Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የኅብረቱ ተዋጊዎች ለሰዓታት..
የኅብረቱ ተዋጊዎች ለሰዓታት.. Print E-mail
Sunday, 30 March 2008
የኅብረቱ ተዋጊዎች ለሰዓታት ከተቆጣጠሯትጆሃር ከተማ ተባረሩ
-በሶማሊያ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ አንዣቧል

የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ተዋጊዎች ባለፈው ረቡዕ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚደገፈውን የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወታደሮችን አጥቅተው የጆሃርን ከተማ ለተወሰኑ ሰዓታት ተቆጣጠሩ፡፡
የጆሃር ከተማ እስካአሁን ድረስ የእስልምና ፍርድ ቤቶች ኅብረት ተዋጊዎች ከተቆጣጠሯቸው ከተሞች ሁሉ በጣም አስፈላጊዋ ናት ብለዋል፡፡ እንደ ሮይተርስ ዘገባ በውጊያው ሕጻናትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከአፍሪካ ህብረት ወታደሮች እገዛ እየተደረገለት እንኳን ሀገሪቱን የመቆጣጠር አቅሙ ውስን መሆኑን ያሳያል ነው የሚሉት ተንታኞች፡፡

የእስልምና ፍርድ ቤት ኅብረት ወታደሮች የአካባቢውን አስተዳደር ሚሊሻዎች ካባረሩ በኋላ ከተማዋን ለተወሰኑ ሰዓታት የተቆጣጠሯት ሲሆን የሽግግር መንግሥቱና የኢትዮጵያ ወታደሮች ደርሰው እንዳስወጧቸው ሮይተርስ ይፋ አድርጓል፡፡

የፍርድ ቤቶች ኅብረት ተዋጊዎች ባለፉት 15 ወራት ውስጥ 6..500 የሚሆኑ ሰዎችን መግደላቸውን የጠቀሰው ዘገባው፣ ከሞቃዲሾ 90 ኪ.ሜ በስተ ሰሜን ርቃ የምትገኘውንና በ1997/98 የሽግግር መንግሥቱ መቀመጫ የነበረችውን ጆሃርን ከማጥቃታቸው በፊት አራት ትንንሽ ከተሞችና ለሞቃዲሾ ቅርብ የሆኑ ወታደራዊ ካምፖችን ተቆጣጥረው ነበር፡፡

ከውጊያው በኋላ የእስልምና ኅብረት ወታደሮች ጆሃርን ሲቆጣጠሩ ሰባት ሰዎች ተገድለው ማየቱን የገለፀው የከተማዋ ነዋሪ የሆነው አብዲ አሊ ኡስማን ከእነዚህ ውስጥ አንዲት የሽግግር መንግሥቱ ወታደር የነበረች ሴት ሞታ አይቻለሁ በማለት የዓይን ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ እንደ አብዲ ምስክርነት ከሆነ የእስልምና ፍርድ ቤቶች ኅብረት ታጣቂዎች በከተማዋ የነበሩ እስረኞችንም አስለቅቀዋል፡፡

የፍርድ ቤቶቹ ኅብረት ቃል አቀባይ አብዱራሂም አሊ አዶ በበኩሉ አራት የመንግሥት ወታደሮች በጥቃቱ እንደሞቱ ተናግሯል፡፡ “ወታደሮቻችን ከጧቱ 12 ሰዓት ነው ጀሃር የደረሱት፡፡ ጥቂት የመንግሥት ወታደሮች ቢዋጉንም በማሸነፍ እንዲሸሹ አድርገናቸዋል” በማለት በስልክ ለሮይተርስ ካልታወቀ ቦታ ተናግሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሞቃዲሾ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የመርካ ከተማን የሽግግር መንግሥቱ ወታደሮች በኢትዮጵያ ወታደሮች በመታገዝ ካለፈው እሁድ ጀምሮ መልሰው መያዛቸውን የአካባቢው ሽማግሌዎች ተናግረዋል፡፡

“የመንግሥት ወታደሮች እኛን ጠሩንና ለደህንነት ጉዳይ እንደ መጡና  የአልሻባብ ታጣቂዎች ከተማዋ ውስጥ እንዳሉ ሰምተው እንደሆነ ነገሩን” በማለት መሐመድ ኩሌ የተባሉ የአባቢው ሽማግሌ በስልክ ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡ አልሻባብ በአሜሪካ መንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀና ከአልቃዒዳ ጋር ግንኙነት ያለው ቡድን ተደርጎ እንደሚወሰድ ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል የቀድሞዋ ቅኝ ገዥ ጣሊያን ረቡዕ ዕለት 10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለፖሊስ ኃይል ማሰልጠኛና ለሌሎች የመንግሥት ተቋማት ማጠናከሪያ መርዳቷን የአፍሪካ ኅብረት አስታውቋል፡፡ ሶማሊያ የዚያድ ባሬ መንግሥት እ.ኤ.አ በ1991 በጦር አበጋዞች ከፈረሰበት ጊዜ አንስቶ መንግሥት መመስረት ተስኗት እርስ በርሳቸው በሚቆራቆሱ ኃይሎች እየተተራመሰች ነው፡፡ ያሁኑ የሽግግር መንግሥትም መሻሻሎችን እንዳያደርግ የፖለቲካ እና ታጣቂ ሃይሎች ፋታ እያሳጡት ነው፡፡

የሶማሊያ እስልምና ፍርድ ቤቶች ኅብረት ተዋጊዎች የሽምቅ ውጊያን በተጠናከረ መልኩ በሽግግር መንግሥቱ ላይ እንደሚቀጥሉና ነገር ግን የሲቪል ተጠቂዎችን ቁጥር በሚቀንስ መልኩ እንደሚሆን ባለፈው ሐሙስ ገልፀዋል፡፡

የምግብ እጥረትና ያለመረጋጋት ሶማሊያን ከፍተኛ ወደሆነ ሰብዓዊ ቀውስ እያመራት እንደሆነ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሱ አርባ ያህል የእርዳታ ድርጅቶች ውጊያውያን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ አሳስበዋል፡፡ እንደ እርዳታ ድርጅቶቹ፣ ሶማሊያ የሚገባትን ያህል ትኩረት ካላገኘች ወደ ማትቋቋመው ሰብዓዊ ቀውስ ታመራለች ብለዋል፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት ሐሙስ እለት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የተመድ ዋና ፀሐፊ ባንኪሙን ባቀረቡት ፕሮፖዛል ላይ ተወያይቷል፡፡ በፕሮፖዛሉ 27,000 ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በሶማሊያ ለማሰማራት ታቅዷል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት መሠረት በየወሩ 20,000 ሰዎች በእስልምና ፍርድ ቤቶች ኅብረት ወታደሮችና የሽግግር መንግሥቱን በሚደግፉ የኢትዮጵያ ወታደሮች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎችን በመፍራት ዋና ከተማዋን ሞቃዲሾን እየለቀቁ ይሰደዳሉ፡፡

በተለይ በደቡባዊ ሶማሊያ ሕይወት አዳጋች እየሆነ ነው፡፡ ከአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች ምግብ ማቅረብ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች በየቀኑ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የአለም አቀፍ እርዳታ ድርጅት የኬር ሰራተኛ የሆኑት ቢ ስፖዲኪኒ ገልፀዋል፡፡ ከሞቃዲሾ በ16 ኪ.ሜ ዙሪያ 250,000 ተፈናቃዮች ይገኛሉም ብለዋል፡፡  

ይህ ሁሉ ችግር ያለባት ሶማሊያ በእጅጉ ተረስታለች የሚለው ደግሞ የሰብዓዊ መብቶች ተንከባካቢ (Human Right Watch) ባልደረባ የሆነው ላስኮው ነው፡፡ የፀጥታ ምክር ቤቱ ሁሉም አካላት የኢትዮጵያ ወታደሮችን ጨምሮ በጣም አደገኛ ጥፋት እያጠፉ እንደሆነ አምኖ መቀበል አለመቻሉ አስገራሚ ነው እንደላስኮው፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው አሜሪካና እንግሊዝ በዚህ ጉዳይ ላይ የችላ ባይነት ይታይባቸዋል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ሶማሊያን መታደግ የሚፈልግ ከሆነ የመጀመሪያው እርምጃ በሶማሊያ ያሉ ሁሉም አካላት ለችግሩ ተጠያቂ እንደሆኑ ማመን ነው፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ተንከባካቢ ድርጅት እንደሚለው፣ የፀጥታው ምክር ቤት በሶማሊያ የተካሄዱትን ወንጀሎችንና ተጠያቂ ግለሰቦችን የሚለይ የመርማሪ ኮሚሽን እንዲያቋቁም ይፈልጋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረትንና የኢትዮጵያ ወታደሮች ይተካሉ የተባሉት የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች ይህን ሁኔታ የሚያሻሽሉት ሥራቸው ሲቪሎችን መጠበቅ ከሆነ ብቻ ነው፡፡

የኬር እርዳታ ድርጅት ባልደረባ የሆነው ቢ በፓንዲሲኒ የሚስማማበት  አሁን በሶማሊያ አንገብጋቢው እና ቶሎ መፍትሄ ሊፈለግለት የሚገባው የሰብዓዊ ቀውሱ ሁኔታ ስለሆነ ውይይቶችና እርምጃዎች ሁሉ በአፋጣኝ በዚህ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ነው፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር
 
< Prev   Next >