Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ድሬዳዋስ?
ድሬዳዋስ? Print E-mail
Wednesday, 09 January 2008

ድሬዳዋ ከኢትዮጵያ ታላላቅ ከተሞች አንዷ ነች፡፡ የኢትዮጵያን የከተሞች የደረጃ ምደባ ይፋ አድርጎ አውጥቶ የገለፀ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር የታወቀ የደረጃ ሰንጠረዥ ባላውቅም፣ በሕይወት ልምድ እንደምናውቀውና እንደምንረዳው ከኢትዮጵያ ታላላቅ ከተሞች መካከል አንዷ ብቻ ሳትሆን ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ድሬዳዋ የሁለተኛውን ደረጃ ትይዛለች፣ ይዛለች ብሎ መገመት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ጊዜ ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው ወይም አገራችን ውስጥ በሚዘጋጀው ለምሳሌ እንደ እግር ኳስ  ያለ ውድድር ጨዋታዎች ይካሄዱ የነበሩት በአዲስ አበባና በአስመራ ስታዲየም እንደነበር እናውቃለን፡፡ ዛሬ ታሪክ ሆኖ የሚነገረውም የሚዘገበውም ይህንኑ ነው፡፡ ከዚህም በላይ አስመራ የኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ከተማ እየተባለች በትክክል ትጠራ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ከሦስት አስርት ዓመታት ጦርነት በኋላ መጨረሻ ላይ በሰላምና ኤርትራውያን ብቻቸውን በሰጡት ውሳኔ ሕዝብ /ሪፈረንደም/ የተፈታው በዚህም መሰረት ኤርትራን ነጻ አገር /ባንዲራ የሚያውለበልብ አገር/ ያደረገው ጉዳይ እንኳንስ በአስመራና በአዲስ አበባ መካከል በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከልም ያልታሰበ ውዝግብ፣ ጭቅጭቅ ከዚያም አልፎ እንደገና ጦር ያማዘዘ ግጭት የፈጠረ የፈጠረውም ችግር አሁንም ገና እልባት ያላገኘ ከነዚህም ችግሮች መካከል አንዱ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የድንበር መስመር ውሳኔ ያላገኘ መሆኑ ነው፡፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እንደገና በተፈጠረው ሌላውና አዲሱ ችግር ውስጥ በተለይም ከዚያኛው ወገን በኩል ከርሮና ጎልቶ የሚታይ አንድ ቢኖር እንኳንስ አስመራ ከአዲስ አበባ፣ ኤርትራም ከኢትዮጵያ በስልጣኔ ትበልጣለች የሚለው ነው፡፡ ይህንን በ1990ዎቹ ውስጥ በነበረው በተለይም በመጀመሪያው አፍላ ወቅትና ከዚያም በኋላ ባለው ቀጣይ ጊዜ በሰማነው ጉራ ድንፋታ አይተነዋል፡፡ ይህንን ቁም ነገር ብሎ ለሚሰማ ጉዳዩን ለማያውቅ ባዶ አስመራ የኢትዮጵያ ሁለተኛ ከተማ አልነበረችም ብሎ የእግድ አለዚያም የአላዋቂ ብይን ሊሰጥ ይችላል፡፡ ሌላው ቢቀር አዲስ አበባ የአገሪቱ ርዕሰ ከተማ ነበርና አዲስ አበባን ከምንለው ደረጃ የሚነቀንቀው ምንም ምክንያት የለም፡፡ ድሬዳዋ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ያለውን ቦታ የወሰደችው እንግዲህ በዚህ ምክንያትና በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንደሚባለው በዲፎልት ነው እንጂ፣ በሌላ የመቅደም ሮጦ በልጦ የመገኘት አዲስ ሪከርድ የመስበር ምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም ድሬዳዋ በእድገት በመደበኛውና ሌላው የኢትዮጵያ ክልል ክፍል በአንጻራዊነት በሚጓዝበት ጎዳና እየሄደች ነወይ ቢባል መልሱ እምብዛም አዎንታዊ አይደለም፡፡

ድሬዳዋ ከአምስት ዓመት በፊት 100ኛውን የቆረቆረችበትን ዘመን፣ ዛሬ 2000 ላይ ደግሞ አንድ መቶ አምስተኛ ዓመቷን አክብራለች፡፡ የክብረ በዓል /የአንቨርሳሪ/ የታወቀና ሁሉም ቦታ የፀደቀ ልምድና ባህል፣ ወግና ሕግ ያቋቋመው አሰራር እንደሚያሳየው አንድ መቶኛው የድሬዳዋ የምስረታ ክብረ በዓል ይበልጥ ክብርና ሞገስ የሚገባው በሆነ ነበር፡፡ በአንጻራዊነት ገዝፎና ጎልቶ የመገናኛ ብዙሃንን ከፍተኛ ትኩረት ስቦ የአገሪቷ ርዕሰ ብሄርና ርዕሰ መስተዳድር በአካል በተገኙበት የተከበረው ግን 105ኛው ክብረ በዓል ነው፡፡ የድሬዳዋን አንድ መቶ አምስተኛ ክብረ በዓል ከ100ኛው /ከአንድ ምዕተ ዓመቱ/ የልደትና የምስረታ በዓል ልዩ የሚያደርገው ለሁሉም ጉዳይና ለእያንዳንዱ ነገር እንደሚባለው ይህ በዓል የሚሌንየሙ የመጀመሪያው የከተማዋ ክብረ በዓል በመሆኑ ነው የሚል መልስ የምናገኝ ስለመሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ድሬዳዋ ግን የተመሰረተችበትን የአንድ መቶኛ ዓመት ከአምስት ዓመት በፊት አስታውሳ ያለፈችው አሁንም የአንድ መቶ አምስተኛ የልደት በዓሏን ያከበርነበት ሌላው የልማት የእድገት ወይም የመልካም አስተዳደር ነገር ቢቀር በአገሪቷ ሕገመንግሥታዊ ማዕቀፋ ውስጥ መደበኛውንና ሕገመንግሥቱ አላት የሚለውን ቦታ ሳታገኝ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ከሽግግር ወቅቱ ጊዜ ጀምሮ የሽግግር መንግሥቱን ብሄራዊ የክልላዊ መስተዳድሮች ለማቋቋም በወጣው የ1984 ዓ.ም ሕግ መሰረትም ሆነ ከዚያ በኋላ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የአገሪቷ የበላይ ሕግ በሆነው በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት እንደተወሰነው ድሬዳዋ የአንዱ ወይም የሌላው ክልል አካል እንጂ የብቻ ህልውና ያላት ግዛት አይደለችም፡፡ ድሬዳዋ ወደ የክልል አራት አለዚያም የክልል አምስት አካል እንጂ የ1984 ዓ.ም የብሄራዊ ክልላዊ መስተዳድሮችን ያቋቋመው፣ በወቅቱ ሕገመንግሥት አካል ደረጃ የነበረው ሕግ ከአስራ አራቱ የአገሪቱ ክልሎች ውጭ አስራ አምስተኛ አድርጎ ያቋቋማት በጭራሽ አልነበረችም፡፡ አሁንም በስራ ላይ ባለው ሕገመንግሥት የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ለዘጠኝ የፌዴሬሽኑ አባላት ክልሎች ሲከፋፈል ድሬዳዋ እንደ አዲስ አበባ የፌዴራል ግባት ሳትሆን ወይም እንደ ሐረር የከተማ መንግሥት /ሲቲ ስቴት/ እንድትሆን ሳይወሰን ወይ በኦሮሚያ ወይ የሶማሊያ ክልል አካል ናት ተብሎ በዚህ ታሳቢ የተተወች ናት፡፡ ሕገመንግሥቱ ከአገሪቱ ርዕሰ ከተማ በስተቀር እሱንም በእቅድና ሆን ተብሎ በታሰበበት ዓላማና ግብ የፌዴራል ግዛት አድርጎ ከመወሰን በስተቀር ድሬዳዋንም እንደ ድሬዳዋም የግዛት የአለኝታ ጥያቄ የተነሳባቸውን ቦታዎች ሁሉ የአዲስ አበባ ዓይነት ቦታና ሁኔታ ይሰጥ ዘንድ አይጠበቅበትም፤ አይገባውም፡፡

የድሬዳዋ ችግር ምንድነው? የድሬዳዋን ችግር መፍታት ያላስቻለው የሕገመንግሥቱስ ችግር ምንድነው? የድሬዳዋ ችግር መጀመሪያ ከሽግግሩ መንግሥትና ከብሄራዊ ክልላዊ መስተዳድሮች መቋቋም ጀምሮ በክልል አራት /ኦሮሚያ/ እና በክልል አምስት /ሶማሌ/ ክልሎች መካከል የተነሳው ድሬዳዋ የኔ ናት የአለኝታ ጥያቄ ነው፡፡ ከ87 ዓ.ም በኋላም ይኸው የአለኝታ ጥያቄ መፍትሄ ሳያገኝ ባለበት ቀጠለ፡፡ ችግሩ እነሆ አስራ ስድስተኛ ዓመቱ ውስጥ ይገኛል፡፡ ከሕገመንግሥቱ መጽደቅ በፊት የነበረው ሕግም ሳይቀር ይህንን ዓይነት የአለኝታ ጥያቄም እፈታበታለሁ የሚለው የመፍትሄ ዘዴ አስቀምጦ /ቢያንስ ቢያንስ አለን ብሎ/ ማለፍ አልቀረም ነበር፡፡ ከዚያ በላይ ግን የዚህ አይነት ችግር እንደሚኖር ከወዲሁ አውቃለሁ ብሎ የሕግ አሰራርና የሥነ ሥርዓት እንዲሁም የተቋም የመፍትሄ ስልት በእርግጠኛነት አለን ያለው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡

አንቀጽ 39ኝን የመሰለ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ አገርም የሚታወቅ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ የሚዘልቅ /የመብትና የነጻነት/ ድንጋጌ የያዘ ሕገ መንግሥታት በእርግጥም ይህን ከቁጥር ማስገባት ይሳነፋል ተብሎ የሚገመት አልነበረም፡፡ ስለዚህም እንዲህ ያለ በአጎራባች ክልሎች መካከል የዳር ድንበር ጥያቄ ቢነሳ በተለይም እንደ ድሬዳዋ ያለ አንድ ከተማን የሚያክል የአለኝታ ጥያቄ በሁለት ክልሎች መካከል ቢያወዛግብ መጀመሪያ ክልሎች በመካከላቸውና እርስ በርሳቸው በውይይትና በመግባባት እንዲፈቱት ይህ ሳይቻል ከቀረ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን /በዳኝነት/ አይቶ ውሳኔ እንዲሰጥ ወይም በውሳኔ ሕዝብ ሕዝቡ የገዛ ራሱን ጉዳይ በገዛ ራሱ እንዲወስን እንዲያደርግ ሕገመንግሥቱ ባለመብት ያደርገውን አሰራር ደንግጓል፡፡ ጉዳዩም የሚያልቅበት ጊዜ በሕገ መንግሥቱ ተወስኗል፡፡

የድሬዳዋ ችግር ግን እስከ አሁን መፍትሄ አላገኘም፡፡ ቻርተሩ በድሬዳዋ ከተማ ያስገኘው አወንታዊ ለውጦች በሚል ርዕስ አዲስ ዘመን ታህሳስ 28 ቀን 2000 ዓ.ም በፖለቲካ ገጹ  ባወጣው ጽሁፍ፣ የድሬዳዋ ከተማ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አንስተውት በነበረው የይገባኛል ጥያቄ አለመግባባት ተፈትቶ ከተማዋ ለረጅም ዓመታት ሌሎች ክልሎች ያገኙትን ሁለንተናዊ ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷን፣ ህብረተሰቡም ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት በአግባቡ ማግኘት ያልቻለበት ሁኔታ ታይቶ እንደነበር፣ ሆኖም በከተማ ያሉት የልማት ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ይሰጡ ዘንድ በ1988 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የወጣው መመሪያ መኖሩ እንደሚታወስ ይህንን መሰረት በማድረግም የፌዴራል መንግሥት ድሬዳዋ ራስን በራስ እንድታስተዳድር የሚያስችላት በ1996 ዓ.ም እንዲፀድቅ መደረጉን ገል..ል፡፡ ከዚህም በመነሳት ቻርተሩ በድሬዳዋ ከተማ ያስገኘውን አወንታዊ ለውጦች ያላቸውን ጽፏል፡፡ ቻርተሩ ግን ድሬዳዋ 100 አመቷን በቆጠረችበት በ1995 ዓ.ም ላይና በማግስቱ ለውይይት በቀረበበት ጊዜና በራሱ በቻርተሩ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው አገር በሰፊው ሕገመንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ለድሬዳዋ ችግር የሰጠው መፍትሄ ሳይሆን ከዚያ ውጭ ሆኖ ቢቸግረው ዘየድኩት ያለው ጊዜያዊ መፍትሄ ነው፡፡ ድሬዳዋ የኦሮሚያና የሶማሊ ክልሎች ችግራቸውን በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ፈትተው ሊስማሙ ባለመቻላቸው አለዚያም ጉዳዩ ሕገመንግሥቱ አበጀሁትና አመቻቸሁት ባለው አሰራር ውስጥ አልፎ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይም በራሱ የድሬዳዋ ሕዝብ ውሳኔ ሊፈታ ባለመቻሉ ከዋናውና ድሬዳዋን ካጋጠማት ችግር ይልቅ የችግሩ መፍትሄ በመጥፋቱ ችግሩ ሕገመንግስታዊ ችግር ሆኗል፡፡

የድሬዳዋ ችግር የራስ እደል በራስ በመወሰን መብት ዞሮ ዞሮ ይፈታል እንኳን እንዳይባል፣ የድሬዳዋ የማንነት የኦሮሚያ ወይስ የሶማሊያ? የሚለው ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በዚህ ዙሪያ የበቀለ ነገር ግን ራሱን ከዋናው ችግር ነጻ ያወጣ የሚመስል ሌላ ድሬዳዋ የትኛዋ ናት የሚልም ችግር ተፈጥሯል፡፡ ከዚህም የተነሳ በቅርቡ ለዜና በበቃ የአንድ ጋዜጣ ዘገባ መሰረት በጊዜያዊው ቻርተር የሚተዳደረው በድሬዳዋ መስተዳድር እና በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር መካከል ከመሬት ልማትና ቤት መስሪያ ቦታ ምሪት አኳያ አለመግባባት የፈጠረ ችግር ተነስቷል፡፡ የዚህ መንስዔ ወይም መገለጫ የኦሮሚያ ክልል ወይም የሶማሊያ ክልል ድሬዳዋ የኔ መሆኗ ቢቀር የድሬዳዋ የሚባለው ከተማ ወደ እኔ ሊሰፋና ሊስፋፋ አይገባም ከሚል በመነጨ መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡ ዘገባውም የሚገልጸው ይህንኑ ነው፡፡ ይህ እውነት ከሆነና አንዱ ወይም ሌላው ክልል ለብቻው /እርስ በርሱ ከሚወዛገብበትና መፍትሄ ሳያገኝ እስከ አሁን ከዘለቀው ችግር በተጨማሪ/ ከድሬዳዋ መስተዳድር ጋር የድንበር ውዝግብ ብቻ የሚያስነሳ ከሆነ ድሬዳዋ የትድረስ ናት የሚለው ጥያቄ ተጨማሪ ችግር ይሆናል፡፡ እንዲህ ያው ብዙ ቦታ የሚታየው ችግር ደግሞ የኢትዮጵያ ብቸኛ መገለጫ የሆነውን አንቀጽ 39 ተፈፃሚነትም ያስናክላል፡፡

በድሬዳዋና በአዲስ አበባ መካከል ጥቂት ተመሳሳይነት ቢኖርም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ያላቸው ችግር ግን የየብቻና የተለያየ ነው፡፡ አዲስ አበባን አንዴ ፈርዶባት ሕገ መንግሥቱ ምናልባትም ሳይቸግረው አዲስ አበባ የምትገኘው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው ብሎ አርፎታል፡፡ ድሬዳዋ ግን እንደ አዲስ አበባ ወይም እንደ ሐረር በአንዱ ወይም በሌላው ክልል ውስጥ ብቻ የምትኖር ደሴት አይደለችም፡፡

ያም ሆኖ ግን የድሬዳዋ ችግር መፈታት ያለበት ከተማዋ የየትኛው ክልል ነች በሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ብቻ ሳይሆን የድሬዳዋ የራሱ ዳር ድንበር ከኦሮሚያም ሆነ ከሶማሊያ አኳያ በውልና በድንበር ሲበጅ ነው፡፡ መልካም መስተዳድር የመጀመሪያው መነሻ፣ የጥበብ መጀመሪያ፣ የአገር ወይም የግዛት ሥልጣን የሚዘረጋበትን ስፍራ ማበጀት መካለል ነው፡፡

 
< Prev   Next >