|
Sunday, 30 March 2008 |
"ለምን ይዋሻል?" ሠይፉስ ለምን ይዋሻል?የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ጉዳይ የሚያጠነጥነው በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በሚተላለፈው የሰይፉ ፋንታሁን "ለምን ይዋሻል?" ፕሮግራም ነው፡፡
"ለምን ይዋሻል?" የተሰኘውን ፕሮግራም አላማ ለማወቅ የግድ ከአዘጋጆቹ ማብራሪያ መጠየቅ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ አላማው ግልጽ ነው፡፡ "እውነትን ተናግሮ ከመሸበት ማደር እየተቻለ ለምን መዋሸት አስፈለገ?" ለማለት ነው፡፡ ዓላማው መልካም ነው፡፡ መልካም የሚሆነው ግን የሌላውን ጉድፍ ከማጋነን በፊት የራሳቸውን ቆሻሻ ለመንቀስ በሚችሉ ሰዎች የተያዘ እንደሆነ ነው፡፡ ማንም ራሱን ከቅጥፈት ሳያፀዳ የሌሎችን ውሸት በመናገሩ ብቻ ንጹህ አይሆንም፡፡ ትችታችን ገንቢና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ከፈለግን በመጀመሪያ እኛ ራሳችን ንጹህ፣ እውነተኛና በጎ አሳቢ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ ወይም ራሳችብ በሂስ "ፀበል" መንከር አለብን፡፡ ራሳችን እየዋሸን፣ ራሳችን እየሰረቅን፣ ራሳችን እያምታታን ሰዎችን ህጸጽ የለሽ እንዲሆኑ ከፈለግን መሳቂያ እንሆናለን፡፡
ሰይፉ ፋንታሁን በሰሞኑ ሲያስተላልፈው በነበረው "ለምን ይዋሻል?" ፕሮግራሙ ላይ ታዋቂውን ድምጻዊ ቴዲ አፍሮን "ዜማ ሰርቀሃል" በሚል ተደጋጋሚ ትችት አቅርቧል፡፡ ሰይፉ የዜማ ስርቆትን የሚጠላ ይመስል፣ የሌላውን ሃሳብና ሥራ የማይቀዳ ይመስል፣ ሌሎችን ብቻ ሲያሳጣ ሰንብቷል፡፡ ሰይፉስ የሌሎችን ፈጠራ አይሰርቅም?
ቴዲ አፍሮ ዜማ ሰርቆ ከሆነ አይተች የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሰይፉ ሌሎችን አርቲስቶች ለምን አጋለጠ አልልም፡፡ ያጋልጥ፡፡ ግን ራሱንም ይወቅ ነው የምለው፡፡ ያጋልጥ ግን በቅን መንፈስ ይሁን ነው የምለው፡፡ ወጣቱ አርቲስት ቴዲ አፍሮ በጥቂት አመታት ውስጥ የሰራቸው ዜማዎች እጅግ የሚያስደንቀውና ክብር የሚያሰጠው ቢሆንም፣ ስህተት ከሰራ ስህተቱ ሊነገረው ይገባል፡፡ በእርግጥ ቴዲ ጥቂት ዘፈኖችን ኮርጇል ተብሎ በመወራቱ ብቻ ከሙዚቃ አፍቃሪው ህዝብ ልብ በቀላሉ እንደማይወጣ አምናለሁ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ለረጅም ዘመናት ከአርቲስቶቻችን አጥተነው የነበረውን ለየት ያሉና ስሜት አነቃቂ የዜማና የግጥም ፈጠራ ችሎታ፣ ከዚህ ወጣት አርቲስት አግኝተናል፡፡ ዘፈኖቻችንን ከሴቶች ዳሌና ጭን አውጥቶ ለአገርና ለክብር መግለጫ እንዲሆኑ ማድረጉ ብቻ የተከበረ አድርጎት ይኖራል፡፡ በድል ስሜት ፈንድቀን ደስታችን የምንገልጽበት መንገድ ስናጣ በአንድ ቀን ዜማና ግጥም ደርሶ እንካችሁ ጨፍሩ ብሎ ያበረከተልንን ስጦታም አንረሳውም፡፡ አዲሱን የኢትዮጵያ ሚሌኒየም አስመልክቶ ቴዲ ባወጣው "አበባ አየሽ ሆይ" ዜማ መንግሥት ከታሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ እስረኞች ጋር ያወረደውን እርቅ አድንቆ አስጨፍሮናል፡፡ ዛሬ አንዳንድ ጋዜጦች ቴዲን ለማሳጣት ከሰይፉ ፕሮግራም ኋላ ሲያጨበጭቡ የምንሰማው ቴዲ አፍሮ በጥረቱ ያገኘውን ውዴታና ክብር ለመደርመስ የተባበሩትም ግላዊ "ጥላቻ" በፈጠረው ስሜት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ስለምወደው ብቻ ቴዲ ስህተት ሲሰራ መተቸት የለበትም የሚል አቋም የለኝም፡፡ ዜማ ኮርጆ ከሆነም በገንቢ መልኩ ስህተቱ ተገልፆለት ለወደፊቱ ከሰራው ስህተት የሚታረምበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ዜማ ኮርጇል የተባለውን ቴዲ አፍሮን የሚተቸው ግለሰብ እውነተኛና ቅን መሆን አለበት፣ ጥፋቴ አልታወቀም ብሎ በማሰብ ራሱ እየኮረጀ፣ ራሱ እየሰረቀ፣ ራሱ እየዋሸ ሌላውን ለመተቸት የሚነሳ ሁሉ ታዓማኒ ሊሆን አይችልም፡፡ ከመጀመሪያው አነሳሱ በጎ ባለመሆኑ ሰይፉ እንደሚለው ለሙዚቃችን ዕድገት አይረዳም፡፡ ለዚህም ነው ከላይ በርዕሱ ላይ "ሰይፉስ ለምን ይዋሻል?" ያልኩት፡፡ ከዚህ ድምዳሜ ላይ እንድትደርስ ያደረገህ ክስተት ምንድ ነው? ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ ምላሼ የሚከተለው ነው፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ሰይፉ ፋንታሁን "ይፈለጋል" የተሰኘ ፊልም ማሳተሙን ታስታውሳላችሁ፡፡ የሬዲዮ አስተናጋጁ ይህንን ፣ይፈለጋል፣ የተሰኘ ፊልም ለመስራት ከሁለትና ከሶስት አመት በላይ እንደፈጀበት ፊልሙ በወጣበት ሰሞን ገልጾ ነበር፡፡ ከአንድ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ አንዳንድ የኢትዮጵያ ፊልም አሳታሚዎች በጥቂት ሺህ ብር ያሳተሙትን ፊልም ሚሊዮን እንዳወጡበት አድርገው ማውራታቸው እንደሚያስገርመው የገለጸው ሰይፉ እርሱ ያሳተመው "ይፈለጋል" ፊልም አንድ ሚሊዮን ብር እንዳወጣ ተናግሯል፡፡ በሰይፉ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ብር የፈጀው ፊልም "ይፈለጋል" ብቻ ነው፡፡ ሚሊየን ብር ያወጣው የፊልሙ ደራሲ ሰይፉ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ "ይፈለጋል" ከሃሳብ እስከ ቃል የተኮረጀ በመሆኑ ያን ያህል የአእምሮ ድካም የለውም፡፡ የሰይፉን "ይፈለጋል" ፊልም የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች "ይህንን ፊልም የት ነው ያየሁት" የሚል ጥያቄ በጭንቅላታቸው እየተመላለሰ ከፊልም አዳራሽ ቢወጡ አይፈረድባቸውም፡፡ ፣ይፈለጋል፣ ከኢሜት ማርክ ፊልም የተኮረጀ መሆኑን የሚያስታውሱ ሰዎች ካሉ ደግሞ ትክክል ናቸው፡፡
የ፣ይፈለጋል፣ ጭብጥ እና ሴራ ሙሉ በሙሉ የተወሰደው እ.ኤ.አ በ2002 ከታተመው "ኢሜትስ ማርክ" ከተሰኘው ፊልም መሆኑን ያላያችሁት ካላችሁ ፊልሙን በማየት ማመሳከር ትችላላችሁ፡፡ በአንድ ሰዓት ልዩነት ውስጥ ሁለቱን ፊልሞች ("ኢሜትስ ማርክንና" "ይፈለጋልን") ቢመለከቱ ሁለት ፊልም ሳይሆን አንድ ፊልም ብቻ የተመለከቱ ሊመስልዎት ይችላል፡፡ በ"ይፈለጋል" ፊልም የተቀመጡት ገጸ ባህሪያትም ከኢሜትስ ማርክ ስለመወሰዳቸውም ቅንጣት ታህል አይጠራጠሩም፡፡ ኩረጃው ምን ያህል ገደቡን የጣሰ መሆኑን ለመገምገም ይረዳ ዘንድ የሁለቱንም ፊልሞች ምልከታ በአጭሩ እንመልከት፡፡
ኢሜትስ ማርክ በ፣ኢሜትስ፣ ማርክ ፊልም ውስጥ መርማሪ ፖሊስ ሆኖ የሚሰራው ኢሜት ያንግ በመታመሙ ህክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታል ይሄዳል፡፡ መርማሪው ፖሊስ ከሆስፒታሉ የተነገረው ውጤት ግን የሚያስደነግጥ ነበር፡፡ ከስንት ጊዜ አንዴ በሰዎች ላይ ይከሰታል በተባለ ድንገተኛ በሽታ መያዙንና በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚሞት፣ በሽታውም አሰቃይቶ እንደሚገድለው በሐኪሞች ይነገረዋል፡፡ ይህ አስደንጋጭ የምርመራ ውጤት የተነገረው ኢሜት ህይወት ጨለመችበት፣ ተስፋ መቁረጥ አንዣበበበት፡፡ በሽታው በጥቂት ሳምንት ጊዜ ውስጥ አሰቃይቶ እንደሚገድለው ማወቁም ሊቋቋመው የማይችለው ስቃይ ሆነበት፡፡ እጮኛው (ሳራ) "ጊዜህን ከእኔ ጋር አታሳልፍም፤ ምንም አይነት ትኩረት አልሰጠኸኝም" በማለት ጥላው ሄዳለች፡፡ ከችግር ላይ ችግር ተደራርቦበታል፡፡
ኢሜት ያንግ በዚህ ጭንቀት ውስጥ እያለ የቀድሞ መርማሪ ፖሊስ መሆኑን ከገለጸለት አንድ ግለሰብ ጋር ይገናኛል፡፡ ያጋጠመውን ችግር ለዚህ ሰውዬ ይነግረዋል፡፡ ኤሜት ያንግ በያዘው በሽታ ተሰቃይቶ እንደሚሞት የተረዳው ይህ ግለሰብም ከአሰቃቂ ሞት ለመገላገል በሚል ሃሳብ ከነፍሰ ገዳይ ጋር ሊያገናኘው ያግባባዋል፡፡
በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወቱን ማጣት ያልፈለገው መርማሪው ፖሊስም በሰውየው ሃሳብ በመስማማት በበሽታው ተሰቃይቶ ከመሞቱ በፊት በነፍሰ ገዳይ ለመገደል ይወስናል፡፡ ግድያውን ለሚፈጽሙ ነፍሰ ገዳይ ግማሽ ክፍያ ፈጽሞ ቀሪውን ክፍያ ደግሞ ከተገደለ በኋላ እንዲወስድ ይስማማሉ፡፡
መርማሪ ፖሊስ ኤሜት ያንግ ይህንን ስምምነት ከፈጸመ በኋላ ግን አንድ ያልታሰበ አስገራሚ ዜና ይሰማል፡፡ ሐኪሙ ስልክ ይደውልለትና የሌላ ሰው የምርመራ ውጤት በስህተት እንደተሰጠው፣ ህመሙም ለሞት እንደማይዳርገው ይነገረዋል፡፡ ኤሜት ያንግ በሰማው ዜና እጅግ ቢደሰትም ወዲያውኑ ግን ሌላ ጭንቀት ውስጥ ይገባል፡፡ ከነፍሰ ገዳዩ ጋር የተዋዋለው ስምምነት እረፍት ነሳው፡፡ በስምምነቱ መሰረት ነፍሰ ገዳዩ ባላሰበውና ባልጠበቀው ሰዓት ሊገድለው እንደሚችል ሲያስብ በጣም ተረበሸ፡፡ ወደ ነፍሰ ገዳዩ ደውሎ "እንድትገድለኝ የተስማማንበትን ጉዳይ ትቼዋለሁ፡፡ የሰጠሁህን ገንዘብ ውሰደው፡፡ አትግደለኝ" ቢለውም ነፍሰ ገዳዩ ፕሮፌሽናል መሆኑን ለመግለጽ ከመግደል እንደማይመለስና ክፍያውንም እንደሚወስድ ይነግረዋል፡፡
በስጋት የተወጠረው ኤሜት ያንግም ከሞት ለማምለጥ መሸሸግ ይጀምራል፡፡ በመጨረሻም ነፍሰ ገዳዩ ኢሜት ያንግ ወደ ተደበቀበት ቤት በመሄድ ሊገድለው ሲል ኤሜት ያንግ ነፍሰ ገዳዩን ቀድሞ በመግደል ራሱን ያድናል፡፡ (ፊልሙም በዚህ ይቋጫል)
"ይፈለጋል" "የይፈለጋል" ገጸ ባህሪ የሆነው ካሌብ አንዲት ልጅ ይወዳል፡፡ ካሌብ የሚወዳት ልጅ አባት ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ ሰይፉን ስለሚንቁት ልጃቸውን እንዲያገባ አይፈልጉም፡፡ አንተ መናጢ ነህ የእኔን ልጅ የምታገባው? በማለት ያጣጥሉታል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽን ያለው ካሌብ ለካምፓኒው ማስፋፊያ በሚል ከአራጣ አበዳሪ ገንዘብ ይበደራል፡፡ የተበደረውን ገንዘብም ይዞ ወደ ቤቱ ይሄዳል፡፡ በደስታ ብዛት ብሩን ከሻንጣ እያወጣ ይጨፍራል፡፡ የፈለግኩትን ላደርግ ነው እያለ ሲፈነድቅ በመሃል ስልክ ይደወልለትና ቤቱን ዘግቶ ይወጣል፡፡
ካሌብ ቤቱን ዘግቶ እንዳወጣ ወደ ቤት የመጣችው የቤት ሰራተኛ ብሩን አልጋ ላይ ተበትኖ ታያለች፡፡ እንዳይጠፋ በመስጋትም የዱቄት ማስቀመጫ ውስጥ ትደብቃለች፡፡ ብሩን ዱቄት ውስጥ ያስቀመጠችው ይችው የቤት ሰራተኛ መርዶ ይነገራትና ብሩን የት እንዳስቀመጠችው ለካሌብ ሳትነግረው ወደ ክፍለ ሀገር ትሄዳለች፡፡ ካሌብ ወደ ቤቱ ሲመለስ ብሩ የለም፡፡ ብሩን ባስቀመጠበት ቦታ ሲያጣው እንደተሰረቀ አመነ፡፡ ከአራጣ አበዳሪ የተበደረውን ገንዘብ በመሰረቁም ተስፋ ቆረጠ፡፡ ህይወት ጨለመችበት፡፡ አራጣ አበዳሪውም ገንዘቡን ካልመለሰ አሰቃይቶና ቆራርጦ የሚገድለው መሆኑን እየገለፀ ያስፈራራው ጀመር፡፡ ውጥረት ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ የተደራረበበት ይህ ሰው ራሱን ለመግደል ሙከራ ቢያደርግም ሰዎች ደርሰው ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ከሞት ያድኑታል፡፡
ራሱን ለመግደል ሙከራ ያደረገው ሰይፉ ከሆስፒታል ወጥቶ ጋዜጣ ሲያነብ ጨካኙ ነፍሰ ገዳይ ድማሙ ከእስር ተፈታ የሚል ዜና ያነባል፡፡ ዜናውን እንዳነበበም ወደ ነፍሰ ገዳዩ በመሄድ የተጠቀለለ ብር ሰጥቶ ፈሪ በመሆኑ ራሱን መግደል እንደማይችል በመግለጽ ሳያሰቃየው እንዲገድለው ይጠይቀዋል፡፡ ተው አትግደለኝ ብልህም አትተወኝ ግደለኝ ይለዋል፡፡ ለነፍሰ ገዳዩ ከሰጠው የቅድመ ክፍያ በተጨማሪም እርሱ ከተገደለ በኋላ ገዳዩ የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽኑን እንዲወርስ የሚያስችለው የኑዛዜ ወረቀት ይሰጠዋል፡፡
ካሌብ የግድያ ስምምነቱን ከነፍሰ ገዳዩ ጋር ከተዋዋለ በኋላ ወደ ቤቱ ሄዶ ተኝቶ እያሰበ ሳለ ሰራተኛው ከክፍለ ሀገር ደውላ ጋሼ ባለፈው ሳልነግርዎት ሄጄ ነው፡፡ ብሩ አልጋ ላይ ተበትኖ ሳየው እንዳይጠፋ ብዬ ዱቄት ውስጥ አስቀምጬዋለሁ፡፡ ብላ ያልገመተውን አስገራሚ ዜና ትነግረዋለች፡፡
ከሰራተኛው በሰማው ዜና የተደሰተው ካሌብ ነፍሰ ገዳዩ ድማሙ ጋር ይደውልና ችግሩ ተፈትቷል፤ ሁሉ ነገር ተስተካክሏል፤ አትግደለኝ ይለዋል፡፡ ድማሙ ግን በስምምነቱ መሰረት እርሱን ከመግደል እንደማይመለስ ይገልጽለታል፡፡ በኑዛዜ ወረቀቱ ላይ ያሰፈረውን የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽንም ካሌብን ከገደለ በኋላ እንደሚወስድ ይነግረዋል፡፡ የነፍሰ ገዳዩን ማስፈራሪያ የሰማው ካሌብም እየበረረ ሄዶ የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽኑን ይሸጥና ይደበቃል፡፡ ነፍሰ ገዳዩ የወራሽነት መብት አለኝ ብሎ ማሽኑን ሊወስድ ሲሄድ ለሌላ ተሸጦ ያገኘዋል፡፡ በዚህ የተበሳጨው ድማሙ የካሌብን የሴት ጓደኛ ይጠልፍና ቀሪውን ገንዘብ እንዲያመጣለት ገንዘቡን ካላመጣ ግን ልጅቷን እንደሚገድልበት ይነገረዋል፡፡ ከነፍሰ ገዳዩ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ያዳመጠው ካሌብም ቀሪውን ገንዘብ እንደሚሰጠው ቢገልጽም በጎን ለፖሊሶች መረጃ ሰጥቶ ገዳዩን በማስከበብ እጮኛውን ከሞት ያተርፋል፡፡ ፊልሙ በዚሁ ይቋጫል፡፡
ይህ ነው እንግዲህ የኢሜትስ ማርክ ፊልምና የ"ይፈለጋል" ፊልም አንድነትና ሁለትነት፡፡ "ለምን ይዋሻል?" በሚለው ፕሮግራሙ ሰዎችን የሚያብጠለጥለው የ"ይፈለጋል" ደራሲ ሰይፉ ፋንታሁን የኩረጃ ብቃት ይህንን ያህል ዘልቆ አድማስ ማዶ ይሻገራል፡፡ ታዲያ ሰይፉ "ለምን ይዋሻል?" ማለት ይቻለዋልን? በኃይሌ ሙሉ |