|
Sunday, 30 March 2008 |
 ቦታው ቦሌ፣ ኒውዮርክ ካፌ ፊት ለፊት ያለው አስፓልት ነው፡፡ ጠዋት በመሆኑ በነበረው የትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት መኪኖች ፍጥነታቸውን ቀንሰው ይሽከረከራሉ፡፡ ጡቷን የሚጠባ ትንሽ ልጇን በጎኗ ይዛ ከሚርመሰመሱ መኪኖች መካከል አንዷን የቤት መኪና ተከትላ ትሮጣለች፡፡ ከሩጫዋ አስቁሜ ለምን እንደምትሮጥ ጠየቅኋት፡፡ "ቀዩዋ መኪና ውስጥ ያለው ፈረንጅ ነው፡፡ ሳንቲም ይሰጠኝ እንደሆነ ልለምነው ብዬ ነው"
በተጠቀሰው አካባቢ ዘወትር ልጇን ይዛ መኪናዎችን በመከታተል የምትለምነው እማዋይሽ ዳርጌ በዚህ ሥራ መተዳደር ከጀመረች ወራትን አስቆጥራለች፡፡ ገና በልጅነቷ ለዚህ ህይወት የዳረጋትን ታሪክ ታስታወሳለች፡፡
እድሜዋ 18 እንደሆነ ብትነግረኝም የፊት ገፅታዋና ቁመናዋን ሳይ ግን ከ16 ዓመት የሚበልጣት አትመስልም፡፡ ተወልዳ ባደገችበት የጎንደር አካባቢ በልጅነቷ ትምህርት ቤት የገባች ቢሆንም ከአራተኛ ክፍል በኋላ መቀጠል አልቻለችም፡፡ ገና በእቅፍ እያለች ቤተሰቦቿ ቃል ለገቡለት ሰው ዳሯት፡፡
እማዋይሽ እንደምትለው ለሰርጓ ሲደገስ አታውቅም፡፡ የሰርጉ እለት ሲደርስም ቢሆን ጎረቤት ለምትገኘው ጓደኛዋ ሚዜ እንደምትሆን ተነግሯት ሽንሽን ቀሚስ፣ አዲስ ነጠላ፣ ሸራ ጫማና ዣንጥላ ተገዛላት፡፡ ድግሱ ለሷ ሰርግ እንደሆነ ያወቀችው ከወንድ ሙሽራ ወገን የመጡ ሰርገኞች ይዘዋት ወደ ባሏ ቤት ሲሄዱ ነው፡፡ "ጓደኛዬንም ለኔ ሚዜ ትሆኛለሽ ብለው ያለብሷታል፡፡ እኔንም ለሷ ሚዜ ትሆኛለሽ ነው ያሉኝ፡፡ እኔ ስለምማር የሚድሩኝ አይመስለኝም ነበር፡፡ ሰርገኞች ይዘውኝ ሲሄዱ ግን ሰርጉ የእኔ እንደሆነ ገባኝ፡፡ አልቅሻለሁ፡፡ እምቢ ማለት ግን አልችልም"
ለቤተሰቧ የመጀመሪያ ልጅ የሆነችው ወይንሸት በአሥራ ሁለት ዓመት እድሜዋ ትምህርቷን አቋርጣ ሳታስበው ለባል ተሰጠች፡፡ ባሏ ቤት እንደሄደችም በቀጥታ ቤቱን የማስተዳደር ኃላፊነት በሷ ላይ ወድቋል፡፡ የቤቷን ሙሉ ሥራ ማከናወን፣ ገበያ ወጥቶ የሚያስፈልጉ ነገሮችን መግዛት፣ ውሃ ከወንዝ ማመላለስ፣ ባለቤቷ እርሻ ሲያርስ እየተከተለች ጉልጓሎ መጎልጎል . . . ያገባች የገጠር ሴት ማድረግ የማገባትን ሥራ ሁለ ታዳጊዋ እማዋይሽ ማከናወን ግዴታዋ ነበር፡፡
እሷ እንደምትናገረው ከሆነ ከሥራ ጫናው ይልቅ ያማረራት የባለቤቷ ዱላ ነበር፡፡ "የቅናት መንፈስ አለበት፡፡ የገጠር ባል ሲወጣም ሲገባም ልማታ ይላል፡፡ በነጋ በጠባ እየደበደበኝ ያሰቃየኛል" ትላለች፡፡ ቤተሰቦቿ ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ብታውቅም አንድ ቀን ባሏን ፈታ ዳግም ትምህርት ቤት እንደምትገባ ታስብ ነበር፡፡ ሳትተገብረው ከአራት ዓመት በላይ ከባሏ ጋር ከረመች፡፡ ይሁንና ባሏን ለመፍታት ከማሰብ ወደ ኋላ ብላ አታውቅም፡፡
አንድ ቀን ግን ሃሳቧን የምታሳካበት መንገድ አገኘች፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው የሚሰሩ የጎረቤቶቿ ልጆች ቤተሰቦቻቸውን ሊጠይቁ ወደ አገር ቤት ብቅ ብለው አገኘቻቸው፡፡ አለባበሳቸው ሳባት፡፡ "እኔም እንደናንተ ሰርቼ መኖር እፈልጋለሁ ውሰዱኝ" አለቻቸው፡፡ እነሱም አዲስ አበባ ብትመጣ ሰርታ "ብዙ" ገንዘብ ማግኘት እንደምትችል ነግረው የበለጠ አማለሏት፡፡ በመጨረሻም ሁለቱ ጓደኛሞች መጓጓዣዋን ችለው፣ ከባሏ አጥፍተው ወደ አዲስ አበባ ይዘዋት መጡ፡፡
ሁለቱ የሚኖሩበት በጋራ ቤት ተከራይተው የተለያየ ቤት ውስጥ በተመላላሽ ሰራተኝነት እየሰሩ ነው፡፡ እንደመጣች ለአንድ ቀን እነሱ ጋር ካሳረፏት በኋላ በማግስቱ ደላላ ጋር ወሰዷት፡፡ በወር 25 ብር ተቀጥራ ገባች፡፡
የተቀጠረችበት ቤት ውስጥ ዋና የስራ ድርሻዋ እንጀራ መጋገር ሲሆን ልብስና እቃ ማጠብ እንዲሁም ቤት ማፅዳት ዓይነት ሥራዎችንም ትሰራለች፡፡ ምግብ ግን አትሰራም ሲሰሩ ቁጭ ብላ እንድታይ ትዕዛዝ ተሰጥቷታል፡፡ ከሦስት ወር በኋላ ግን በዛው ደሞዝ ምግብም እየሰራች ማገልገል ጀመረች፡፡
እማዋይሽ ሥራዋን እየሰራች በነፃነት የምትኖርበትን ህይወት ወዳዋለች፡፡ ከአምስት ወር በኋላ ግን የቤቱ እማወራ በህልሟም በእውንም አስባው የማታውቀውን ግን እያገጠጠባት ያለውን እውነት ነገሯት፡፡ "ነፍሰ ጡር ነሽ አሉኝ፡፡ አይደለሁም ብዬ ተከራከርኩ፡፡ ሆዴ አድጎ ነበር ግን የወፈርኩና ቦርጭ ያወጣሁ ነበር የሚመስለኝ፡፡"
ጊዜው በገፋ ቁጥር አብሮ ወደፊት የማያድግ ሆዷን ስታይ ግን የተነገራት እውነት መሆኑን አመነች፡፡ ተቀጥራ የገባችበት ሰባተኛ ወር ሲያልቅ የቤቱ ባለቤት ደሞዟን ቆጥረው አስረከቡና ከቤት አስወጧት፡፡
ከመውለዷ በፊት የወር አበባ አይታ እንደማታውቅ የምትናገረው እማዋይሽ ከባሏ ቤት ጠፍታ የመጣችው ነፍሰጡር መሆኗን ባለማወቋ እንደሆነ ትገልፃለች፡፡
የተሰጣትን የሰባት ወር ደሞዝ (175 ብር) ይዛ መንገድ ላይ ስትጓዝ ላገኘቻት አንዲት ሴት የሆነችውን ሁሉ ዘርዝራ በመንገር መፍትሔ እንድትፈልግላት ለመነቻት፡፡ በወር 15 ብር እየከፈለቻት ቤት ልታጋራት የምትችል አሮጊት ሴት እንዳለች ነግራት ወሰደቻት፡፡ እንደተባለው እየከፈለች የቀን ሥራ እየሰራች ከምትተዳደረው አሮጊት ጋር መኖር ጀመሩ፡፡ አሮጊቷ የሰው ቤት እንጀራ እየዞሩ ይጋግራሉ፡፡ ከጋገሩበት ቤት አንድ እንጀራ በፌስታል ቋጥረው ወደ ቤት ይገባሉ፡፡ እማዋይሽ ቤት ውስጥ የተገኘውን ሰርታ ትጠብቃለች፡፡ በዚሁ መልኩ እስከምትወልድ ድረስ ኑሯቸውን ቀጠሉ፡፡
ተቀጥራ ትሰራበት ከነበረው ቤት የተሰጣት ደሞዝ እያለቀ ነው፡፡ ሳንቲም ተቸግረዋል፡፡ በወለደች በወሯ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ወስደው ከነልጇ በር ላይ ካስቀመጧት በኋላ "እዚሁ ቁጭ በይ ሰው አሥርም አምስትም ይሰጥሻል" ብለዋት አሮጊቷ ወደ ሥራቸው ሄዱ፡፡ "ሰው ቀና ብዬ አላይም፡፡ ድምፅ አውጥቼ በመናገርም አልለምንም፡፡ ማታ ያገኘትን ሁለትም ትሁን ሦስት ብር ይዤ ወደ ቤት እገባለሁ"
እማዋይሽ እንደምትለው እንደድሮው ሳንቲም እጇ ላይ ባለመኖሩ አሮጊቷም ገቢያቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ለሁለት ለመኖር ተቸግረዋል፡፡ በመሆኑም አሮጊቷ ማባረር ፈልገዋል፡፡ በወር 15 ብር ትከፍል የነበረውን ገንዘብ "ካሁን ወር ጀምሮ 4ዐ ብር አድርገሽ ካላመጣሽ ቤቴን ልቀቂ" አሏት፡፡
"በወቅቱ ልጄ ሦስት ወር ሆኖት ነበርና ልጄ ጠንክሮልኛል አሁን መሥራት እችላለሁ" በሚል ወኔ ሠራተኝነት ለመቀጠር ልጇን አቅፋ ደላላ ቤት ሄደች፡፡ ሰራተኛ ለመቅጠር ከሚመጡት መካከል ጠያቂ አጣች፡፡ ወደ ማታ አንዲት ሴት ጠጋ ብለው ጠየቋት ሰራተኝነት መቀጠር እንደምትፈልግ ስትነግራቸው የመለሱላት መልስ ደግሞ ተስፋ ቆርጣ እንድትመለስ አድርጓታል፡፡ "የእኔን ሥራ ልትሰሪ ነው ልጅሽን ልታሳድጊ አንቺን የምቀጥረው" በማለት ነበር ያፌዙባት፡፡ ይህም ጠዋት ይዛው የወጣችውን እሰራለሁ የሚል ወኔ እንድታጣ አድርጓታል፡፡
እማዋይሽ ይህ ሁሉ ካለፈ በኋላ ነበር ልጇን ይዛ ወደ ጎዳና ለመውጣት የተገደደችው፡፡ አሁን የምትኖረው ሽሮ ሜዳ አካባቢ ሲሆን በከተማ አውቶቡስ እየተመላለሰች ቦሌ አካባቢ ስትለምን ትውላለች፡፡
ጠዋት ያገኘችውን ለልጇ አብልታ ካገኘች እሷም አፏን ሽራ በጥዋት ወደ ቦሌ ትሳፈራለች፡፡ ስትለምን ውላ ማታ ወደ ቤቷ ትመለሳለች፡፡ ጎዳና ላይ ስትኖር ሴት በመሆኗ ሌላ አደጋ እንዳይደርስባት በመስጋት በደባልነት 35 ብር እየከፈለች ቤት ተከራይታ ትኖራለች፡፡
"መንገድ ላይ የሚያዩኝ ብዙ ሴቶች አንቺን የመሰለች ቆንጆ እንዴት ትለምናለች? ሰርተሽ አትበይም ይሉኛል፡፡ ግን ማን ያሰራኛል፡፡ እንደዛ የሚሉኝን ሰዎች አልለቃቸውም፡፡ ሰው ጉድ እስኪል ድረስ ልብሳቸውን ይዤ የምስራበት ቦታ አስገቡኝ፣ ውሰዱኝ እያልኩ እጨቀጭቃቸዋለሁ፡፡ እስከ ዛሬ ግን ለሥራ የወሰደኝ የለም፡፡ ሰው የሚናገረው ለአፉ ብቻ ነው" ትላለች፡፡ ስራ ካገኘች ግን ልጇ እስኪያድግ ድረስ ያለ ደሞዝም ቢሆን የመሥራት ፍላጎት እንዳላት ትናገራለች፡፡
ወራትን ባሳለፈችበት የልመና ኑሮ ልቧን የሚያደሙ ንግግሮችን እንደምትሰማ አንዳንዴም ቁጭ ብላ እንደምታለቅስ አጫውታኛለች፡፡ "ስባልግ፣ ሆን ብዬ የወለድኩት እንደሆነ አስበው ብዙ ሰዎች ይሰድቡኛል፡፡ ለልመና እጄን ስዘረጋ ፣ለመለመኛ ነው አይደል የወለድሽው፡፡ ሂጂ የወለደልሽ ይስጥሽ ለእኔ የወለድሽ መሰለሽ?፣ ይሉኛል"
እማዋይሽ እንደምትለው ወደ ቤተሰቦቿ የመመለስ እድቅ የላትም፡፡ ልጇን ይዛ የሚያሰራት ሰው ካገኘች ያለደሞዝም ቢሆን የመስራት ፍላጎት እንዳላት ትናገራለች፡፡ ካልሆነ ግን ልጇ አድጎ ትምህርት ቤት እስኪገባ ድረስ ከተንከባከበችው በኋላ ትምህርት ቤት ገብቶ መማር ሲጀምር መንገድ ላይ ለመነገድ ታስባለች፡፡ ይህም ማለት አሁን ልጇ የዘጠኝ ወር እድሜ ያለው ሲሆን ትምህርት ቤት እስኪገባ ከዚህ በኋላ ቢያንስ ለአምስት ዓመት መንገድ ላይ መለመን ይጠበቅባታል፡፡ በትዕግሥት ዘሪሁን |