| የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎችና... |
|
|
| Wednesday, 02 April 2008 | |
|
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ለለውጥ ያላቸው ቅርበት
ሩሲያ ፕሬዚደንት የነበሩት ቭላድሚር ፑቲን በሜድቬደቭ በመጭው ግንቦት ይተካሉ፡፡ የፈረንሳይ ኘሬዚደንት የነበሩት ዣክ ዥራክ በሳርኮዚ ተተክተዋል፡፡ የእንግሊዝ ኘሬዚደንት የነበሩት ቶኒ ብሌርም በጎርደን ብራውን ተተክተዋል፡፡ ሃገራቱ ግን የነበረ እንቅስቃሴአቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲሞክራሲ፣ በመልካም አስተዳደርና በልማት ወደፊት ይገሰግሳሉ፡፡ አሜሪካም በቅርቡ ጆርጅ ቡሽን በኦባማ፣ በሒላሪ ወይም በማኬይን ትተካለች፡፡ የአለም የበላይነቷ ግን ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የነበሯት መሪ የቀድሞው ኘሬዚዳንት የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አሁንም አሉ፡፡ ቢያንስ እስከ 2ዐዐ2 ዓ.ም. ድረስም ይኖራሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፓርቲ ኢሕአዴግም ሆነ መቼ እንደተፈጠሩ ሳናውቅ መፍረሳቸውን ቀድመን የምንሰማላቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነት ግራ እንዳጋባን የዲሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት መንገዱም አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ እንዳለ አለን፡፡ በቅርቡ የሚካሄደው የማሟያና አካባቢ ምርጫ በቀዘቀዘ ስሜት መካሄዱ ማሳያ ነው፡፡ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከሌሎች አህጉሮች (በተለይም ከአውሮፓ) የፖለቲካ ፓርቲዎች በምን ይለያሉ? አፈጣጠራቸው ምን ይመስላል? ዋነኛ ተግባራቸው ምንድን ነው? የፓርቲ አመራርና የፓርቲው አንቀሳቃሽ አካሎች ግንኙነት ምን ይመስላል? ከለውጥና ቀጣይነት ጋር ያላቸው ተዛምዶስ? በአፍሪካ የመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ የተጀመረው በ2ዐኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ነው፡፡ የምዕራባውያኑ ግን በጥቂቱ ሁለት ክፍለ ዘመኖችን ተሻግሯል፡፡ በአፍሪካ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ባህሉ ገና ያልዳበረ ሲሆን ምዕራባዊያኑ በቅኝ ግዛት ያልተጠቁ፣ ድህነት ያልተንሰራፋባቸው፣ ፖለቲካዊ ባህላቸው ያልተበረዘ በመሆኑ በሁሉ መስክ እያደጉ ያሉ ናቸው፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች በህዝብ ምርጫ ሥልጣን የሚይዙና የሚለቁ ሰላማዊ የትግል ቦታቸውም በብዛት ፓርላማ የሆኑ ናቸው፡፡ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የፓርላማ ቡድንና የምርጫ ኮሚቴ ወሳኝ አካላት ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈጠሩት ያለፓርላማና ምርጫ ኮሚቴ ነው፡፡ በዘመነ ቅኝ አገዛዝ የተፈጠሩት እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዲሞክራሲያዊና ተቀባይነት ያላቸው አልነበሩም፡፡ ፖለቲካዊ ተቋማት በአፍሪካ ያልተሳካላቸው አፍሪካዊ ደምና ግንድ ስለሌላቸውና ከምዕራቡ ዓለም በራሳቸው በምዕራባውያን ወደ አፍሪካ የተላከና የገባ በመሆኑ ነው ብለው የሚከራከሩም አሉ፡፡ እነዚህ ተከራካሪዎች በተለይ በድህረ ቅኝ ግዛት ፓርላማና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወድያው መጀመራቸው ብጥብጥ እንደጋበዘ ያምናሉ፡፡ በተለይ የበርካታ ሺህ ጎሳዎች መኖሪያ የሆነችው አፍሪካ የጎሳ ፖለቲካ ከተጀመረ ወዲህ አሰቃቂና የማትመች አህጉር መሆኗን በምሳሌነት ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምዕራባውያኑ ቅርፅና ተግባር ዓይነት ይዋቀሩ እንጂ ብዙዎቹ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሩትን አገር ህዝብ ለውስጣዊ ቅኝ ተገዥነት አጋልጠውታል ሲሉም ይከራከራሉ፡፡ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈጠሩት በዲሞክራሲያዊ ከባቢ አየር አልነበረም፡፡ አገራቱን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ በማውጣት በኩል ትልቅ ሚና የተጫወቱትና ነፃነት የጠማውን ነገር ግን የተለያየ ማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ታሪካዊ ባህል ያላቸውን አካሎች ያስተባበሩት በአንድ ፓርቲ ፍፁማዊ አመራር ነበር፡፡ አፍሪካ በ197ዐዎቹ እ.ኤ.አ በአብዛኛው በአንድ ፓርቲ ቀንበር ስር አርፋ ነበር፡፡ በየሀገራቱ የነበሩ ፓርቲዎች ብሔራዊ ንቅናቄን እንደ ትልቅ መሳሪያ የሚጠቀሙ ሲሆን በተለያየ ምክንያት እውቅና የነበራቸው መሪዎቹ ከእነሱ የተለየ አመለካከትና አቋም ያላቸውን ኃይሎች በሙሉ የአንድነት፣ የእድገት፣ የስልጣኔና የብልፅግና ፀር ናቸው በማለት ሊያጠፏቸው የማይፈነቅሉት ድንጋይና የማይምሱት ጉድጓድ አልነበረም፡፡ ፣እኔ ሁሉን አውቃለሁ፣ ለምን እንደሚሉ ሲጠየቁም የተደራጁ ተቃዋሚዎች ጐሰኝነትንና መከፋፈልን በማስፋፋት የተለያዩ ፍላጎቶችንና ስሜቶችን ይፈጥራሉ ይህ ደግሞ ለሀገር ህልውና አደገኛ ነው ይሉ ነበር፡፡ ይህን አደጋ ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት ግን የሚመሩት ህዝብ ፣ለጋና ያልደረሰ ብሎም ያልተዘጋጀ፣ እንደሆነ ለመግለፅ ግን አያመነቱም ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ግን የተለያዩ ከፓርቲው ከራሱ የሚነሱ አለመግባባቶችንና የውጭ ዓመፆችን ለመግታት ግን እራሳቸው ፣ከፋፍለህ ግዛ፣ የሚል መርህን ይከተሉ ነበር፡፡ ከቅኝ አገዛዝ አፍሪካ ነፃ በወጣችበት ዘመን በምዕራቡ ዓለም የካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለምና የምስራቁ ሶሻሊስት ርዕዩተ ዓለም በከፍተኛ ሁኔታ የቀዝቃዛውን ጦርነት ጥላ ሲያንዣብብበት አፍሪካንም የውድድሩ አንዱ ቦታ አድርጓት ነበር፡፡ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ በመሠረታዊ ሁኔታ በርዞት የሄደው እኛን የተቀራመተን የሶሻሊስቱ ዓለም ርዕዮት የፓርቲ ዲሲኘሊን በፍፁም ቁጥጥር ስር የዋለና ነገሮቹን ሁሉ በጥርጣሬና በህቡዕ የሚፈፅም ስርዓት ነበር፡፡ ይህም ማለት የህዝብ ተሳትፎን ከቁብ የማይቆጥርና የማያበረታታ የአንድ ፓርቲ ስርዓትን ወደ መድብለ ፓርቲ ስርዓት መቀየራችን ከላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ያየነውን አስቀያሚ የፖለቲካ ገፅታ ለመቀየር የሚያስችል ይሆናል ተብሎ ይታሰብ ነበር፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ እንኳን በብዛት ቢመሰረቱም ወይ ጠፍተዋል አልያም ተዳክመዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት የእያንዳንዱ ዜጋ ስጋት ከነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ላላቀቃትና የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ላወጀው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ አመስጋኝ ነች፡፡ ረሃብ፣ ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ ግልፅ ያልወጡ ጦርነቶችን በመፍታት በኩል ግን አመርቂ ደረጃ ላይ ነው ያለነው ለማለት ግን አይቻልም፡፡ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን የሚያሽከረክሩት ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶችና አስፈፃሚው አካል አሰራራቸው አሁንም አንዳንድ ጥርጣሬዎችን የሚጥል ነው፡፡ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ አባል የሆኑት ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ ሀገሪቱን እየመራ ያለው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከአባልና አጋር ድርጅቶቹ ጋር ለፓርቲ ውስጥ መከፋፈልና መለያየት (በአካልም በሀሳብም) የሚሰጡት ምላሽ እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ እርስ በርስ በመከባበርና አብሮ በመስራት በኩልም የእኛ ሀገር የፖለቲካ ፓርቲዎች መሠረታዊ ችግር ነበረባቸው፡፡ አለባቸው፡፡ የርዕዮተ ዓለም፣ የታክቲክና የስትራቴጂ ልዩነት እንደተፈጥሮ ክስተት ሳይሆን እንደ መገዳደያ ምክንያት ይቆጥሩት ነበር፡፡ የዛሬዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች አፈጣጠር፣ አደረጃጀት፣ እይታ፣ አላማ፣ ስብስብ፣ የቁስና የሰው ኃይል፣ ነፃነት፣ ለተፅእኖ ያላቸው ልልነት፣ ለውጥ ፈጣሪነትና የአመራር ሚና እንዲሁም አስተዳደሩ በጣት በሚቆጠሩ ፈላጭ ቆራጮች ስለመሞላቱ እርግጠኛ እንሁን እንጂ በአሰራር ግልፅነት እጦት የተነሳ ስለምንም ነገራቸው እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም፡፡ እስከ ምርጫ 97 ድረስ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ እንዳያድግ ኢሕአዴግ ከባድ ጫና ያሳድራል የሚለው ትችት ለብዙዎቹ እንደ ወረደ የሚቀበሉት እውነት የነበረ ቢሆንም ድህረ ምርጫ 97 በኋላ ግን ፣ተቃዋሚ ፓርቲዎችስ?፣ የሚለው ጥያቄ መነሳት ጀምሯል፡፡ ምንም እንኳን ኢህአዴግን አሁንም ከደሙ ንፁህ ባያደርገውም፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር ሆሆታ የሚያበዙት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የህዝብ ድጋፍ ለማግኘትና በብዙ መለኪያዎች ለመጠናከር የሚያደርጉት ጥረት ደካማ የሚባል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁ ችግር ውስጣዊ የፓርቲው አደረጃጀት ለአባላቱም ሆነ ለደጋፊው የነፃ ተሳትፎ እድልን ያላመቻቸ መሆኑ ነው፡፡ ፓርቲዎቹ የሚሰነጠቁት፣ የሚከፈሉትና የሚከስሙት ልዩነታቸውን ለማቻቻል የሚሆን የቤት ሥራ የማይሰሩ በመሆናቸው ነው፡፡ ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ "African Political Parties: Evolution, Institutionalisation and Governance" በሚል ርዕስ በወጣውና በርካታ አፍሪካዊ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን የየአገሮቻቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጨባጭ ሁኔታ ባሰፈሩበት መፅሀፍ ላይ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥርና ስም፣ የኘሮግራም ይዘት፣ የገንዘብ ምንጭ፣ የመሪዎቹን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የኋላ ታሪክ፣ የፓርቲዎቹ ውስጣዊ አደረጃጀትና አሰራር እንዲሁም የአባላት ስብጥርን በአጭሩ ለማየት ሞክረዋል፡፡ ዶ/ር ካሳሁን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ከመንግሥት ጫና እንዳለባቸው ነገር ግን ከመንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት፤ ፓርቲዎቹ እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት፤ አባላትና ደጋፊያቸውን የሚያሳትፉበት አሰራር፤ ከህዝባዊ ድርጅቶች፣ የንግድ ማህበራትና ሲቪል ማህበረሰቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት ባሉበት ለመቆየት፣ ለመጠናከርና ለማደግ ብሎም ለመስፋፋት እንዳላስቻላቸው ይገልፃሉ፡፡ ፓርቲዎቹ በፖለቲካ ኘሮግራማቸው ላይ ፅንፈኛ አቋም ያንፀባርቃሉ፡፡ አንዳንዶች ብሔራዊ አንድነትን ዋነኛ አላማቸው ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ ለተለያዩ ጎሳዎችና ቋንቋዎች ልዩ ጥበቃና እውቅና በመስጠት ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ለዲሞክራሲ፣ ለመልካም አስተዳደር፣ ለእድገትና ልማት እንደሚሰሩ ይሰብካሉ፡፡ አንዱ ጥሪውን ለመላው ኢትዮጵያዊያን ሲያደርግ ሌላው ግን በተለየ መልኩ ለአንድ ብሔርና ጎሳ ጥሪ ያደርጋል፡፡ አንዱ አንዱን የመጠራጠር ባህል ስላዳበረ ነገሮችን እንደወረዱ ለመረዳት ህብረት ለመፍጠር ለመተግበር ያለው እድል ከነገሮቹ ጀርባ ያለውን ሀሳብ ለማግኘት በሚደረግ ጥረት ይከስማል በማለትም ዶክተር ካሳሁን ይከራከራሉ፡፡ በተጨማሪም እንደ ዶክተር ካሳሁን እምነት ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ህዝቡን ወደ ራሳቸው ለመሳብ በርካታ አባላትም በድጋፍ እንዲያግዙት ለማድረግ የሚደረገው ጥረት በደህንነት፣ በቁስና በሰው ኃይል እጥረትና በክልል መንግሥታት ለተቃዋሚወች ባለ ጥላቻ የተነሳ አልተሳካም፡፡ ይህን የተደራጀ ድጋፍ ማጣት ደግሞ ለፓርቲዎቹ ህልውና አሳሳቢ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሥልጣን በሚያደርጉት ፉክክር ኢሕአዴግን ለመቃወም የተባበሩ እጆች ይኑራቸው እንጂ ከኢሕአዴግ በመለስ የሚያስማማቸው ተጨማሪ ነገር የጥላቻ ፖለቲካ፣ አለመተማመንና ግለሰባዊ የክብር ግጭቶች ናቸው፡፡ የአንድ ፓርቲ አባላት የሆኑ ግለሰቦችም ቢሆኑ የሚለያዩባቸው ምክንያቶች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አንድ ጠንካራ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ህብረት በመፍጠር ለሕዝቡ ከኢሕአዴግ ፖሊሲና ስትራቴጂ ውጭ ሌላ አማራጭ እንዲያገኝና በክርክር፣ ውይይትና መተማመን መንግሥት ላይ ጫና በማሳደር የፖለቲካ ባህላችንን ለመለወጥ ያልቻሉት ከዓላማ በላይ ለግለሰቦች ክብርና ኩራት ቅድሚያ በመሰጠቱ ነው፡፡ ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ በመጨረሻ በዳሰሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ህዝባዊ ድርጅቶች፣ የንግድ ማህበራትና ሲቪል ማህበረሰቦች የእርስ በርስ ግንኙነት ደካማ መሆኑን ነው፡፡ መንግሥት በቅርብ ዓመታት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር እና የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኀበር ኮንፌደሬሽን መሪዎችና ድርጅቶች ጋር የፈጠረውን አለመግባባት ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ተቃዋሚው የነበሩትን የቀድሞ መሪዎች በማስወገድ ተስማሚ የሆኑ መሪዎችን ወደ ሥልጣን ማምጣቱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ነፃ እንዲሆኑ ከሚጠብቋቸው ሲቪክና ሙያ ማኀበራት ጋር ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት እንዲኖራቸው እንዳደረገም ገልፀዋል፡፡ ከላይ የተገለፀው "African Political Parties: Evolution, Institutionalisation and Governance" በሚል ርዕስ የተፃፈውን መፅሀፍ አርትኦት የሰሩት ኘሮፌሰር መሐመድ ሳልሕ ስለ አፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች በፃፉት የለውጥ ሒደት ላይ የጠቀሷቸው ነጥቦች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሌሎች አፍሪካዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያመሳስላቸዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ሥልጣን ከመያዝ በዘለለ የህዝቡን አመለካከትና ባህሪ በመቅረፅና ተፅእኖ በማሳደር በኩል ደካማ ናቸው፡፡ የፓርቲዎቹ ቅርፅ፣ የገንዘብ ምንጭ፣ የኃላፊዎች ምርጫ ወይም ሹመት፣ የፓርቲ ውስጥ ስርዓትና አስተዳደር ይመሳሰል እንጂ በርዕዮተ ዓለም ግን የተራራቁ ናቸው፡፡ ይህም የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከምዕራባውያኑ ጋር በቅርፅ እንጂ በይዘት አንድ እንዳልሆኑ ያሳያል፡፡ የምዕራባውያኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰው ኃይልም ሆነ በገንዘብ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ የመልካም ስም፣ የገንዘብና የመራጭ ድጋፍ እያገኙ የፓርቲ ውስጣዊ አንድነትንም የሚጠብቁ ሲሆኑ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች (በተለይም የኢትዮጵያ) ግን እነዚህን ሦስት ወሳኝ ነጥቦች ይስታሉ፡፡ መራጩን ህዝብ ለመስማት እንኳን ምርጫን ይጠብቃሉ፡፡ በመንግሥት ፖሊሲ ላይ ራሳቸውም ሆነ አጠቃላይ ሕዝቡ ውል ያለው ተፅእኖ እንዲያሳድር የሚያደርግ አሠራር የላቸውም፡፡ አባሎቻቸው በጋራ ርዕዮተ ዓለም የተሳሰሩ (መንፈሳዊ ወይም ቁሳዊ”፣ ስሜትና ፍላጎታቸው የተቀናጀ ባለመሆኑና የተለያዩ ግለሰባዊና የቡድን ፍላጎቶችን ያቀፉ ባለመሆናቸው ሁልጊዜም ራሳቸውን ለግጭት፣ ለመለያየትና ለማጥፋት ያጋልጣሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ185ዐ የመጀመሪያውን ዘመናዊ የፖለቲካ ፓርቲ በመመስረት ያላቋረጠ እድገት በማምጣት የዓለም ልዕለ ኃያል የሆነችውን አሜሪካን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢትዮጵያ ጋር ማነፃፀር ሞኝነት ነው፡፡ ይሁንና ደጋግመን ገዢውንም ሆነ ተቃዋሚዎችን እንደምንለው “የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንደሚባለው አያያዛችሁ የለውጥ አየር እንዲያንዣብብበት አድርጉን፡፡ ለጊዜው ግን አያያዛችሁ ኘሮፌሰር መሐመድ ሳልህም ሆኑ ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ ከአራት ዓመት በፊት በጥርጣሬ ካዩት እይታ የተለየ አይደለም፡፡ በሠለሞን ጐሹ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |