| የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን... |
|
|
| Wednesday, 02 April 2008 | |
የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የግዢ ሥርዓት ተተቸየኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የግዢ መመሪያ እንደሌለው የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥናት አመለከተ፡፡ ኮርፖሬሽኑ በበኩሉ ቀድሞውንም የግዢ ደንብ እንዳለው፣ አዲስ ደንብ በመጋቢት ወር እንዳፀደቀ አስታውቋል፡፡ ጥናቱ እንደሚያመለክተው የኮርፖሬሽኑ 80 በመቶ ግዢ የሚከናወነው ከአገር ውጭ ነው፡፡ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ በሚካሄድ ግዢ የግዢ ደንብ አለመኖሩ አሰራሩ ለሙስና የተጋለጠ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ግዢ ላይ ችግር ቢገኝ እንኳ አጥፊውን አካል ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል የፀደቀ ደንብ የለም፡፡ የመንግሥት የግዢ ደንብ ማነቆ እንደሆነ ኮርፖሬሽኑ በተደጋጋሚ እንደሚገልፅ የገለፀው የጥናቱ ክፍል "በአገር ደረጃ የመጣን መመሪያ ለመቀየር ወይም ለማሻሻል ፈቃጅ አካል እንዲፈቅድ ካልተደረገ ግለሰቦች እንደፈለጉ እንዲያዙበት ያደርጋል" ሲል የኮርፖሬሽኑን ምክንያት ለመቀበል ያዳግተዋል፡፡ ሃያ በመቶ ለሚሆነው የአገር ውስጥ ግዢ እንኳን የፀዳ የግዢ ደንብ ግልፅነትና ተጠያቂነትን አስፍኖ አለመዘጋጀቱ በጥናቱ ተካቷል፡፡ ጥናቱ ከተካሄደ በኋላ ከኮርፖሬሽኑ ማኔጅመንት አካላት ጋር ውይይት መካሄዱን የገለፀው አንድ ለጥናቱ ቅርበት ያላቸው "ኮርፖሬሽኑ አለኝ የሚለውን የግዢ ደንብ በመረጃነት ለማቅረብ ተቸግሯል" ብለዋል፡፡ አያይዘውም ኮርፖሬሽኑ ሲፈልገው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የግዢ መመሪያ፣ ሲፈልገው አሻሻልኩት የሚለውን፣ ሲፈልገው የዓለም አቀፍ ደንቦችን በመጥቀስ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ግዢ እንደፈለገ ሲያከናውን መቆየቱን አመልክተዋል፡፡ ኮሚሽኑ የመንግሥት የግዢ መመሪያ መከተል ካልተቻለ በሚል ባቀረበው አማራጭ ለፈቃጁ አካል ቀርቦ አንድ የግዢ መመሪያ መፅደቅ እንዳለበት ይጠቁማል፡፡ በሌላም በኩል ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የግዢ ደንብ ተዘጋጅቶ ሳይፀድቅ መቆየቱንም ይወቅሳል፡፡ የኮርፖሬሽኑ የማቴሪያልና የሎጀስቲክ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አባይነህ ኮርፖሬሽኑ የግዢ ደንብ እንዳለው ገልፀው "በቅርቡ ከፀደቀው በተጨማሪ የተሻሻለ አዲስ ደንብ በመጋቢት 2008 ፀድቋል" ብለዋል፡፡ 80 በመቶ ሳይሆን አብዛኛው የኮርፖሬሽኑ ግዢ ከውጪ አገር እንደሚከናወን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ "ማንኛውም መስሪያ ቤት የግዢ ደንብ ሲያወጣ ዋናውን የመንግሥት የግዢ ደንብ የሚቃረን ከሆነ መስሪያ ቤቱ የለም ማለት ነው፡፡ እኛም ይህንን አድርገን ከሆነ አለን ሊባል አይችልም" ሲሉ በጥናቱ ላይ መገለፁ ተጠቅሶ ለተጠየቁት መልስ ሰጥተዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ባካሄደው የአሰራር ማሻሻያ መሰረት ሰፕላይ ቼይን ማኔጅመንት (Suply chain management) ግምጃ ቤት፣ ግዢና ፋይናንስ በመቀላቀል የክፍያ አፈፃፀምን የማቀላቀል ሥራ በአዲሱ የግዢ ደንብ መካተቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ "የአገሪቱ የግዢ ሕግ ለአገሪቱ ሊጠቅም ይችላል፡፡ እንደ ዓለም ባንክ ዓይነት አበዳሪ ድርጅት ሲያበድር ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስገዳጅ ሁኔታ በአገሪቱ የግዢ ሕግ ሊስተናገድ አይችልም" ያሉት አቶ አለባቸው ይህም ቢሆን ግዢን በጥንቃቄ ከማስኬድ አንፃር ኮርፖሬሽኑ የሚወቀስ ሳይሆን ለሌሎች አርአያ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ "የግዢ ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ነው? ለሙስና በር አይከፍትም? ተብለው ለተጠየቁት "የአሰራር ስርዓታችን ሳይሆን ግለሰቦች የአሰራር ስርዓቱን በመጣስ ሊያበላሹት ይችሉ ይሆናል" በማለት ዳይሬክተሩ መልስ ሰጥተዋል፡ የፌዴራል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በኮርፖሬሽኑ የግዢ ሥርዓት ላይ ያጠናውን ጥናት በቅርቡ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ያጋጠመውን የኃይል ችግር እንዳይባባስ በቁጠባ መጠቀም የሚያስችል የጥናት ሃሳብ ዛሬ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለዚሁ ጉዳይ የተሰየመው አጥኚ ቡድን በጥናቱ ኤሌክትሪክ በፈረቃ ከመጠቀም በተጨማሪ ሌሎች ርምጃዎች እንዲወሰዱ ሃሳብ ያቀርባል፡፡ አሁን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በፈረቃ በመጠቀም ብቻ ሊያስቀጥል የሚችል አለመሆኑን ምንጮች ገልፀዋል፡፡ የኃይል አቅርቦቱና የፍላጎቱ አለመጣጣም ሥጋት ማሳደሩንና በየግድቡ ካለው ውሃ ከፍተኛ መጠን እንደሚተን ተናግረዋል፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |