Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow ልማት ባንክ በአንዳንድ አበባ አምራቾች...
ልማት ባንክ በአንዳንድ አበባ አምራቾች... Print E-mail
Wednesday, 02 April 2008
Image
አቶ ግርማ ብሩ
ልማት ባንክ በአንዳንድ አበባ አምራቾች መጭበርበሩን ሚኒስትሩ አመኑ

የውጭ ኮንትራክተሮች ሲሚንቶ እንዲያስገቡ እንደገና ተፈቀደ

ልማት ባንክ በአንዳንድ አበባ አምራቾች ሲጭበረበር መቆየቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ ግርማ ብሩ አመኑ፡፡ የውጭ ኮንትራክተሮች ያለማናቸውም ዓይነት የታክስ ክፍያ ከውጭ ሲሚንቶ እንዲያስገቡ እንደገና ተፈቀደ፡፡

የመሥሪያ ቤታቸውን የስምንት ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት አበባ አምራቾች ያጋጠሟቸውን ችግሮች በመጥቀስ የምክር ቤቱ አባላት ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ ግርማ አንዳንድ አበባ አምራቾች 7ዐ በመቶ ብድር ለማግኘት ሲሉ ያልሰሩትን ሥራ የሰሩ አስመስለው ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

የኤዴአፓ መድህን ፓርቲ ተወካይ አቶ ደረጀ ደበበ መንግሥት ለአበባ አምራቾች ይሰጥ የነበረውን ብድር በማቆሙ አበባ አምራቾች ወደ ግል ባንክ በመሄድ ለከፍተኛ ወለድ እየተዳረጉ መሆኑን ቢገልፁም ሚኒስትሩ አቶ ግርማ ብሩ ግን ልማት ባንክ ለአበባ አምራቾች ገንዘብ አላበድርም ብሎ እንደማያውቅ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት አበባ አምራቾች የሚፈልጉትን ብድር ከልማት ባንክ ማግኘት ያልቻሉት ባንኩ የሚጠይቀውን ቅድመ ሁኔታ ባለማሟላታቸው ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር 7ዐ በመቶ መበደር የፈለገ አንድ የአበባ አምራች 3ዐ በመቶ የሚሆነውን ሥራ መስራት ይጠበቅበት እንደነበር የገለፁት አቶ ግርማ አንዳንድ የአበባ አምራቾች ከሰራተኞች ጋር በመመሳጠር 3ዐ በመቶ የሰሩ በማስመሰል ብድር የወሰዱበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ችግር መኖሩን የተረዳው ልማት ባንክም የአበባ አምራቾቹ ኘሮጀክት ይጠና ብሎ እንቅስቃሴ ሲጀምር አንዳንድ አበባ አምራቾች ወደ ግል ባንክ መሄድ መጀመራቸውን ሚኒስትሩ አክለው ገልፀዋል፡፡

መንግሥት ለአበባ ምርት ልማት የሚሰጠውን ድጋፍ እንደማያቋርጥ የገለፁት አቶ ግርማ፣ አበባ አምራቾች ብድር ለመበደር የሚያከናውኑት የ3ዐ በመቶ ሥራ ዝቅ እንዲል ጥናት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአገሪቱ የሚስፋፋ ኢንዱስትሪዎች በአካባቢ ላይ ተፅእኖ የሚፈጥሩ ከሆነ መንግሥት ምን ዓይነት እርምጃ ሊወስድ ይችላል? በሚል ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ግርማ ሁሉም ልማቶች ተፅእኖ እንደሚፈጥሩ ጠቁመው እያንዳንዱ ባለሀብት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሲወስድ የሚሰራቸው ሥራዎች በአካባቢው ላይ ተፅእኖ የማፈጥሩ ከሆነ ሁሉንም ወጪ በመሸፈን ተፅእኖዎቹን ለማስወገድ ቃል እንደሚገባና በገባው ቃል መሰረትም እንደሚፈፅም አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው ከ1998-2000 ዓ.ም. በሚቆየው የዘላቂ ልማትና ድህነት ማስወገድ እቅድ ውስጥ የላቀ ግምትና ትኩረት የተሰጠው የአበባ ልማት ዘርፍ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ በአበባ የተሸፈነው መሬት 1ዐዐዐ ሄክታር መሆኑን፣ እስከ ሰኔ 3ዐ/2000 ባለው ጊዜ ደግሞ በአበባ የሚሸፈነው መሬት 12ዐዐ ሄክታር እንደሚደረስ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የሥራ እድል መፍጠርን በተመለከተም በግንባታ ሥራውና በአበባ ልማቱ በድምሩ 7ዐ ሺ ያህል ሰዎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

አቶ ግርማ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንደገለፁት በአበባ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የተለያዩ እቅዶች ተይዘዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ልምድ ባላቸው ባለመያዎችና በዘርፉ ማህበር ተጠንቶ የተዘጋጀ የአሰራር ስርዓት (code of practice) መተግበር ተጀምሯል፡፡ ይህ የአሰራር ስርዓት ስለእርሻ አመራር፣ የሰራተኛ አቀጣጠር፣ ስለጤንነት አጠባበቅ፣ ስለ ስልጠና፣ ከኢንዱስትሪው ጋር በተያያዘ አደጋን ስለመከላከል፣ ስለኬሚካልና ማዳበሪያ አያያዝና አጠቃቀም ያካተተ ነው፡፡ ስርዓቱ በሚጠበቀው ደረጃ መተግበሩን ለመከታተልም ከሚመለከታቸው መንግሥታዊና ሌሎች አካላት ጋር የመግቢያ ሰነድ መፈረሙን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በተያያዘ ዜና በአገሪቱ ውስጥ በሚታየው የሲሚንቶ እጥረት ምክንያት የውጭ ኮንትራክተሮች ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በፍራንኮቫሉታ (በራሳቸው የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ) ያለማናቸውም አይነት የታክስ ክፍያ ከውጭ ሲሚንቶ እንዲያስገቡ እንደሚደረግ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ያጋጠማትን የሲሚንቶ እጥረት ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ ሁለት ዓመት እንደሚወስድባት አቶ ግርማ ጠቁመው እስከዚያው ድረስ ግን የውጭ ኮንትራክተሮች ያለ ታክስ ክፍያ ከውጭ ሲሚንቶ እንዲያስገቡ የሚፈቀድላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በያዝነው በጀት ዓመት መጨረሻ ስምንት ፕሮጀክቶች ሲሚንቶ ወደ ማምረት የሚሸጋገሩ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ከእነዚህ ፋብሪካዎች 767 ሺህ ቶን ሲሚንቶ ይመረታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

አቶ ግርማ እንዳሉት የኢንቨስትመንት ሁኔታው በተያዘው መንገድ ከቀጠለ በ2001 ዓ.ም አሁን ካለው በተጨማሪ 3.2 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ይመረታል፡፡ በ2002 ዓ.ም ማብቂያ ደግሞ የአገሪቱ የሲሚንቶ ምርት ከ9 እስከ 10 ሚሊዮን ቶን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ተግባራዊ ሆነው የአገሪቱን አጠቃላይ የሲሚንቶ ፍላጎት እስከሚያረኩ ድረስም የውጭ ኮንትራክተሮች ያለምንም ታክስ ክፍያ ከውጭ ሲሚንቶ እንዲያስገቡ ይደረጋል፡፡

ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ላይ እንደገለፁት እስከ የካቲት 30 ቀን 2000 ዓ.ም ድረስ ሲሚንቶ ለማምረት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ካወጡ 24 ድርጅቶች ውስጥ ሶስቱ ሲሚንቶ ማምረት ጀምረዋል፡፡ አስር ፕሮጀክቶች ደግሞ የፋብሪካ መገንቢያ ቦታ አግኝተው በተለያየ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቀሪዎቹ አስራ አንድ ፕሮጀክቶች የጥሬ እቃ ጥናት በማድረግና ለፋብሪካ መገንቢያ ቦታ ለማግኘት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ናቸው፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሳምንት በፊት በፍራንኮ ቫሉታ ሲሚንቶ እንዲያስገቡና እንዲሸጡ ፈቃድ ለሰጣቸው ድርጅቶች ከጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ በመግዛት የውጭ ምንዛሬ መዛባትን ፈጥረዋል በሚል እንዳያስገቡ በድንገት መከልከሉ ይታወሳል፡፡

በተያያዘ ዜና በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስምንት ወራት ብቻ በፌደራል የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ አማካይነት አገልግሎት ሊያገኙ ለሚገባቸው የካፒታል መጠኑ 77.5 ቢሊዮን ብር ለሚገመቱ 3761 ፕሮጀክት የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱ በሚኒስትሩ ሪፖርት ላይ ተገልጿል፡፡ ከ1998 ጀምሮም እስከ አሁን ድረስ የካፒታል መጠኑ 254.7 ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ 16ሺህ 231 ፕሮጀክቶች በፌደራል ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ደረጃ ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡

የ2000 ዓ.ም በጀት ዓመት አጠቃላይ የአገሪቱን ዕቅድ በማስፈጸም ረገድ ያጋጠሙ ፈታኝ ሁኔታዎች ተብሎ በሚኒስትሩ የተጠቀሰው ትላልቅ ፕሮግራም ተደርገው የሚወሰዱ ስራዎችን ጎን ለጎን መፈጸም የሚያስገድድ ሁኔታ መፈጠሩ ነው፡፡

የልማት እቅዶቹን ለማስፈጸም ከ1998 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግና አገሪቱ ከዚህ የባሱ ሌሎች ግዙፍ ፕሮግራሞችን ጎን ለጎን ተግባራዊ እንምታደርግ የጠቆሙት አቶ ግርማ ለሁሉም ፕሮግራሞች የሚበቃ የተፋጠነና ቀልጣፋ የሎጅስቲክ ድጋፍና የፕሮጀክት ማስፈጸም አቅም አለመኖሩ ችግር የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ፈታኝነቱ የተገለፀው ሌላው ጉዳይ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ የማፍራት አቅም ከህዝቡ የልማት ፍላጎት ጋር የተመጣጠነ ያለመሆኑ ነው፡፡ ሚኒስትሩ እንዳሉት ተከማችቶ የቆየን የልማት ጥያቄ በአንድ ጊዜ ለመመለስ ጥረት ሲደረግ የማስፈጸም አቅም ውስንነት ሆነ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ቢኖር ሊገርም አይገባም፡፡

በኃይሌ ሙሉ
 
< Prev   Next >