| “ልናክምህ እንችላለን እንጂ... |
|
|
| Wednesday, 02 April 2008 | |
|
“ልናክምህ እንችላለን እንጂ ማዳን አንችልም ብለው ደብዳቤ ላኩልኝ”
ታምራት ሞላ ድምፃዊ ታምራት ሞላ ከ1955 ዓ.ም ጀምሮ በሙዚቃው ዓለም ውስጥ እንዳለ ነው፡፡ በሕዝብ ዘንድ ዝናን ካተረፈባቸው ዘፈኖቹ መካከል “ታምሜ ተኝቼ” እና “ሰበቡ” ይጠቀሳሉ፡፡ የአምስት ልጆች አባት የሆነው ታምራት በአሁኑ ጊዜ ጤናው በከፍተኛ ደረጃ ታውኳል፡፡ በጤንነቱና በሙያው ዙሪያ ሔኖክ ያሬድ አነጋግሮታል፡፡ ጤንነትህ እንዴት ነው? - አሁን ደህና ነኝ፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ጠበል እየተጠመቅኩ ነው፡፡ እንቀሳቀሳለሁ፣ እመገባለሁ፡፡ የበሽታው ዓይነት ከበድ ይላል፡፡ የደም ካንሰር ሉኪሚያ ነው፡፡ ክሮኒክ ሆኗል ብለውኛል፡፡ ታይላንድ ጥሩ ነው ብለውን ስንጽፍ በየሦስት ሳምንት 10..000 ዶላር እየከፈልህ ልናክምህ እንችላለን እንጂ ማዳን አንችልም ብለው ደብዳቤ ላኩልኝ፡፡ ለሕክምናው ምን ያህል ያስፈልግሃል? - እስከ 600,000 ዶላር ያስፈልጋል ነው የሚሉኝ፡፡ በእኔ አቅም ይህን ያህል ገንዘብ ሊኖረኝ ቀርቶ ጽፌውም አላውቅም፡፡ እግዚአብሔር የፈቀደውን ያደርጋል፤ መቼ ነው ሕመሙ የጀመረህ? - ሲጀምር ከአምስትና ስድስት ዓመት በፊት ሰውነቴ (አካላቴ) እየቀነሰ ይመጣል፡፡ ብዙ ሰዎች ስኳር ይዞሃል ወይ ይሉኛል፡፡ እኔ ደግሞ አልኮል ጠጥቼ አላውቅም፡፡ ብዙ ጊዜ ምግቤ ከማር የተለየ አይደለም፡፡ የስኳር ምልክት የሚያሳየኝ ምንም ነገር የለም ብዬ ችላ ስለው ጓደኞቼ ሐኪም ወስደውኝ ስመረመር ስኳር የለብኝም፣ ኩላሊቴ፣ ጉበቴም፣ ሳምባዬም፣ ጣፊያዬም ንጹህ ነው፡፡ ምንም የሚያሰጋህ ነገር የለም፡፡ ግን የነጭ ደም ሴልህ በጣም በዝቷል ብለው ወደ ሌላ ሐኪም ላኩኝ፡፡ የአንድ ሰው ነጭ ደም ሴል ከ5 እስከ 10 ሺህ መሆን ይገባዋል፡፡ የእኔ ግን 225 ሺህ ሆኗል፡፡ ስኳር የለብህም ስባል ደስ አለኝ፡፡ ትልቅ በሽታ ነው ብዬ አላሰብኩትም፡፡ እንደገና ስመረመር ለጊዜው የሚረዳህ ብለው መድኃኒት አዘዙልኝ መድኃኒቱን ስወስደው ጠቅላላ ውስጤ ጉበቴም፣ ኩላሊቴም አበጠ፡፡ ጣፊያዬ በጣም አብጦ ወደ ውጭ ወጣ፡፡ ተሰቃየሁ፤ በረዶ ሆዴ ላይ እያደረግሁ ነበር የምተኛው፡፡ 12 ቀን በተከታታይ መድኃኒቱን ስወስድ ልሞት ሆነና አቆምኩት፡፡ አንተን ለመታደግ ውጭ ሀገር ያሉ አርቲስቶች ሲዲ እየሸጡ መሆናቸውን ነግረኸኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥስ ምን እየተደረገ ነው? - እስከ አሁን ድረስ የሚደረግ ምንም እንቅስቃሴ የለም፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮው ንሮ ከአቅም በላይ የሆነበት ጊዜ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ሊረዳ የሚችልበት ጊዜ አይደለም፡፡ በጀርመን ራዲዮና በአሜሪካው ቪኦኤ የሰሙ ሰዎች ምን እንርዳ እያሉ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ በስሜ ሂሳብ ከፍቻለሁ፡፡ በዚያ የሚመጣውን አላውቅም፡፡ የሙያ አጋሮችህ አርቲስቶቹ ይጠይቁሃል? - በአገር ውስጥ ያሉት ብዙዎቹ የሰሙ አይመስለኝም፡፡ የሰሙት ምኒልክ ወስናቸው፣ አብራር አብዶ፣ የዱሮ ጓደኞቼ እነ ጥላዬ ጨዋቃ፣ አመሃ ተወዳጅ እየመጡ ይጠይቁኛል፡፡ ወጣት አርቲስቶቹ ግን ሁልጊዜ ማታ ስለሚያመሹ የሰሙ አይመስለኝም፡፡ እስካሁን መጥቶ የጠየቀኝ የለም፡፡ የሙዚቀኞች ማኅበር፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መረዳጃ ማኅበር የሚባሉ አሉ፡፡ እነሱስ ምን ምላሽ ሰጡ? - የሙዚቀኞች ማኅበር ገና ራሱን ያላቋቋመና ምንም የሌለው ነው፡፡ የሙዚቃ ማኅበሩ ከአርቲስቱ መዋጮ አገኛለሁ ብሎ ነው ሲመሠረት፣ ዛሬ ብዙ አባል ያለው አይመስለኝም፤ ይህን ያህል የተጠናከረ አይደለም፡፡ ማሕሙድ ሊቀመንበር እኔም አባል የሆንኩበት መረዳጃ ማኅበር ነበር፡፡ እርሱ የተወሰነ ሥራ ሠራንና ሥራ ላጡ፣ ሸምግለው ለወደቁ ያገኘናትን ትንሽ ገንዘብ ለእነርሱ አከፋፈልን፡፡ ምንም ነገር የለውም፡፡ አይንቀሳቀስም እንደቆመ ነው፡፡ ከፍተኛ ባለሀብቶች ሲረዱ እንሰማለን፡፡ እነርሱን ለማግኘት የቻልክበት አጋጣሚ የለም? - እስካሁን ድረስ ከማንም ጋር ግንኙነት አላደረግሁም፡፡ የሙያ ጓደኞቼ እነ ጥላሁን፣ ማሕሙድ፣ ታማኝ በውጭ ሲዲዬን እየሸጡ እየተሯሯጡ ነው፡፡ በጣም እንቅስቃሴ ያለው አሜሪካ ነው፡፡ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እየደወሉ በአስቸኳይ ሲዲው ይላክልን እያሉ ነው፡፡ አባዝታችሁ በየአገሩ ላኩ ከማለት ውጪ በእኛ አገር ካሉ ባለሀብቶች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ወይም ንግግር የለኝም፡፡ እዚህ ካሉት፣ አብረውህ ከነበሩት አርቲስቶች ዝግጅት ለማስተባበር፣ እርዳታ ለመጠየቅ፣ የሙዚቃም ሆነ ሌላ ዝግጅት ለማድረግ የሞከረ የለም? - አለ፡፡ ድምፃዊ አያሌው መስፍን ከእኔ በላይ አስቦበታል፡፡ መታመሜን በኢንተርኔት መልዕክት ለመጀመሪያ ጊዜ አሜሪካ ያስተላለፈው እርሱ ነው፡፡ ብዙ እየደከመ ነው፡፡ የተወሰነ ትርዒት ቢታይ ወይም ትላልቅ ሆቴሎች አስፈቅዶ አድናቂዎች የሆኑ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እየተሯሯጠ ነው፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ያለው የኑሮ ደረጃ ስለማያወላዳ አርቲስቶች ሲታመሙ በተደጋጋሚ ሥራ ቢሠራም አመርቂ የሆነ ነገር ተገኝቶ አያውቅም፡፡ የአገር ውስጥ ሚዲያ ስለ አንተ መታመም ምን ያህል ሽፋን ሰጥቶታል? - በኤፍ ኤም አዲስ 97.1፣ ኤፍ ኤም 98.1፣ ኤፍ ኤም 90.7 አስተላልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ግን ጠይቀውኝ አያውቁም፡፡ የዱሮ ዘፈኖችህ ሲዲ ሽያጭ ሪፖርት ልከውልሃል? - ለመጀመሪያ ጊዜ ሲደውሉልኝ አብርሃም ብዙነህ የሚባል ዱሮ ሙዚቃ የሚቀርጽ በገዛ ፈቃዱ ሁሉንም ወጪ ሸፍኖ አንድ ሺህ ሲዲዎች አሳትሞ ለጓደኞቼ በነፃ ሰጥቶ እየተሸጠ ነው፡፡ እየደወሉ አይዞህ እያሉኝ ነው፡፡ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ እስካሁን የማውቀው ነገር የለም፡፡ በሙዚቃው ዓለም ስንት ዓመት ቆየህ? - የሙዚቃውን ዓለም ከ45 ዓመት በላይ አገልግያለሁ፤ ድምፃዊነቱን የጀመርኩት ከ1955 ጀምሮ ነው፡፡ መጀመሪያ ዘፋኝ ሳልሆን በ1953 ዓ.ም በክብር ዘበኛ ሠራዊት ውስጥ የልጅ ወታደር የሚባል ከትምህርት ቤት ጠፍቼ ገባሁኝ፡፡ አንድ ዓመት እንኳን ሳላገለግል በታኅሣሥ ግርግር ሲበተን እኔም አንደሌሎቹ ተበተንሁ፡፡ ወደ ምድር ጦር ገባሁና በ1955 ዓ.ም ዘፋኝ ሆንኩ፡፡ ያን ጊዜ ጦር ሠራዊት ኦርኬስትራ ነበር የሚባለው? - ተነቃናቂው የምድር ጦር ኦርኬስትራ ነበር የሚባለው፡፡ በዚያን ዘመን ብዙዎቹ ኦርኬስትራዎች ኖታ ከፊታቸው ደርድረው ቁመው ነበር ሙዚቃ የሚጫወቱት፡፡ በእኛ ግን ኖታው ተጠንቶ ይጫወቱ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ምድር ጦር ኦርኬስትራ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ነበር፡፡ ኖታውን በጭንቅላታቸው ይዘው፣ አጥንተው፣ እንደተወዛዋዥ ሲሰሩ ስለነበር ተነቃናቂው ኦርኬስትራ ተብሏል፡፡ በድምፃዊ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው እነ ጥላሁን ገሠሠ ብዙነሽ በቀለ የያዘው ክብር ዘበኛ ሲሆን፣ በሴቶች ተወዛዋዦች ፖሊሲ ሠራዊት የተሻለ ነበር፡፡ ዘመኑ የውድድር ነበር፡፡ በ1957 አሸናፊ ሆኜ ዋንጫ ተሸልሜያለሁ፡፡ በፎቶህ ላይ እንዲሁም በቴሌቪዥንም እንዳየነው አደናነስህ፣ መድረክን የመያዝ ችሎታ አለህ፡፡ ሕይወት ትሰጠዋለህ አለባበስህ ዘናጭ፣ እንቅስቃሴህ ልዩ ነው፤ - ሰው እንደ እይታው ነው፡፡ በእነጥላሁን ገሠሠ፣ በእነምኒልክ፣ በእነዓለማየሁ ደረጃ የምቆጠር አይደለሁም፡፡ ወጣትነት አለ፤ በሙዚቃም ትገዛለህ፤ መድረክ ላይ ስወጣ ራሴን የምረሳበት ጊዜ አለ፡፡ ጨርሰህ ስትወጣ ሰው ሲያደንቅህ፣ ሲያጨበጭብልህ ነው የምታውቀው እንጂ ያን ጊዜ አታውቀውም ስሜት ውስጥ ትገባለህ፡፡ የተለየ ነገር ኖሮኝ አይደለም ከእኔ የተሻሉ የበለጡ ዘፋኞች አሉ፡፡ በዚያን ዘመን ከአቅሜና ከሥራዬ በላይ የሆነ ስም ነበረኝ፡፡ ጥላሁን ገሠሠን ለማየት እግዚአብሔር ከምድር የወረደ ያህል ይቆጠር በነበረ ጊዜ፣ ጥላሁን ገሠሠን የሚያስንቅ ዘፋኝ ብለው በጋዜጣ ላይ ጽፈው ነበር፡፡ ያ መንፈሴ የሚቀበለው አይደለም፡፡ እንኳን ያን ጊዜ አሁንም የጥላሁን እኩያ አይደለሁም፡፡ ጥላሁንን እከሌ የሚባል ዘፋኝ የሚተካው አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ለሞራልህ ድጋፍ ይሰጥሃል፡፡ እንድትራመድ ያደርግሃል፡፡ በሙያው ላይ ወደፊት እንድትቀጥል ያደርግሃል፡፡ ዘመናዊ ሙዚቃ ብቻ አይደለም ባህላዊ አሻራም አለህ፡፡ በርኖስ ለብሰህ የተጫወትከው “ሰበቡ” ትዝ ይለኛል፤ - ያን ጊዜ ዘመናዊ ኦርኬስትራ ባህሉንም አካትቶ ነው የሚሠራው፡፡ ባህሉን እነ “ሰበቡን”፣ “የሾላ ፍሬ ነሽ” የመሳሰሉ ባህላዊ ዘፈኖች በዘመናዊ ኦርኬስትራ እንሠራ ነበር፡፡ ለባህላዊ ሙዚቃ ቀረቤታ ነበረኝ፡፡ ጎንደሬ ነኝ፡፡ ጎንደር ደግሞ የዜማ አገር ነው ይባላል፡፡ የያሬድ ልጅ ነኝና በቤተ ክርስቲያን ትምህርት የገፋ እውቀት ባይኖረኝም ከሕፃንነቴ ጀምሮ እየሰማሁ ያደግሁ ነኝ፡፡ የሙዚቃ ሸክላና ካሴቶች ምን ያህል አሳትመሃል? - በእኛ ጊዜ ሸክላ ይህን ያህል ዋጋ አለው ተብሎ አይታሰብም፤ ትልቅ ሪል ክር ነበር፡፡ ለሽያጭ የሚሆን ነገር የለም፡፡ የሚያሳዝነው የእኛ ራዲዮና ቴሌቪዥን ያኔ በነፃ የሰጠናቸውን ዘፈን ዛሬ ለአንዳንድ ጉዳይ ፈልገን ስንጠይቃቸው ገንዘብ ክፈሉ ይሉናል፡፡ በሌላው በሰለጠነው ዓለም ያንተ ሙዚቃ በራዲዮ ወይም በቴሌቪዥን ሲተላለፍ በፕሮግራም በተዘፈነበት ደቂቃ ይከፈላል፡፡ ያ እንኳ ቀርቶብን የራሳችን ሙዚቃ መልሰን ከልሰን በካሴት እናውጣው ወይም ደግሞ ለአንዳንድ ነገር እንሥራው ስንላቸው በጎ ፈቃደኝነት የላቸውም፡፡ በሸክላ ደረጃ ስድስት፣ በካሴት ሰባት ያህል የታተሙ ሥራዎች አሉኝ፡፡ በተለይ በካሴቱ ዓለም ዘግይቼ ነው የጀመርኩት፡፡ ከአብዮቱ ፍንዳታ በኋላ አብዮታዊ ሙዚቃዎችን እንዘፍን ስለነበር ሙዚቃ መነገድና ብዙ ጊዜ የፍቅር ዘፈን መዝፈን አልተፈቀደልንም፡፡ እኛ በተከለከልንበት ጊዜ ከውጭ ያሉት እንደልባቸው በመሆናቸው ስም አገኙበት፡፡ በሙዚቃ ሙያህ ተጠቅመህበታል? - እኛ ዕድለኞች ነን፤ ሕዝብ ከጎናችን አለን፡፡ አልተጠቀምንበትም፡፡ ሕዝብ ግን ስንጠቅም ኖረናል፡፡ ለአገራችን ከጦር ግንባር እስከ መሐል ከተማ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር ለቅስቀሳ ተንቀሳቅሰናል፡፡ ሁለተኛ ለመስከረም ዘመን መለወጫ የምታቀርበው ሙዚቃ ሰው ይቀበለኝ ይሆን? እያልክ ትጨነቅበታለህ፡፡ ከሙዚቃህ አልፎ ከአለባበስህ ጭምር ነው የሚጠብቅህ፡፡ በሙዚቃ ሕይወትህም ሆነ በሌላ ያዘንክበት ጊዜ አለ? - ብዙ ሰው እኛ ስለምንዘፍን ደስተኞች ነው የምንመስለው፡፡ እኛ ግን ከደስታችን ሐዘናችን ይበልጣል፡፡ ሕዝብ አጨብጭቦ ሲቀበለን ብንደሰትም ከሕዝብ ተለይተን ወደ ቤታችን ስንመለስ ግን ኑሯችንን ስናየው በዚህ ሙያ ምንድን ነው የተጠቀምነው? እንላለን፡፡ ከልጆቻችን እንኳ አንዱ ሙያውን የሚፈልግ የለም፡፡ አንተ እንዲህ ሆነህ እያየሁ ምንድን ነው ብሎ ነው ምላሽ የሚሰጠው፡፡ አልገባቸውም እንጂ የእኛ ጊዜና አሁን ይለያያል፡፡ አሁኑ ጥሩ ነው፡፡ የሚረባም ይሁን የማይረባ መገናኛ ብዙሃኑ አጯጭኸው ልጆቹ ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ ተፈጥሯል፡፡ የሚያሳዝነኝ ሙዚቃችን ወደ ኋላ እየሄደ ነው፡፡ የእኛ አገር ችግር ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዓለምም ያለ ነው፡፡ ከውጪ ራፕ የሚባል ንግግር አትለው ሙዚቃ አትለው እየመጣ ነው፡፡ ሙዚቃውን አርሞ ይኼ ይህን ይመስላል፣ ይኼ ደግሞ መልዕክት የለውም ብሎ የሚያርም ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ቋንቋ ባህልና ሙዚቃ ባላት አገር የራፕ ስልት ገብቶ ሙዚቃውን እየቀየጠና እያበላሸ በመሆኑ አዝናለሁ፡፡ በእናንተ ጊዜ በትልቅ ባንድ (ኦርኬስትራ) ነበር፡፡ አሁን ግን በአንድ ኪቦርድ ነው የሚያልቀው፤ - ዋነኛው ችግር እርሱ ነው፡፡ ሁሉም የሚተቸው ነው፡፡ ዛሬ ቴክኖሎጂ አድጎ የሰዎች ድምፅ ማጣፈጫ እየተደረገላት ክር ላይ ይወጣል፡፡ ያን ክር ስትሰማው ጥሩ ነው ትላለህ፡፡ ዘፋኙን መድረክ ላይ ስታመጣው ግን ከዚያ ጋር አይመሳሰልም፡፡ እኛ እኮ በንግግር ማይክራፎን ነው የዘፈንነው፡፡ የተፈጥሮ ድምፃውያን ነበሩ፡፡ አሁን ግን እስቲ ልሞክረው፣ ካሴት ላውጣ ነው፤ ያልታሰበ ሰው እዚያ ላይ ታገኘዋለህ፡፡ በዚህ ዕድሜዬ የምሽት ክበብ መጫወት አይገባኝም ነበር፡፡ ደሃ ስለሆንኩ ምሽት ክበብ እሠራለሁ፡፡ ስሠራ አንድም አዳዲስ ዘፈን ሳይሆን የድሮ የነጥላሁን፣ ዘፈኖችን ነው ሕዝቡ የሚጠይቀው፡፡ ይኸ ምንድን ነው የሚያሳየው ሙዚቃው ምን ያህል አንድ ቦታ ላይ እንደቆመ ነው፡፡ የሙዚቃ ማኅበር ሥራዎች በጥራት የሚወጡበትን መንገድ መተለም ቅንብሩን መከታተል ይገባዋል፡፡ በምድር ጦር እያለሁ አንድ ዘፈን እደርሳለሁ፡፡ ለአቀናባሪው ካቀረብኩለት በኋላ በክፍላችን ኮሚቴ ተቋቁሞ ይገመግመዋል፡፡ ጣዕም ያለው ዘፈን ተዘጋጅቶ ዘፈኑና ዘፋኙ ተገናኝተው ሲቀናበር መልዕክቱ ጥሩ ይሆናል፡፡ አሁን ግን አንድ ግጥም ሲቀርብ ዜማው ከተለያየ ቦታ ይወሰድና ይቀርባል እንጂ ሕዝብ ምን ይለናል? ለሕዝብ ምንድን ነው የምናቀርበው? የሚለው ቀርቷል፡፡ በዚህ ምክንያት የሙዚቃው እድገት ቆመ፡፡ ሕይወቴን ችግር ውስጥ ያስገባሁበት ሙያ ነው፡፡ ከቤተሰብ የተራራቅኩበት ሙያ ስለሆነ ሲወድቅ ማየት አልፈልግም፡፡ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ምሁራንና የሙዚቃ አዋቂዎች አንዳንድ ነገሮችን ካላስተካከሉ የወደፊቱ የኢትዮጵያ ሙዚቃ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው የሚደርሰው፡፡ ያስደሰተህስ? - በወጣትነቴ ያሳለፍኩበት ዘመን ያስደስተኛል፡፡ የሕዝብ ፍቅር ዛሬም አብሮን አለ፡፡ ይንከባከበናል፡፡ ድህነቱና ችግሩ አይሰማንም፡፡ ደግሞም ደሀ አይደለንም፡፡ የሰለጠነውን አገር አርቲስቶች እያየን ነው፡፡ የላዩን ብቻ ማየት ሳይሆን ወደ ታች መመልከትም ይገባል፡፡ በሙዚቃ ሥራዎችህ መካከል ለየት ያለ ያጋጠመህ ነገር አለ? - “ሰበቡ” ጥንታዊና ሕዝባዊ ዘፈን ነው፡፡ ግጥሙን ሲራክ ታደሰ ሲጽፈው ቤት አይመታም፡፡ ሻምበል ታደሰ የሚባል አለቃችን አመጣውና አጥኑ ተባለና ከሌሎቹ እኔ ተሽዬ ተገኘሁ፡፡ ቤት የማይመታ ግጥም ስለሆነና በጋዜጣና በራዲዮ ልታሰድቡኝ ነው ብዬ በተደጋጋሚ አልሠራም በማለቴ ተከስሼ ከ60 ብር ደመወዜ በተለያየ ጊዜ 15 ብር ቅጣት ተጣለብኝ፡፡ እምቢተኝነቴን ያዩ ጓደኞቼ ምንቸገረህ ጋዜጠኞች ቢተቹህ ታዝዤ ነው ትላለህ ብለውኝ ተስማምቼ ተጫወትኩት፡፡ ያልጠበቅኩት ነገር አጋጠመኝ፡፡ የዓመቱ ኮከብ ዘፈን ተብሎ በጋዜጣ ወጣ፡፡ 50 ብር ደሞዝ ተጨመረልኝ፡፡ አሁን በምንድን ነው የምትተዳደረው? - ጡረታ ወጥቻለሁ፡፡ አሞኝ እስከተኛሁ ድረስ ምሽት ክበብ እሠራ ነበር፡፡ ከአርባ ዓመት በፊት የሠራሁትን ዘፈን በዱሮው ደረጃ ነው የምሠራው፤ ለውጥ የለውም፡፡ ምክንያቱም ሱሰኛ አይደለሁም፡፡ አልጠጣም፣ አልቅምም፣ አላጨስም፡፡ ይህም አስተዋጽዖ ያለው ይመስለኛል፡፡ ከታመምሁ በኋላ ምሽት ክበብ አልሠራም፤ ከቤቴም አልወጣም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |