| የጋምቤላ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮና... |
|
|
| Wednesday, 02 April 2008 | |
|
የጋምቤላ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮና የከተማው ነጋዴዎች ተጋጩ
በጋምቤላ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ነጋዴዎችና የከተማው ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በንግድ አሰራር ሂደት ዙሪያ ውዝግብ ውስጥ መግባታቸውን በከተማው የሚገኙ ነጋዴዎች አስታወቁ፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የከተማው ነጋዴዎች የከተማው ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ዝቅተኛ የእቃ መሸጫ ተመን በማውጣት ለኪሳራ እየዳረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነጋዴዎቹ በአስተዳደሩ ኢፍትሃዊ እርምጃ ምክንያት የከተማው የንግድ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉንና በከተማይቱ ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ ሱቆች መዘጋታቸውን ነጋዴዎች ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ያለፈው ሳምንት ከከተማው የፖሊስ ኃይል ጋር ግጭት መፈጠሩንና ከሦስት መቶ በላይ ነጋዴዎች ለእስራት መዳረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ የከተማው ታጣቂ ኃይሎች በነጋዴዎቹ ላይ ባደረሱት ወከባና ድብደባ ሁለት ሰዎች ተጎድተው ሆስፒታል መግባታቸው የደረሰን ዜና ያስረዳል፡፡ የከተማው ነጋዴዎች የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ባወጣው ፍትሃዊ ባልሆነ የዋጋ ዝርዝር ለመሸጥ መገደዳቸውን አስታውቀዋል፡፡ የከተማው ፖሊስ "ወንጀለኛ ነኝ፣ ከአሁን በኋላ በዝቅተኛ ዋጋ እሸጣለሁ" የሚል ቅጽ በማዘጋጀት አስገድዶ እንዳስፈረማቸው ነጋዴዎቹ ይናገራሉ፡፡ የከተማው ነዋሪዎች በበኩላቸው በከተማው ውስጥ የሸቀጣሸቀጥ መሸጫ ሱቆች፣ ዳቦ ቤቶች፣ ቴሌ ሴንተሮችና ወፍጮ ቤቶች መታሸጋቸውን፣ በዚህም በከተማው ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ በመስተጓጎሉ መቸገራቸውን ነዋሪዎች አስታውቀዋል፡፡ የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዴንግ ኡቻላ የታሰሩ ነጋዴዎች ቁጥር መጋነኑን "ከሕገወጥ ንግድ ጋር በተያያዘ ሰላሳ ነጋዴዎች ብቻ" መታሰራቸውን አስታውቀዋል፡፡ ኮሚሽነሩ በከተማው ውስጥ ከሚገኙ ነጋዴዎች ጋር የተፈጠረው ውዝግብ በውይይት መፈታቱንና የታሰሩት ነጋዴዎች መለቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተሾመ ንቁ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |