| የፕሬሱ ረቂቅ ውይይት “ዲያሎግ”... |
|
|
| Wednesday, 02 April 2008 | |
![]() በ”መገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ረቂቅ” ውይይት ተሳታፊዎች ባለፈው ቅዳሜና እሁድ (መጋቢት 20ና 21) በሂልተን ሆቴል በ”መገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ረቂቅ” ውይይት ተካሄደ፡፡ አብዛኛዎቹ የውይይቱ ተሳታፊዎች ረቂቁ የፕሬስን ነፃነት የሚገድብና በ”ክልከላ” ላይ ያተኮረ መሆኑን ተችተዋል፡፡ የሕግ አርቃቂ ቡድን ተወካይ በበኩላቸው ረቂቁ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት የሚያጎለበትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ይበልጥ ለማረጋገጥ ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ውይይቱ የተጀመረው ቅዳሜ ጠዋት በአወያይ አቶ ፋንታሁን ሀይሌ “የእንኳን ደህና መጣችሁ” የመክፈቻ ንግግር ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ ቀጥሎ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ ብርሃን ሃይሉና በአሜሪካ ኤምባሲ የቺፍ ኦፍ ሚሽን ምክትል የሆኑት ሚስ ዲቦራ ማላክ ስለውይይቱ ጠቃሚነትና ዓላማ አስመልክቶ አጭር ንግግር አድርገዋል፡፡ ሚስ ዲቦራ ነፃ፣ በቂና አሳታፊ የሆነ ውይይት ተደርጎ ተቀባይነት ያለው ረቂቅ እንዲያፀድቅ ያለቸውን ፍላጎት ገልፀዋል፡፡ በመክፈቻ ንግግር መድረኩን የተቀበሉት “የመድረኩ አዘጋጅ ኮሚቴ” አባላት የሆኑት የሚዲያ ባለሙያዎች ማህበራት ተወካዮች ናቸው፡፡እነዚህ ፎርሞች/ማህበራት ተወካዮች ቀደም ሲል በጉዳዩ ላይ ተነጋግረው በረቂቁ ላይ አዎንታዊና አሉታዊ አስተያየቶች በማስቀመጥ መስተካከል አለባቸው ባሏቸው ነጥቦች የራሳቸው አቋም የያዙ ፅሑፎች አዘጋጅተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከነዚህ መካከል ከኢጋማ አቶ ፀጋ ልኡል ወ/ኪን፣ ከኢነጋማ አቶ ወንድወሰን መኮንን፣ ከኢብጋሕ አቶ አንተነህ አብርሃም እንዲሁም ከሚዲያ ፎረም ወ/ሪት ብሌን ፍፁም ይገኙባቸዋል፡፡ ከማህበራቱ ተወካይ ንግግር መረዳት እንደተቻለው ኢጋማ ቀላል የሚባሉ ማሻሻያዎች እንዲደረግ በመጠየቅ ለረቂቁ ድጋፍ ሰጥቷል፣ ኢብጋሕና የሚዲያ ፎረም በረቂቁ ላይ ጠንካራና ደካማ ጎኑ በመግለፅ በረቂቅ ሕጉ የጋዜጠኞች አነስተኛ የደሞዝ ስኬል በማስቀመጥ ጥቅማቸው እንዲረጋገጥ የጠየቀ ሲሆን ኢነጋማ ለረቂቁ “ተቃውሞ” ሊሰኝ የሚችል አቋሞች አሰምተዋል፡፡ አዘጋጅ ማህበራቱ ባስቀመጡዋቸው የረቂቁ ጠንካራና ደካማ ጎኖች፣ የአሁኑ ረቂቅ ሕግ ከዚህ በፊት ቀርበው ከነበሩት ረቂቅ ሕጎች በርካታ መሻሻሎችና ጠንካራ ጎኖች ያሉዋቸውን ዘርዝረዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በፕሬስ ሥራ ላይ ለመሰማራት የነበሩት ክልከላዎች መቀነሳቸው፣ ጋዜጠኞች በመረጡት ማህበር እራሳቸውን እንዲያደራጁ ነፃነቱን ለባለሙያዎቹ መተው፣ በመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞች ላይ ለሚቀርቡ ክሶች አነስተኛ የይርጋ ጊዜ መቀመጡ፣ የፕሬስ ሕግን በመተላለፍ በሚፈፀሙ ወንጀሎች እስር እንዲቀር መደረጉ፣ መረጃ የማግኘት መብት በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ ተደንግጎ መሰጠቱ፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ መረጃ የመስጠትን ግዴታ መጣሱ፣ ለመረጃ ነፃነት መብት ላይ የሚጣል ገደብ በወጣና በተደነገገ ሕግ መሰረት ብቻ እንደሆነ መመልከቱ የረቂቅ ሕጉ ጠንካራ ጎኖች በማለት አስቀምጠዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ማህበራት በኋላም በተወያዮች ተደጋግሞ የተነሳው የረቂቁ ድክመት የፕሬስ ሕጉና የመረጃ ሕጉ አንድ ላይ መውጣቱ ሲሆን በረቂቁ አጠቃላይ ይዘትና የአንቀጾች አወቃቀር ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ በማስረዳት ተቃውሞታል፡፡ እንዲሁም ሌሎች እንደድክመት ከተጠቀሱት መካከል የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በምዝገባ ሂደት የቁጥጥር ሥልጣን እንዲኖረው መደረጉ፣ የወጣቶችን ደህንነት ለሚመለከት መገናኛ ብዙሃን ያሉባቸውን ኃላፊነቶች ህፃናትን ከወሲባዊ ጥቃት የመጠበቅን በግልፅ አለመካተቱ፣ የመረጃ ነፃነት በተመለከተ ከአንቀፅ 13-20 የተደነገጉት አንቀፆች መረጃን ከመስጠት ይልቅ ወደ መከልከል ማመዘናቸው፣ መረጃ የመስጠት ግዴታ የግል ተቋማትን ያለመካተቱ፣ መረጃ የማግኘት መብትን ድንጋጌዎች በስራ ላይ የሚውሉት ከሁለት ዓመት በኋላን ይገኙባቸዋል፡፡ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች የተሰነዘሩ ሲሆን አንዱ ተወያይ እንዲህ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ “ስለረቂቅ ሕጉ ከመነጋገራችን በፊት እጅግ አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ፕሬስን የሚመለከቱ ሕጎች በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ፣ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ማቋቋሚያ ሕግ፣ በብሮድካስት ሕግ ተበጣጥስ የመውጣታቸው ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ሕጎች በዚህ መልኩ ከወጡ በኋላ አሁን ስለፕሬስ ሕግ ማውራቱ ትርጉም የለውም፡፡” ቀጥሎ መድረኩን የተረከቡት የሕገ አርቃቂዎች ቡድን ወክለው በውይይቱ የተገኙት አቶ ሽመልስ ከማል ናቸው፡፡ አቶ ሽመልስ ከማል ረቂቅ ሕጉን አስመልክተው የማርቀቅ ሒደቱን በመተንተን እንደ ግብዓት የተጠቀሙባቸው የሌሎች አገሮች ዶክመንቶችን ተሞክሮዎች ለተሳታፊው አሳውቀዋል፡፡ አቶ ሽመልስ እንዳሉት ከሆነ የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅን ለማዘጋጀት የተለያዩ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት አሰራሮችን መርሆዎች እንደ ግብዓትነት ተጠቅመዋል፡፡ ለረቂቁ መነሻ ከሆኗቸው የመገናኛ ብዙሃን ሕግ የደቡብ አፍሪካ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት ተጠቅሰዋል፡፡ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ሕብረትና የአፍሪካ ህብረት የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችና ውሳኔዎች አርቃቂ ቡድኑ እንደመነሻ አድርጎ መጠቀሙ አስገንዝበዋል፡፡ በሚዲያ ማህበራትና ፎረሞች እንዲሁም ከተወያዮች የቀረቡት አስተያየቶችን መሰረት አድርገው መልስ የሰጡት የአርቃቂ ቡድኑ ተወካይ አቶ ሽመልስ ከማል በክፍሎችና በምዕራፎች ከፋፍለው ሃሳባቸውን ሰጥተውበታል፡፡ እንደ እሳቸው አገላለፅ የፕሬስና የመረጃ ነፃነት ምንጭ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት መሰረት በውይይት የቀረበው ረቂቅ የቅድሚያ ምርመራን የተከለከለ መሆኑን በሕግ ለማረጋገጥ ያለመ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃንና ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅ፣ ከመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚፈልጉትን መረጃ ለማግኘት መንገዱን ክፍት እንዲሆንና “የመንግሥት አሰራር ለሕዝቡ ግልፅ መሆን አለበት” የሚል (የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 12) ቃል ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ረቂቁ ገዳቢ ነው” ለሚለው የባለሙያዎች አስተያየት መንግሥት የነፃነትን አከባበር አስመልክተው ገደብ ለመጣልና አጥሩን ለመከለል መነሻ ካደረጓቸው መካከል ብሄራዊ ደህንነትን፣ የሕዝብ ሰላምን እና የሕዝብ ጤንነትና ሥነ ምግባር ዓበይት ጉዳዮች መሆናቸው በመግለፅ ለእነዚህ የላቁ የአገር ጉዳዮች ሲባል የተወሰነ የመረጃ ክልከላ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ አቶ ሽመልስ ከማል ፕሬስን የሚመለከቱ ህጎች ተጣጥሰው ስለመቅረባቸው በቀረበው ጥያቄ “ሕጎች በተለያየ አግባብ ሊወጡ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ አገሮች የፕሬስ ሕግን አሰባሰበው በአንድ ሕግ ያቀርባሉ፡፡ አንዳንዶቹ በተለያዩ ሕጎች ውስጥ ፕሬስን የሚመለከቱ ያወጣሉ፡፡ ስለዚህ አሰራሩ ብቻ ችግር ያለበት አይደለም” የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሳካት መንግሥት የሚዲያ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ መፈለጉንና የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ማረጋገጡ ግድ ይለዋል ብለዋል ኃላፊው፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ ብርሃን ኃይሉ በበኩላቸው የረቂቁ መንፈስና ዓላማ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ የሚዲያ ነፃነት በሕግ ማውጣት ያስፈለገው የመረጃን ነፃነት ለመገደብ ሳይሆን መንግሥት አሰራሩን ግልፅ በማድረግ መስሪያ ቤቶች በሙሉ ለመገናኛብዙኃንና ለዜጎች ክፍት ሆኖ አስፈላጊውን መረጃ በተፈለገው ፍጥነት እንዲገኝ ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የፕሬስ ሕግ ማፅደቅ ያስፈለገውም ይህንን ለማረጋገጥ እንጂ የሰዎችን የመናገር ነፃነት ለመገደብ አለመሆኑ ለማስገንዘብ ሞክረዋል፡፡ ሕግ አርቃቂውና የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በሞያ ማህበራት የቀረቡ ትችቶችን መሰረት አድርገው የረቂቁን መንፈስ ለማብራራት በክፍሎች ከፋፍለው ከተሳታፊዎች ለመወያየት ሞክረዋል፡፡ በተከፈተው የውይይት መድረክ መሰረት ከተወያዮች በየክፍሉ በርከት ያሉ ጥያቄዎችና ትችቶች ተሰንዝረዋል፡፡ ከተወያዮች የቀረቡ ጥያቄዎች በሶስት ደረጃዎች ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያውን የከረሩ ጥያቄዎች በፕሬስ ነፃነት ላይ ሕግ ማውጣት ለምን አስፈለገ? መንግሥት ሕግ ማውጣት ያስፈለገው የፕሬስና የመረጃን ነፃነት ለመገደብ መሣርያ እያበጀ ነው ወዘተ የሚል ሲሆን ይህንን ረቂቅ ሕግ ሆኖ እንዳይፀድቅ የሚቃወሙ የተወያዮች አስተያየት ያቀፈ ነው፡፡ ሁለተኛው፣ አብዛኛዎቹ ጠያቂዎች ደጋግመው ያቀረቡት የፕሬስ ህግና የመረጃ ሕግ ተለያይተው መውጣት አለባቸው የሚል ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ ጥያቄዎች የፕሬስ ሕግና የመረጃ ሕግ በመደባለቁ በሕጎች አንቀፅ አደረጃጀትና የይዘት ግልፅነት እንዳይኖራቸው ማድረጉና በተግባር አተረጓጎም ላይ ከፍተኛ ችግር እንደሚያስከትል የሚያትቱ ጥያቄዎች ተንፀባርቀዋል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ሊገለፁ የሚችሉ ጥያቄዎች በረቂቁ እያንዳንዱ አንቀፆች ያሉት ዓረፍት ነገሮች፣ ግልፅነት፣ አቀራረብና ይዘት ማሻሻያ እንዲደረግባቸው የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ አቅራቢዎች የሕጉን መረቀቅ የማይቃወሙና ሆኖም በረቂቁ የሰፈሩ ፍሬ ሃሳቦች “ከገዳቢነት” መንፈስ ተላቀው “በነፃነት” ላይ እንዲያተኩሩ እንዲሁም ከመረጃ መከልከል ይልቅ መረጃን ለመስጠት በሚፈቅድ መልኩ እንዲሻሻሉ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በውይይቱ የተገኙት ወገኖች ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ መድረኩን ያዘጋጁ ማህበራትና አባሎቻቸው በአንድ ወገን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ታዳሚ ባለሙያዎችን ጋዜጠኞች በሌላ ወገን ተገኝተዋል፡፡ በውይይቱ መጀመሪያ አካባቢ (ቅዳሜ) የውይይቱ መንፈስ አመርቂ አልነበረም፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደጠበቁት ነፃ ሆነው ጥያቄያቸው ማቅረብ አልቻሉም፡፡ ለጥያቄና አስተያየት የተሰጠው ጊዜ በየክፍሉና አንቀጹ የተደራጁ በመሆኑ በረቂቁ ላይ ጠቅለል ያለ አስተያየት መስጠት ለሚፈልግ እንዲሁም አንዱ የረቂቁ አንቀፁ ከሌላው አንቀፅ በማያያዝ ያለውን ትስስርና ወጥነት እርስ በርሱ የመጣጣምና የመጣረስ ለማሳየት የሚሞክር ሰው ዕድል ተነፍገዋል፡፡ በዚህ ወቅት ከተወያዮች ይቀርቡ የነበሩት ጥያቄዎች በመድረክ አዘጋጆች መታፈናቸው ለተሳታፊዎች ተስፋ ያስቆረጠና ያስደነገጠ ነበር፡፡ በመድረኩ ላይ የነበሩት አካላትም የተቃውሞ ሃሳብ ለመሰማት ፍቃደኛ ያልሆኑና፣ የውይይቱ አስፈላጊነትም ጥያቄ ውስጥ ያስገባ አካሄድ ተከትለው ነበር፡፡ በርዕሱ እንደተገለፀው መድረኩ የውይይትና ክርክር መሆኑ ቀርቶ የዲስኩር “የሌክቸር” ሆኖ ነበር፡፡ የሕጉ አርቃቂው የተወያዮች አስተያየትና ሃሳብ እንደ ግብዓት የመጠቀም አዝማሚያ አልነበራቸውም፡፡ የመጀመሪያው የውይይት ቀን የምክክርና የክርክር መድረክ መሆኑ ቀርቶ የሰለቸ ረቂቁን በማስረዳትና በዲስኮር ላይ ያተኮረ የአንድ አቅጣጫ ሃሳብ የሚሰጥበት ነበር፡፡ በመሆኑም የውይይቱ መንፈስ “ዲያሎግ” መሆኑ ቀርቶ አንድ ሰው ብቻ የሚደሰኩርበት “ሞኖሎግ” ሆነ፡፡ ያኮረፈና የተበሳጨ በዛ፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች የሚያቀርቡት አስተያየትና ሃሳብ እንደግብ ከመጠቀምና ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የሃሳብ ነፃነት የገደብ መድረክ ሆኖ ቀረ፡፡ ይህን ተከትሎ በመድረኩ ተስፋ ቆርጠው ውይይቱን ጥለው የሚወጡ ወገኖች በርካቶች ነበሩ፡፡ በሁለተኛው የውይይት ቀን (እሁድ) በተለይ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ ብርሃን ኃይሉ ባደረጉት ንግግርና ባሳዩት የተሳታፊዎች ሃሳብን በነፃነት የማዳመጥ መንፈስ መድረኩ የተሻለ አየር ነፈሰበት፡፡ በቅዳሜው ዕለት የነበረ ጭቅጭቅና የተካረሩ ቃላት ልውውጥ ቀርቶ መድረኩ የተሻለና አስታፊ እየሆነ መጣ፡፡ በመሆኑም በተለይ በሶስተኛ ደረጃ የጥያቄዎች መደብ የተካተቱ ማለትም በአንቀፆች፣ ዓረፍተ ነገሮችና ሃሳቦች ላይ መለስተኛ መሰረታዊ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ጥያቄዎች ተበራከቱ፡፡ እውነትም በተወያዮችና በመድረክ ያሉት ሰዎች የመቀራረብ፣ የመከራከርና የመተራረም መንፈስ እየጎለበተ መጣ፡፡ ይሁን እንጂ የቅዳሜ ውይይት በከንቱ በመባከኑ ለውይይት የቀረው የረቂቁ ክፍል ላይ ለመወያየት በቂ ጊዜ አልነበረም፡፡ በርካታ ተወያዮችም ተስፋ ቆርጠው ሳይመለሱ ቀርተዋል፡፡ እንዲህ ሆኖም በርካታ ዓረፍተ ነገሮች እንዲሻሻሉ ለቀረበው ጥያቄ አብዛኛዎቹ አዎንታዊ ምላሽ እያገኙ የተወያዩ ሃሳብም በረቂቁ ላይ እንደግብዓት መዋሉ የሚነበብት መድረክ እየተፈጠረ ሄደ፡፡ ከአንዳንድ መሰረታዊና ዋና ዋና ጥያቄዎችና አስተያየቶች በስተቀር አብዛኛዎቹ ተቀባይነት ያገኙት ማስተካከያዎች ገንቢ ሆነው ለረቂቁ ውበት ጨመሩበት፡፡ አንዳንድ ጥያቄዎችም ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት ባያገኙም አርቃቂዎች ደግመው እንዲያዩዋቸው (To be re considered) ቃል ገብተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚሁ ልክ ጥቂት የማይባሉ መሰረታዊና ዓበይት ጉዳዮች አስመልክቶ የቀረቡ ጥያቄዎች ከመድረኩ መሪዎች ተቀባይነት ሳያገኙ በተሳታፊዎችና በመድረክ ሰዎች መካከል በልዩነት ቀርተዋል፡፡ በውይይቱ መዝጊያ አካባቢ ፕሮግራሙ እያለቀ በመሆኑ በተሳታፊዎች ጥያቄ ለትንሽ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ተጨማሪ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ አግኝተዋል፡፡ በውይይቱ መጨረሻ የተገኘው የተሳታፊዎች ቁጥር ግን የመነመነ ነበር፡፡ ስለውይይቱ አጠቃላይ ውጤት የመዝግያ ንግግርና አስተያየት ቀርበዋል፡፡ አንዳንድ ተሳታፊዎች ስለ ውይይቱ ሂደትና መንፈስ አስተያየት የሰጡበት ሲሆን መንግሥት እንዲህ አይነት ውይይት በተለያዩ ጉዳዮች ከሚመለከታቸው ወገኖች የመወያየት ሁኔታ ሊቀጥልበት እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ አንዳንዶቹም አቋማቸውን ሳይለውጡ በልዩነታቸውና በአቋማቸው ፀንተው ወጥተዋል፡፡ በመጨረሻም በመድረክ ሰዎች የውይይቱ ማጠቃለያና የመዝጊያ ንግግር ተደርጓል፡፡ የመድረኩ አወያይ አቶ ፋንታሁን ሃይሌ የውይይቱ መንፈስ በማድነቅ እንዲህ ዓይነት መድረኮች ለወደፊት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ ብርሃን ኃይሉ በበኩላቸው ከተሳታፊዎቹ የቀረቡት በርካታ አስተያየቶችና ትችቶች እንደግብዓት በመጠቀም አርቃቂ ቡድኑ የሚያሻሽላቸውና እንደገና የሚያያቸው ጉዳዮች መኖራቸው አስገንዝበው የተሻለ ረቂቅ እንደሚዘጋጅ ለተሳታፊዎች ቃል ገብተዋል፡፡ ባለሥልጣኑ የውይይቱን መንፈስ ተረድተው ተጨማሪ ቅሬታዎችን አስታየየቶች በፅሑፍና በቃል ለማስተናገድ ፍላጎት እንዳላቸው ተስፋ ሰጪ የመዝግያ ንግግር አሰምተዋል፡፡ ውይይቱ ካለቀ በኋላ ውይይቱን ያዘጋጀ “የመድረኩ አመቻች ኮሚቴ” በበኩሉ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የኮሚቴው አባላት ከኢጋማ፣ ከኢነጋማ፣ ከኢብጋህና ከሚዲያ ፎረም ተወካዮች ያቀፈ ሲሆን ውይይቱ ስኬታማ እንደነበረና በውይይቱ የተደረሱ ስምምነቶች ማሻሻያዎች ተደርገውበት ረቂቅ ሕጉ ለፓርላማ እንዲቀርቡ መስማማቱና አመቻች ኮሚቴው ተልዕኮውን በመጨረሱ መበቱኑ አሳውቀዋል፡፡ በውይይቱ የታደሙ ተሳታፊዎች ግን በተደራጀ መልኩ አቋማቸውን በግልፅ የሰጡበት ሁኔታ ስላልነበረ ማን ምን ዓይነት አቋም ይዞ እንደወጣ አልታወቀም፡፡ አንዳንድ ለሪፖርተር ጋዜጣ አስተያየት የሰጡን ተሳታፊዎች ግን መድረኩ ከአምስት ዓመት በፊት እንደተደረገው ለወደፊት አሳታፊና ነጻ የሆነ ቀጣይ ውይይት እንዲደረግበት አሳስበዋል፡፡ መድረኩን እንዲዘጋጅ አስፈላጊ ትብብር ያደረጉት የአሜሪካን ዩኤስአይድና (USAD) ፓክት ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ በየማነ ናግሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |