ ነው፡፡ እስከአሁን በኢትዮጵያ የተቋቋሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያዳከመው ይኸው ነው፡፡ አሉባልታ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ራሱን የቻለ አንድ ባህል ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ አንዳቸው በሌላው ላይ የበላይነት ለመጎናፀፍና ለመጣል አሉባልታ ማስወራት እንደትልቅ መሳሪያ ነው የሚታየው፡፡ ስለዚህ ይሄ አዲሱ ትውልድም ከዚህ ዓይነቱ መጥፎ በሽታ ገና ያልተላቀቀ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በሂደት ሊፈታ ይችላል፡፡


ሌላው ችግር በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ልዩነት ሲፈጠር ልዩነቱ አግባብ ባለውና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ የሃሳብ እጥረት ሲኖርባቸው አቋራጭና ቀላሉ መንገድ አሉባልታን ማውራት ነው፡፡ የፈጠራ ወሬ አስወርቶ ወደ ህብረተሰቡ በማዳረስ የሰዎችን የፖለቲካ ተክለ ሰወነት መግደል ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ኃላፊነት የሚሰማቸው ነፃ መገናኛ ብዙሃን ሲፈጠሩና ለህብረተሰቡ እውነታውንና ሚዛናዊ የሆነውን መረጃ ማስተላለፍ ሲችሉ የአሉባልታ ጉልበት የሚሰበር ይመስለኛል፡፡ አስከ አሁን በነበረው ሁኔታ ግን አንዳንድ ፕሬሶች ራሳቸው የአሉባልታው ሰለባዎች ስለሆኑ ችግሩን ሲያባብሱት እንጂ ሲፈቱት አልታዩም፡፡ ስለዚህ በሂደት ከህብረተሰቡ የንቃተ ህሊና ጋራ፣ ከመገናኛ ብዙሃን ዕድገትና በአጠቃላይ የፖለቲካ ባህላችን ጋር ..እየተለወጠ የሚመጣ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ከቅንጅት በወጡ ወቅት በእርስዎ ላይ ሲባል ለነበረው አስተያየት ሕዝቡ እውነታውን ሲያውቅ ወደ እኔ ይመለሳል ሲሉ ነበር፡፡ ሕዝቡ ተመለሰ ወይስ?

አቶ ልደቱ፡- ፍጥነቱ ምን ያህል ነው የሚለው ለ..ጠያይቅ ይችላል፡፡ አንዳንዱ ኃላፊነት የሚሰማቸው ጥቂት የግል ጋዜጦችና ሚዲያዎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ስርጭታቸው በጣም ጠባብ ነው፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ አንድ ነገር በአግባቡ ለመረዳት በአጭር ጊዜ አይችልም፡፡ ከዚህ አንፃር ብዙ ሰዎች በተቃዋሚ ጎራ ምርጫውን ተከትሎ የነበረውን እውነት ለመረዳት ብዙ ጊዜ ፈጅቶባቸዋል፡፡ ለአንዳንዶቹ ወደፊትም ተጨማሪ ጊዜ ሊፈጅባቸው ይችላል፡፡ ያም ሆኖ ግን ነገሩን ቆም ብሎ በሰከነ መንፈስ የመመርመር ሁኔታ እንዳለ እያየን ነው፡፡

በእኛ ላይ ሲወራ የነበረው ነገር ምን ያህል ሀሰት እንደሆነ ህብረተሰቡ አሁን በገሃድ እያየ ነው፡፡ ይህን አሉባልታ ያወሩ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች እነማን እንደሆኑ፣ ማንነታቸውም ምን እንደሆነ ይበልጥ በሂደት እያየ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ የቱንም ያህል ሃቁን ቢሰማና ቢያይ ለመረዳትም ራሱን ያላዘጋጀ ነው፡፡ ጭፍን ጥላቻ ያለበት፣ የሚያስበውና የሚፈልገወን ነገር ብቻ እንዲሆን የሚፈልግ የህብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ እሱን ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- ይሁን እንጂ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ኢዴአፓ-መድህን ከኢህአዴግ ጋር የሚመሳሰል አመለካከት ሲታይበት ይስተዋላል፡፡ ይሄ በፊት የነበረውን ..አሉባልታ.. እውነት አያስመስለውም?

አቶ ልደቱ፡- ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ኢትዮጵያ ውስጥ በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቱዎች መካከል ያለው ልዩነት የእኛን ጨምሮ በጣም ሰፊ ነው፡፡ በኢህአዴግና በኢዴአፓ-መድህን መካከል መሠረታዊ የሆኑ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የአስተሳሰብ  ልዩነቶች አሉ፡፡ በህገ መንግሥት ደረጃም የሚገልፁ ልዩነቶች አሉን፡፡

በአንዳንድ ጉዳዮች ግን ተቀራራቢ አስተሳሰቦች የለንም ማለት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ገዢው ፓርቲ የሚሰራቸው ሥራዎች ሁሉ በአንድ ላይ ጨፍልቆ መጥፎ አድርጎ የማቅረብ፣ ከገዢው ፓርቲ ምንም ጥሩ ነገር እንደሌለ አድርጎ የማየት እንደ ጥሩ የተቃዋሚነት ሚና ነው ሲታይ የነበረው፡፡ ከዚህ አንፃር በኢህአዴግ የተሰሩ ጥሩ ነገሮች ደግፈን ስንቆም ህብረተሰቡ ከዚህ ከነባሪው ባህል ጋር እየተጋጨበት ሲደናገጥና የተሳሳተ ትርጉም ሲሰጥ እናያለን፡፡ ይሄ የህብረተሰባችን አጠቃላይ የፖለቲካ ባህል ችግር ነው፡፡ ኢህአዴግ ጥሩ ነገሩን እያበረታታን መጥፎውን ደግሞ እንተቸዋለን፣ እንቃወመዋለን፣ እንታገለዋለንም፡፡ በጭፍን ኢህአዴግ የሰራውን ነገር ሁሉ መጠፎ አድርጎ ማቅረብ ለአገርም ለሕዝብም የማይጠቅም ጎጂ ባህል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የኑሮ ውድነቱን አስመልክተው በቅርቡ ለፓርላማ ያቀረቡት ሪፖርት አለ፡፡ ችግሩን ለመፍታት እናንተስ ምን ያህል ተንቀሳቀሳችኋል?

አቶ ልደቱ፡- በመሠረቱ በሪፖርቱ የቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ እጅግ የዘገየ ነው፡፡ አንደኛ ይሄ የመፍትሄ ሃሳብ ኢዴአፓ-መድህን ማቅረብ የጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ነው፡፡ በቴሌቪዥን በተከራከርንበት ወቅት ተቀባይነት አላገኘም፡፡ እንደገና ከአንድ ዐመት በኋላ ነገሩ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ አጀንዳ አስይዘን ለፓርለማ ውይይት እንዲቀርብ አድርገናል፡፡ በፓርለማው ድምፅ ሲሰጥ ግን ሃሳቡን ውድቅ አደረገው፡፡ በፓርላማ ያቀረብናቸው የመፍትሄ ሃሳብ ናቸው አሁን መንግሥት ይህንን ችግር ለመፍታት ያስችለኛል ብሎ እየተከተላቸው ያሉት፡፡ ያለአግባብ ሁለት ዓመት ባክኗል ማለት ይቻላል፡፡ አሁንም በመፍትሄነት የተቀመጠው ነገር ጉድለት አለበት፡፡ አንደኛ፣ ገዢው ፓርቲ አጠቃላይ በኢኮኖሚ ውስጥ ግሽበቱ እያባባሰ ያለው ከፍተኛ የሆነው የገንዘብ መጠን ለመቀነስ ወሰድኩት ያላቸው “ጠንካራ” እርምጃዎች ኢህአዴግ እንደ አመነው የገንዘብ መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ጠንካራ እርምጃ ወስዶ ቢሆን ኑሮ ችግሮቹ ይወገዱ ነበር ወይም ቢያንስ ይቀንሱ ነበር፡፡

እኛም ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ያቀረብነውን መፍትሄ ኢህአዴግ አልተቀበለውም፡፡በገበያ ያለውን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ለመቀነስ ኢንቨስትመንት በተወሰነ ደረጃ አዝጋሚ መሆን አለበት፡፡ እየተገኘ ያለው የልማት ውጤት ቀጣይና አስተማማኝ እንዲሀን ከተፈለገ በአንድ ጊዜ አድጎ የሚንከታኮት ኢኮኖሚ ከመገንባት ይልቅ እያዘገመ ጤነኛ ሆኖ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት መገንባት ይመረጣል፡፡ ይሄ የመፍትሄ ሃሳብ ኢህአዴግ የፖለቲካ ጥያቄ አድርጎ ስለአየው አልቀበልም ብሏል፡፡ ማስተካከያዎች እስካልተደረጉ ድረስ ችግሩ በሌሎች መፍትሄዎች ብቻ ይቀረፋል ብሎ ማሰብ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡

ኢህአዴግ እነዚህን ውጤቶች እያሳየ የፖለቲካ ድጋፍና ተቀባይነት ከሕዝቡ ለማግኘት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን እያየው ያለው ከኢኮኖሚ አንፃር ሳይሆን ከፖለቲካ አንፃር ነው፡፡ ዕድገቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን እንዲንኮታኮት የሚያደርግ ከሆነ ኢህአዴግ የፖለቲካ ውድቀትም ይደርስበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ ተጨባጭ ሁኔታውን ምን ያህል ከግምት ያስገባ ነው? ተግባራዊነቱስ?

አቶ ልደቱ፡- በኑሮ ውድነቱ ለይ አሁንም መንግሥት ተቀባይነት ያላቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ተቀብሏል፡፡ ድጎማና የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በበቂ ሁኔታ እየተገበራቸው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ድጎማን ብናይ ስንዴ ለህብረተሰቡ እያቀረበ ነው፡፡ ግን ብቻውን መፍትሄ አይደለም፡፡ ስንዴ ለህብረተሰቡ ማቅረብ የኑሮ ውድነቱ በእንጀራና በዳቦ ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ብቻ ነው የሚረዳው፡፡ የኑሮ ውድነቱ ግን በወጥ፣ በትራንስፖርት፣ በአልባሳት፣ በቤት ኪራይም ላይ ተፈጥሯል፡፡ ድጐማው በመንግሥት እጅ ላይ ባሉ አገልግሎቶች እንደ ውሃ፣ ስልክ፣ መብራት መሳሰሉት ላይ ጊዜያዊ ድጎማ ማድረግ አለበት፡፡ ይህ በተወሰነ ደረጃ ህብረተሰቡን ሊያስታግሰው ይችላል፡፡

ሲሚንቶን በተመለከተ ሙገር የሲሚንቶ ፋብሪካ የመንግሥት ነው፡፡ ሙገር በነዳጅ ላይ ጭማሪ በተደረገ ቁጥር የሲሚንቶ ዋጋ ጭማሪ ያደርጋል፡፡ ሙገርን የመሳሰሉ የልማት ድርጅቶች በእጅ ይዞ ያቆያቸው የገበያ ቀውስ ሲፈጠር ለማረጋጋት ነው፡፡ ሆኖም ይህ አይታይም፡፡ በቅርቡ ሙገር 30 ብር ጭማሪ አድርጓል፡፡ ሆኖም እንደሌላ የንግድ ድርጅት ወጪ በጨመረበት ቁጥር ዋጋ መጨመር የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ወደ 112 የልማት ድርጅቶች በአንደኛ ደረጃ አትራፊ ነው፡፡ የሚሰራው የነጋዴ እንጂ የልማት ድርጅት ሥራ አይደለም፡፡ መንግሥት ይሄን እያደረገ በሲሚንቶ ያለው የዋጋ ንረት እቀንሳለሁ ማለት የሚያስኬድ አይደለም፡፡

በገበያ ውስጥ ህገወጥ የሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ ይኖራል የሚል ግምት አለኝ፡፡ በፍፁም በኢኮኖሚስቶች አስተሳሰብ ሊደረስበት የሚችል አልሆነም፡፡ መንግሥት እዚህ ላይ እርግጠኛ እንዳልሆነ ነግሮናል፡፡ “እንቅስቃሴ ውስጥ ህገወጥ ገንዘብ ሊኖር ይችላል ፣ እርግጠኛ ሆኜ የለም ማለት አልቻለም፡፡ ግን መጠኑ ይሄን ያህል የኢኮኖሚ ቀውስ ሊፈጥር የሚችል አይደለም” ብለዋል፡፡

ስለመኖሩና አለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ካልቻለ መጠኑን መገመት አይቻልም፡፡ መንግሥት ይህን አጥብቆ ሊከታተልና ሊፈትሽ ይገባዋል፡፡ በተለይ በአገራችን አሁን እየተከሰተ ያለውን ከፍተኛ የሙስና ሁኔታ ስናይ ህገወጥ የሆነ ገንዘብም ወደ ገበያው አልገባም ለማለት እቸገራለሁ፡፡

እድገቱም የፍትሃዊነት ችግር አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ 85 በመቶ የገበሬ ችግር የፈታ ዕድገት ስለሆነ የፍትሃዊነት ችግር የለበትም ብለዋል፡፡ ፍትሃዊነት የሚባለው የብዙሃኑን የጠበቀ የአነስተኛውን ከፍል የሚጎዳ አይደለም፡፡ ፍትሃዊነት የጥቂቱንም ሆነ የብዙሃኑን ጥቅም ተገቢ በሆነ መልኩ የሚፈታ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እየተደረገ ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ 85 በመቶ ገበሬውን ጠቅሞ 15 በመቶ የሆነውን ሸማቹ ህብረተሰብ ከጎዳ ይሄ የፍትሃዊነት ችግር አለበት፡፡ ፍትሃዊ እንዲሆን ከተፈለገ አምራቹም ሸማቹም በእኩል ተጠቃሚ መሆን አለበት፡፡
 
< Prev   Next >