| “መሥሪያ ቤቱ የትራፊክ ፖሊስ መቅጣት እንጂ... |
|
|
| Wednesday, 02 April 2008 | |
“መሥሪያ ቤቱ የትራፊክ ፖሊስ መቅጣት እንጂ ማስተማር የለበትም ብሎ መመሪያ አልሰጠም”ዋና ሳጅን አሰፋ መዝገቡ ዋና ሳጅን አሰፋ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ መቆጣጠሪያና ምርመራ ዋና መምሪያ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ናቸው፡፡ ብርሃነ ዓለሙ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- በትራፊክ አደጋ ኢትዮጵያ ትመራለች የሚሉ አሉ፡፡ ይህ አባባል አሁንስ ተለውጧል? ዋና ሳጂን አሰፋ፡- ከእኛ የባሰ አደጋ የሚደርስባቸው አገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከአሥር ሺህ ተሽከርካሪ የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ ከበፊቱ ቀንሷል፡፡ ከአሥር ሺህ ተሽከርካሪ ብዛት ሲደመርና ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር እኩል አይደለም፡፡ አገራችን በየአሥር ሺው ተሽከርካሪ ብዙ አደጋ ከሚደርስባቸው አገሮች ተርታ የምትሰለፍ ናት፡፡ በጣም በሰለጠነው ዓለም በየአሥር ሺው ተሽከርካሪ ሦስት ወይም አራት ሰው ነው የሚሞተው፡፡ በእኛ አገር ግን 114 ስለሆነ መቀነስ አለበት፡፡ ሪፖርተር፡- የትራፊክ አደጋዎቹ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀሩ እየቀነሱ ናቸው ወይስ እየጨመሩ? ዋና ሳጂን አሰፋ፡- በሁለት መልኩ ነው የምናየው፡፡ አንደኛ ከተሽከርካሪ፣ ከኀብረተሰቡ፣ ከመንገዶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር አንፃር ስናየው የትራፊኩ አደጋ ያን ያህል ጨመረ የምንለው አይደለም፡፡ የዘንድሮን (ከሐምሌ 1999 እስከ ታህሳስ 2000) ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ስድስት ወር ጋር ስናነፃፅረው የሞት አደጋው በአምስት (2.7 በመቶ..፣ ከባድ የአካል ጉዳት በ81 (23 በመቶ) ቀንሷል፡፡ በዝርዝር ሲታይ በስድስት ወር የደረሰ የሞት 174፣ ከባድ የአካል ጉዳት 271፣ ቀላል የአካል ጉዳት 451፣ በንብረት ላይ 3714 በአጠቃላይ 4610 አደጋ ደርሷል፡፡ አምና ተመሳሳይ ስድስት ወር የነበረው የሞት 179፣ ከባድ የአካል ጉዳት 352፣ ቀላል የአካል ጉዳት 428፣ በንብረት ላይ የደረሰ 3573 በአጠቃላይ 4532 ነበር፡፡ አደጋው በ78 (1.6 በመቶ) ጨምሯል፡፡ የሞትና ከባድ የአካል ጉዳት አደጋው ግን በ86 ቀንሷል፡፡ በተሻለ መጠን የትራፊክ አደጋውን ለመቀነስ መሥሪያ ቤታችን በተቻለ መጠን እቅዶችን በማውጣት ላይ ነው፡፡ ለአደጋ መንስዔ የሚሆኑ ጥፋቶችን በመለየት፣ የአደጋ ቦታዎችንና የአደጋ ሰዓትን በመለየት ቀንና ማታ ይቆጣጠራል፡፡ በደንብ ተላላፊዎች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ ከአምና ጀምሮ በእቅድ በመንቀሳቀስ የቴክኒክ ብቃታቸው አነስተኛ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር ስናደርግ፣ ለእግረኞች ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች በእምነት ተቋማት፣ ሰዎች በተሰበሰቡበት፣ በየትምህርት ቤቱ በእግረኛ ማቋረጫ ዜብራ እንዲጠቀሙ ትምህርት ይሰጣል፡፡ የተቻለውን ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ችግሩ ተቀርፏል ማለት ግን አይቻልም፡፡ ልንገፋበትና ልንቀጥልበት ይገባል፡፡ ልንቀጥል የምንችለው የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች (መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት) ለመሥሪያ ቤቱ ዕርዳታ ሲያደርጉ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በአነስተኛ ደረጃ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ በተለይ በአሽከርካሪዎች ላይ የምናደርገው ቁጥጥር በልምድ የምናደርገው ነው፡፡ ቴክኖሎጂን የሚጠይቁ መሳሪያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የራዳር መቆጣጠሪያ አሽከርካሪዎች አልኮል መጠጣታቸውን የሚያረጋግጥ መሳሪያ ያስፈልጋሉ፡፡ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዘው የሚመጡ መሣሪያዎችን (አገልግሎቶች) በሚመለከት ሕግ የሚወጣላቸው አሉ፡፡ ሞባይል እያነጋገሩ ማሽከርከር፣ የደህንነት ቀበቶ ሳያስሩ መሄድንና የመሳሰሉት ሕግ ሊወጣላቸው የሚገቡ ናቸው፡፡ ከፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በጋራ ጥናት አጥንተን ለሕግ አውጪው ቀርቧል፡፡ ከዳር ለማድረስ መንግሥት የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት፡፡ ሪፖርተር፡- ሰሞኑን የጀመራችሁት “ዜብራ ክሮስ ኦኘሬሽን” ምንድነው? ዋና ሳጂን አሰፋ፡- እግረኞች በእግረኛ ማቋረጫ ዜብራ ብቻ እንዲያቋርጡ፣ በቀጥታ ጉዞም በእግረኛ መንገድ ላይ ብቻ፣ የእግረኛ መሄጃ ከሌለም የግራ መስመራቸውን ይዘው እንዲጓዙ ይገደዳሉ፡፡ እነዚህንና የመሳሰሉትን በማድረግ እግረኞች ላይ ጫና እየፈጠርን ነው፡፡ በአደባባዮች፣ በትራፊክ መብራቶች አካባቢ፣ ከአጥር ውጭ ባለ መስመሮች ላይ እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡ ከአንዳንድ እግረኞች በስተቀር ብዙዎች ቀና ምላሽ እየሰጡን ነው፡፡ አንዳንድ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግን የትራፊክ ፖሊስ የሚመደበው ለአሽከርካሪ ብቻ እንደሆነ በመገመት ተገቢ ያልሆነ መልስ ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች መታረም ስላለባቸው ሕግ ፊት መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ባለፈው ዓመት መጨረሻ የቴክኒክ ብቃታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን በድንገተኛ ቁጥጥር ለመያዝ መግለጫ ሰጥታችሁ ነበር፡፡ ይህን ስታደርጉ ግን አትታዩም፡፡ ለምን? ዋና ሳጂን አሰፋ፡- አሁንም እየተቆጣጠርን ነው፡፡ ማንኛውም ተሽከርካሪ የጎን መመልከቻ መስተዋት ሳይኖረው መሄድ አይችልም፡፡ ጎማው ሊሾ የሆነ መኪና ማሽከርከር አይቻልም፡፡ የትራፊክ ፖሊስ ቁጥጥር እያደረገ ነው፡፡ ደንብ የሚተላለፉ ሰዎች ተከስሰው ለሕግ ቀርበው ተቀጥተው መኪናቸውን ያስተካክላሉ፡፡ የተቋረጠ ነገር የለም፡፡ ሪፖርተር፡- በተጠናከረ መንገድ የቀጠለ ግን አይመስልም፤ ዋና ሳጂን አሰፋ፡- እየቀጠለ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- እያሽከረከሩ የሞባይል ስልክ ማነጋገር፣ የደህንነት ቀበቶ አለማሰር ጥፋት መሆኑ በተደጋጋሚ ስትገልፁ ትሰማላችሁ፡፡ በዚህ ላይ ሕግ ማውጣት ለምን አልተቻለም? ዋና ሳጂን አሰፋ፡- የትራፊክ ፖሊስ ሕግ አስከባሪ ነው፡፡ የወጣውን ሕግ የማስከበር እንጂ ሕግን የማውጣት አቅም የለውም፡፡ ችግሩን የማቅረብ ነወ፡፡ ይህን ጉዳይ የያዘው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ነው፡፡ ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ስለሆነ በፍጥነት ሕግ ሊወጣለት ይገባል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ችግር በሚፈጥሩ አሽከርካሪዎች ላይ (ሞባይል እያነጋገሩና ቀበቶ ሳያስሩ በሚሄዱት) ላይ ቁጥጥር እያደረገ ጥሩ ውጤት አግኝቷል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ የብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የአፍሪካ ኀብረት መቀመጫና የኢትዮጵያም ርዕሰ ከተማ እንደመሆኗ መጠን በሕግ መልክ ወጥቶ ጥንቃቄ እንዲደረግበት መጠቆም እወዳለሁ፡፡ ከሕይወት ጋር የተያያዘ ስለሆነ መቆየት የለበትም፡፡ የደህንነት ቀበቶ ታስሮና ሳይታሰር የሚደርስ አደጋ በጣም ብዙ ልዩነት አለው፡፡ ቀበቶ ሳያስሩ አደጋ ደርሶባቸው ከመኪና ወጥተው አስፋልት ላይ ሞተው ያየናቸው አሉ፡፡ ቀበቶ ያሰሩት ብዙም ጉዳት ሳይደርስባቸው ይታያሉ፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ እኛን ስለማይመለከት ጉዳዩ የት እንደደረሰ አላወቅኩም፡፡ ሪፖርተር፡- የትራፊኩ ሕጉ ከማስተማር ይልቅ ቅጣት ላይ ያነጣጠረ ነው በማለት የሚተቹት አሉ፤ ዋና ሳጂን አሰፋ፡- አሽከርካሪዎች እንዲህ ይላሉ፡፡ የትራፊክ ፖሊሶች ላይ ምንም ስህተት የለም ማለት አልችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ማስተማር እንዳለባቸው እናምናለን፡፡ መንግሥትም ሆነ የትራፊክ መሥሪያ ቤቱ ማንኛውም የትራፊክ ፖሊስ መቅጣት እንጂ ማስተማር የለበትም ብለው መመሪያ አልሰጡም፡፡ አንድ አሽከርካሪ መንጃ ፈቃድ ሲያወጣ የትራፊክ ሕጉን አውቆ ነው የሚያወጣው፡፡ ጠንቅቆ ተምሮና አውቆ ያወጣውን የመንጃ ፈቃድ ህግ ወደ ተግባር የመለወጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ያንን ሕግ ባለማክበሩ አደጋ ይደርሳል እያልን ነው፡፡ አንድ አሽከርካሪ በእግረኛ ማቋረጫ ላይ ለእግረኛ ቅድሚያ ባለመስጠቱ አደጋ ይደርሳል፡፡ አደጋ እንዳይደርስ የትራፊክ ፖሊስ ሕግን ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ያጠፋውን መክሰስ አለበት፡፡ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር፣ በአጋጣሚ ያጠፉትን አታስተምር የሚል መመሪያ በመሥሪያ ቤታችን በኩል የለም፡፡ እናስተምራለን፡፡ ጉዳዩን የበለጠ ለማጠናከር ደግሞ ቅጣት ይኖራል፡፡ ለአደጋ መንስኤ ከ85 በመቶ በላይ የአሽከርካሪ ስህተት እንደሆነ ከጥናቶቻችንም ከዳታዎችም እየተገነዘብን ስለሆነ አሽከርካሪዎች ላይ ጫና ፈጥሮ ሕግን እንዲያስከብሩ ለማድረግ ቅጣት አንዱ መፍትሄ ነው፡፡ ዱሮ አሽከርካሪው አጥፍቶ የትራፊክ ፖሊሱ ያልፈው ከነበረ ዛሬ ላያልፈው ይችላል፡፡ ምክንያቱም አደጋ ለመቀነስ ጥረት በመደረግ ላይ ስለሆነ፡፡ በዚህ ምክንያት ቁጥጥሩ የጠበቀበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሪፖርተር፡- የትራፊከ ፖሊሶችን ሥነ ምግባር ጉድለት በሚመለከት በተደጋጋሚ ሲነሳ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ምን የተደረገ ነገር አለ? ዋና ሳጂን አሰፋ፡- የትራፊክ ፖሊሱን ሥነ ምግባር ለማስተካከል ሥልጠናዎች እየተሰጡ ነው፡፡ በቅርቡም የትራንስፖርት ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ሕግን፣ የትራፊክ ፖሊስ ሥነ ምግባርን፣ የሲቪል ሰርቪሱን ሕግ በተመለከተ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ በየቀኑ ለትራፊክ ፖሊሱ ገለፃ ይደረግለታል፡፡ አንድ አሽከርካሪ ጥፋት ሲያጠፉ የትራፊክ ፖሊሱ አስቁሞ፣ ሰላምታ ሰጥቶ፣ ጥፋቱን አስረድቶ መንጃ ፈቃዱን ተቀብሎ በሦስት ደቂቃ ውስጥ መቅጫ ፅፎ መስጠት አለበት፡፡ ካስተማረ ወዲያውኑ አስተምሮ መልቀቅ አለበት የሚል በየቀኑ የግንዛቤ ማዳበሪያይሰጣል፡፡ ይህንን ሳይፈጽም ቢገኝ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የመሥሪያ ቤቱ የውስጥ ደንብ አለ፡፡ በዚያ መሠረት ቻርጅ እየሞሉ የሚቀጡበት መንገድ አለ፡፡ በተረፈ ብዙውን ነገር የሚያየው ሕብረተሰቡ ነው፡፡ ትራፊክ ፖሊሱ ችግር ከፈጠረ ለመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ቀርቦ ለማስረዳት፣ ለመክሰስና ለማስቀጣት የመሥሪያ ቤቱ በሮች ክፍት ናቸው፡፡ ሪፖርተር፡- በትራፊክ ፖሊሶች ላይ ድንገተኛ ቁጥጥር አይደረግም? ዋና ሳጂን፡- ከመምሪያ ኃላፊ ጀምሮ የትራፊክ ፖሊሶች ከተሠማሩ በኋላ በትራፊክ ሰዓት ላይ ይወጡና የትራፊክ ፖሊሱ ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ያያሉ፡፡ በአግባቡ የማያስተናግዱት ያርማሉ፡፡ መቀጣት ካለባቸው ያስቀጣሉ፡፡ ከመምሪያ ኃላፊ እስከ የቡድን ኃላፊዎች ድረስ እየተዟዟሩ ይቆጣጠራሉ፡፡ የክፍለ ከተማ የትራፊክ ዋና ክፍል ኃላፊዎችም በዚሁ መልኩ እስከ ተረኛ ኃላፊ ድረስ ያሉት ወጥተው እየተቆጣጠሩ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ ሪፖርተር፡- አንዳንድ የትራፊክ ምልክቶች ላይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ ለምሳሌ ከሲኒማ ራስ እስከ ተክለ ኃይማኖት አደባባይ፣ ከስታዲየም እስከ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ለታክሲዎች ማቆም የተከለከለ ነው፡፡ ሌሎችም በታዎች ላይ እንደዚሁ፡፡ በዚህ ምክንያት ተሳፋሪ ረዥም ጉዞ ይጓዛል፡፡ ምልክቶች ሲታከሉ በቂ ጥናት ይደረግባቸዋል? ዋና ሳጂን አሰፋ፡- የትራፊክ ምልክቶች የሚተከሉት በአንድ መሥሪያ ቤት ፍላጎት አይደለም፡፡ በአዳዲስ መንገዶች ላይ እንደጊዜውና እንደ መንገዱ ሁኔታ ምልክቶች ሊለዋወጡ ይችላሉ፡፡ የአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በጋራ ክፍለ ከተሞችን ጨምሮ ቦታው ላይ ምልክት ያስፈልጋል ወይ፣ ይህ ምልክት መነሳት አለበት ወይ ብለው ይወያያሉ ሦስቱም የኮሚቴ አባላት ይቀርቡና ምልክቱ መነሳት ካለበት እንዲነሳ ያደርጋሉ፡፡ መተከል ካለበትም ያስተክላሉ፡፡ በምሳሌነት የተነሳው ከሲኒማ ራስ እስከ ተክለ ኃይማኖት አደባባይ ተሻግሮ ባለው መንገድ ላይ ታክሲ ቢቆም ሌሎች ተላላፊ ተሽከርካሪዎች መቆሚያ ቦታ አይኖራቸውም፡፡ እግረኞች ችግር እንደሚገጥማቸው ይገባናል፡፡ ከሲኒማ ራስ እስከ ተክለ ኃይማኖት አደባባይ በእግራቸው ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ መንገድ ተዘጋግቶ መጨናነቅ ከሚፈጠር በእግር መምጣት ይሻላል፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ታክሲዎች ሲቆሙ ሌሎች ተሽከርካሪዎች መተላለፍ አይችሉም፡፡ ጥናት ተደርጎ ነው ለታክሲዎች የተዘጋው፡፡ ሪፖርተር፡- በግለሰቦች ተጠያቂነትም ምልክት ሲታከል ወይም ሲነሳ ይታያል፤ ዋና ሳጂን አሰፋ፡- የግለሰቦች መብትም ይጠበቃል፡፡ አንድ ሰው ደጃፉ ላይ ያልሆነ ምልክት ቢተከልበት አስፈላጊ ካልሆነ ደብዳቤ ጽፎ ለመንገዶች ባለሥልጣን ግልባጭ ለትራፊክና ለቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ሲያቀርብ ሦስቱም መሥሪያ ቤቶች ቦታው ላይ ተገኝተው እንዲነሳ ያደርጋሉ፡፡ አንዳንድ ትምህርት ቤቶችም ምልክት እንዲቆምላቸው ደብዳቤ ይፅፋሉ፡፡ ቦታው ታይቶ እንዲተከል ይደረጋል፡፡ ያለ ጥናት ምንም ዓይነት ምልክት አይተከልም፤ አይነሳምም፡፡ ሪፖርተር፡- የተማሪ ትራፊኮች በብዛት ይታዩ ነበር፡፡ አሁን ግን የሉም፡፡ ዋና ሳጂን አሰፋ፡- የተማሪ ትራፊኮቹ ከ1998 በፊት አንፃር አሁን ቀንሰዋል፡፡ የበጀት ችግር ነበር፡፡ ክበባቱ ግን አሁንም እየሠሩ ነው፡፡ ክፍለ ከተማ ያሉት የትራፊክ ኃላፊዎች ከተማሪ ትራፊኮች ጋር በጋራ እየሠሩ ነው፡፡ ከቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ባገኘነው ዕርዳታ 350 የሚሆኑ የተማሪ ትራፊኮችን በከተማ አቀፍ ደረጃ እያሰለጠንን ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ይመረቃሉ፡፡ ሪፖርተር፡- የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንጃ ፈቃድ ያላቸን ሰዎች እንደገና በአዲስ መልክ ለመፈተን አቅዷል፡፡ እናንተ በዚህ ላይ አስተያየት ሰጥታችሁበታል? በአዲስ መልክ መፈተኑ መፍትሄ ያመጣል? ዋና ሳጂን አሰፋ፡- መፍትሄ የሚያመጣው በሁለት መንገድ ነው፡፡ የሬደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የቢ.ፒ.አር ጥናት ያደረገበት ነው፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥ አንዱ የአሽከርካሪዎች የሥራ ሂደት ነው፡፡ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጥ ነው፡፡ ያንን ብቃት ማረጋገጥ የሚቻለው አዲስ መንጃ ፈቃድ ለሚያወጡት አዲስ ሥርዓት በማዘጋጀት ነው፡፡ ከነበረው ሥርዓት ውጪ አዲስ ካሪኩለም ተቀርፆ እንዲማሩ ማድረግ ነው፡፡ የፈተና አሰጣጡንም ማንዋል ከማድረግ ኮምፒተራይዝድ በሆነ መንገድ እንዲሠራ ማድረግ ነው፡፡ እነዚህን የፌደራሉ ትራንስፖርት ባለሥልጣን እያዘጋጀ ነው፡፡ ያለውን መንጃ ፈቃድ ማጣራት ተገቢ ነው፡፡ ፎርጅድ መንጃ ፈቃድ የያዙ ብዙ አሉ፡፡ መንጃ ፈቃዳቸው በፌደራል ትራንስፖርት ፋይል ያልተደረገ አሉ፡፡ እነዚህን መለየት የግድ ይሆናል፡፡ ሕጋዊ ያልሆኑት ወደ ሕጋዊነት እንዲመጡ የሚያደርግ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የማቆሚያው ወሰን የት ነው የሚሆነው፡፡ ዲኘሎማ፣ ዲግሪ ወዘተ. የሚሰጡ የትምህርት ተቋሞችም ልክ እንደ ፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዱሮ የሰጠነው ቀርቶ በአዲስ መልክ ፈትነን ዲኘሎማ፣ ዲግሪ፣ ማስተር ወዘተ. እንሰጣለን ቢሉ ማን ይከለክላቸዋል? ዋና ሳጂን አሰፋ፡- ወሰኑ በእጃቸው መንጃ ፈቃድ ያለ ሰዎችን መለየት ነው፡፡ አዲሱ መንጃ ፈቃድ አንደኛ በፎርጅድ የሚሰራ አይደለም፡፡ መንጃ ፈቃዱ ሲቀየር እዚያ ላይ ይቆማል፡፡ ሁለተኛው በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ ዓይነት መንጃ ፈቃድ እንዲሰጥ ነው፡፡ ደረጃውን እኩል እንዲሆን ነው፡፡ አንዳንዶች እዚህ ማውጣት ሲያቅታቸው ክልል ድረስ እየሄዱ የሚያወጡበት ሁኔታ እንዲቀር ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |