|
Sunday, 30 March 2008 |
|
ሜታ ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የማስፋፊያ ሥራ ጀመረ • በሁለት ሚሊዮን የገዛው ቦይለር ከአገልግሎት ውጪ ሆነ
ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ የምርት መጠኑን ለማሳደግ የሚያስችለውን የማስፋፊያ ሥራ ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በማከናወን ላይ ነው፡፡ አዳዲስ ምርቶችን ለማምረት በዝግጅት ላይ እንደሆነም ተጠቆመ፡፡
የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ከበደ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ በአሁኑ ጊዜ የሚያመርተው ምርትና የምርት ፍላጐቱ የተጣጣመ ባለመሆኑ ለመንግሥት በቀረበው ጥያቄ መሠረት መንግሥት ለማስፋፊያ ሥራው በጀት በመልቀቁ ሥራው በመከናወን ላይ ነው፡፡
የማስፋፊያ ሥራውን በጨረታ በተመረጡ ሦስት የጀርመን ኩባንያዎች አማካይነት የሚሠራ ሲሆን ኩባንያዎች የመጭመቂያ፣ የመጭመሊያ የሙሌት ክፍሉን ግንባታዎች በተናጠል እየሠሩት ነው፡፡ ብሮሃዝ የተባለው የጀርመን ኩባንያ ደግሞ የማማከር የግንባታ ቁጥጥሩን በማካሄድ ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡
የማስፋፊያ ሥራው የፋብሪካውን የማምረት አቅም በ60 በመቶ የሚያሳድገውና ይህም በዓመት 750 ሺህ ሔክቶ ሌትር ቢራ ለማምረት ያስችለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለሥራው የሚያገለግሉ የአዳዲስ መሣሪያዎች ግዥ የተፈፀመና አብዛኛው መሳሪያዎችም ወደ አገር ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ በእቅዱ መሠረት የሙከራ የማምረት ሥራውን ከሰባት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከማስፋፊያ ሥራው ጋር በተያያዘ ፋብሪካው ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደረገበትን ቦይለር ግዢ ከጅቡቲ ወደብ ወደ አዲስ አበባ በመጓጓዝ ላይ እያለ አደጋ ደርሶበት ከጥቅም ውጪ በመሆኑ በነበረው የመድን ዋስትና አዲስ ቦይለር በድጋሚ ተገዝቶ በመምጣት ላይ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
ከ40 ዓመታት በላይ እድሜ ያለው የሜታ አቦ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ምርት በጀመረበት ወቅት የማምረት አቅሙ በዓመት 50 ሺህ ሔክቶ ሊትር የነበረ ሲሆን አሁን 450 ሺህ ሔክቶ ሊትር፣ የማስፋፊያ ሥራው ሲጠናቀቅ ደግሞ 75ዐ ሺህ ሔክቶ ሊትር ይደርሳል፡፡
አቶ ሰለሞን እንዳሉት፣ ፋብሪካው ትኩረት ያደረገው ምርት ማሳደግ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ምርቶችን ለመጀመርም አቅዷል፡፡ በአዲስ መልክ ለመጀመር ከታቀዱ ምርቶች ውስጥ ተቋርጦ የነበረውንና ሜታ ፕሪሚየር እየተባለ የሚጠራውን ቢራ በአዲስ የጠርሙስ ዲዛይን ማቅረብንም ያጠቃለለ ነው፡፡ በዳዊት ታዬ |