|
Sunday, 30 March 2008 |
 አቶ አብዱልፈታህ አብደላ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መጻሕፍት ተቋም (ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ) በመጋቢት የመጀመሪያ ሳምንት አዘጋጅቶት በነበረው ዐውደ ርዕይና ሽያጭ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ አንዱ ደራስያንና ተርጓሚያን ከሥራዎቻቸው ጋር በማቅረብና ከታዳሚዎች ጋር በማገናኘት የውይይት መድረክ ማመቻቸቱ ነበር፡፡
ከ100 ዓመት በፊት በወለኔ ሸክ ዑመር በሽር በዓረብኛ ቋንቋ ተጽፎ የኖረውን "ጥሮነ - የኢትዮጵያ ቀደምትና ታላላቅ ዑለማዎች ታሪክ" በአንድ የትርጉም ቡድን አማካይነት ወደ አማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ቀርቧል፡፡ በዐውደ ርዕዩ የውይይት መድረክ ላይ አዘጋጁ አቶ አብዱል ፈታህ አብደላ ስለ መጽሐፉ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
መጽሐፉ በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች አንደኛው ስለ ሐበሻና ሐበሻን ልዩ ስለሚያደርገው ሁኔታ፣ መልክዐ ምድሯን፣ የሕዝቦች ሁኔታ ሲገልጽ፣ ሁለተኛው በአፄ ምኒልክና በኢማም ሐሰን አንጃሞ መካከል የተፈጠረውን የፖለቲካ ግጭትና ጦርነትን ይተርካል፡፡
ኢማም ሐሰን ከአዲስ አበባ ደቡብ የሚገኙትን ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ወለኔ፣ ቀቤና ይመራ የነበረውን የአካባቢው መንግሥት የጦርና የፖለቲካ መሪ ነበሩ፡፡
ጸሐፊው ሸክ ዑመር በወቅቱ በሕይወት የነበሩና በሁለቱም ወገን ለ14 ዓመታት የተካሄደውን ትግል ካዩት አንፃር ሲተርኩ፣ በሦስተኛው የመጽሐፉ ትኩረት በጊዜውና ከዚያ ቀደም የነበሩትን ኢትዮጵያውያን የሙስሊም መሪዎችና ምሁራን ታሪክ ተንትነውበታል፡፡
ከሙስሊሙ ዓለም ሐበሻን ልዩ የሚያደርገውን 12 ነጥቦች መጽሐፉ ይዘረዝራል፡፡ እንደ ወለኔው ሼክ መግለጫ የሐበሻ መልክዓ ምድር ሰፊ ግዛትን ያካለለ ነው፡፡
"ጨዋማ ባሕር ከሆነው የሐበሻ ክፍል አንስቶ ሂጃዦች እስከ ነጩ ባሕር ያዋስኑታል፡፡ ርዝመትዋም ከኮፈር መጨረሻ እስከ ሕንድ መዳረሻ ድረስ ያለው ነው፡፡ ይህም አብዱራህማን ኾጀሌ የተባሉት ሰው አገር ድረስ ይዘልቃል፡፡ በዚህም ሁኔታ ሱዳን ከፊሏ ከሐበሻ ሲሆን፣ ከፊሏ ደግሞ ከመግራብ (ሰሜን አፍሪካ አገሮች) እንደሆነ ያሳያል፡፡ . . .የሐበሻ ምድር ስፋትዋ ሦስት ወርና ቁመትዋም ሦስት ወር ያህል የሚያስኬድ ነው፡፡"
ሐበሻን ከዓለም ሁሉ የሚለየው የመጀመሪያ ነጥብ ነቢዩን ያጠባን መሆናችን ነው ይላሉ፡፡ እንደ አቶ አብዱልፈታህ ማብራሪያ ዑሙ አይመን በረከተለ ሀበሻ የተባለች ሴት ከአባታቸው ከአብደላህ የወረሷት ስትሆን፣ ተወርሳ በመሄድ ነቢዩ መሐመድን ያጠባች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቡሰይሪ የተባለው ዓሊም "ሀምዚያ" በተባለው ግጥም ላይ እንዳስቀመጠው ዑሙ አይመንም ለነቢዩ አጥቢያቸው እንደሆነችና ክብሯም "የሰማይ ያህል የሰፋ" እንደሆነ ገልጾታል፡፡ የነቢዩ ጋቢ ጉዳይ ጠቅሶ የሐበሻን ታላቅነት፣ ጀግንነትና የጦር ኃያልነት በዚያ ጊዜ ሳይቀር የታወቀና ነገራቸው ሁሉ ጠንቃቃነት የተሞላበት እንደሆነ አሳውቋል፡፡
ሁለተኛውንም ጉዳይ ሲያስቀምጡ "ዐረቦች ላይተናኮሉን ነቢዩ ማዘዛቸው ያም "ሐበሾችን ሳይነኳችሁ አትንኳቸው" መባሉ ለሌላ አገር ያልተሰጠ፣ ኢትዮጵያ የተከበረችበት ነው፡፡ በ7ኛው ምእት ዓመት የነቢዩ ስደተኞችን ሐበሻ ማስጠለሏ፣ አሕመድ ነጃሺ ኢስላምን መቀበሉ የዘረዘሩት አቶ አብዱልፈታህ የመላው ዓለም ሙስሊሞች ጸሎት ለማድረስ የሚያሰሙት አዛን ከሐበሻው ቢላል የተገኘ መሆኑ ገልጸዋል፡፡ ቢላል ከጉራጌ ወገን መወለዱን የወለኔው ሼኽ ዑመር በሽር በሚከተለው መልኩ ገልጸውታል፡፡
"እንደሚባለው ቢላል ከጉማ (ከጅንጅር) እንደሆነ ይነገራል፡፡ እነቆር የሚባል ቦታ በሄድኩ ጊዜ ሙጎ የምትባል ገጠር ደረስኩ. . .ሙጃጅ በተባለ ሥፍራ በአንዲት ለየት ባለች ዛፍ ሥር የተሰበሰቡ ሰዎችን ተመለከትኩ፡፡ ዛፍዋም በወለኔ የምትገኝ"ስትሆን፣ ቦታዋ ቢላል ኢብ ኑረባህ የተወለደባት ናት፡፡"
ከሐበሻ የታላቅነት መገለጫዎች አንዱ የዓባይ ወንዝ ምንጭ ከኢትዮጵያ መሆኑን የገለጸው ሐታታ ዓባይ በሰማያትም ላይ እንደሚፈስ ተጽፎለታል፡፡ ኢስማኢላል "ሩሁል በያን" በተባለው ኪታቡ ውስጥ ዓባይ በጀነት ዛፎች ሥር የምትፈስ እንደሆነች ከገለጸ በኋላ ከሐበሻ አልፋ ለምስር (ግብጽ) ሰዎች የሕይወታቸው ምሰሶ እንደሆነችም አስፍሯል፡፡
በዱሮ ጊዜ ውሃው በሚቆምበት ወቅት ከሴት ልጆቻቸው ቢክር (ልጃገረድ) የሆነችዋን በመምረጥ ለውሃው ይወረውሩለት ነበር፡፡ በዓባይ ወንዝ ቦታ ላይ ጂኖች ሥልጣን በመያዝ ማንም ሰው እንዳይቀርብ ባደረጉበትና ጥቃት በመሰንዘር ባስቸገሩበት ወቅት ዙልቀርነይ የተባለ ሰው የጫት ተክል በማምጣትና በመትከል ጂኖችን የማባረሪያ መድኃኒት አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡ አነቃቂውና መድኃኒትነት ያለው በዓባይ አካባቢ ያለው ጫት እንደሆነ ይታመንበታል፡፡
ጸሐፊው ሼኽ ከማምነው ሰው የሰማሁት የጫት ዜና ብለው የጠቀሱት ነጥብ አለ፡፡ "አንድ ቀን አንድ ሰው በጂን ከተወሰደ በኋላ ወደጂኖች ስብሰባ ቦታ አቀረበው፡፡ ሰውየውን ይዞ እንደመጣ አሳይቶአቸው ሳይጨርስ በደስታ ሁሉም ሊቀራመቱት መጠጋት ጀመሩ፡፡ ሲጠጉትም ይዞት የነበረው የጫት ሽታ ሲያገኛቸው እየተሯሯጡ ለማምለጥ ሩጫ ገቡ፡፡ ይህ ሰው በጨርቁ ጫፍ ላይ ጫት ቋጥሮ ይዞ ነበር፡፡ ጠልፎ የወሰደውም ጂን ይህንን ሲያይ ሰውየውን ከጠለፈበት ቦታ መልሶ ለማምለ"ጥ ችሏል፡፡"
"ጥሮነ" በዐሥራ ዘጠኝ ምዕራፎች ርእሰ ጉዳዮች የቀረቡበት ነው፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ በቤተ ጉራጌዎች አካባቢ በ19ኛው ምዕት በአካባቢው ገዢዎችና በማዕከላዊው መንግሥት መካከል የተደረጉ ግጭቶችና ጦርነቶች ከነርሱ ዓይን ተዘግቧል፡፡ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የነበሩ የታላላቅ ሰዎች የቤተ ጉራጌ ታላላቅ ዑላማዎች ታሪክ የሸክ ኑር ሁሴን፣ የኢማም አሕመድ (ግራኝ) ታሪኮች፣ የዝነኞቹ የሴት መሻኢኮች ታሪክ ተካትቷል፡፡
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ላጵሶ ጌታሁን ድሌቦ እንደገለጹት መጽሐፉ የወሎ፣ የወለኔ - ገደባኖ፣ የጉራጌ፣ የቀቤና፣ የስልጤ፣ የመስቃን፣ የሐረር፣ የጅማ፣ የባሌ. . .ዑላማዎች ገድልና ትምህርት ሌላ በዘመኑ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎችና መንገዶች የተነሱ የአገር፣ የመንግሥት፣ የጦርና የሃይማኖት መሪዎችንና ባለሥልጣኖች በተለይ የአፄ ዮሐንስን፣ የአፄ ምኒልክን፣ የኢማም ሀሰን አንጃሞን፣ የኢማም ዑመር በቅሳን፣ የዑመር ፋርዳን፣ የዓሊ ደነቦን፣ የራስ ጎበና ዳጨው፣ የራስ ወልዴ አሻገርን፣ የሱልጣን ጅማ አባ ጅፋርን፣ የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን፣ የእቴጌ ጣይቱን፣ የልጅ ኢያሱን፣ የንጉሥ ሚካኤልን፣ የንግሥት ዘውዲቱን፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴንና የሸዋ ጦር አበጋዞችን አንፃራዊ ፖሊሲና ተግባር በልዩ ልዩ መንገድና ደረጃ በዐረብኛ ሰነድ ቀርጾ ለታሪክና ለትውልድ ያቆየ ባለውለታ ዓሊም ነው፡፡
በውይይቱ ሂደት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ፈቃደ አዘዘ፣ ሁልጊዜ አንድ ድምጽ እየሰሙ መኖር እንደማይቻልና ሁሉም ድምጽ መሰማት እንደሚገባው ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ ውስጥና በውጭ አገር ያሉ መረጃዎችን ማሰባሰብና በአንድ ማዕከል ውስጥ ማስቀመጥ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ አያይዘውም በሕዝብና በሕዝብ መካከል የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ግጭት እየፈጠሩ ለመጠቀም የሚፈልጉትን መረጃዎች ሲወጡና ዕውቀት ሲሆኑ ወጣቱ ትውልድ እየተማረ እያሰበ ይሄዳልና እየተካሄደ ያለው ጥረት እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡ በሔኖክ ያሬድ |