| ከእንጨት ፈላጭነት እስከ. . . |
|
|
| Wednesday, 02 April 2008 | |
![]() አቶ ሙሰማ ሽፋ የእግር ኳስ ሜዳ ተብሎ የታጠረውን ቦታ ከለቀቀ በኋላ ለቆርቆሮ ቤትና አጣናዎች ለተቀመጡበት ቦታ ለግለሰብ በወር አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር እየከፈለ ሥራውን እንደቀጠለ ከአቶ ሙሰማ ንግግር ለመረዳት ችለናል፡፡ ለዚሁ ቦታ በወር ሁለት ሺህ ብር ግብር እንደሚከፍልም ገልጿል፡፡ ቀደም ሲል ገጠር፣ ግብርና ከዚያ በኋላ ደግሞ ለአራት ዓመታት ያህል በየመንደሩ እየዞረ የማገዶ እንጨት ፈልጧል፡፡ በዚያ ጊዜ ያገኝ የነበረው ገቢ ከእለት ጉርሱ አልፎ ተቀማጭ ለመቆጠብ የሚያስችል ስላልነበር በቤተሰብ ድጋፍ ሳሪስ አዲስ ሰፈር የማገዶ እንጨት፣ አጣናና ችርቻሮ ከሰል መነገዱን በስፋት ጀመረ፡፡ ይህን ሥራ በጀመረበት ወቅት አዲስ ሰፈር ውስጥ የበርካታ ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ ስለነበር ለቤት መሥሪያ የሚሆኑ አጣናዎች ብዙም ፈላጊ አልነበራቸውም፡፡ ነገር ግን ያልተጠናቀቁ ቤቶችን ለመጨረስና ሰርቪስ ቤቶችን ለመስራት የተወሰኑ ግለሰቦች አጣና ይገዙት እንደነበር አቶ ሙሰማ አልደበቀም፡፡ “አጣናም ሆነ የማገዶ እንጨት መሸጥ በጀመርኩበት ወቅት አዲስ ሰፈር ውስጥ ያሉ ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ኮርኒስ ለማስጨረስና ሰርቪስ ቤቶች ለመስራት ይንቀሳቀሱ ነበር” ብሏል፡፡ የሚሰሩት ከታናሽ ወንድሙ ጋር ሲሆን የአቶ ሙሰማ ድርሻ ከፍ ይላል፡፡ አቶ ሙሰማ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ሲሆን ታናሽ ወንድሙም ባለትዳር ነው፡፡ የሚኖረው እዚያው አዲስ ሰፈር ሲሆን ወንድሙ ደግሞ የመሸጫ ሱቁ ውስጥ ይኖራል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እንጨት የሚያመጡት ክፍለ ሀገር ነው፡፡ አጣናዎቹ የሚመጡት ምንም እንኳ ከክፍለ ሀገር ቢሆንም የሚገዙት ከነጋዴ ላይ በመሆኑና ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት ለትራንስፖርት የሚወጣው ገንዘብ ከፍተኛ ስለሆነ ሥራው አትራፊ ነው ለማለት እንደማይቻል አስረድቷል፡፡ የአካባቢውን ኅብረተሰብ የማገዶ ፍላጎት በማስመልከት፣ የአካባቢው ኗሪ በእለት ከእለት እንቅስቃሴው የኤሌክትሪክ ኃይል የመጠቀም አማራጭ ቢኖረውም ለማገዶ እንጨት ያለው ፍላጎት ግን ቋሚ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የሚያነሳው የኤሌክትሪክ ኃይል ውድ መሆንንና ተጠቃሚ ለመሆንም የሁሉም ሰው የኢኮኖሚ አቅም እኩል አለመሆኑን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የኅብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ሙሉ ለሙሉ ዘመናዊ አለመሆኑ ለማገዶ ተፈላጊነት አስተዋኦ እንደሚኖረው አመልክቷል፡፡ በዚህ ሥራ የእርሱና የወንድሙ ድርሻ የእንጨት ግዢን፣ ትራንስፖርትንና የእለት ከዕለት ሽያጭን መቆጣጠር ነው፡፡ የማገዶ እንጨት የሚፈልጡ ደግሞ ሁለት ሠራተኞች አሏቸው፡፡ እነዚህ እንጨት ፈላጮች የሚከፈላቸው በፈለጡት እንጨት ብዛት ነው፡፡ የሚሸጠው የማገዶ እንጨት ሁለት ዓይነት ሲሆኑ ባለ ሁለትና ባለ አራት ብር የሚሸጡ እስር የማገዶ እንጨቶች ናቸው፡፡ በአንድ የባለ አራት ብር እስር እንጨት ሰላሳ ወይም አርባ ሳንቲም ለፈላጮች ይከፈላል፡፡ በቀን ብዙ እንጨት ተፈለጠ ከተባለ አንድ ፈላጭ እስከ አስራ አምስትና ሃያ እስር እንጨት ይፈልጣል፡፡ የማገዶ እንጨት ገበያ ባለ እለት ሙሰማና ወንድሙም እንጨት ይፈልጣሉ፡፡ በተለይም የበዓላት ዋዜማ ላይ ከተቀጣሪ ፈላጮች እኩል እንደሚሰሩ ገልፆልናል፡፡ ጥሩ ገበያ ተገኘ ከተባለ በቀን ከመቶ ሃምሳ ብር በላይ አይገኝም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለጉልበት ሠራተኛ የሚከፈለው ወጪ ከኪራይና ከግብር ጋር ተዳምሮ ሥራውን ከባድ እንዳደረገው አቶ ሙሰማ አልደበቀም፡፡ በእነ ሙሰማ ስራ የእረፍት ቀን የሚባል የለም፡፡ ከሳምንት እስከ ሳምንት ከጠዋት አንድ ሰዓት እስከ ምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት ድረስ ይሰራሉ፡፡ “የምንተዳደረው ከዚህ ሥራ በምናገኘው የእለት ገቢ በመሆኑና ሥራውም ዘና የሚያደርግ ስላልሆነ የበዓላት ቀንን መዝጋት ይከብዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የማገዶ እንጨቶቹም ሆኑ አጣናዎቹ የሚውሉትም ሆነ የሚያድሩት ደጅ በመሆኑ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የምንጠብቀው ደግሞ እኛው ራሳችን ነን” ብሏል፡፡ የትራንስፖርት ወጪን በመፍራትና መነሻ ገንዘብ በማጣታቸው እንጂ አዳዲስ የቤት ግንባታዎች ወደሚካሄዱበት ሰፈር በመሄድ ለመስራት ሁኔታዎችን ማጥናታቸውን ገልጾልናል፡፡ በምሕረት አስቻለው |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |