Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow በ”አረም” የማይመለሱበት ስህተት
በ”አረም” የማይመለሱበት ስህተት Print E-mail
Wednesday, 02 April 2008
ሃብታሙ በቀለ

በአንድ ፈሪ ሰው “ታሪክ” አስተያየቴን እጀምራለሁ፡፡ አንድ ፈሪ የሆነ ሰው ከጓደኛው ጋር በተኛበት ቦታ ጅብ መጥቶ የዘረጋውን እግሩን ይይዘዋል፡፡ ቢደነግጥም ዝም ይላል፡፡ ጅቡ አጥንቱን ሲቆረጥመው ህመሙን ችሎ፣ እንዳይጮህ ጨርቁን ጎስጉሶ ዝም ብሏል፡፡
አብሮት የተኛው ጓደኛው አጥንት ሲቆረጠም በሰማው ድምፅ ነቅቶ “አንተ ምንድን ነው የሚጮኸው?” ቢለው “ተው እንዳይጨርሰን ዝም በል፡፡ ጅቡ እግሬን እየቆረጠመ ነው” አለው ይባላል፡፡

ሰውዬው “ከመሞት መሰንበት” ይሻላል በሚለው አስተሳሰብ ያደገና ያመነበት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ጅቡ በእግሩ ብቻ እንደማይመለስ፣ እግሩም ቢሆን ሊድን ከሚችለው በላይ ከተበላ ሊገድለው እንደሚችል ረስቶታል፡፡ እስከሚሞት ድረስ ያለው ጊዜም የስቃይ ቆይታ፣ የጭንቅ ቆይታ፣ መሆኑን ፍርሃቱ አስረስቶታል፡፡ በእግሩ ብቻ የሚመለስለት ቢሆን እንኳ አካላቱን እንዳጎደለው፣ እንደልቡ እንዳይራመድ የሚያደርገው መሆኑ የፍርሃቱ ብዛት ለማሰብ አላስቻለውም፡፡

በግልና በማህበራዊ የኑሮ ልምዳችን ውስጥ እንደዚህ ዓይነት የፍርሃትና የሥጋት ወይንም ስለሚመጣው ወደፊት፣ ተራምዶ ባለማየት ከባድ ስህተት እንሰራለን፡፡ ጊዜው ካለፈ በኋላ “በአረም” የማይመለሱበት ጥፋት እንሰራለን፡፡ በአጭሩና አደጋው ሳይከፋ ሊነቀስ የሚችል ችግር ማቃለል ከመሞከር ይልቅ፣ በሽታው ለሁሉም ከተዳረሰ በኋላ፣ እግሩን ጨርሶ ራሱ ላይ ከወጣ በኋላ፣ ወይም ጋንግሪን ከሆነ በኋላ፣ ሰማይ ላይ ቢወጡ፤ ከመሬት ቢፈርጡ ለማዳን የማይቻል መሆኑን አናስበውም፡፡ የጥቂቶች የሚመስለው ችግርም የሃገር ምድሩና የሁሉም እንደሚሆን የአለማሰብ ድክመት ጦሱ ብዙ መሆኑን እንረሳዋለን፡፡


በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የመሬት ውስጥም ሆነ ከመሬት በላይ አየሩ፣ የበቀለውና የተንጠለጠለው ጭምር የሕዝቦቿ ንብረትና ሃብት ነው፡፡ የባለቤትነት ምዝገባ በመንግሥት ይሁን በግል፣ በድርጅት ይሁን በቡድን፣ በቤተክርስቲያን ይሁን በመስጊድ ሁሉም የሃገሪቱ ንብረት ነው፡፡ በንብረቱም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሕዝቦቿ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ሕዝቦቹ ንብረታቸውን ካልጠበቁና፣ ካልተንከባከቡትና ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፍ ካላደረጉት፣ በራሳቸው ዘመን ብቻ አኝከውና ተፍተው ከጣሉት፣ በእጅ ያለ ወርቅ ጥሎ የማያውቁትን፣ “ወርቅ” ለመፈለግ መማሰን ይሆናል፡፡ ንብረታቸውን የባለቤት ስያሜ በማየት፣ አያገባኝም የሚሉ ከሆነ ነገ በራሳቸው ሲደርስ ቢጮሁና ቢሩዋሩዋጡ የበረሃ ጩኸት፣ የአሸዋ ላይ ሩጫ ሆኖ ይቀራል፡፡

ለምሳሌ፣ በአሁኑ ጊዜ በቅርስነት የሚታዩ ቦታዎች ባለቤታቸውም ማንም ይሁን ማን፣ የቱሪዝም ኢንዱስትሪን የሚያስፋፉ እንደመሆናቸው ገቢው ሁሉንም ኢትየጵያውያን ያገለግላል፡፡ ዛሬ ማዕድን የሚወጣባቸው አካባቢዎች ባለቤታቸው ማንም ይሁን ማን፣ ከገቢው በሚገኘው ጥቅም ተካፋይ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው.... በዚህ ሁኔታ አስፍተን ካላየናቸው አንዳንዶች ባለቤቱን ብቻ ተመልክተው ሊያጠፉት ቢሞክሩ ወይም ሲጠፋ ዝም ቢሉ ጉዳቱ የሃገር፣ ጉዳቱ የሕዝብ፣ መሆኑን ባለማሰባቸው የጉዳት ፈፃሚዎቹ ግብር አበር መሆን አይቀርላቸውም፡፡   

የዚህ መንደርደሪያ መነሻ የሆነኝ በእሁድ የሪፖርተር ጋዜጣ የተዘገበውና ወር ባልሞላ ጊዜ የገዳማት መቃጠል፣ የምክንያቱም አለመታወቅና አደጋውን ለመቋቋም የተደረገው ጥረት ጎልቶ አለመታየት ነው፡፡

ለጊዜው የገዳማቱ መቃጠል ምክንያት ምን እንደሆነ መንግሥት እስኪያሳውቀን ድረስ (ማሳወቅም ግዴታው ነው) ለጊዜው እንተወውና እንደዚህ ያሉ አደጋዎች እንዳይደርሱ ምን ጥንቃቄ ይደረጋል፤ ከደረሱስ በኋላ የፌዴራሉና የክልሉ መንግሥታት፣ ከዚያም አልፎ የአካባቢው ማኅበረሰብ ምን ማድረግ አለባቸው? ምንስ ሲያደርጉ ታይተዋል የሚለውን እንነጋገርበት፡፡

የአሰቦት ሥላሴም ሆነ የዝቋላ አቦ፣ ወይም የየረር ባዕታና የዋልድባና ሌሎች ዘመን ያስቆጠሩ ጥንታዊ ገዳማት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ንብረት ብቻ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ በአገሪቱ ክልል ውስጥ ያሉ ገዳማትም ሆኑ አድባራት በውስጣቸውም ያሉ ዕቃዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት ናቸው፡፡ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ተግባር የሚጠቀሙበት ቤተክርስቲያኗም ቢሆን በሃገር ቅርስነቱና ንብረትነቱ ግን የሁሉም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ መስጊዶች ራሳቸው መስጊዶቹም ሆኑ በውስጡ ያሉት ቅርሶች አምልኮት የሚፈፀምባቸው በሙስሊም ቢሆንም ንብረትነታቸው የሃገር ነው የሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ጥፋታቸው የሁሉም ጉዳት እንደሚሆን መረዳት ያስፈልጋል፤ እንዳይጠፋም መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

የገዳማቱ አፀዶች በሰፊው ሄክታር ደረጃ ተቃጥለዋል፡፡ በቃጠሎው ምክንያት ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው ደን ተጎድቷል፡፡ በውስጡ የነበሩት ብርቅዬ አራዊቶች አንድም ሸሽተዋል ወይም ሞተዋል፡፡ በውስጡ የሚኖሩት መናንያን እጣ ፈንታ አልታወቀም፡፡

ስለዚህ እንደጋራ ሃብትነቱ ጥፋቱን ሃይማኖትና ብሔር ሳይለይበት ልንጨነቅበትና ልንታደገው መረባረብ ያስፈልገናል፡፡ መንግሥትም የአስተባባሪነቱን ተግባር ለመወጣት ሁልጊዜም የድሃ ሃገር መንግሥት እንደሚያደርገው ወደ ሕዝቡ ችግሩን ማቅረብ አለበት፡፡

ሰሞኑን የተከሰተው በተለይም በአሰቦት ሥላሴ ገዳም የደረሰው የቀናት ቃጠሎ፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ባለመዘገቡ ወይም ሕዝቡ ሊመለከትና ሊያዳምጥ በሚችልበት ሁኔታ ባለመቅረቡ ሕዝቡ የራሱን ንብረት መጥፋትና መዳን እንዳያውቅ አድርጎታል፡፡ የሰደድ እሳትን ለማጥፋት የመንግሥት አቅም ቢያንሰው እንኳ ከጀርባው ሕዝቡን አሰልፎ ለቀጣይ ተመሳሳይ ጉዳት ለመዳን የሚቻልበትን መንገድ ለማዘጋጀት የሚያስችል ሙከራ ማድረግ አልቻለም፡፡ ወይም አልፈለገም፡፡ የሰው ሃይል ሊቋቋመው በሚችልበት ደረጃ እንዲያግዝ የአካባቢውን ሕዝብ ምን ያህል ማንቀሳቀስ እንደተቻለ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ይኸ ሁሉ ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ይመስለኛል፡፡ እንኳንስ የሃገር ንብረት ለሚባለውና የማንነታችን መገለጫ የሚሆኑት ቅርሶች ያሉበትን ቦታ፣ የግለሰብ ቤትና ንብረት “አደራ” ሰጥተን የተቀመጥነው ለመንግሥት አይደለምን? ነገር ግን ለአደራው የማይበቃ ከሆነ፣ አደራውን እንደሚጠብቅ እየማለ የጠፋውን ንብረት ለመግለፅ እንኳ ካፈገፈገ ልንነቅፈው አግባባችን ነው፡፡

በገዳማቱ የደረሰውን ቃጠሎ ለማዳን የተደረገውን ርብርብ እንደዚህ ነው ብለን ለመግለፅ የሚያስችለን መረጃ ስለሌለን ቃጠሎው መቼ እንደቆመና ወይም አለመቆሙን ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ግን ማወቅ የለብንምን?

በገዳማቱ አሁን የደረሰው የቃጠሎ ችግር በተለይ በአሰቦት በሌላ መልኩ ሊታይ ይችላል፡፡ ነፍስ ጠፍቷል፡፡ በየአድባራቱና በየመስጊዱ ያሉ ቅርሶች ሁሉ አንድ ጊዜ በዘራፊዎች አንድ ጊዜ በቃጠሎ ሲጠፉ ርግጠኛው አላማቸው ምንድን ነው? ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ እውነት በቅርሶቹ ውድነት የተነሳ ሊያገኙ በሚችሉ ገንዘብ ብቻ እየጎመዡ ከዚህ ሁሉ ጀርባ ማን አለ? እያሉ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

በገዳማቱ መቃጠልም ሆነ በቅርሶቹ መጥፋት ከላይ እንደገለፅሁት ሃይማኖት ሳይለየው ብሔር ሳይገድበው ለመጠበቅ መተባበር መነሳት አለበት፡፡ ሙስሊሙ የክርስቲያኑ ንብረት ነው፣ ብሎ ጥፋቱን ከማስቆም መቆጠብ የለበትም፡፡ ቦታው የሚገኘው በዚህኛው ብሔር ስለሆነ ያኛው አያገባኝም፤ ብሎ ተመልካች መሆን የለበትም፡፡ አለበዚያ ነገ ራስ ወዳዶች ወደሌላውም መራመዳቸው ስለማይቀር በተናጠል መጠቃት ይመጣል፡፡ የአንደኛው አለመኖር ለሌላው መዳከም የአንደኛው እድገት የሌላው ማግኘት መሆኑን ለመረዳት ሌላ ሚሌኒየም መጠበቅ የለብንም፡፡

ሃይማኖትን፣ ብሔርን ወይም ፆታን ለይተው ለሚነሱ ጥቃቶች የሁሉንም አብሮነት፣ የሁሉንም የተባበረ ክንድ መፍትሔ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ከላይ እንደገለፅሁት መተባበሩ ንብረትን ለማዳን ብቻ ሳይሆን ቀጣይ አደጋንም ከወዲሁ መቆጣጠር ያስችላል፡፡ የቀጣይ ትውልድን ድርሻም ማቆየት ይሆናል፡፡

የጥቃቱ መነሻ ምንም ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው ሁሉ ግምት እንዳለ ሆኖ እርስ በርስ በቤተክርስቲያኑ አገልጋዮችም መካከል ሊሆን ይችላል፡፡ ያም ቢሆን ”በገዛ ትዳሬ ውሃ ቢሞላበት ማን አገባው” አይባልም፡፡ አደጋውን ተቆጣጥሮ አጥፊውን ማጋለጥ ይገባል፡፡

በሃይማኖት ምክንያት ጥላቻ እንዲሰርፅና በሃይማኖት ስም እሳት የሚያቀጣጥሉ ሲኖሩ በመጀመሪያ ሊዋጓቸው የሚገባ የዚያው ሃይማኖት አባሎች ጭምር መሆን አለባቸው፡፡ የብሔር ጥላቻን አስፋፍተው ሕዝብ ከሕዝብ ለማጫረስ የሚፈለጉ ሲኖሩ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን መዋጋት የሚገባቸው በቅድሚያ የዚያው ብሔር ተወላጆች መሆን አለባቸው፡፡ ዘራፊዎችን በቅድሚያ ለማጋለጥ መሩዋሯጥ ያለባቸው የሚዘርፈው ዕቃ ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ወይም ቤተሰቦች ናቸው፡፡ አለበለዘያ በመነጣጠላችን ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁለ ቀዳዳዎቹን እያሰፉ ይጫወቱብናል፡፡ ተጫውተውብንም አይለቁንም፡፡ ይበጫጭቁናል እንጂ፡፡

በሃይማኖት ወይም በጎሳ፣ ወይም በፆታ ምክንያት የሚመጡ ጥፋቶችን በመተባበር እንኳንስ ራስ ወዳድ የሆኑ ቡድኖችን መንግሥትንም ማቆም እንደሚቻል በአዲስ አበባ የተፈፀመውን ድርጊት ማስታወስ ይቻላል፡፡

የመርካቶ ራጉኤል ቤተክርስቲያን በጊዜው በነበሩ የቤተክህነት ባለሥልጣኖችና የመንግሥት ባለስልጣኖች ፍላጎት ወደ እንጦጦ እንዲዛወር በታዘዘበት የደርግ ዘመን ወቅት ተቃውሞው የኃይል እርምጃ የተጨመረበት ነበር፡፡ የዚያን ዕለቱ ተቃውሞ ከክርስቲያኑ ጋር ተባብረው ድጋፉን የሰጠው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ነበር፡፡ በሁለቱ እምነቶች መተባበራቸው በጊዜው በሁሉም በእምነት ላይ አነጣጥሮ ለነበረው መንግሥት፣ ልብ እንዲገዛ አድርጎታል፡፡ ትክክለኛን ነገር ለመቃወም ሁሉም ካልተባበሩ በተናጠል እንደሚጠቁ ያን ጊዜ የተገነዘቡ ይመስላሉ፡፡

አሁን ከዳር እስከ ዳር በሚከበረው የሚሌኒየም በዓል ሁሉም የሃይማኖት መሪዎች፣ ሁሉም የክልል ባለሥልጣናት የሚናገሩት ተሰማምቶና ተፋቅሮ ተቻችሎ የመኖር አስፈላጊነትን ነው፡፡ ይኸ ሁሉ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን የመቻቻል አንዱ መገለጫ በኦሮሚያ አካባቢ ለተፈጠረው ችግር ወይም አደጋ፣ ሌሎች ክልሎች የጋራ ትብብር መግለጫ በመስጠት አይደለምን፡፡ በቤተክርስቲያንም ሆነ በመስጊድ ለሚደርስ አደጋ አንዱ ለሌላው የሚደግፍና ትብብርን የሚገልፅ መግለጫና ድጋፍ ሲያሳይ አይደለምን? በዚህ ረገድ በሦስቱም ገዳማት ለደረሰው አስጊና አደገኛ ጥፋት የሙስሊሙም ሆነ የፕሮቴስታንቱ የድጋፍና የትብብር መግለጫዎች ማውጣትና መረዳት ይገባቸዋል ባይ ነኝ፡፡ በአሁኑ ሁኔታ የታየው ግን ራሷ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያኗ ለምዕመናኖቿ የደረሰውን ጥፋትና አስጊ ሁኔታ በቤተክርስቲያን ስትገልፅ አልተሰማችም፡፡

ገዳማቱ የአሉበት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው፡፡ ኦሮሚያ በሥሩ የሚያስተዳድራቸውን ተቋሞች (እንደ ተራ ተቋም የሚታዩ አለመሆናቸውን እያሰብን) ተደፍረዋል፡፡ ለአካባቢው ሊያግዝ የሚችለው ደኑ በስፋት ተቃጥሎበታል፡፡ በውስጡ ያሉ አራዊት ተጎድተዋል፡፡ ገፋ ብለን ካሰብንም በውስጡ የሚኖሩት መናንያን እጣ ፈንታ አስጊ ነው፡፡ ስለዚህ ለኦሮሚያ ክልል ከየክልሎቹ የድጋፍ መግለጫ ሊላክለት ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት መተጋገዝ በሰለጠኑት አለማት የሚሰራበት ነው፡፡ አላማውም ድርጊቱን ማውገዝ አጥፊዎቹን የሥነ አእምሮ ጫና ሊፈጥርባቸው ሲችል የሕዝቦችንም የጋራነት ሊያጠናክር ይችላል፡፡ ነገር ግን ራሱ የኦሮሚያ ክልል ስለአደጋው በሚዲያዎች ሲገልፅ ስላልሰማነው ሌሎች ክልሎች ምን ሊሉ ይችላሉ?

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ባለአደራ የመሳሰሉት ተቋሞችስ የመንገድ ወሬ እየሰሙ መቀመጥ አለባቸውን፤ የቅርሶቹ ቦታዎች እየጠፉ ካለቁ እነሱ በማን ላይ ሊሾሙ እንደሚችሉ አስበውታል? በእርግጥ ዛሬ የተወሰኑት ስለሆኑ ሌሎች ቅርሶችና የቱሪዝም መስህቦች ካሉ አንነቃነቅም ብለው አስበው ይሆናል? ይኸ ዓይነት ሂደት መቆሚያው ካልተገደበለት መጨረሻው የት ሊሆን እንደሚችል ያጤኑት አይመስለኝም፡፡

በሙቀቱ ሃይል የተነሳ ቃጠሎ ገዳማቱን እየመረጠ አቃጥሏል ቢባል እንኳ የፀሐይ ሙቀት፣ ሌሎችንም ገዳማት እንዲያቃጥላቸው፣ የፀሐዩ ሙቀት ሌሎቹንም የዱር አራዊት መገኛ ቦታዎች እንዳይለበልባቸው ምን ታስቧል መባል አለበት፡፡ ለተጎዱት በምን ያህል ፍጥነት እንደርስላቸዋለን? ብለን ማሰብም አለብን፡፡

አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን ፊት ለፊት ለመነጋገር አለመቻላችን የበለጠ ጉዳት እየጋበዘ ይመስለኛል፡፡ በእምነት ስም፣ በብሔር ስም የሚደረጉ ጥፋቶችን ፊት ለፊት ለመነጋገር የማይነካ (taboo) እያደረግነው “ስሜት ያስቆጣል” እየተባለ በድብቅ በተያዘ ቁጥር ለአጥፊዎቹ ይመቻል፡፡ መደበቂያ ዋሻም ይሆናል፡፡ በመጨረሻ ቅሬታውና ቂሙ በመንግሥት ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ይቀራል፡፡

ስለዚህ መፍትሔው ቀላልና አጭር ነው፡፡ ሁሉም ካልተባበረ ግን ችግሩ ለሁሉም ይተርፋል፡፡ ከተባበረ ግን ሁሉም አሸናፊ ሆኖ ችግሩ ይቀንሳል፡፡ እንደፈሪ ሰውም አንዳንድ አካሉን እያስበላና እያስቆረጠመ ቆይቶ በመጨረሻ ራሱ ይበላል፡፡
 
< Prev   Next >