Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow ሥጋ ደዌና ቲቢ ዋነኛ የጤና ችግሮች
ሥጋ ደዌና ቲቢ ዋነኛ የጤና ችግሮች Print E-mail
Sunday, 30 March 2008
የአዲስ አበባ አስተዳደርንና የድሬዳዋ አስተዳደር ካውንስልን ጨምሮ በአምስት ክልሎች የሚገኙ 13 የማኅበራዊ ተሃድሶ ፕሮጀክቶች ከ28ሺህ በላይ ለሚሆኑ ችግሮች የሥጋ ደዌና ቲቢ ተጠቂዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን የጀርመን ሥጋደዌና ቲቢ እርዳታ ማኅበር የኢትዮጵያ ተጠሪ አስታወቁ፡፡

 

የጀርመን ሥጋዴዌና ቲቢ ዕርዳታ ማኅበር ኢትዮጵያ 50ኛ ዓመቱን መጋቢት 18 ቀን 2000 በተከበረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ተጠሪው አቶ አህመድ መሀመድ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቶቹ ችግረኛ የሥጋደዌና ቲቢ ተጠቂዎችን የብድር አገልግሎትና የትምህርት ድጋፍ በመስጠት፣ እንዲሁም የማሰልጠኛ ተቋማትን የመኖሪያና የትምህርት ቤቶች በመገንባት ይረዳሉ፡፡

በዘጠኝ ክልሎች፣ በአዲስ አበባ አስተዳደርና በድሬዳዋ ጊዜያዊ አስተዳደር ካውንስል የሚገኙ የአካል ድጋፍ ማምረቻ ወርክሾፖች፣ አምስት ሆስፒታሎች፣ የአለርት የሥልጠና ክፍልና የብሄራዊ ሥጋደዌ ማኅበር ከጀርመን ሥጋደዌና ቲቢ ዕርዳታ ማኅበር ተገቢውን እርዳታና ድጋፍ እንደሚያገኙም አስረድተዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከ100ሺህ በላይ የሚሆኑ የሥጋደዌ ተጠቂዎች በሕክምና ይድናሉ፡፡ በዓመት እስከ 5ሺህ የሚሆኑ አዳዲስ ተጠቂዎችም ይገኛሉ፡፡

የጀርመን ሥጋደዌና ቲቢ ዕርዳታ ማኅበር በገንዘብ፣ በማቴሪያልና በቴክኒክ የሚደግፋቸውና ወደ ስምንት የሚጠጉ ወርክሾፖች በዓመት 20ሺህ ለሚሆኑ የሥጋደዌ አካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፍ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡

"በዓለም በቲቢ ችግር ከተጠቁ 22 አገሮች መካከል፣ እንዲሁም አፍሪካ ውስጥ ችግሩ በጣም ከሚበዛባቸው ሦስት አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት" ያሉት አቶ አህመድ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይህንን ችግር ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥናት ላይ ማኅበሩ የትብብር አድማሱን ማስፋፋቱን አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን፣ በድሬዳዋ አስተዳደር ካውንስል፣ በሐረሪና በትግራይ ክልሎች ቲቢን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የአጭር ጊዜ የሕክምና ስልት እ.ኤ.አ ከ1996 ጀምሮ በመስጠት የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ መሆኑን ተጠሪው ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ እ.ኤ.አ ከ1992 እስከ 1996 ድረስ በሀገሪቱ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ አዲስ የቲቢ ሕሙማን ተመዝግበው ሕክምና እንዲያገኙ ጥረት ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ከቲቢ ጋር ባለው ጠንካራ ግንኙነት የተነሳ በቲቢ ላይ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ ይህንንም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የቲቢና የኤች.አይ.ቪ ጥምር ተግባር በቢሲዲሞ ሆስፒታል እንዲጀመር ተደርጓል፡፡

የጀርመን ሥጋደዌና ቲቢ ዕርዳታ ማኅበር በአቅም ግንባታ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሃድሶ የሚያበረክተው ድጋፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሥጋደዌ ማኅበር ከአድሎና መገለል ነፃ የሆነ ዓለም ለማየት ላነገበው ራዕይ እውን መሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ የብሔራዊ ሥጋ ደዌ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ልዑል ሰገድ ብርሃኔ ገልፀዋል፡፡

ዶክተር ክላሰ ዲተር በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር "ቲቢ በዓለም ውስጥ እጅግ አስከፊ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ከማስከተሉ ሌላ በባክቴሪያ የሚተላለፍ አንድ ቁጥር ጉዳይ በሽታ ነው" ብለዋል፡፡ በዓመቱ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰዎች በቲቢ እንደሚጠቁም 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑትም ለሞት እንደሚዳረጉ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባና በሊፕዚግ ከተሞች መካከል ሕብረት መፍጠር እህትማማች ከተሞች እንደሆኑ ሁሉ የጀርመን ስጋደዌና ቲቢ ዕርዳታ ማህበር ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኝባት የውርዘበርግ ከተማና የሐረር ከተማ አህትማማች ከተሞች እንዲሆኑ ቢደረግ መልካም መሆኑን አምባሳደሩ ጠቅሰው ይህ አይነቱ የእህትማማች ግንኙነት የሁለቱ አገሮች ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክረው አስረድተዋል፡፡

የጀርመን ሥጋ ደዌና ቲቢ ማኅበር እ.ኤ.አ ከ1958 ጀምሮ በሥጋ ደዌ ቁጥጥር ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት ሠርቷል፡፡ ስለሆነም ከ50 ዓመት በፊት በተፈጠረው አጋርነት ምክንያት ለኢትዮጵያ ልዩ ግምትና ቦታ ሊሰጥ ችሏል፡፡ ለኢትዮጵያ ሥጋደዌ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፕሮግራም ሲሰጥ የቆየውን የፋይናንስ፣ የሎጂስቲክና የቴክኒክ ድጋፎች አድማስ ከፍ እንዲል በማድረግ እ.ኤ.አ ከ1994 ጀምሮ ጣምራ የቲቢና ሥጋደዌ በኋላም ከ2004 ጀምሮ የቲቢና ኤች.አይ.ቪ ቁጥጥር ሥራዎችን ጨምሮ ለመደገፍ በቅቷል፡፡

በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ ለጀርመን ሥጋደዌና ቲቢ እርዳታ ማኅበር መሥራችና የረጅም ዘመን በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ፣ እንዲሁም ረዥም ዘመን ላገለገሉ የሥጋደዌ ቁጥጥር ፕሮግራም ሠራተኞች፣ ውጤታማ ሥራ ላከናወኑ የማኅበረሰብ ተሃድሶ ተጠቃሚዎች፣ ለሥጋደዌ ማኅበር ምሥረታ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ ግለሰቦች ልዩ ልዩ ዓይነት የማነቃቂያ ሽልማቶች ተሰጥቷቸዋል፡፡
በታደሰ ገብረማርያም

 
< Prev   Next >