|
ኢትዮጵያውያን ከቻይናውያን ዲያስፖራ.... |
|
|
|
Sunday, 30 March 2008 |
|
ኢትዮጵያውያን ከቻይናውያን ዲያስፖራ መማር ያለባቸው
ዲያስፖራው ለትውልድ አገሩ እድገት እንደ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና የሰው ኃይል ካፒታልን በውስጡ አምቆ የያዘ በመሆኑ የዲያስፖራው የየትውልድ አገራት መንግሥታት ይህንን እምቅ ሃብት ለመጠቀም ዲያስፖውን የሚጋብዝ ድባብ መፍጠር አለባቸው፡፡
ዲያስፖራው ያለውን አቅምና ሃብት ለየትውልድ አገሩ ሶሽዮ-ኢኮኖሚክ እንቅስቃሴ እንዲያውለው መንግሥታት ያለባቸው ሃላፊነት ዲያስፖራው በአገሩ ሊሰራ የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡
በእድገት ሽግግር ላይ ያሉ አገራት ዲያስፖራውን ከትውልድ አገሩ ለማገናኘት ዘርፈ ብዙ የግንኙነት መስመሮች እየመሰረቱ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ባደጉትም ሆነ በማደግ ላይ በሚገኙት አገራት የፖሊሲ አውጪዎች ችግር ዲያስፖራው ለትውልድ አገሩ ሊያበረክት የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ድርሻ ለመጠቀም አበረታችና ደጋፊ የሆነ ድባብ መፍጠር ነው፡፡
እንደ አለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) ሪፖርት በአለም ከፍተኛ የዲያስፖራ ስርጭት አላቸው ከሚባሉት አገሮች የምትመደበው ቻይና በዲያስፖራ የሚገኙትን ከ50 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎቿን አጠናክራ በመጠቀም እንደ ምሳሌ የምትጠቀስ አገር ናት፡፡
የቻይና ዲያስፖራ በደቡብ ምሥራቅና በምስራቅ እስያ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጠንካራ የንግድ ኔት ወርክ የዘረጋው ቀደም ባሉ አመታትም ሲሆን ቻይና ለደረሰችበት ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያደረጉት እነሱ ናቸው፡፡
አብዛኞቹ አገሮች ለዲያስፖራው አመቺ የንግድ ወይም የሥራ ድባብ ለመፍጠር የሚቸገሩ ቢሆንም የቻይና መንግሥት በዲያስፖራ ለሚገኙ ወገኖቹ አመቺና አበረታች የሆነ የሥራ ድባብ በመፍጠር በቻይና ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ ወሳኝ ስፍራ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡
የቻይና ዲያስፖራም ቢሆን በሃብት የበለጸገ፣ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ለመሰማራት እውቀቱ ያለው፣ ጠንካራ በሆነ የንግድ ኔትዎርክ የተሳሰረና ለትውልድ አገሩ እስከ ትርፍ ካፒታል በሚደርስ ኢንቨስት ማድረግ የሚችል ነው፡፡ ለቻይና ዲያስፖራ የፖለቲካ ልዩነት በአገሩ ኢንቨስት ከማድረግ አያግደውም፡፡
የቻይና መንግሥትም የኢኮኖሚ አጋሯ የሆነውን ዲያስፖራ ለመጠቀም ለዲያስፖራው ያወጣው አበረታች ፖሊሲም በቻይና ለውጥን በማምጣት እንደ ምሳሌ የሚጠቀስ ነው፡፡
ፖሊሲው የቻይና ዲያስፖራን አግባብነት ያላቸው መብቶች ማለትም በማንኛውም ሁኔታ የማይሸራረፍ መብት የሰጠ በመሆኑ በውጭ የሚኖሩ ቻይናዊያን በአገራቸው ከንግዱም ባሻገር ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ አስችሏቸዋል፡፡
የቻይና ዲያስፖራ መብቱና ፍላጎቱ እንዲጠበቅለት፣ የተሰጠውን መብትና ሃይል ለማስፈጸም ለካቢኔቱ ኃላፊነት የመስጠት፣ በፓርላሜንት ኮሚቴ የማስቀመጥ መብትም አለው፡፡
የቻይና መንግሥት እ.ኤ.አ በ1990 አጽድቆት የነበረውን በውጭ የሚኖሩ ቻይናዊያንና ቤተሰቦቻቸው መብትና ፍላጎት ለማስጠበቅ የወጣውን ሕግ በ2000 በማሻሻል ዲያስፖራው በፖለቲካና ሰብዓዊ መብቶች፣ በፖለቲካ የመሳተፍ መብት፣ አገራቸውን የመጎብኘትና ሃብት የማካበት መብት ማጎናፀፉ ቀድሞውንም በአገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ፍላጎት ለነበረው የቻይና ዲያስፖራ በር የከፈተ ነበር፡፡
መንግሥት ለዲያስፖራው ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግ፣ በብሔራዊና በክልል ደረጃ ተመላሽ ዲያስፖራው ውክልና እንዲያገኝ መደረጉ፣ መብቱን ሊያስጠብቁለት የሚችሉ ሕዝባዊ ድርጅቶች ማቋቋም መቻሉ፣ ኢንቨስት እንዲያደርግና በንግድ እንዲሳተፍ መደረጉ፣ የቀረጥና የታክስ ቅነሳ ማግኘቱ ዲያስፖራው የቻይናን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ያለው ተሳትፎ ከፍተኛ አድርጎታል፡፡
በቻይና የተረጋጋና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣትም አገራቸው ተመልሰው በልማቱ የሚሳተፉ ቻይናዊያን ልዩ ጥበቃ የሚያገኙበትን ህግ የቻይና መንግሥት በ2004 ማጽደቁ ቻይናዊያን በአገራቸው ገብተው እንዲያለሙ ያበረታታ የፖሊሲ ማሻሻያ ነበር፡፡
የቻይና ዲያስፖራ ከማንኛውም በመንግሥት ደረጃ ካሉ አካላት ማለትም ከማዕከላዊ መንግሥት፣ ከከፍተኛ ህግ አውጪ፣ በክልልና ከተማ እንዲሁም ከኤምባሲ ደረጃ የመደራደርና የመወያየት መብት ያላቸው ሲሆን ይህም ችግሮቻቸውን ለመፍታትና የሥራ ሂደቶችን ለማቅለል ጠቅሟቸዋል፡፡
ዲያስፖራውም ጠንካራ የመረጃ መረብ ዘርግቷል፡፡ እንዲሁም የዘር ሃረጉን እንዲያገኝ ሁኔታዎች ተመቻችተውለታል፡፡
በኢንቨስትመንት እንዲሰማራም አገልግሎት ያገኛል፣ ልዩ የሆነ እንክብካቤ ማለትም የታክስ መነሳት/መቀነስ፣ ለልማት አመቺ የሆነ መሬት መስጠት፣ የመሬት ነፃ ታክስ ወይም ቅነሳና የሥራ ሂደትን በማፋጠን ዲያስፖራውን ማበረታታት ይገኙበታል፡፡
በተመሳሳይ የንግድ ዘርፍ የተሰማሩትን ለማገናኘት ትላልቅ የንግድ ትርዒቶችን በማቅረብ፣ መሠረታዊ መብቶችንና ፍላጎቶችን ለማስጠበቅ የወጣውን ህግ በማስፈጸም፣ ችግሮችን በአፋጣኝ በመፍታት፣ በቱሪዝም ላይ አዋጭ ምክር በመስጠት የቻይና መንግሥት ለዲያስፖራው እያደረገ ያለው ጥበቃ ለአገሪቱ አፋጣኝ እድገትን አምጥቷል፡፡ ኢትዮጵያስ ከቻይና ዲያስፖራ ምን ትማራለች? በጋዜጣው ሪፖርተር |