Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ክቡር ሚኒስትር
ክቡር ሚኒስትር Print E-mail
Wednesday, 02 April 2008
(በውጭ ምንዛሬ ማግኛ መንገድ ሁሉ ጥብቅ አሰራር እንዲኖርና አላስፈላጊ ብክነት እንዳይኖር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባዘዙት መሰረት የአበባ ኤክስፖርት እንቅስቃሴን የሚከታተል አንድ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ በክቡር ሚኒስትሩ ይመራል፡፡ ዛሬ የኮሚቴው የመጀመሪያ ስብሰባ ነው)

- የዚህ ኮሚቴ አስፈላጊነት ለናንተ የተሰወረ አይደለም ብዬ ነው፤ ለመዘርዘር ጊዜ ያልፈጀሁት፡፡
- ግልጽ ነው፤ ክቡር ሚኒስቴር፡፡ ከሰባት ዓመት በፊት መቋቋም የነበረበት ኮሚቴ ነው፡፡
- እንዴት ከሰባት ዓመት በፊት? የኑሮ ውድነት፣ የወርቅ ማጭበርበር፣ የዶላር ጥቁር ገበያ ምንዛሬ፣ የመሳሰሉት ነገሮች የተከሰቱትኮ ዘንድሮ ነው፡፡
-  የአበባ ኤክስፖርትን በትክክል ለማወቅ ወርቅ መጭበርበር ነበረበት ክቡር ሚኒስትር?
- ከዛ በፊት ችግር አልነበረም፤ ማለቴ ነው፡፡
- ችግር ነበር እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡ አበባ ተሸጦ ገንዘቡ አገር ውስጥ ይግባ፤ አይግባ፤ እንዴት እናውቅ ነበር?
-  ራሳቸው የአበባ አምራቾች ማህበር መሪዎች ይነግሩን ነበርኮ፡፡ በቀደም የጋራ የእራት ግብዣና ስብሰባ ተካሄዶ፣ በቪዲዮ የተደገፈ መግለጫ ሰጥተውን የለ? በቴሌቪዥን ቀርበው ቃለ መጠይቅ ተደርገው የለ? ዓለም የሰማው ጉዳይ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይቅርታ ይደረግልኝና እኔ እዚህ ኮሚቴ ውስጥ አባል እንድሆን ተመርጠሃል ተብዬ ሲነገረኝ ልቀበለው አልቀበለው ተጨንቄ ነበር፡፡ ግን ግዴታ ስለሆነብኝ ተቀብያለሁ፡፡
- ለምን?
- ክቡር ሚኒስትር፣ በዚህ የአበባ ጉዳይ ተደማጭነት ያላቸው ራሳቸው የመንግሥት ገንዘብ ወስደው የአበባ ሽያጭ ገንዘቡን ወደ አገር የማይመልሱት ግለሰቦች ናቸው፡፡ እኛ ባለሙያ የተባልነው የሚያዳምጠን  የለም፡፡
- እነሱ መታመን የለባቸውም ማለትህ ነው?
- ሁለት ዓይነት አበባ አምራቾች ናቸው፤ ያሉት ክቡር ሚኒስትር፡፡ ከልብና በቅንነት የሚሰሩ አሉ፡፡ አጭበርብረው ገንዘብ ወስደው “ምላስ” ብቻ የሚሸጡ አሉ፡፡ መግለጫና ቃለ መጠየቅ የሚያበዙና ከራሱ ከአበባው ይልቅ መግለጫቸው ይበልጥ ፈክቶ፣ ደምቆ የሚታይ የማህበር መሪዎች አሉ፡፡
- እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ሳምንት ነው ሪፖርት ይድረስልኝ ያሉት፡፡ እነሱን ለመውቀስ ጊዜ ያለን አይመስለኝም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፣ እኔም በዚህ ስብሰባ እንውቀሳቸው፣ እንርገማቸው ማለቴ አይደለም፡፡ ተጨባጭ ጥናት ለማድረግ እንቅስቃሴ አድርገን፣ ተጨባጭ ሪፖርት እናቅርብ ማለቴ ነው፡፡
- ምንድነው የምንጠናው?
- ክቡር ሚኒስትር፣ መንግሥት ምን ያህል ገንዘብ እንዲበደሩ በባንክ እንዳስቀመጠላቸው፣ ምን ያህሉን ወሰዱት? ምን ያህል አበባ ተሸጠ? ምን ያህል አገር ውስጥ ገባ? የዓለም ገበያና የእኛ አበባ ሽያጭ ምን ይመስላል? ክትትላችንና ቁጥጥራችን ምን ይመስላል? ወዘተ.
- እሺ በቃ አሁን ንግግር አናብዛ፡፡ ቀጥታ ወደ ጥናት እንግባ፡፡ በሳምንት ውስጥ ሪፖርቱን ማቅረብ ግዴታ ነው፤ ብለው ወጥረውኛል፡፡ እዛ ሄጄ ሪፖርት የለኝም፤ አልደረሰልኝም ብዬ ማፈር አልፈልግም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይህ የአበባ ችግር ፀሐይ የመታውና ከአሁን በፊትም ተነግሮ፣ ተነግሮ ሰሚ ያጣ ጉዳይ ነው፡፡ ሰሚ ከተገኘ ሪፖርቱ በሰባት ቀንም ይደርሳል፡፡
- ሰሚ የለም ስትል ኢሕአዴግ አይሰማም ማለትህ ነው አይደል?
- አንዳንድ ሰዎች አይሰሙም ማለቴ ነው፡፡ አንዳንድ ስልም እርስዎን ማለቴ አይደለም፡፡ ሌሎች አንዳንድ ማለቴ ነው፡፡
- ከመጀመሪያው እንደዛ ብለህ በግልጽ ማስቀመጥ ነበረብህ!
- ይቅርታ፡፡
- በተባባልነው መሰረት በየቀኑ ለአንድ ሰዓት እየተገናኘን ስለአገኘነው ሁኔታ እንወያያለን፡፡ የዛሬውን በዚህ ጨርሰናል፡፡

(ማታ አካባቢ ክቡር ሚኒስትሩ በሞባይላቸው ተደወለላቸው)

- ሃሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሃሎ ማን ልበል?
- ከአበባ አምራቾች ማህበር አመራር አባል አንዱ ነኝ፡፡ አንዳንድ አጭበርባሪዎች መረጃ እንሰበስባለን፤ ብለው ስንት አመረታችሁ፣ ስንት ሸጣችሁ፤  እያሉ ሰዎቻችን እየጠየቁ አስቸግረዋል፡፡ እንድናስተካክል ብለን ነው፡፡
- ያቋቋምነው ኮሚቴ ነው፤ አጭበርብሪዎች አይደሉም፡፡ አንዳንዶቹ ጥሩ ተባብረውናል ብለው ነግረውን ነበር፤ ችግሩ ምንድነው?  
- ክቡር ሚኒስትር የሚፈልጉት ካለ እኛን ያነጋግሩ እንጂ በተናጠል መጠየቅ የለባቸውም፡፡ የማህበር ጥቅሙ ምንድነው ታዲያ፡፡ መረጃውን ይዘው ኋላ ለሻዕቢያ ቢሰጡት፡፡
- እሺ በስብሰባችን ላይ አነሳዋለሁ፡፡

(ሁለተኛ ስብሰባ)
- የማህበሩ መሪዎች ደውለውልኝ ነበር፡፡ በማህበር ደረጃ እንጂ በተናጠል አትጠይቁ ብለዋልና በማህበር አመራር ደረጃ ይሁን ጥናታችሁ፡፡
- አይሆንም፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ቀና አመለካከት ያላቸው አምራቾች ነግረውናል፡፡ ስለ ግል እንቅስቃሴያችን ጉዳይ በግል አነጋግሩን ብለዋል፡፡ ቅንና ሽፍጠኛ አለ፡፡ በየግል አናግሩን ብለውናል፡፡
- መረጃው እንዳይባክን የሚል ስጋት አላቸው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፤ እንደውም እነሱ የሰብሰባ መረጃ ነው ለአገር ጥቅም የማይውለው፡፡ በቀደም በቴሌቪዥን ሰባት መቶ ሚሊዮን ዶላር አስገብተናል፤ ብለው ነበር መግለጫ የሰጡት፡፡ ያገኘነው ግን የተለየ ነው ሰማይና መሬት ነው፡፡
- ምንድነው ያገኛችሁት?
- ክቡር ሚኒስትር የሰባት ዓመት ሂደት ስናይ መንግሥት ለማበረታቻ ሊበደሩ የሚችሉት 3.2 ቢሊዮን ብር ባንክ አስቀመጠላቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ 600 ሚሊዮን ተበደሩ፡፡ እነሱ በሰባት ዓመት ያስገቡት ግን 7 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡
- ምን?
- ይኸው ነው ሃቁ፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ቢሰሙ ምን ይሉናል?
- ክቡር ሚኒስትር፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ባይጠረጥሩ ኖሮ ኮሚቴ ይቋቋም ይሉ ነበር?
- አሻሻጡ እንዴት እንደሆነ አጥንታችኋል፡፡
- እሱ ለነገ ይደርሰናል፡፡
- እሺ ነገ እንገናኝ፡፡ የዛሬውን በዚህ ጨርሰናል፡፡

(ክቡር ሚኒስትር ቢሮ ውስጥ ናቸው፡፡ ፀሐፊዋ ከፍታ ገባች)

- ክቡር ሚኒስትር አንድ ስልክ ነበር፡፡
- ሁለት የአበባ አምራቾች ማህበር አመራር አባላት በግላቸው እርስዎንና ኮሚቴውን እራት ለመጋበዝ ይፈልጋሉ፡፡ መልስ እየጠበቁ ናቸው፡፡ ለዛሬ ነው፡፡
- ዛሬ ምን አለኝ እስቲ አጀንዳውን እይ፡፡
- አጀንዳው ምንም የለውም፡፡ ግን እሺ ባይሉ ይሻላል፡፡
- ለምን?
- ኮሚቴው ስራ ላይ ስለሆነ ሰው ሲያይ ጥሩ አይደለም ብዬ ነዋ፡፡
- ከየት አመጣሽው ይህን ሃሳብ?
- አንድ የኮሚቴ አባልም አነጋግሬው ነበር፡፡ ጉቦ ሊሰጡንና የተሳካ ሪፖርት እንድናቀርብ ፈልገው ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሌቦች ናቸው፡፡ አንጋበዝም በያቸው አለኝ፡፡
- እንትና ነው አይደል? እሱ ሰውዬ ከሰው ጋር የመግባባት ባህሪይ የለውም፡፡ ከኮሚቴው እናንሳው ወይ እያልኩኝ ነው፡፡
- ወይ ክቡር ሚኒስትር፣ እሺ እጅግ በጣም ሃቀኛ ሰው ነው፡፡ በሰራተኛውም ይወደዳል፡፡ ሌላው ዋጋ የለውም በእሱ ግን እተማመናለሁ፡፡
- የሆነ ግንኙነት ያላችሁ ይመስላል፡፡
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ሰውየውን ከኮሚቴው ያስወጡት፡፡ እራቱንም እሺ ልበላቸው፡፡
- አይ አትቆጪ፡፡ አንችን ለማስቆጣት አይደለም እንደዛ ያልኩት፡፡ እሺ አንቺ ባልሽው ይሁን፡፡ እራት አይሆንም በያቸው፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስር፡፡

(ሶስተኛው ሰብሰባ)
- አበባው እንዴት እንደሚሸጥ፣ በስንት እንደሚሸጥ ማጥናት ነበር የያዝነው ጉዳይ፡፡
- አዎን ክቡር ሚኒስትር እጅግ በጣም የሚገርም ነገር ነው ያገኘነው፡፡
- እኮ ምንድነው?
- መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ቅን የሆኑ ነገሩን ብዙዎች ሊነግሩን ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ በኮንሳይመንት ነው የማስበው አለ፡፡
- እኮ በኮንሳይመንት ቢሆንም ስንት?
- ይለዋወጣል፡፡ ብዙ ጊዜም ፀሐይና ነፋስ ሲያበላሸው አበባውን እንጥለዋለን አሉ፡፡
- እና ምን ይመስላችኋል?
- ክቡር ሚኒስትር፣ እኛም እዛ የገበያው ድርጅት ድረስ ስልክ ደውለን መረጃ ለማግኘት ሞክረን ነበር፡፡
- ምን አገኛችሁ?
- ኢትዮጵያዊያኑ አበባ አምራቾችና ሻጮች ..አትናገሩብን.. ስላሉን አንነግራችሁም አሉን፡፡
- አትንገሩብን?
- አዎን አትንግሩብን ተብለናልና አንነግርም አሉን፡፡ ውል አላቸው መሰለኝ፡፡
- ሁሉም እምቢተኛ ሆኑ ማለታችሁ ነው፡፡
- አንዳንዶቹ እዚህ ያሉት አምራቾች ነግረውናል፡፡ በግልፅ ነግረውናል፡፡ አንዳንዶቹ አልነገሩንም ብቻ ሳይሆን በነገሩን ላይም ዘመቻ ጀምረዋል፡፡   
- መንግሥት ራሱ የዓለም ገበያን የሚያጠና አካል በብሄራዊ ባንክም በሌላም አለው፡፡ እሱን ለምን አትጠቀሙም?
- ክቡር ሚኒስትር፣ እኛ ያሰብነውም ይህ የዓለም ገበያ የሚከታተለውን መምሪያ ማነጋገርና የእነሱ ጥናትና አስተያየትን መቀበል ነው፡፡
- እሺ ጊዜ የለም ቶሎ ዛሬ ጨርሱ፡፡

(አራተኛው ስብሰባ)
- እሺ መመሪያው ምን አለ?
- ክቡር ሚኒስትር መምሪያው የለም!
- ምን ማለት ነው መመሪያው የለም?
- ክቡር ሚኒስትር ፈርሷል!!
- መምሪያው ፈርሷል?!
- አዎን ክቡር ሚኒስር ፈርሷል፡፡
- ማን አፈረሰው?
- ራሱ ፈርሷል፡፡
-  ምን ማለት ነው ራሱ ፈርሷል?
- መንግሥት አላፈረሰወም፣ ባንክ አላፈረሰውም፡፡
- ማን አፈረሰው ታዲያ?
- እንግዲህ አንዳንድ ነጋዴዎች ይሆናሉ፡፡
- ነጋዴዎች መንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ ገብተው መምሪያ ሊያፈርሱ?
- ምን ችግር አለ ክቡር ሚኒስትር? መመሳጠርያ ማፍረስ ነው፡፡
- ኃላፊዎችን አነጋገራችሁ?
- ደነገጡ፡፡ መፍረሱንም አልተገነዘቡትም ነበር፡፡
- ስለ መምሪያ፣ ስለአወቃቀር ነውኮ እያወራን ያለነው፡፡ ከኪስ ወድቆ ስለጠፉ ሳንቲም አይደለም፡፡
- ምክንያቱ በትክክል ማወቅ አልተቻለም በማያጣሩ ሁኔታ ግን የዓለም ገበያ ይከታተላል የነበረው መምሪያ ፈርሷል፡፡
- እሺ ገዜ የለም አሁን ነገ ተሰብስበን ሪፖርቱን እናጠናቅቃለን፡፡

(አምስተኛው ስብሰባ)
- አንዳንድ የማህበሩ አባላት ማህበሩ ከዓለም በአበባ ኤክስፖርትነት ያገኘነው ዓለም አቀፍ ሽልማት ጥናት መጥተው አሳዩኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፣ እነሱ ራሳቸው ሽልማት ላኩልን ብለው ያሰሩት ነው፡፡ ቀላል ነው በገንዘብ ይገዛል፡፡ በየድርጅቱኮ የምናምን ተሸላሚ የሚል ተንጥልጥሏል፡፡ አሁን ማጣራት ስንጀምር የገዙት ነው፡፡
- እና ይህ ሁሉ ጥረትና ልፋት የተደረገበት አበባ ማምረትና የኤክስፖርት ሥራ ዋጋ የለውም እያላችሁ ነው?
- አይደለም፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ሃቀኛነትና ሸፍጠኝነት ይለዩ፡፡ ሃቀኛውን እናበረታታና ቀጣፊውን እንቅጣ፡፡ ገንዘብ የሚያመጣውን እንደግፍ፡፡ ገንዘብ ወደ አገር እንዲገባ የማያደርገውን እናጋልጥ፡፡
- ስለመፍትሔ ሃሳቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ሃሳብ አንድ ፎርሙላ አቅርቡ ቢሉን ምን እናቀርብላቸዋለን?
- ክቡር ሚኒስትር፣ ስለመፍትሄው ፎርሙላ ማቅረብ ለራሳቸው እንተወው፡፡ እስካሁን ያለው የአበባ ሁኔታ ፎርሙላው ምን ይመስላል ብለን ግን ልናስቀምጥላቸው እንችላለን፡፡
- አንተ ማስቀመጥ ትችላለህ?
- አዎን፣ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እስቲ ፎርሙላውን አስቀምጥና
ብድር የተፈተቀደለት አበባ
+ ወደ ውጭ የተላከ አበባ
+ ውጭ የተሸጠ አበባ
- ለአገር ጥቅም ያስገኘ አበባ
= ጎመን
 
< Prev   Next >